ስለ ሲኦል እውነቱን ማወቅህ በአንተ ላይ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው እንዴት ነው?
ስለ ሲኦል እውነቱን ማወቅህ በአንተ ላይ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው እንዴት ነው?
ሲኦል የመሠቃያ ቦታ ነው ብለው የሚያስተምሩ ሰዎች ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ባሕርያቱ የሚሰጡት መረጃ ፈጽሞ የተዛባ ነው። እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ክፉዎችን እንደሚያጠፋ ይናገራል። (2 ተሰሎንቄ 1:6-9) ሆኖም የጽድቅ ቁጣ የአምላክ ዋነኛ ባሕርይ አይደለም።
አምላክ ክፉ ወይም ቂመኛ አይደለም። እንዲያውም “በውኑ ኀጢአተኛ ሲሞት ደስ ይለኛልን?” ሲል ጠይቋል። (ሕዝቅኤል 18:23) አምላክ በኃጢአተኞች ሞት የማይደሰት ከሆነ እነዚህ ሰዎች ለዘላለም ሲሠቃዩ ማየት እንዴት ሊያስደስተው ይችላል?
የአምላክ ዋነኛ ባሕርይ ፍቅር ነው። (1 ዮሐንስ 4:8) በተጨማሪም “እግዚአብሔር ለሁሉ ቸር ነው፤ ምሕረቱም በፍጥረቱ ሁሉ ላይ ነው።” (መዝሙር 145:9) እሱም በምላሹ በሙሉ ልባችን እንድንወደው ይፈልጋል።—ማቴዎስ 22:35-38
ለተግባር የሚያነሳሳህ ለሲኦል ያለህ ፍራቻ ነው ወይስ ለአምላክ ያለህ ፍቅር?
ነፍስ በሲኦል ውስጥ ትሠቃያለች የሚለው ትምህርት አንድ ሰው ለአምላክ ጤናማ ያልሆነ ፍርሃት እንዲያድርበት ያደርጋል። በአንጻሩ ስለ ይሖዋ ትክክለኛ እውቀት ያገኘና ለእሱ ፍቅር ያደረበት ሰው ለአምላክ ጤናማ ፍርሃት ይኖረዋል። መዝሙር 111:10 “እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ ነው፤ ትእዛዙንም የሚፈጽሙ ጥሩ ማስተዋል አላቸው” ይላል። እንዲህ ዓይነቱ አምላካዊ ፍርሃት የሚያርበደብድ ሳይሆን ለፈጣሪ ባለን አድናቆት ተገፋፍተን የምናሳየው ጥልቅ አክብሮት ነው። ይህም እሱን ላለማሳዘን ጤናማ ፍርሃት እንድናሳይ ይገፋፋናል።
ቀደም ሲል የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኛ የነበረችው የ32 ዓመቷ ካትሊን ስለ ሲኦል እውነቱን ማወቋ እንዴት እንደረዳት እንመልከት። አዘውትራ ጭፈራ ቤት ትሄድ የነበረ ሲሆን የዓመፅ ድርጊቶችንና የሥነ ምግባር ብልግና ትፈጽም ነበር፤ ለራሷም ጥሩ ግምት አልነበራትም። “የአንድ ዓመቷን ልጄን አያትና ‘ልጄን ምን እያደረግኳት ነው? መቼስ ይህን እያደረግኩ በሲኦል መቃጠሌ አይቀርም’ ብዬ አስብ ነበር” ስትል ተናግራለች። ካትሊን ከዕፅ ሱስ ለመላቀቅ ብዙ ጥረት ብታደርግም አልተሳካላትም ነበር። “ጥሩ ሰው ለመሆን እፈልግ የነበረ ቢሆንም በሕይወቴ ውስጥ
የሚያጋጥመኝም ሆነ በዓለም ላይ የማየው ነገር ሁሉ የሚያበሳጭ ነበር። ጥሩ ሰው እንድሆን የሚያነሳሳኝ ምንም ነገር አላገኘሁም” ብላለች።ካትሊን ከጊዜ በኋላ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘች። “ሲኦል የመቃጠያ ቦታ እንዳልሆነ ተማርኩ። የቀረበልኝ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ አሳማኝ ነበር። በሲኦል ውስጥ እንደማልቃጠል ማወቄ ትልቅ እፎይታ አስገኝቶልኛል” ብላለች። በተጨማሪም ሰዎች ከክፋት በጸዳች ምድር ላይ ለዘላለም ሊኖሩ እንደሚችሉ አምላክ ስለሰጠው ተስፋ ተማረች። (መዝሙር 37:10, 11, 29፤ ሉቃስ 23:43) “አሁን በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር አስተማማኝ ተስፋ አለኝ!” በማለት በደስታ ትናገራለች።
ካትሊን በሲኦል ውስጥ እቃጠላለሁ የሚለው ፍርሃቷ ሳይኖር ከዕፅ ሱሷ መላቀቅ ትችል ይሆን? እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ዕፅ እንድወስድ የሚገፋፋ ኃይለኛ ስሜት ሲሰማኝ ይሖዋ አምላክ እንዲረዳኝ እጸልያለሁ። ይሖዋ እንዲህ ላሉት የሚያረክሱ ድርጊቶች ያለውን አመለካከት አስባለሁ፤ እሱን ማሳዘን ደግሞ አልፈልግም። ይሖዋም ጸሎቴን መልሶልኛል።” (2 ቆሮንቶስ 7:1) ካትሊን አምላክን ላለማሳዘን ያላት እንዲህ ያለው ፍርሃት ከነበሩባት ሱሶች እንድትላቀቅ ረድቷታል።
አዎ፣ የአምላክን ፈቃድ እንድናደርግ ሊገፋፋን የሚችለው በሲኦል እሠቃያለሁ የሚለው ፍርሃት ሳይሆን ለአምላክ ያለን ፍቅርና ጤናማ ፍርሃት ነው፤ ይህ ደግሞ ዘላቂ የሆነ ደስታ ያስገኝልናል። መዝሙራዊው “እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሁሉ፣ በመንገዱም የሚሄዱ የተባረኩ ናቸው” በማለት ጽፏል።—መዝሙር 128:1
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ከሲኦል የሚወጡት እነማን ናቸው?
አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ጊኤና እና ሔዲስ የሚሉትን ሁለት የተለያዩ የግሪክኛ ቃላት “ሲኦል” በማለት በአንድ ቃል የሚተረጉሟቸው ሲሆን ይህም ሰዎች ግራ እንዲጋቡ አድርጓል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጊኤና የሚለው ቃል ትንሣኤ በሌለው ሁኔታ ሙሉ በሙሉ መጥፋትን ያመለክታል። በአንጻሩ ግን በሔዲስ ውስጥ ያሉ ሙታን የትንሣኤ ተስፋ አላቸው።
ስለዚህ ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ሞቶ ከተነሳ በኋላ ‘በሲኦል እንዳልተተወ’ ለአድማጮቹ ተናግሮ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 2:27, 31, 32፤ መዝሙር 16:10) በዚህ ጥቅስ ላይ “ሲኦል” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል ሔዲስ ነው። በመሆኑም ኢየሱስ እሳታማ ወደሆነ ቦታ አልሄደም። ኢየሱስ የነበረበት ሔዲስ ወይም “ሲኦል” መቃብር ነበር። ይሁንና አምላክ ከኢየሱስ በተጨማሪ ከሔዲስ የሚያወጣቸው ሌሎች ሙታን አሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ ከትንሣኤ ተስፋ ጋር በተያያዘ ሲናገር “ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ውስጥ የነበሩትን ሙታን ሰጡ” ይላል። (ራእይ 20:13, 14) “ሲኦል” ባዶ ይሆናል ሲባል አምላክ ትንሣኤ ማግኘት ይገባቸዋል ብሎ የፈረደላቸው ሁሉ ዳግመኛ ሕያው ይሆናሉ ማለት ነው። (ዮሐንስ 5:28, 29፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15) ይህ እንዴት ያለ ግሩም ተስፋ ነው! በሞት የተለዩን የምንወዳቸው ሰዎች ከመቃብር ሲወጡ ማየት ምንኛ አስደሳች ነው! በፍቅሩ ተወዳዳሪ የሌለው አምላካችን ይሖዋ ይህን እንደሚያደርገው ጥርጥር የለውም።