በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች ባልና ሚስት ያለያያሉ?

የይሖዋ ምሥክሮች ባልና ሚስት ያለያያሉ?

የይሖዋ ምሥክሮች ባልና ሚስት ያለያያሉ?

ብዙ ሰዎች “አንደኛው የትዳር ጓደኛ ሃይማኖቱን ከለወጠ ትዳሩ ይፈርሳል” በማለት ይናገራሉ። ባለትዳር የሆነ ሰው የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ሲወስን አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ያለ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል። ይሁንና ይህ አባባል ሁልጊዜ ትክክል ነው?

አንድ ሰው ለሃይማኖት ፍላጎት ማሳደር ሲጀምር ወይም ለረጅም ጊዜ ሲያምንበት የኖረውን ሃይማኖታዊ አመለካከት ሲለውጥ የትዳር ጓደኛው በሁኔታው ግራ ሊጋባ ይችላል። እንዲሁም ስጋት ሊያድርበት፣ ሊያዝን ሌላው ቀርቶ በጣም ሊበሳጭ ይችላል።

ብዙውን ጊዜ ሃይማኖቷን መቀየር እንዳለባት አስቀድማ የሚሰማት ሚስት ነች። ባለቤትህ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ እያጠናች ከሆነ ይህ ትዳራችሁን የሚነካው እንዴት ነው? በሌላ በኩል ደግሞ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ በማጥናት ላይ የምትገኚ ሚስት ከሆንሽ ባልሽ የሚሰማውን ጭንቀት ለመቀነስ ምን ማድረግ ትችያለሽ?

አንድ ባል የሰጠው አስተያየት

በአውስትራሊያ የሚኖረው ማርክ ባለቤቱ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ስትጀምር ለ12 ዓመታት በትዳር ቆይተው ነበር። ማርክ እንዲህ ይላል፦ “በትዳሬ ደስተኛ የነበርኩ ከመሆኑም በላይ ጥሩ ሥራ ነበረኝ። ሕይወታችን በአጠቃላይ አስደሳች ነበር። ከዚያም ባለቤቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች። በዚህ ጊዜ ሕይወቴ ሊለወጥ እንደሆነ ስለተሰማኝ ስጋት አደረብኝ። መጀመሪያ ላይ ባለቤቴ ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍላጎት ማሳደሯ እምብዛም አላስደሰተኝም ነበር፤ ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን መወሰኗን ስትነግረኝ ግን ሁኔታው ይበልጥ አሳሰበኝ።”

ማርክ፣ ሚስቱ አዲስ ሃይማኖት በመያዟ ምክንያት ትዳራቸው ሊፈርስ እንደሚችል በማሰብ መጨነቅ ጀመረ። ባለቤቱ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቷን እንድታቆምና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታቋርጥ ለማድረግ አሰበ። ይሁንና ማርክ ስሜታዊ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ጥቂት ጊዜ ለመታገሥ ወሰነ። ታዲያ የትዳራቸው መጨረሻ ምን ሆነ?

ማርክ እንዲህ ብሏል፦ “የሚያስደስተው ነገር፣ አሁን ትዳራችን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ጠንካራ ሆኗል። ባለቤቴ ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ከሆነች በኋላ ባሉት 15 ዓመታት ውስጥ ትዳራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል።” ትዳራቸው ስኬታማ እንዲሆን የረዳቸው ምንድን ነው? ማርክ እንደሚከተለው ሲል ተናግሯል፦ “መለስ ብዬ ሳስበው፣ በዋነኝነት ትዳራችን ስኬታማ ሊሆን የቻለው ባለቤቴ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ግሩም ምክሮች ተግባራዊ በማድረጓ ነው ማለት እችላለሁ። ሁልጊዜ እኔን በአክብሮት ለመያዝ ጥረት ታደርግ ነበር።”

የተሳካላቸው ሚስቶች የሰጡት ሐሳብ

ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ላይ የምትገኚ ሚስት ከሆንሽ የባለቤትሽን ጭንቀት ለመቀነስ ምን ማድረግ ትችያለሽ? በተለያየ የዓለም ክፍል የሚኖሩ ሚስቶች የሰጧቸውን የሚከተሉትን ሐሳቦች ተመልከቺ።

በጃፓን የምትኖረው ሳኪኮ እንዲህ ብላለች፦ “በትዳር ሕይወት 31 ዓመታት ያሳለፍኩ ሲሆን ሦስት ልጆች አሉኝ። የይሖዋ ምሥክር የሆንኩት ከ22 ዓመታት በፊት ነው። ባለቤቴ እምነቴን የማይጋራ መሆኑ አንዳንድ ጊዜ ሁኔታዎች ፈታኝ እንዲሆኑብኝ ያደርጋል። ያም ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ለመስማት የፈጠንን፣ ለመናገር የዘገየን፣ ለቊጣም የዘገየን’ እንድንሆን የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ የቻልኩትን ያህል ጥረት አደርጋለሁ። (ያዕቆብ 1:19) ባለቤቴን በደግነት ለመያዝና ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር የሚጋጭ ነገር እንዳደርግ እስካልጠየቀኝ ድረስ ፍላጎቱን ለማሟላት እጥራለሁ። ይህም ትዳራችን የተሳካ እንዲሆን አድርጎታል።”

በሩሲያ የምትኖረው ነድዬዥደ እንዲህ ብላለች፦ “በትዳር ሕይወት 28 ዓመታት ያሳለፍኩ ሲሆን የይሖዋ ምሥክር ከሆንኩ 16 ዓመት ሆኖኛል። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከመጀመሬ በፊት ባለቤቴ የቤተሰቡ ራስ መሆን እንዳለበት አድርጌ አላስብም ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ባለቤቴን ሳላማክር ውሳኔ ማድረግ ያስደስተኝ ነበር። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረጌ ለቤተሰባችን ሰላምና ደስታ አስተዋጽኦ እንዳደረገ እየተገነዘብኩ መጣሁ። (1 ቆሮንቶስ 11:3) ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ለባለቤቴ መገዛት እየቀለለኝ የሄደ ሲሆን እሱም የማደርገውን ለውጥ ያስተውል ነበር።”

በብራዚል የምትኖረው ማርሊ እንዲህ ብላለች፦ “ትዳር ከመሠረትኩ 21 ዓመታት ያለፉ ሲሆን ሁለት ልጆች አሉኝ። የይሖዋ ምሥክር የሆንኩት ከ16 ዓመት በፊት ነው። ይሖዋ አምላክ ባልና ሚስት እንዲለያዩ እንደማይፈልግ ተገነዘብኩ። ስለዚህ ጥሩ ሚስት ለመሆን እንዲሁም ይሖዋንና ባለቤቴን የሚያስደስት ነገር ለመናገርም ሆነ ለማድረግ ጥረት ማድረግ ጀመርኩ።”

በሩሲያ የምትኖረው ላሪሳ እንዲህ ብላለች፦ “የዛሬ 19 ዓመት ገደማ የይሖዋ ምሥክር ስሆን በሕይወቴ ውስጥ ለውጥ ማድረጌ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ተገነዘብኩ። ባለቤቴ፣ መጽሐፍ ቅዱስን መማሬ ጥሩ ሚስት እንድሆን እንደረዳኝና ይበልጥ እሱን እንዳደንቀው እንዳደረገኝ ማስተዋል ችሎ ነበር። መጀመሪያ ላይ ልጆቻችንን እንዴት ማሳደግ አለብን በሚለው ጉዳይ ላይ አንስማማም ነበር። በኋላ ግን የነበረንን አለመግባባት መፍታት ቻልን። አሁን ባለቤቴ ልጆቻችንን እኔ ወደምሄድባቸው ሃይማኖታዊ ስብሰባዎች እንድወስዳቸው ይፈቅድልኛል። ምክንያቱም በዚያ የሚማሩት ነገር ለሕይወታቸው የሚጠቅም መሆኑን ተገንዝቧል።”

በብራዚል የምትኖረው ቫልኪሪየ እንዲህ ብላለች፦ “የአንድ ወንድ ልጅ እናት ስሆን በትዳር ውስጥ 19 ዓመታት አሳልፌያለሁ። ከ13 ዓመት በፊት የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ። መጀመሪያ ላይ ባለቤቴ በስብከቱ ሥራ እንድካፈል አይፈልግም ነበር። ሆኖም የሚያስጨንቁትን ነገሮች በተመለከተ በገርነት ማስረዳትና መጽሐፍ ቅዱስ በባሕርዬ ላይ ያመጣው ጥሩ ለውጥ እንዲታየው ማድረግ ቻልኩ። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ባለቤቴ በስብከቱ ሥራ መካፈሌ ለእኔ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ መረዳት ጀመረ። አሁን ከመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቼ ጋር በተያያዘ ሙሉ ድጋፍ ያደርግልኛል። ከመኖሪያችን ራቅ ብለው በሚገኙ ገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት ስሄድ በመኪናው ይወስደኛል፤ እንዲሁም አስጠንቼ እስክጨርስ ድረስ በትዕግሥት ይጠብቀኛል።”

ለትዳር የሚጠቅሙ መመሪያዎችን ይዟል

የትዳር ጓደኛህ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ የምታጠና ከሆነ እንዲህ ማድረጓ ትዳራችሁን ሊያፈርሰው እንደሚችል አይሰማህ። በተለያየ የዓለም ክፍል የሚኖሩ በርካታ ባለትዳሮች እንደተገነዘቡት መጽሐፍ ቅዱስ ለትዳር የሚጠቅሙ መመሪያዎችን ይዟል።

የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ አንድ ባል እንደሚከተለው ሲል በግልጽ ተናግሯል፦ “ባለቤቴ የይሖዋ ምሥክሮችን እምነት መከተል ስትጀምር አዝኜ ነበር፤ በወቅቱ ራሴን ከሁኔታው ጋር ማስማማት ከብዶኝ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ጥቅም እንዳገኘሁ ይሰማኛል።” ሌላ ባል ደግሞ ስለ ሚስቱ እንዲህ ብሏል፦ “ታማኝነቷን፣ ቁርጠኝነቷንና የአቋም ጽናቷን መመልከቴ ለይሖዋ ምሥክሮች ከፍተኛ አድናቆት እንዲኖረኝ አድርጓል። እምነቷ ትዳራችን ስኬታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ አበርክቷል። አንዳችን የሌላውን ድክመት በትዕግሥት የምናልፍ ከመሆኑም በላይ ትዳራችንን የዕድሜ ልክ ጥምረት እንደሆነ አድርገን እንመለከተዋለን።”

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ትዳር ያላቸው አመለካከት

የይሖዋ ምሥክሮች፣ መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት እንደተጻፈ ያምናሉ። በመሆኑም ትዳርን አስመልክቶ የሚሰጠውን ምክር በቁም ነገር ይመለከቱታል። መጽሐፍ ቅዱስ ለሚከተሉት ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ ተመልከት፦

የይሖዋ ምሥክሮች አባሎቻቸውን የእነሱን እምነት ከማይከተል የትዳር ጓደኛቸው እንዲለዩ ያበረታታሉ? በፍጹም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ያላመነች ሚስት ያለው ወንድም ቢኖርና ሚስቱ አብራው ለመኖር የምትፈቅድ ከሆነ፣ ሊፈታት አይገባውም። ያላመነ ባል ያላት ሴት ብትኖርና እርሱም አብሮአት ለመኖር የሚፈቅድ ከሆነ፣ ልትፈታው አይገባትም።” (1 ቆሮንቶስ 7:12, 13) የይሖዋ ምሥክሮች ይህንን ትእዛዝ ያከብራሉ።

አንዲት የይሖዋ ምሥክር ባሏ የእሷን እምነት የማይከተል ከሆነ ፍላጎቱን ችላ እንድትል ትመከራለች? በፍጹም። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሚስቶች ሆይ፤ . . . ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ አንዳንድ ለቃሉ የማይታዘዙ ቢኖሩ፣ ያለ ቃል በሚስቶቻቸው አኗኗር ተማርከው ይመለሳሉ፤ ይህም የሚሆነው ንጹሕና ፍጹም አክብሮት የተሞላውን ኑሮአችሁን ሲመለከቱ ነው።”—1 ጴጥሮስ 3:1, 2

የይሖዋ ምሥክሮች፣ ባል ገደብ የለሽ ሥልጣን እንዳለው ያስተምራሉ? በፍጹም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “ይህን እንድታውቁ እወዳለሁ፤ የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ ነው፤ የሴትም ራስ ወንድ ነው፤ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር ነው።” (1 ቆሮንቶስ 11:3) አንዲት ክርስቲያን ሚስት፣ ባሏን የቤተሰቡ ራስ እንደሆነ አድርጋ በመመልከት ታከብረዋለች። ይሁን እንጂ የባል ሥልጣን ገደብ አለው። አንድ ባል በአምላክና በክርስቶስ ፊት ተጠያቂ ነው። በመሆኑም አንዲት ክርስቲያን ሚስት፣ ባሏ የአምላክን ሕግ የሚቃረን ነገር እንድትፈጽም ቢጠይቃት ‘ከሰው ይልቅ ለአምላክ ትታዘዛለች።’—የሐዋርያት ሥራ 5:29

የይሖዋ ምሥክሮች፣ ፍቺ ጨርሶ የተከለከለ እንደሆነ ያስተምራሉ? በፍጹም። ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሏል፦ “እላችኋለሁ፤ በትዳሯ ላይ ዝሙት [የጾታ ብልግና] ፈጽማ እስካልተገኘች ድረስ ሚስቱን ፈትቶ ሌላ ሴት የሚያገባ ሁሉ አመንዝራ ይሆናል።” (ማቴዎስ 19:9) በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች ከኢየሱስ አመለካከት ጋር በመስማማት ምንዝር ለፍቺ በቂ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ። ይሁንና ትዳር በማይረቡ ምክንያቶች መፍረስ እንደሌለበትም ጠንካራ እምነት አላቸው። አባሎቻቸውንም ኢየሱስ የሰጠውን የሚከተለውን ምክር በጥብቅ እንዲከተሉ ያበረታታሉ፦ “ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣመራል፣ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ . . . ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው።”—ማቴዎስ 19:5, 6