በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ ዘላለማዊ እሳት አለ ብሎ አስተምሯል?

ኢየሱስ ዘላለማዊ እሳት አለ ብሎ አስተምሯል?

ኢየሱስ ዘላለማዊ እሳት አለ ብሎ አስተምሯል?

ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ዐይንህ ብታሰናክልህ ጎልጉለህ አውጣት፤ ሁለት ዐይን ኖሮህ ወደ ገሃነም ከመጣል፣ አንድ ዐይን ኖሮህ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ይሻልሃል፤ በገሃነም ትሉ አይሞትም፤ እሳቱ አይጠፋምና።”—ማርቆስ 9:47, 48

በሌላ ወቅት ኢየሱስ፣ በፍርድ ጊዜ ክፉ ሰዎችን “እናንተ የተረገማችሁ፤ ለዲያብሎስና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀው የዘላለም እሳት ከእኔ ተለይታችሁ ሂዱ” እንደሚላቸው ተናግሯል። በተጨማሪም እነዚህ ሰዎች “ወደ ዘላለም ፍርድ [“ቅጣት፣” የ1954 ትርጉም]” እንደሚሄዱ ገልጿል።—ማቴዎስ 25:41, 46

ኢየሱስ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት መጀመሪያ ላይ ሲታዩ ዘላለማዊ እሳት አለ የሚለውን ትምህርት የሚደግፉ ሊመስሉ ይችላሉ። ኢየሱስ ይህን ሲናገር “ሙታን ግን ምንም አያውቁም” በማለት በግልጽ የሚናገረውን የአምላክን ቃል መጻረሩ እንዳልሆነ የታወቀ ነው።—መክብብ 9:5

ታዲያ ኢየሱስ “ወደ ገሃነም” ስለመጣል ሲናገር ምን ማለቱ ነበር? ኢየሱስ የጠቀሰው “የዘላለም እሳት” ቃል በቃል እሳትን የሚያመለክት ነው ወይስ ምሳሌያዊ? ክፉዎች “ወደ ዘላለም ቅጣት” ይሄዳሉ ሲባል ምን ማለት ነው? እስቲ እነዚህን ጥያቄዎች አንድ በአንድ እንመርምር።

ኢየሱስ “ወደ ገሃነም” ስለመጣል ሲናገር ምን ማለቱ ነበር? በማርቆስ 9:47 ላይ “ገሃነም” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ጊኤና ነው። ይህ ቃል “የሄኖም ሸለቆ” የሚል ትርጉም ካለው ጌህ ሂኖም ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የመጣ ነው። የሄኖም ሸለቆ ከጥንቷ ኢየሩሳሌም ወጣ ብሎ የሚገኝ ቦታ ነበር። በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ይህ ስፍራ አምላክ ያወገዘው አስጸያፊ ተግባር የሚፈጸምበት ይኸውም ሕፃናት መሥዋዕት የሚደረጉበት ቦታ ነበር። አምላክ እንዲህ ያለውን የሐሰት አምልኮ የሚፈጽሙትን እንደሚያጠፋ ተናግሮ ነበር። ይህ ትንቢት ፍጻሜውን በሚያገኝበት ጊዜ የሄኖም ሸለቆ “የዕርድ ሸለቆ” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን የእነዚህ ሰዎች ሬሳ ሳይቀበር የሚጣልበት ቦታ ይሆናል። (ኤርምያስ 7:30-34) በዚህ መንገድ ይሖዋ የሄኖም ሸለቆ በሕይወት ያሉ ሰዎች የሚሠቃዩበት ቦታ ሳይሆን የብዙዎች ሬሳ የሚጣልበት ቦታ እንደሚሆን ትንቢት ተናግሯል።

ኢየሱስ በምድር በኖረበት ዘመን የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች የሄኖም ሸለቆን ቆሻሻ መጣያ አድርገው ይጠቀሙበት ነበር። ከባድ ወንጀል የፈጸሙ አንዳንድ ሰዎችን አስከሬን በዚህ ቦታ ይጥሉ የነበረ ሲሆን ወደዚያ ይጣል የነበረውን ቆሻሻና አስከሬን ለማቃጠል እሳቱ ሁልጊዜ እንዲነድ ይደረግ ነበር።

ኢየሱስ ስለማይሞቱ ትሎችና ስለማይጠፋ እሳት ሲናገር በተዘዋዋሪ መንገድ ኢሳይያስ 66:24⁠ን መጥቀሱ ሊሆን ይችላል። ኢሳይያስ “[በአምላክ] ላይ ያመፁትን ሰዎች ሬሳ” አስመልክቶ ሲናገር “ትላቸው አይሞትም፤ እሳታቸው አይጠፋም” ብሏል። ኢየሱስም ሆነ ያዳምጡት የነበሩ ሰዎች ኢሳይያስ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት ቀብር የማይገባቸው ሰዎች አስከሬን ምን እንደሚደረግ የሚገልጹ እንደሆኑ ያውቁ ነበር።

ስለዚህ ኢየሱስ የሄኖም ሸለቆን ወይም ገሃነምን ትንሣኤ የሌለውን ሞት ለማመልከት ተስማሚ ምሳሌ አድርጎ ተጠቅሞበታል። ኢየሱስ፣ አምላክ “ነፍስንና ሥጋን በገሃነም ማጥፋት” እንደሚችል በተናገረ ጊዜ ይህን ነጥብ ግልጽ አድርጎታል። (ማቴዎስ 10:28) በመሆኑም ገሃነም ዘላለማዊ ሥቃይን ሳይሆን ዘላለማዊ ሞትን ያመለክታል።

ኢየሱስ የጠቀሰው “የዘላለም እሳት” ቃል በቃል እሳትን የሚያመለክት ነው ወይስ ምሳሌያዊ ነው? በማቴዎስ 25:41 ላይ የሚገኘው ኢየሱስ የጠቀሰው “የዘላለም እሳት” “ለዲያብሎስና ለመላእክቱ” የተዘጋጀ እንደሆነ ልብ በል። እሳት መንፈሳዊ ፍጥረታትን ማቃጠል የሚችል ይመስልሃል? ወይስ ኢየሱስ “እሳት” የሚለውን ቃል የተጠቀመበት ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ነው? በዚሁ ንግግሩ ላይ የተጠቀሱት “በጎች” እና “ፍየሎች” ቃል በቃል የሚወሰዱ እንዳልሆኑ የታወቀ ነው፤ እነዚህ ቃላት ሁለት ዓይነት ሰዎችን የሚያመለክቱ ምሳሌያዊ አገላለጾች ናቸው። (ማቴዎስ 25:32, 33) ስለዚህ ኢየሱስ የጠቀሰው የዘላለም እሳት ክፉዎችን ሙሉ በሙሉ አቃጥሎ የሚያጠፋቸው በምሳሌያዊ መንገድ ነው።

ክፉዎች “ወደ ዘላለም ቅጣት” ይሄዳሉ ሲባል ምን ማለት ነው? በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በማቴዎስ 25:46 ላይ “ቅጣት” የሚለውን ቃል የሚጠቀሙ ቢሆንም እዚህ ላይ የገባው ኮላሲን የሚለው የግሪክኛ ቃል መሠረታዊ ትርጉም “የዛፎችን እድገት መግታት” ወይም ዛፎችን መግረዝና የማያስፈልጉ ቅርንጫፎችን መቁረጥ የሚል ነው። በመሆኑም በግ መሰል ሰዎች የዘላለም ሕይወት ሲያገኙ ንስሐ የማይገቡ ፍየል መሰል ሰዎች ግን ‘ዘላለማዊ ቅጣት’ ስለሚደርስባቸው ከሕይወት ለዘላለም ይቆረጣሉ።

አንተስ ምን ትላለህ?

ኢየሱስ ሰዎች የማትሞት ነፍስ አለቻቸው ብሎ አላስተማረም። ከዚህ ይልቅ ሙታን እንደሚነሱ በተደጋጋሚ ተናግሯል። (ሉቃስ 14:13, 14፤ ዮሐንስ 5:25-29፤ 11:25) ኢየሱስ ነፍስ አትሞትም ብሎ ያምን ከነበረ ሙታን ይነሳሉ ብሎ እንዴት ሊናገር ይችላል?

ኢየሱስ፣ አምላክ በጭካኔ ተነሳስቶ ክፉዎችን ለዘላለም ያሠቃያል ብሎ አላስተማረም። ከዚህ ይልቅ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአል” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 3:16) ኢየሱስ በእርሱ የማያምኑ ሰዎች ለዘላለም የሚሠቃዩ ከሆነ እንደሚሞቱ አድርጎ ለምን ይናገራል? በሲኦል ውስጥ በእሳት እየተሠቃዩ ለዘላለም ይኖራሉ ማለት ፈልጎ ከሆነ ይህንኑ በግልጽ አይናገርም ነበር?

ሲኦል የመሠቃያ ቦታ ነው የሚለው ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የክርስትና ትምህርት እንደሆነ ተደርጎ የሚቀርብ የአረማውያን እምነት ነው። ( ገጽ 6 ላይ የሚገኘውን “የሲኦል ትምህርት አጭር ታሪክ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) አምላክ ሰዎችን በሲኦል ለዘላለም አያሠቃይም። ታዲያ ሲኦልን በተመለከተ እውነቱን ማወቅህ ስለ አምላክ ባለህ አመለካከት ላይ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

 የሲኦል ትምህርት አጭር ታሪክ

ከአረማውያን እምነት የመነጨ ትምህርት ነው፦ የጥንቶቹ ግብጻውያን ሲኦል እሳታማ ቦታ ነው ብለው ያምኑ ነበር። በ1375 ከክርስቶስ ልደት በፊት የተዘጋጀው ዘ ቡክ አምቶት የተባለው መጽሐፍ “ወደ እሳቱ ጉድጓድ ተዘቅዝቀው ስለሚወረወሩ እንዲሁም . . . ከጉድጓዱ መውጣትም ሆነ . . . ከነበልባሉ ማምለጥ ስለማይችሉ” ሰዎች ይናገራል። የግሪክ ፈላስፋ የሆነው ፕሉታርክ (46-120 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ) በታችኛው ዓለም ያሉ ሰዎችን አስመልክቶ ሲጽፍ “አስፈሪ ሥቃይ ሲደርስባቸው እንዲሁም የሚያዋርድና ለመቋቋም የሚከብድ ቅጣት ሲፈጸምባቸው የዋይታ ጩኸት ያሰማሉ” ብሏል።

የሲኦል ትምህርት ወደ አይሁድ እምነት ዘልቆ ገባ፦ ታሪክ ጸሐፊው ጆሴፈስ (37-100 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ) ከአይሁድ እምነት ተገንጥለው የወጡት ኤሴናውያን “ነፍስ አትሞትም፤ ከዚህ ይልቅ ለዘላለም ትኖራለች” ብለው ያምኑ እንደነበር ጽፏል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ከግሪካውያን አስተሳሰብ ጋር ተመሳሳይ ነው . . . ግሪካውያን መጥፎ የሆኑ ነፍሶች ማቆሚያ የሌለው ቅጣት እየተቀበሉ በጨለማ በተዋጠ አስፈሪ ቦታ ውስጥ እንደሚኖሩ አድርገው ያስባሉ።”

“በክርስትና” ሃይማኖቶች ዘንድ ተቀባይነት አገኘ፦ በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ አፖካሊፕስ ኦቭ ፒተር የተባለው የአዋልድ መጽሐፍ ስለ ክፉዎች ሲናገር “የማይጠፋ እሳት ተዘጋጅቶላቸዋል” ይላል። አክሎም እንዲህ ሲል ይገልጻል፦ “የቁጣ መልአክ የሆነው ኤዝሪየል ግማሽ አካላቸው የተቃጠለ ወንዶችንና ሴቶችን አምጥቶ በጨለማ ወደተዋጠው የወንዶች ሲኦል ይወረውራቸዋል። እዚያም አንድ የቁጣ መንፈስ ያሠቃያቸዋል።” በሁለተኛው መቶ ዘመን የአንጾኪያው ቲኦፈለስ ግሪካዊቷ ነቢዪት ሴበል፣ ክፉዎች ስለሚደርስባቸው ቅጣት የተናገረችውን ትንቢት በመጥቀስ “በእናንተ ላይ የሚነድ እሳት ይመጣል፤ በየዕለቱ በእሳት ስትቃጠሉ ትኖራላችሁ” ሲል ጽፏል። ይህ አባባል ቲኦፈለስ “እውነተኛ፣ ጠቃሚ፣ ትክክለኛና ለሁሉም ሰው ፋይዳ ያላቸው” ብሎ ከገለጻቸው ቃላት መካከል ይገኛል።

በመካከለኛው መቶ ዘመን ሰዎች የኃይል እርምጃ ለመውሰድ ሲኦልን እንደ ሰበብ አድርገው ይጠቀሙበት ነበር፦ ወደ 300 የሚሆኑ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮችን በእንጨት ላይ ሰቅላ ያቃጠለችው የእንግሊዟ ንግሥት ቀዳማዊት ሜሪ (1553-1558) “የመናፍቃን ነፍሶች ከሞቱ በኋላ ለዘላለም በሲኦል ስለሚቃጠሉ እነሱን ምድር ላይ በማቃጠል ከመለኮታዊው የበቀል እርምጃ ጋር የሚመሳሰል ድርጊት ከመፈጸም የተሻለ ትክክለኛ ነገር ላደርግ አልችልም” እንዳለች ይነገራል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለሲኦል የተሰጠ ፍቺ፦ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አንዳንድ ሃይማኖቶች ስለ ሲኦል በሚያስተምሩት ትምህርት ላይ የተወሰኑ ማስተካከያዎች አድርገዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ዶክትሪን ኮሚሽን ኦቭ ዘ ቸርች ኦቭ ኢንግላንድ በ1995 እንዲህ ብሏል፦ “ሲኦል ዘላለማዊ መሠቃያ ቦታ ሳይሆን [አንድ ሰው] አምላክን ሙሉ በሙሉ በመቃወም የሚያደርገው የመጨረሻና የማይለወጥ ምርጫ ነው፤ ውጤቱም ጨርሶ ከሕልውና ውጭ መሆን ነው።”

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

‘የእሳት ባሕር’ ምንድን ነው?

ራእይ 20:10 ዲያብሎስ ወደ ‘እሳት ባሕር’ እንደሚጣልና “ቀንና ሌሊት ከዘላለም እስከ ዘላለም” እንደሚሠቃይ ይናገራል። ዲያብሎስ ለዘላለም እንዲሠቃይ ከተፈለገ አምላክ በሕይወት ሊያቆየው ይገባል፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ ዲያብሎስን ‘እንደሚደመስሰው’ ይናገራል። (ዕብራውያን 2:14) ምሳሌያዊው የእሳት ባሕር ‘ሁለተኛውን ሞት’ ያመለክታል። (ራእይ 21:8) ይህ ዓይነቱ ሞት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መጀመሪያ ላይ ከተገለጸው ይኸውም በአዳም ኃጢአት ምክንያት ከመጣውና ትንሣኤ ሊገኝበት ከሚችለው ሞት የተለየ ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:21, 22) መጽሐፍ ቅዱስ ‘የእሳት ባሕር’ በውስጡ ያሉትን ሙታን ይሰጣል ስለማይል “ሁለተኛው ሞት” የተለየና ሊቀለበስ የማይችል ዓይነት ሞትን የሚያመለክት መሆን አለበት።

ታዲያ ‘በእሳት ባሕር’ ውስጥ ያሉ ለዘላለም የሚሠቃዩት እንዴት ነው? አንዳንድ ጊዜ “ማሠቃየት” የሚለው ቃል አንድን አካል “ማገድ” የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል። በአንድ ወቅት ኢየሱስ ከአጋንንት ጋር በተገናኘ ጊዜ “ጊዜው ሳይደርስ ልታሠቃየን [በጥልቁ ውስጥ ልታግደን] መጣህን?” በማለት ጮኸው ነበር። (ማቴዎስ 8:29፤ ሉቃስ 8:30, 31) ስለዚህ ‘በባሕሩ’ ውስጥ ያሉ ሁሉ የሚደርስባቸው ‘ሥቃይ’ ለዘላለም መታገድን ወይም ‘ሁለተኛውን ሞት’ ያመለክታል።