በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች የሚድኑት እነሱ ብቻ እንደሆኑ ያምናሉ?

የይሖዋ ምሥክሮች የሚድኑት እነሱ ብቻ እንደሆኑ ያምናሉ?

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ

የይሖዋ ምሥክሮች የሚድኑት እነሱ ብቻ እንደሆኑ ያምናሉ?

የይሖዋ ምሥክሮች እውነተኛውን ሃይማኖት እንደያዙ ይሰማቸዋል። እንዲህ ባይሆን ኖሮ እምነታቸውን ይቀይሩ ነበር። የሌላ ሃይማኖት ተከታዮች እንደሚያስቡት ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮችም ለመዳን ተስፋ ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ እነማን እንደሚድኑ የመወሰን ወይም የመፍረድ ሥልጣን እንደሌላቸውም ያምናሉ። የመጨረሻውን ፍርድ የሚሰጠው አምላክ ሲሆን ማን መዳን እንዳለበትና እንደሌለበት የሚወስነውም እሱ ነው።—ኢሳይያስ 33:22

የአምላክ ቃል፣ መዳን የሚያገኙ ሰዎች ለመዳን መፈለግ ብቻ ሳይሆን ከአዳኛቸው ጋር መተባበር እንዳለባቸው ይገልጻል። ይህንን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ በምድረ በዳ ላይ የሚጓዝ አንድ ሰው አቅጣጫ ጠፋበት እንበል። ሰውየው ትክክለኛውን አቅጣጫ ለማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት እንደሚኖረው አያጠራጥርም። ይህ ሰው ምድረ በዳ ውስጥ ቀልጦ ይቀራል ወይስ በሕይወት ይተርፋል? የዚህ ሰው መጨረሻ የተመካው ለሚቀርብለት እርዳታ በሚሰጠው ምላሽ ላይ ነው። ሰውየው ያለበት የኩራት ባሕርይ ሊያድነው የመጣው ግለሰብ የሚሰጠውን እርዳታ እንዳይቀበል ሊያግደው ይችላል። በአንጻሩ ደግሞ እርዳታውን በትሕትና ከተቀበለ ያሰበበት ቦታ በሰላም ይደርሳል።

በተመሳሳይም መዳን የሚያገኙት፣ የሰው ዘር አዳኝ ከሆነው ከይሖዋ አምላክ ጋር የሚተባበሩ ናቸው። ድነት ከአምላክ የተገኘ ስጦታ ቢሆንም ሁሉም ሰው ሊያገኘው አይችልም። የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “በሰማይ ያለውን ያባቴን ፈቃድ ሳይፈጽም ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማይ አይገባም።”—ማቴዎስ 7:21

የይሖዋ ምሥክሮች፣ አምላክ የሚያድነው በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት የሚያምኑትንና የእሱን ትምህርቶች በጥብቅ የሚከተሉትን ብቻ እንደሆነ ያምናሉ። (የሐዋርያት ሥራ 4:10-12) ለመዳን የሚፈልጉ ሰዎች ሊያሟሏቸው የሚገቡ በአምላክ ቃል ውስጥ የተገለጹ ሦስት መሥፈርቶችን እንመልከት።

(1) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 13:35) ኢየሱስ ለሌሎች ሲል ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠት የተወው ምሳሌ ፍቅር ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን ያጎላል። ለሌሎች ፍቅር የሚያሳዩ ሰዎች ለመዳን የሚያስፈልገውን ወሳኝ ባሕርይ እያንጸባረቁ ነው።

(2) ኢየሱስ ለአባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ “ስምህን አስታወቅኋቸው” ብሏል። (ዮሐንስ 17:26 የ1954 ትርጉም) ኢየሱስ፣ ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም ለአባቱ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያውቅ ነበር። ስለሆነም የአባቱ ስም ‘እንዲቀደስ’ ጸልዮአል። (ማቴዎስ 6:9) የአምላክን ስም መቀደስ ሲባል ስሙን ማወቅን እንዲሁም በጣም አስፈላጊና ቅዱስ እንደሆነ አድርጎ መመልከትን ይጨምራል። ኢየሱስ እንዳደረገው ሁሉ መዳን የሚፈልጉ ሰዎችም በአምላክ ስም መጠቀም ይገባቸዋል። ስለ አምላክ ስምና ስለ ባሕርያቱ ለሌሎች ማስተማርም ይኖርባቸዋል። (ማቴዎስ 28:19, 20) እንዲያውም የሚድኑት የአምላክን ስም የሚጠሩ ብቻ ናቸው።—ሮሜ 10:13

(3) ኢየሱስ ለጳንጥዮስ ጲላጦስ “የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለም” ብሎታል። (ዮሐንስ 18:36) በአሁኑ ጊዜ የሚገኙ ብዙ ሰዎች ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ በተሾመበት በአምላክ መንግሥት ላይ እምነት እንዳላቸው አያሳዩም። ከዚህ ይልቅ በሰብዓዊ ድርጅቶች ይታመናሉ። በተቃራኒው መዳን የሚያገኙ ሰዎች የአምላክን መንግሥት በታማኝነት የሚደግፉ ከመሆኑም በላይ ይህ መንግሥት ታማኝ የሆኑ ሰዎችን ከችግር የሚያላቅቀው እንዴት እንደሆነ ለሌሎች ያስተምራሉ።—ማቴዎስ 4:17

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ለመዳን ስለሚያስፈልጉ አንዳንድ ብቃቶች ከተማሩ በኋላ “ታዲያ፣ ማን ሊድን ይችላል?” በማለት ጠይቀው ነበር። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “በሰው ዘንድ የማይቻል በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል” ሲል መለሰላቸው። (ሉቃስ 18:18-30) የይሖዋ ምሥክሮች ቀደም ሲል የተጠቀሱትን ለመዳን የሚያስፈልጉ ብቃቶች ለማሟላት ትጋት የተሞላበት ጥረት ያደርጋሉ። ሌሎችም መዳን እንዲያገኙ ለመርዳት የተቻላቸውን ሁሉ ይጥራሉ።