በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ—ልንከተለው የሚገባን ፍጹም አርዓያ

ኢየሱስ—ልንከተለው የሚገባን ፍጹም አርዓያ

ኢየሱስ—ልንከተለው የሚገባን ፍጹም አርዓያ

ደስተኛና ጥሩ ሰው መሆን ትፈልጋለህ? ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ዓይነት ሰው መሆን የምንችለው እንዴት እንደሆነ ሲገልጽ “ክርስቶስ ስለ እናንተ መከራን የተቀበለው የእርሱን ፈለግ እንድትከተሉ ምሳሌን ሊተውላችሁ ነው” በማለት ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 2:21) በእርግጥም ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወቱን በጣም ጥሩ በሆነ መንገድ ስለመራ ከእሱ ልንማር የምንችለው ብዙ ነገር አለ። ስለ ኢየሱስ በመማርና አርዓያውን በመከተል ደስተኛና ጥሩ ሰው መሆን እንደምንችል ምንም ጥርጥር የለውም። ይህ ታላቅ ሰው የነበሩትን አንዳንድ ባሕርያት በማጥናት እሱ ከተወው ምሳሌ እንዴት ጥቅም ማግኘት እንደምንችል እንመልከት።

ኢየሱስ ሚዛናዊ ነበር። ኢየሱስ ‘ራሱን የሚያስጠጋበት ቦታ እንዳልነበረው’ ቢናገርም የብህትውና ሕይወት አልኖረም፤ ሌሎችም እንዲህ ዓይነት ሕይወት እንዲመሩ አላበረታታም። (ማቴዎስ 8:20) እንዲያውም በተለያዩ ግብዣዎች ላይ የተገኘባቸው ጊዜያት ነበሩ። (ሉቃስ 5:29) በአንድ የሠርግ ድግስ ላይ ተገኝቶ ውኃውን ወደ ጥሩ ወይን ጠጅ እንደለወጠ የሚናገረው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው የመጀመሪያ ተአምር ኢየሱስ ራሱን ከሌሎች የሚያገል ሰው እንዳልነበር ያሳያል። (ዮሐንስ 2:1-11) ሆኖም ኢየሱስ በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ምን እንደሆነ በግልጽ ሲናገር “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውን መፈጸም ነው” ብሏል።—ዮሐንስ 4:34

በሕይወትህ ውስጥ ለመንፈሳዊ ነገሮችና ለሌሎች ጉዳዮች በምትሰጠው ቦታ ረገድ ሚዛንህን እንዴት መጠበቅ እንደምትችል አስበህ ታውቃለህ?

በቀላሉ የሚቀረብ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን አፍቃሪና ወዳጃዊ መንፈስ የሚታይበት ሰው እንደነበረ አድርጎ ይገልጸዋል። ሰዎች ችግሮቻቸውን ሲነግሩት አሊያም ግራ ያጋቧቸውን ጥያቄዎች ሲጠይቁት አይበሳጭም ነበር። በአንድ ወቅት ብዙ ሕዝብ ከብቦት ሳለ ለ12 ዓመታት በበሽታ ስትሠቃይ የኖረች አንዲት ሴት ከሕመሟ እንደምትድን ተስፋ በማድረግ የኢየሱስን ልብስ ነካች። ሴትየዋ ያደረገችው ነገር በሌሎች ዘንድ እንደ ድፍረት ተደርጎ ሊታይ ቢችልም ኢየሱስ ግን አልገሠጻትም። ከዚህ ይልቅ በደግነት “ልጄ ሆይ፤ እምነትሽ አድኖሻል” አላት። (ማርቆስ 5:25-34) ልጆችም እንኳ ሳይቀሩ ፊት ይነሳናል ብለው ስለማይሰጉ ከእሱ ጋር መሆን ያስደስታቸው ነበር። (ማርቆስ 10:13-16) ደቀ መዛሙርቱንም ቢሆን ሁልጊዜ በግልጽና ወዳጃዊ መንፈስ በሚንጸባረቅበት መንገድ ስለሚያነጋግራቸው ወደ እሱ ለመቅረብ አይፈሩም ነበር።—ማርቆስ 6:30-32

አንተስ በቀላሉ የምትቀረብ ሰው ነህ?

ራሱን በሌሎች ቦታ የሚያስቀምጥና ርኅሩኅ ነበር። ኢየሱስ ከነበሩት ግሩም ባሕርያት መካከል አንዱ ራሱን በሌሎች ቦታ ማስቀመጥ መቻሉ ነው። ይህ ባሕርይው የሰዎችን ስሜት እንዲረዳና እነሱን የሚጠቅም ነገር እንዲያደርግላቸው አነሳስቶታል። ማርያም በወንድሟ በአልዓዛር ሞት ምክንያት ስታለቅስ ኢየሱስ ባያት ጊዜ “መንፈሱ በኀዘን ታውኮ” ‘እንባውን እንዳፈሰሰ’ ሐዋርያው ዮሐንስ ተናግሯል። በወቅቱ ሁኔታውን ይመለከቱ የነበሩ ሰዎች ኢየሱስ ለዚህ ቤተሰብ ጥልቅ ፍቅር እንደነበረው በቀላሉ ማስተዋል ይችሉ ነበር፤ ኢየሱስም ይህን ስሜቱን በሰዎች ፊት መግለጽ አላሳፈረውም። ከዚያም ወዳጁን አልዓዛርን ከሞት በማስነሳት በእርግጥም ከልቡ የሚራራ መሆኑን አሳይቷል!—ዮሐንስ 11:33-44

በሌላ ጊዜ ደግሞ፣ ከሰዎች ተገልሎ እንዲኖር ባደረገው የሥጋ ደዌ በሽታ የተያዘ አንድ ሰው ኢየሱስን “ጌታ ሆይ፤ ብትፈቅድስ ልታነጻኝ ትችላለህ” በማለት ለመነው። ኢየሱስ ያደረገው ነገር በእርግጥም ልብ የሚነካ ነበር፤ “እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና፣ ‘ፈቃዴ ነው፤ ንጻ!’ አለው።” (ማቴዎስ 8:2, 3) ኢየሱስ ሰዎችን ይፈውስ የነበረው ትንቢት ለመፈጸም ብሎ ብቻ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ከሥቃያቸው ሊያሳርፋቸው ይፈልግ ስለነበረ ነው። ኢየሱስ በአንድ ወቅት “ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው” ብሎ ነበር። ኢየሱስ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ ከብዙዎች አእምሮ የማይጠፋውን ይህን አባባል እንደሠራበት ያሳያሉ።—ሉቃስ 6:31

የምታደርገው እያንዳንዱ ነገር በችግር ውስጥ ለወደቁ ሰዎች እንደምትራራ የሚያሳይ ነው?

የሰውን ስሜት የሚረዳና አስተዋይ ነበር። ኢየሱስ ምንም ስሕተት ያልሠራ ቢሆንም ሌሎች ፍጹም እንዲሆኑ አይጠብቅም ነበር፤ ወይም ከሌሎች የተሻለ እንደሆነ ለማሳየት አልሞከረም። እንዲሁም ስለ አንድ ሁኔታ የተሟላ ግንዛቤ ሳይኖረው ምንም ነገር አላደረገም። በአንድ ወቅት፣ በከተማው ውስጥ ኃጢአተኛ በመሆኗ የምትታወቅ አንዲት ሴት የኢየሱስን እግር በእንባዋ በማራስ እምነቷንና አድናቆቷን ገልጻ ነበር። ኢየሱስን በእንግድነት የተቀበለው ሰው የሴትየዋ ድርጊት ተገቢ እንዳልሆነ ቢያስብም ኢየሱስ አድራጎቷን አለመቃወሙ አስገርሞታል። ይሁንና ኢየሱስ ሴትየዋ ቅን መሆኗን ስለተረዳ በኃጢአቷ ምክንያት አልገሠጻትም። ከዚህ ይልቅ “እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ” አላት። ኢየሱስ በፍቅር ስለተቀበላት ሴትየዋ የቀድሞ አኗኗሯን እርግፍ አድርጋ ለመተው ተነሳስታ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።—ሉቃስ 7:37-50

አንተስ በሌሎች ዘንድ የምትታወቀው ለማመስገን ፈጣን በመሆንህና ለመውቀስ ባለመቸኮልህ ነው?

የማያዳላና ሰዎችን የሚያከብር ነበር። ባሕርያቸው ስለሚጣጣምና ምናልባትም የሥጋ ዝምድና ስለነበራቸው ሳይሆን አይቀርም ኢየሱስ ለደቀ መዝሙሩ ዮሐንስ ለየት ያለ ፍቅር ነበረው። * ያም ቢሆን ለእሱ እንደሚያደላ የሚያሳይ አንድም ነገር አላደረገም፤ እንዲሁም ከሌሎቹ ደቀ መዛሙርት አስበልጦ አልተመለከተውም። (ዮሐንስ 13:23) እንዲያውም ዮሐንስና ወንድሙ ያዕቆብ በአምላክ መንግሥት ውስጥ የተሻለውን ቦታ እንዲሰጣቸው በጠየቁት ጊዜ ኢየሱስ “በቀኜ ወይም በግራዬ መቀመጥ . . . እኔ የምሰጠው ነገር አይደለም” በማለት መልሶላቸዋል።—ማርቆስ 10:35-40

ኢየሱስ ምንጊዜም ሰዎችን ያከብር ነበር። በዘመኑ እንደነበሩት ሰዎች ለሌሎች ጭፍን ጥላቻ አልነበረውም። ለምሳሌ ያህል፣ አብዛኛውን ጊዜ ሴቶች ከወንዶች እንደሚያንሱ ተደርገው ይታዩ ነበር። ኢየሱስ ግን ለሴቶች ተገቢውን ክብር አሳይቷቸዋል። ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ በግልጽ የተናገረው ለአንዲት ሴት ነበር። የሚገርመው ሴትየዋ አይሁዳዊት ሳትሆን ሳምራዊት ነበረች፤ አይሁዳውያን ደግሞ ለሳምራውያን ከፍተኛ ንቀት ስለነበራቸው ሰላምታ እንኳ ሊሰጧቸው አይፈልጉም ነበር። (ዮሐንስ 4:7-26) በተጨማሪም ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን ከሌሎች ቀድመው እንዲያውቁ ያደረገው ለሴቶች መሆኑ እንደሚያከብራቸው ያሳያል።—ማቴዎስ 28:9, 10

ከአንተ የተለየ ዘር፣ ጾታ፣ ቋንቋ ወይም ዜግነት ካላቸው ሰዎች ጋር ባለህ ግንኙነት ከአድልዎ ትርቃለህ?

ለቤተሰቡ ያለበትን ኃላፊነት በመወጣት ረገድ ቁም ነገረኛ ነበር። የኢየሱስ አሳዳጊ አባት ዮሴፍ የሞተው ኢየሱስ ገና ወጣት ሳለ ሳይሆን አይቀርም። በመሆኑም ኢየሱስ አናጢ ሆኖ በመሥራት እናቱን እንዲሁም ታናናሽ ወንድሞቹንና እህቶቹን ያስተዳድር እንደነበር ጥርጥር የለውም። (ማርቆስ 6:3) በሕይወቱ መጨረሻ አካባቢ ደግሞ፣ እናቱን ማርያምን እንዲንከባከብለት ለደቀ መዝሙሩ ዮሐንስ አደራ ሰጥቶታል።—ዮሐንስ 19:26, 27

አንተስ የቤተሰብ ኃላፊነትህን በመወጣት ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ ትከተላለህ?

እውነተኛ ወዳጅ ነበር። ኢየሱስ በጣም ጥሩ ወዳጅ ነበር። ይህን ያሳየው እንዴት ነው? ወዳጆቹ በተደጋጋሚ አንድ ዓይነት ስሕተት ይሠሩ የነበረ ቢሆንም እንኳ አልራቃቸውም። ደቀ መዛሙርቱ እሱ እንደሚጠብቅባቸው ሆነው ያልተገኙባቸው ጊዜያት ነበሩ። ያም ቢሆን መጥፎ ሰዎች እንደሆኑ ከማሰብ ይልቅ በመልካም ባሕርያቸው ላይ በማተኮር እውነተኛ ወዳጃቸው መሆኑን አሳይቷል። (ማርቆስ 9:33-35፤ ሉቃስ 22:24-27) የእሱን አመለካከት እንዲቀበሉ ሳይጫናቸው ስሜታቸውን በነፃነት እንዲገልጹ አጋጣሚ ይሰጣቸው ነበር።—ማቴዎስ 16:13-15

ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢየሱስ ለወዳጆቹ ፍቅር ነበረው። (ዮሐንስ 13:1) ምን ያህል ይወዳቸው ነበር? ኢየሱስ “ስለ ወዳጆቹ ሕይወቱን አሳልፎ ከመስጠት የሚበልጥ ፍቅር ማንም የለውም” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 15:13) አንድ ሰው ከገዛ ሕይወቱ የበለጠ ለወዳጆቹ ሊሰጥ የሚችለው ምን ነገር ይኖራል?

አንተስ ጓደኞችህ በሚያበሳጩህ ወይም ቅር በሚያሰኙህ ጊዜ እውነተኛ ወዳጅ መሆንህን ታሳያለህ?

ደፋርና ቆራጥ ነበር። ኢየሱስ በአንዳንድ ሃይማኖታዊ ሥዕሎች ላይ እንደሚታየው ምንም ማድረግ የማይችል አቅመ ቢስ ሰው አይደለም። የወንጌል ዘገባዎች ኢየሱስ ጠንካራና ጎበዝ ሰው እንደሆነ ይናገራሉ። ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ይነግዱ የነበሩ ሰዎችን ከነሸቀጦቻቸው ሁለት ጊዜ አባሯቸዋል። (ማርቆስ 11:15-17፤ ዮሐንስ 2:14-17) በአንድ ወቅት ሰዎች “የናዝሬቱን ኢየሱስን” ለመያዝ በመጡ ጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ መሃል ወጣ ብሎ በድፍረት “እርሱ እኔ ነኝ” ብሏቸው ነበር። ከዚያም ደቀ መዛሙርቱን ከችግር ለመጠበቅ ሲል ጠንከር ባለ አነጋገር “‘እርሱ እኔ ነኝ’ ብያችኋለሁ እኮ፤ እኔን የምትፈልጉ ከሆነ፣ እነዚህ፣ ይሂዱ ተዉአቸው” አላቸው። (ዮሐንስ 18:4-9) ጳንጥዮስ ጲላጦስ፣ ኢየሱስ በታሰረና እንግልት በደረሰበት ጊዜ ያሳየውን ድፍረት ሲመለከት “እነሆ፤ ሰውየው!” በማለት መናገሩ የሚያስገርም አይደለም።—ዮሐንስ 19:4, 5

አንተስ አንድ ነገር እንድታደርግ የሚያስገድድ ሁኔታ ሲያጋጥምህ በቆራጥነትና በድፍረት እርምጃ ትወስዳለህ?

ኢየሱስ ፍጹም አርዓያችን ነው እንድንል የሚያደርጉን እነዚህና ሌሎች ግሩም ባሕርያት ያሉት መሆኑ ነው። የእሱን አርዓያ ለመከተል የምንጥር ከሆነ ደስተኛና ጥሩ ሰዎች እንሆናለን። ሐዋርያው ጴጥሮስም ክርስቲያኖች የኢየሱስን ፈለግ በጥብቅ እንዲከተሉ ማሳሰቢያ የሰጠው በዚህ ምክንያት ነው። የኢየሱስን ፈለግ የቻልከውን ያህል በጥብቅ ለመከተል ጥረት ታደርጋለህ?

ልንከተለው የሚገባን አርዓያ ብቻ አይደለም

ኢየሱስን ልንከተለው የሚገባን አርዓያ ብቻ አድርገን አንመለከተውም። ኢየሱስ ስለ ራሱ ሲናገር “መንገዱ እኔ ነኝ፤ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” ብሏል። (ዮሐንስ 14:6) ኢየሱስ፣ ስለ አምላክ እውነቱን በማሳወቅ ሰዎች ወደ ፈጣሪ መቅረብ የሚችሉበትን መንገድ የከፈተ ከመሆኑም በላይ ታማኝ የሆኑ ሁሉ ሕይወት እንዲያገኙ አስችሏል።—ዮሐንስ 3:16

ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበት አንዱ ምክንያት ሰዎች ሕይወት እንዲያገኙ መሆኑን ሲገልጽ “የሰው ልጅ እንዲያገለግሉት ሳይሆን፣ ለማገልገልና ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት መጥቶአል” ብሏል። (ማቴዎስ 20:28) ኢየሱስ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ከፍቷል። ከዚህ ዝግጅት ተጠቃሚ ለመሆን በግለሰብ ደረጃ ምን ማድረግ አለብን? ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት መልሱን ሰጥቷል፦ “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።”—ዮሐንስ 17:3

አዎን፣ አንድ ሰው የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ከፈለገ ስለ ኢየሱስ ማወቅ፣ ሕይወቱን የመራበትን መንገድ መኮረጅና በመሥዋዕታዊ ሞቱ ላይ እምነት እንዳለው በተግባር ማሳየት ያስፈልገዋል። ይህ እውቀት የሚገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሲሆን ይህን መጽሐፍ ጊዜ ወስደህ እንድታጠና እንዲሁም የያዛቸውን ምክሮች ልክ እንደ ኢየሱስ በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት እንድታደርግ እናበረታታሃለን። *

ምሳሌ ሊሆነን ከሚችለው ከኢየሱስ ሕይወት ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለብን ትምህርት እናገኛለን። የኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት ከኃጢአትና የኃጢአት ደሞዝ ከሆነው ከሞት ነፃ ያወጣናል። (ሮሜ 6:23) ኢየሱስ ክርስቶስ በሕይወታችን ላይ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድር ግሩም ምሳሌ ባይተውልን ኖሮ ምን እንሆን ነበር? በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥሙህ ውጣ ውረዶችና ጭንቀቶች እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ የተወውን ምሳሌ ለማወቅና በጥብቅ ለመከተል የምታደርገውን ጥረት እንዲያስተጓጉሉብህ ፈጽሞ አትፍቀድ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.12 የዮሐንስ እናት ሰሎሜ እና የኢየሱስ እናት ማርያም እህትማማቾች ሳይሆኑ አይቀሩም። ማቴዎስ 27:55, 56⁠ን ከማርቆስ 15:40 እና ከዮሐንስ 19:25 ጋር አወዳድር።

^ አን.26 ኢየሱስ በምድር ላይ ስላሳለፈው ሕይወት ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

▪ ኢየሱስ ለማንም የማያዳላና ሰዎችን የሚያከብር ነበር

▪ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ እውነተኛ ወዳጅ መሆኑን አሳይቷል

▪ ደፋር ነበር

የኢየሱስን ፈለግ የቻልከውን ያህል በጥብቅ ለመከተል ጥረት ታደርጋለህ?

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ሚዛናዊ . . .

በቀላሉ የሚቀረብ . . .

ርኅሩኅ ነበር