በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ—ሰዎች ስለ እሱ ምን ይላሉ?

ኢየሱስ—ሰዎች ስለ እሱ ምን ይላሉ?

ኢየሱስ—ሰዎች ስለ እሱ ምን ይላሉ?

“የናዝሬቱ ኢየሱስ . . . በታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው ሰው እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም።”—ኤች. ጂ. ዌልስ፣ እንግሊዛዊ የታሪክ ምሁር

“ክርስቶስ በታሪክ ውስጥ ከሚጠቀሱት ታላላቅ ሰዎች በሙሉ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ነው።”—ፊሊፕ ሻፍ፣ የስዊስ ተወላጅ የሆነ የሃይማኖትና የታሪክ ምሁር

እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ሰው ተብሎ ለመጠራት ብቃት የሚኖረው ማን ነው? የአንድ ሰው ታላቅነት መመዘን የሚኖርበት በምንድን ነው? በወታደራዊ ስልት አዋቂነቱ? በአካላዊ ጥንካሬው ወይስ በአእምሮ ችሎታው? ወይስ ደግሞ የተናገራቸውና ያደረጋቸው ነገሮች የሰዎችን ሕይወት ምን ያህል መለወጥ ችለዋል እንዲሁም ምን ጥሩ ምሳሌ ትቷል በሚለው ነው?

ቀደም ባሉት ጊዜያት የነበሩም ሆኑ አሁን ያሉ የታሪክ ተመራማሪዎች፣ የሳይንስ ሊቃውንት፣ ምሁራን፣ ጸሐፊዎች፣ የፖለቲካ መሪዎችና ሌሎች ሰዎች ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ምን እንዳሉ ተመልከት፦

“በእነዚህ ሁለት ሺህ ዓመታት ብቻ ሳይሆን በሰው ዘር ታሪክ በሙሉ በጣም ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረው ሰው የናዝሬቱ ኢየሱስ መሆኑን መካድ ምክንያታዊነት የጎደለው አስተሳሰብ ይሆናል።”—ሬይኖልድስ ፕራይስ፣ አሜሪካዊ ጸሐፊና የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር

“ምንም በደል ያልፈጸመ ቢሆንም ጠላቶቹን ጨምሮ ለሌሎች ጥቅም ሲል ራሱን መሥዋዕት አድርጎ በመስጠት ለዓለም ቤዛ የሆነ ሰው ነው። ከዚህ ጋር ሊወዳደር የሚችል በጎ ተግባር ሊገኝ አይችልም።”—ሞሃንዳስ ኬ. ጋንዲ፣ የሕንድ የፖለቲካና መንፈሳዊ መሪ

“ልጅ ሳለሁ በመጽሐፍ ቅዱስና በታልሙድ ላይ የሰፈሩትን መመሪያዎች ተምሬያለሁ። አይሁዳዊ ብሆንም የናዝሬቱ ኢየሱስ ልዩ ባሕርይ በጣም ይማርከኛል።”—አልበርት አንስታይን፣ የጀርመን ተወላጅ የሆነ የሳይንስ ሊቅ

“ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አምላክ ልጅም ሆነ እንደ ሰው ልጅ ስመለከተው በታሪክ ዘመናት ሁሉ እሱን የሚተካከል አላየሁም። የተናገረውና ያደረገው እያንዳንዱ ነገር በዛሬው ጊዜ ለምንገኝ ሰዎች ጠቃሚ ነው፤ በሕይወት ካሉትም ሆነ ከሞቱት ሰዎች መካከል እንዲህ ሊባልለት የሚችል ማንም የለም።”—ሾለም አሽ፣ የፖላንድ ተወላጅ የሆነ ጸሐፊ፣ ክርስቺያን ሄራልድ ከተባለ መጽሔት ላይ የተወሰደ (ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ አይደለንም)

“ለ35 ዓመታት ያህል በምንም ነገር የማላምን ሰው ነበርኩ። ከአምስት ዓመት በፊት ግን ኢየሱስ በሕይወት የነበረ ሰው መሆኑን አመንኩ። በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቶች ላይ እምነት ሳሳድር መላ ሕይወቴ መለወጥ ጀመረ።”—ሊዮ ቶልስቶይ፣ ሩሲያዊ ደራሲና ፈላስፋ

“በታሪክ ውስጥ [የኢየሱስን] ያህል በብዙ ሰዎች ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ያሳደረ ሰው የለም። ወደፊትም የበለጠ ተጽዕኖ ማሳደሩን ይቀጥላል።”—ኬኔት ስኮት ላቱሬቴ፣ አሜሪካዊ የታሪክ ምሁርና ደራሲ

“የኢየሱስ ታሪክ ተራ ልብ ወለድ እንደሆነ አድርገን ማሰብ ይኖርብናል? ወዳጄ፣ ልብ ወለድ ነው የሚያስብል ምንም ነገር የለውም። ትክክለኛነቱን ማንም ሰው የማይጠራጠረው የሶቅራጥስ ታሪክ እንኳ የኢየሱስ ክርስቶስን ያህል በበቂ ማስረጃ የተደገፈ አይደለም።”—ዣን ዣክ ሩሶ፣ ፈረንሳዊ ፈላስፋ

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ በሕይወታችን ውስጥ ልንከተለው የሚገባ አርዓያ የሚሆን ሰው የለም። ኢየሱስ ተከታዩ እንዲሆንና ስለ እሱ ለአሕዛብ እንዲመሠክር በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረውን ጳውሎስን መርጦት ነበር። ይህ የተማረ ሰው ኢየሱስን በትኩረት ‘እንድንመለከት’ አሳስቦናል። (ዕብራውያን 12:2፤ የሐዋርያት ሥራ 9:3) ሕይወታችንን እንዴት መምራት እንዳለብን ከኢየሱስ ምን ትምህርት እናገኛለን? ኢየሱስ ሕይወቱን የመራበት መንገድ ሊጠቅምህ የሚችለው እንዴት ነው?