ፍትሕን የሚወድ አምላክ
ወደ አምላክ ቅረብ
ፍትሕን የሚወድ አምላክ
የፍትሕ መጓደል ደርሶብህ ወይም የጭካኔ ድርጊት ተፈጽሞብህ ያውቃል? ምናልባትም በደል የፈጸመብህ ሰው ሳይቀጣ ወይም የጸጸት ስሜት ሳያሳይ ቀርቶ ይሆን? እንዲህ ያለውን ሁኔታ ችሎ ማለፍ በጣም ከባድ እንደሚሆን የታወቀ ነው፤ በተለይ ደግሞ የበደለህ ግለሰብ ይወደኛል እንዲሁም ያስብልኛል ብለህ የምትጠብቀው ሰው ከሆነ ሁኔታውን ይበልጥ ከባድ ያደርገዋል። ‘አምላክ እንዲህ ያሉ ነገሮች ሲፈጸሙ ዝም ብሎ የሚመለከተው ለምንድን ነው?’ በማለት ትጠይቅ ይሆናል። * እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ይሖዋ አምላክ ማንኛውንም ዓይነት ኢፍትሐዊ ድርጊት ይጠላል። የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኃጢአት የመሥራት ልማድ ያላቸው ጨካኝ ሰዎች ከመለኮታዊ ቅጣት እንደማያመልጡ ማረጋገጫ ይሰጠናል። በዚህ ረገድ ሐዋርያው ጳውሎስ በዕብራውያን 10:26-31 ላይ ያሰፈረውን ሐሳብ እንመርምር።
ጳውሎስ “የእውነትን ዕውቀት ከተቀበልን በኋላ ሆን ብለን በኀጢአት ጸንተን ብንመላለስ፣ ከእንግዲህ ለኀጢአት የሚሆን ሌላ መሥዋዕት አይኖርም” በማለት ጽፏል። (ቁጥር 26) ሆን ብለው ኃጢአት የሚሠሩ ሰዎች እጅግ በደለኞች ናቸው። ለምን? በመጀመሪያ ደረጃ፣ እነዚህ ሰዎች ኃጢአት የሚሠሩት ባለባቸው ድክመት ተሸንፈው አይደለም፤ ሁላችንም ብንሆን ፍጹማን ባለመሆናችን አልፎ አልፎ ስህተት እንሠራለን። እነዚህ ሰዎች ግን ኃጢአት መሥራትን ልማድ አድርገውታል። በሁለተኛ ደረጃ፣ ኃጢአት የሚሠሩት ሆን ብለው ነው። መጥፎ ነገሮችን የመሥራት ልማድ ስላላቸው ክፋት በልባቸው ውስጥ ሥር ሰድዷል። በሦስተኛ ደረጃ፣ ኃጢአት የሚሠሩት ባለማወቅ አይደለም። ስለ አምላክ ፈቃድና ስለ መንገዶቹ ትክክለኛ የሆነ ‘የእውነት እውቀት’ አላቸው።
ታዲያ አምላክ ሆን ብለው ክፉ ድርጊት የሚፈጽሙና ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞችን እንዴት ይመለከታቸዋል? ጳውሎስ “ከእንግዲህ ለኀጢአት የሚሆን ሌላ መሥዋዕት አይኖርም” ብሏል። አምላክ ለሰው ልጆች የሰጠው ስጦታ ይኸውም የክርስቶስ መሥዋዕት ፍጹማን ባለመሆናችን ምክንያት የምንሠራውን ኃጢአት ይሸፍንልናል። (1 ዮሐንስ 2:1, 2) ይሁን እንጂ ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞች ለዚህ ውድ ስጦታ አክብሮት እንደሌላቸው ያሳያሉ። አምላክ እነዚህ ሰዎች ‘ልጁን እንደረገጡና ደሙን እንደ ተራ ነገር እንደቈጠሩ’ አድርጎ ይመለከታቸዋል። (ቁጥር 29) እንዲህ ያሉ ሰዎች ለኢየሱስ ንቀት እንዳላቸውና ደሙን ኃጢአተኛ ከሆነ ሰው ደም የበለጠ ዋጋ እንደሌለው “ተራ ነገር” አድርገው እንደሚመለከቱት በድርጊታቸው ያሳያሉ። ምስጋና ቢስ የሆኑት እነዚህ ሰዎች ከክርስቶስ መሥዋዕት ተጠቃሚ አይሆኑም።
ክፉዎች ምን ይጠብቃቸዋል? የፍትሕ አምላክ “በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ” ብሏል። (ቁጥር 30) ከኃጢአት አካሄዳቸው ለመመለስ አሻፈረኝ በማለት በሌሎች ላይ ፍትሕ የጎደለው ድርጊት የሚፈጽሙ ሁሉ የሚከተለውን ሐቅ ልብ ሊሉት ይገባል። የአምላክን የጽድቅ ሕግጋት ሆን ብለው የሚጥሱ ሁሉ ከቅጣት አያመልጡም። ብዙውን ጊዜ ክፉ ሥራቸው ራሱ ለጉዳት ይዳርጋቸዋል። (ገላትያ 6:7) አሁን ጉዳት ባይደርስባቸውም እንኳ አምላክ በቅርቡ ምድርን ከማንኛውም ዓይነት ኢፍትሐዊ ድርጊት ሲያጸዳ ዋጋቸውን ይቀበላሉ። (ምሳሌ 2:21, 22) ጳውሎስ “በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ እጅግ የሚያስፈራ ነው” በማለት አስጠንቅቋል።—ቁጥር 31
ይሖዋ አምላክ፣ ሆን ብለው ኃጢአት የሚሠሩ ሰዎችን በቸልታ እንደማያልፍ ማወቅ ሁላችንንም በተለይም ደግሞ በክፉዎች ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች በእጅጉ ያጽናናል። በመሆኑም ለመበቀል ከመሞከር ይልቅ የፍትሕ መጓደልን የሚጠላው ይሖዋ ብድራታቸውን እንደሚከፍላቸው በማመን ጉዳዩን ሙሉ በሙሉ ለእሱ እንተወዋለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.1 አምላክ በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው ለምን እንደሆነ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ከፈለግህ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 106-114 ተመልከት።