በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ እምነት

በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ እምነት

በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ እምነት

“በሕልሜ በሲኦል ውስጥ ስቃጠል ይታየኛል። እሳት ውስጥ ስጣል አልምና እየጮኽኩ እባንናለሁ። በመሆኑም ኃጢአት ላለመሥራት ምን ያህል ጥረት አደርግ እንደነበር መገመት ትችላላችሁ።”—አርሊን

ሲኦል ኃጢአተኛ የሆኑ ሰዎችን ለማሠቃየት የተዘጋጀ ቦታ ነው ብለህ ታምናለህ? ብዙ ሰዎች እንዲህ ብለው ያምናሉ። ለምሳሌ ያህል በ2005 በስኮትላንድ የሚገኘው የሴይንት አንድሪው ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑ አንድ ምሁር ባደረጉት ጥናት ከስኮትላንድ ቀሳውስት መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት፣ ከአምላክ የራቁ ሰዎች “በሲኦል ውስጥ ዘላለማዊ የአእምሮ ሥቃይ” ይደርስባቸዋል ብለው እንደሚያምኑ መረዳት ችለዋል። አንድ አምስተኛ የሚሆኑት ደግሞ በሲኦል ውስጥ ያሉ ሰዎች አካላዊ ሥቃይ እንደሚደርስባቸው ያምናሉ።

በበርካታ አገሮች የሚገኙ ብዙ ሰዎች ሲኦል የመቃጠያ ስፍራ ነው ብለው ያምናሉ። ለአብነት ያህል፣ በዩናይትድ ስቴትስ በ2007 የሕዝብ አስተያየትን በመሰብሰብ የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳመለከተው አስተያየት እንዲሰጡ ከተጠየቁት ሰዎች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ሲኦል የመቃጠያ ስፍራ ነው ብለው ያምናሉ። የሃይማኖት ዝንባሌ የሌላቸው በርካታ ሰዎች በሚኖሩባቸው አገሮችም እንኳ እንዲህ ዓይነቱ እምነት ተስፋፍቷል። በካናዳ በ2004 የሕዝብ አስተያየትን በመሰብሰብ የተካሄደ ጥናት እንዳመለከተው 42 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ሲኦል የመቃጠያ ስፍራ ነው ብለው ያምናሉ። በታላቋ ብሪታንያም 32 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች የመቃጠያ ስፍራ አለ የሚል እምነት አላቸው።

ቀሳውስት ምን ብለው ያስተምራሉ?

በርካታ ቀሳውስት ሲኦል ቃል በቃል ሰዎች በእሳት የሚሠቃዩበት ስፍራ ነው ብለው ማስተማር አቁመዋል። ከዚህ ይልቅ በ1994 በታተመው ካቴኪዝም ኦቭ ዘ ካቶሊክ ቸርች በተባለው መጽሐፍ ላይ ከተገለጸው ሐሳብ ጋር የሚመሳሰል ፍቺ ይሰጣሉ። መጽሐፉ “በሲኦል ውስጥ ያለው ዋነኛ ቅጣት ከአምላክ ለዘላለም እንዲለዩ መደረግ ነው” ሲል ይገልጻል።

ያም ሆኖ ብዙዎች፣ በሲኦል ውስጥ ያሉ ሰዎች የአእምሮ ወይም የአካል ሥቃይ ይደርስባቸዋል ብለው ያምናሉ። ይህን መሠረተ ትምህርት የሚያስፋፉ ሰዎች ይህ ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ነው ይላሉ። የሳውዘርን ባፕቲስት ቲኦሎጂካል ሴሚናሪ ፕሬዚዳንት የሆኑት አልበርት ሞለር “ይህ ትምህርት በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ እውነት እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም” በማለት ተናግረዋል።

የምታምነው ነገር ለውጥ ያመጣል የምንለው ለምንድን ነው?

ሲኦል በእርግጥ የመሠቃያ ስፍራ ከሆነ ሊያስፈራህ ይገባል። ይህ ትምህርት እውነት ካልሆነ ግን ይህን መሠረተ ትምህርት የሚያስተምሩ የሃይማኖት መሪዎች ሰዎችን ግራ እያጋቡ ከመሆኑም በላይ እነሱን በሚያምኑ ሰዎች ላይ አላስፈላጊ የሆነ ጭንቀት እየፈጠሩ ነው። በተጨማሪም የአምላክን ስም እያጎደፉ ነው።

የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በተመለከተ ምን ይላል? የሚቀጥሉት ርዕሶች ለሚከተሉት ሦስት ጥያቄዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መልስ ይሰጣሉ፦ (1) ሰው ሲሞት ምን ይሆናል? (2) ኢየሱስ ዘላለማዊ እሳት አለ ብሎ አስተምሯል? (3) ስለ ሲኦል እውነቱን ማወቅህ በአንተ ላይ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው እንዴት ነው?