በዘመናችን ‘ተአምራዊ ፈውስ’ የሚከናወነው በአምላክ ኃይል ነው?
በዘመናችን ‘ተአምራዊ ፈውስ’ የሚከናወነው በአምላክ ኃይል ነው?
በአንዳንድ አገሮች፣ ሃይማኖተኛ የሆኑ ሰዎች “በማይድን” በሽታ የተያዙ ብዙዎች ፈውስ እንዳገኙባቸው ወደሚታሰቡ ቅዱስ ስፍራዎች ሲጓዙ ማየት የተለመደ ነው። በሌሎች አገሮችም፣ መለኮታዊ ኃይል በመጠቀም በሽተኞችን እንደሚፈውሱ የሚናገሩ ሰዎች አሉ። በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ በአንዳንድ መንፈሳዊ ፕሮግራሞች ላይ፣ የታመሙ ሰዎች ፈውስ እንዳገኙ በመናገር ከተሽከርካሪ ወንበራቸው ላይ ተነስተው ሲዘሉ አሊያም ምርኩዛቸውን ሲወረውሩ ይታያሉ።
እንዲህ ያሉትን ፈውሶች የሚያከናውኑት ሰዎች በአብዛኛው ሃይማኖታቸው የተለያየ ነው፤ ብዙውን ጊዜም አንዳቸው ሌላውን ከሃዲ፣ ሐሰተኛና አረማዊ እንደሆነ አድርገው ይመለከታሉ። በመሆኑም ‘አምላክ እርስ በርስ በሚቃረኑ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ተጠቅሞ ተአምር ይሠራል?’ የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል። ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ፣ “እግዚአብሔር የሰላም አምላክ እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 14:33) ታዲያ እንዲህ ያሉት ‘ተአምራዊ ፈውሶች’ የሚከናወኑት በእርግጥ በአምላክ ኃይል ነው? ፈውስ የሚያከናውኑ አንዳንድ ሰዎች ይህን የሚያደርጉት በኢየሱስ ኃይል እንደሆነ ይናገራሉ። እስቲ ኢየሱስ ሰዎችን እንዴት እንደፈወሰ እንመልከት።
ኢየሱስ ሰዎችን የፈወሰው እንዴት ነበር?
ኢየሱስ በሽተኞችን የፈወሰው በዘመናችን ፈውስ ከሚያከናውኑ ሰዎች ፍጹም በተለየ መንገድ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ እርዳታ ፈልገው ወደ እሱ የመጡትን ሕመምተኞች በሙሉ ፈውሷል። ከታመሙ ሰዎች መካከል የተወሰኑትን ፈውሶ የተቀሩትን እንዲሁ አልተዋቸውም። ከዚህም በተጨማሪ ሰዎችን የፈወሰው ሙሉ በሙሉ ከመሆኑም ሌላ ሁልጊዜ ማለት ይቻላል ሰዎቹ ከበሽታቸው የሚድኑት ወዲያውኑ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “ኀይል ከእርሱ እየወጣ ሁሉንም ይፈውስ ስለ ነበር፣ ሰዎቹ ሁሉ እርሱን ለመንካት ይፈልጉ ነበር” በማለት ይናገራል።—ሉቃስ 6:19
አንድ የታመመ ሰው ካልተፈወሰ ይህ የሆነው ግለሰቡ እምነት ስለሌለው እንደሆነ በመናገር ሰበብ ከሚደረድሩት በዘመናችን የሚገኙ ፈዋሾች በተቃራኒ ኢየሱስ በእሱ ላይ እምነት የሌላቸውን አንዳንድ ሰዎችን እንኳ ፈውሷል። ለአብነት ያህል፣ ማየት የተሳነው አንድ ሰው እንዲፈውሰው ባይጠይቀውም ኢየሱስ ግን ፈውሶት ነበር። በኋላም ኢየሱስ “በሰው ልጅ ታምናለህን?” ሲል ጠየቀው። ሰውየውም መልሶ “ጌታዬ፤ አምንበት ዘንድ እርሱ ማን ነው?” አለው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “ከአንተ ጋር የሚነጋገረው እርሱ ነው” በማለት መለሰለት።—ዮሐንስ 9:1-7, 35-38
‘ኢየሱስ ሰዎችን የሚፈውሰው እምነታቸውን መሠረት አድርጎ ካልሆነ የፈወሳቸውን ሰዎች ብዙውን ጊዜ “እምነትህ አድኖሃል” ይላቸው የነበረው ለምንድን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። (ሉቃስ 8:48፤ 17:19፤ 18:42) ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ሲናገር እንደሚፈወሱ አምነው ወደ እሱ የመጡት ሰዎች እንደተፈወሱና ይህን ያላደረጉት ግን አጋጣሚውን ሳይጠቀሙበት እንደቀሩ መግለጹ ነበር። ከበሽታቸው የዳኑት ሰዎችም ቢሆኑ የተፈወሱት በእምነታቸው ሳይሆን በአምላክ ኃይል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር . . . በመንፈስ ቅዱስና በኀይል ቀባው፤ እርሱም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ነበረ በደረሰበት ሁሉ መልካም እያደረገ በዲያብሎስ ሥልጣን ሥር የነበሩትን ሁሉ ፈወሰ።”—የሐዋርያት ሥራ 10:38
በዘመናችን፣ ያለ ገንዘብ ‘ፈውስ’ ማግኘት የሚቻል አይመስልም። ፈውስ የሚያከናውኑ ሰዎች ገንዘብ በመሰብሰብ ረገድ የተዋጣላቸው ናቸው። ከእነዚህ ፈዋሾች መካከል አንዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባከናወነው ሥራ በአንድ ዓመት ውስጥ ከ850 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንዳገኘ ተገልጿል። አብያተ ክርስቲያናትም ፈውስ እንደሚያገኙ ተስፋ በማድረግ ቅዱስ ወደሆኑ ስፍራዎች ከሚመጡ ሃይማኖተኛ ሰዎች ከፍተኛ ትርፍ ያጋብሳሉ። በአንጻሩ ግን ኢየሱስ ከፈወሳቸው ሰዎች ፈጽሞ ገንዘብ አልጠየቀም። እንዲያውም በአንድ ወቅት የፈወሳቸውን ሰዎች መግቧቸው ነበር። (ማቴዎስ 15:30-38) ደቀ መዛሙርቱን ለስብከት ሲልካቸው እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “በሽተኞችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አስወጡ፤ በነጻ የተቀበላችሁትንም በነጻ ስጡ።” (ማቴዎስ 10:8) ታዲያ በዘመናችን ፈውስ የሚያከናውኑ ሰዎች የሚያደርጉት ነገር ከኢየሱስ የተለየ የሆነው ለምንድን ነው?
“ፈውስ” የሚያከናውኑት በማን ኃይል ነው?
ባለፉት ዓመታት፣ በሕክምና መስክ የተሰማሩ አንዳንድ ሰዎች በአምላክ ኃይል ፈውስ እንዳከናወኑ የሚናገሩ ሰዎች አደረግን የሚሉት ነገር እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ሞክረዋል። ታዲያ ምን ውጤት አገኙ? በለንደን የሚታተም ዴይሊ ቴሌግራፍ የተባለ ጋዜጣ በዚህ ጉዳይ ላይ ለ20 ዓመታት ጥናት ያካሄዱ በእንግሊዝ የሚገኙ አንድ ሐኪም የሰጡትን ሐሳብ ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ “ተአምራዊ ፈውስ እናከናውናለን የሚሉ ሰዎች የሚናገሩት ነገር እውነት መሆኑን የሚያረጋግጥ በሕክምናው መስክ የተገኘ አንድም ማስረጃ የለም።” ያም ሆኖ በርካታ ሰዎች እንደ ቅዱስ ተደርገው የሚታዩ ነገሮችን በመጠቀም፣ ቅዱስ ወደሆኑ ቦታዎች በመሄድ ወይም የአምላክ ኃይል እንዳላቸው በሚናገሩ ሰዎች አማካኝነት እንደተፈወሱ በቅንነት ያምናሉ። ታዲያ እነዚህ ሰዎች ተታልለው ይሆን?
ኢየሱስ ዝነኛ በሆነው የተራራ ስብከቱ ላይ፣ አስመሳይ የሆኑ የሃይማኖት ሰዎች “ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ በስምህ . . . ብዙ ታምራት አላደረግንምን?” እንደሚሉት ተናግሯል። እሱ ግን መልሶ “ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንት ክፉዎች፤ ከእኔ ራቁ!” ይላቸዋል። (ማቴዎስ 7:22, 23) ሐዋርያው ጳውሎስ ተአምር እንደሚፈጽሙ የሚናገሩ ሰዎች ኃይል የሚያገኙት ከማን እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “የዐመፀኛው አመጣጥ በሰይጣን አሠራር ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ ይህም በሐሰተኛ ታምራት በምልክቶችና በድንቅ ነገሮች ሁሉ ይሆናል፤ እንዲሁም . . . በሚያታልል በተለያየ የክፋት ሥራ ይመጣል።”—2 ተሰሎንቄ 2:9, 10
በተጨማሪም እንደ ቅዱስ ተደርገው በሚታዩ ነገሮች፣ በጣዖታትና በምስሎች አማካኝነት የሚከናወኑት “ፈውሶች” በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም። እንደዚህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የአምላክ ቃል “ከጣዖት አምልኮ ሽሹ” እንዲሁም “ራሳችሁን ከጣዖቶች ጠብቁ” የሚል ግልጽ መመሪያ ይሰጣል። (1 ቆሮንቶስ 10:14፤ 1 ዮሐንስ 5:21) እንዲህ ያሉት “ፈውሶች” ዲያብሎስ ሰዎችን ከእውነተኛው አምልኮ ለማራቅ ከሚጠቀምባቸው መሠሪ ዘዴዎች መካከል የሚመደቡ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ ለመምሰል ራሱን ይለዋውጣል” ይላል።—2 ቆሮንቶስ 11:14
ኢየሱስና ሐዋርያቱ ሰዎችን የፈወሱት ለምን ነበር?
በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙ እውነተኛ ተአምራዊ ፈውሶች ኢየሱስና ሐዋርያቱ የአምላክ መልእክተኞች እንደሆኑ በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው። (ዮሐንስ 3:2፤ ዕብራውያን 2:3, 4) ኢየሱስ ያከናወነው ተአምራዊ ፈውስ ሲሰብክ የነበረውን መልእክት የሚደግፍ ነበር፤ “በምኩራቦቻቸው እያስተማረ፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ቃል እየሰበከ፣ በሕዝቡ መካከል ማንኛውንም ደዌና ሕመም እየፈወሰ በመላው ገሊላ ይዘዋወር ነበር።” (ማቴዎስ 4:23) ኢየሱስ የታመሙትን መፈወስን ብቻ ሳይሆን በርካታ ሰዎችን መመገብን፣ የተፈጥሮ ኃይላትን መቆጣጠርንና ሙታንን ማስነሳትን ጨምሮ ያከናወናቸው ሌሎች ታላላቅ ነገሮች ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር ምን እንደሚያደርግላቸው የሚያሳዩ ናቸው። በእርግጥም ይህ የምሥራች ነው!
ኢየሱስና ሐዋርያቱን ጨምሮ በዚያ ዘመን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ተቀብለው የነበሩ ሰዎች በሙሉ ከሞቱ በኋላ አምላክ እንዲህ ያሉ ተአምራትን የመፈጸም ችሎታን ወይም የመንፈስ ስጦታዎችን ለሰዎች መስጠት አቁሟል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ነገር ግን ትንቢት ቢሆን ይሻራል፤ [ተአምራዊ በሆነ መንገድ የሚነገር] ልሳንም ቢሆን ይቀራል፤ [በመለኮታዊ ኃይል የሚገለጥ] ዕውቀትም ቢሆን ይሻራል።” (1 ቆሮንቶስ 13:8) ለምን? መፈወስን ጨምሮ እነዚህ ተአምራት ዓላማቸውን ካከናወኑ ማለትም ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ መሆኑን እንዲሁም የክርስቲያን ጉባኤ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱን ካረጋገጡ በኋላ ቀርተዋል ወይም ‘ተሽረዋል።’
ያም ቢሆን ኢየሱስ ያከናወናቸው ተአምራዊ ፈውሶች ለእኛ ትልቅ ትርጉም አላቸው። ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት ላስተማራቸው ትምህርቶች ትኩረት የምንሰጥና በትምህርቶቹ ላይ እምነት የምናሳድር ከሆነ ‘በዚያ ተቀምጦ “ታምሜአለሁ” የሚል አይኖርም’ የሚለው በመንፈስ መሪነት የተነገረ ተስፋ በመንፈሳዊም ሆነ በአካላዊ ፍጻሜውን የሚያገኝበትን ጊዜ በጉጉት መጠባበቅ እንችላለን።—ኢሳይያስ 33:24፤ 35:5, 6፤ ራእይ 21:4