በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆቻችሁን አስተምሩ

ዳዊት ያልፈራው ለምን ነበር?

ዳዊት ያልፈራው ለምን ነበር?

ፈርተህ ታውቃለህ?— * አንዳንድ ጊዜ ሁላችንም ፍርሃት ይሰማናል። ፍርሃት ሲሰማህ ምን ታደርጋለህ?— ከአንተ ወደሚበልጥና ጠንካራ ወደሆነ ሰው ትሄድ ይሆናል። እርዳታ ለማግኘት ምናልባት ወደ አባትህ ወይም ወደ እናትህ ትሄዳለህ። ፍርሃት ሲሰማን ከማን እርዳታ ማግኘት እንደምንችል ከዳዊት ብዙ እንማራለን። ዳዊት “እምነቴን በአንተ ላይ አደርጋለሁ። . . . በእግዚአብሔር ታምኛለሁ፤ አልፈራም” በማለት ዘምሯል።—መዝሙር 56:3, 4

ዳዊት መፍራት እንደሌለበት የተማረው ከማን ይመስልሃል? ከወላጆቹ ነው?— ከወላጆቹ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ታማኝ የነበረው አባቱ እሴይ፣ አምላክ “የሰላም ልዑል” እንደሚሆን አስቀድሞ የተናገረለት የኢየሱስ ክርስቶስ ቅደመ አያት ነበር። (ኢሳይያስ 9:6፤ 11:1-3, 10) የእሴይ አባት ማለትም የዳዊት አያት ኢዮቤድ ይባላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በኢዮቤድ እናት ስም የተሰየመ አንድ መጽሐፍ አለ። የኢዮቤድ እናት ማን እንደሆነች ታውቃለህ?— የቦዔዝ ሚስት የነበረችው ታማኟ ሩት ናት።—ሩት 4:21, 22

እርግጥ ነው፣ ሩትና ቦዔዝ የሞቱት ዳዊት ከመወለዱ ከረጅም ጊዜ በፊት ነው። የቦዔዝ እናት ማለትም የዳዊት ቅም አያት ማን እንደሆነች ሳታውቅ አትቀርም። ይህቺ ሴት ትኖር የነበረው በኢያሪኮ ሲሆን ሁለት እስራኤላውያን ሰላዮችን ከመሞት አድናለች። የኢያሪኮ ግንብ በፈረሰበት ጊዜ በመስኮቷ በኩል ቀይ ገመድ በማንጠልጠሏ ቤተሰቧ ከጥፋት ሊተርፍ ችሏል። ይህች ሴት ማን ነች?— ከጊዜ በኋላ የይሖዋ አምላኪ የሆነችው ረዓብ ነች። ረዓብ ድፍረት በማሳየት ረገድ ክርስቲያኖች ሊኮርጁት የሚገባ ምሳሌ ትታለች።—ኢያሱ 2:1-21፤ 6:22-25፤ ዕብራውያን 11:30, 31

ወላጆች ታማኝ ስለሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች ለልጆቻቸው እንዲያስተምሩ ታዝዘው ስለነበር የዳዊት አባትና እናትም ስለ እነዚህ ሰዎች ታሪክ ልጃቸውን እንዳስተማሩት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ዘዳግም 6:4-9) የአምላክ ነቢይ የሆነው ሳሙኤል፣ የእሴይን የመጨረሻ ወንድ ልጅ ማለትም ዳዊትን ከጊዜ በኋላ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን እንዲቀባው ትእዛዝ ተሰጠው።—1 ሳሙኤል 16:4-13

አንድ ቀን፣ እሴይ የአምላክ ጠላቶች ከሆኑት ከፍልስጥኤማውያን ጋር በመዋጋት ላይ ለነበሩት ሦስት ትልልቅ ወንዶች ልጆቹ ስንቅ እንዲያደርስ ዳዊትን ላከው። ዳዊት ወንድሞቹ ወደሚዋጉበት ጦር ሰፈር ሲደርስ ግዙፉ ጎልያድ ‘በሕያው አምላክ ሠራዊት’ ላይ ሲሳለቅ ሰማ። ጎልያድን ሊገጥም የደፈረ አንድም እስራኤላዊ አልነበረም። ዳዊት፣ ጎልያድን ለመግጠም እንደሚፈልግ ንጉሥ ሳኦል ሲሰማ አስጠራው። ሆኖም ዳዊት ትንሽ ልጅ መሆኑን ሲያይ “አንተ ገና አንድ ፍሬ ልጅ ነህ” አለው።

ዳዊት ከዚህ ቀደም የቤተሰቡን በግ ነጥቆ ሊወስድ የነበረን አንድ አንበሳ እንዲሁም ድብ እንደገደለ ለሳኦል ነገረው። አክሎም “[ጎልያድም] ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል” አለ። ሳኦል “ሂድ፤ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ካንተ ጋር ይሁን” አለው። ከዚያም ዳዊት አምስት ድቡልቡል ድንጋዮች መርጦ በእረኛ ኮረጆው ውስጥ ከጨመረ በኋላ ወንጭፉን ይዞ ግዙፉን ጎልያድን ለመግጠም ሄደ። ጎልያድ፣ ዳዊት አንድ ፍሬ ልጅ መሆኑን ሲያይ “እስቲ ወደኔ ና! ሥጋህን ለሰማይ አሞሮች . . . እሰጣለሁ” በማለት ጮኸ። ዳዊትም ‘እኔ ግን [በይሖዋ] ስም እመጣብሃለሁ’ አለው፤ እንዲሁም “መትቼ እጥልሃለሁ” ሲል ድምፁን ከፍ አድርጎ ተናገረ።

በዚህ ጊዜ ዳዊት ወደ ጎልያድ እየሮጠ በመሄድ ከኮሮጆው አንድ ድንጋይ ወስዶ ወንጭፉ ላይ አደረገ፤ ከዚያም ወደ ጎልያድ በማስወንጨፍ ግንባሩን መታው። ፍልስጥኤማውያንም ጀግናቸው መሞቱን ባዩ ጊዜ በጣም ስለፈሩ መሸሽ ጀመሩ። ከዚህ በኋላ እስራኤላውያን እነሱን ማሳደዱን ተያያዙት፤ በመጨረሻም ፍልስጥኤማውያንን ድል አደረጓቸው። በ⁠1 ሳሙኤል 17:12-54 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ሙሉውን ታሪክ ከቤተሰብ ጋር ሆነህ አንብበው።

ወጣት በመሆንህ የአምላክን ትእዛዝ መከተል አልፎ አልፎ ያስፈራህ ይሆናል። ኤርምያስ፣ አምላክ እንዲሰብክ ትእዛዝ ሲሰጠው ገና ወጣት ስለነበር መጀመሪያ ላይ ፈርቶ ነበር። አምላክ ግን ‘እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ’ አለው። በመሆኑም ኤርምያስ ፍርሃቱን በማሸነፍ አምላክ ያዘዘውን ፈጽሟል። አንተም እንደ ዳዊትና እንደ ኤርምያስ በይሖዋ የምትታመን ከሆነ ፍርሃትህን ማሸነፍ ትችላለህ።—ኤርምያስ 1:6-8

^ አን.3 ይህን ርዕስ የምታነበው ከልጆች ጋር ከሆነ፣ ይህ ሰረዝ የተደረገው ቆም ብለህ ጥያቄውን ለልጆቹ እንድታቀርብላቸው ለማስታወስ ተብሎ ነው።