በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ግሪክኛ በሚነገርባቸው አገሮች የነበሩት የጥንቶቹ ክርስቲያኖች

ግሪክኛ በሚነገርባቸው አገሮች የነበሩት የጥንቶቹ ክርስቲያኖች

ግሪክኛ በሚነገርባቸው አገሮች የነበሩት የጥንቶቹ ክርስቲያኖች

የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ከሰበኩላቸው ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ግሪክኛ ተናጋሪዎች ነበሩ። እነዚህ ክርስቲያኖች ስለ ኢየሱስ የሚገልጸውን መልእክት ለማብራራት የተጠቀሙባቸው ቅዱሳን መጻሕፍት የተጻፉት በግሪክኛ ነበር። ከጊዜ በኋላ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት የተባሉትን ጽሑፎች በመንፈስ መሪነት ከጻፉት ሰዎች አብዛኞቹ መጻሕፍቱን የጻፉት በግሪክኛ ነው፤ እነዚህ ጸሐፊዎች የተጠቀሙባቸው አገላለጾችና ምሳሌዎች የግሪክ ባሕል ተጽዕኖ አሳድሮባቸው በነበሩ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች በቀላሉ የሚረዷቸው ነበሩ። ይሁንና ኢየሱስም ሆነ ሐዋርያቱ እንዲሁም ከክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ጸሐፊዎች መካከል አንዳቸውም ግሪካውያን አልነበሩም። ሁሉም አይሁዳውያን ነበሩ።—ሮሜ 3:1, 2

ግሪክኛ፣ ለክርስትና መስፋፋት እንዲህ ያለ ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያበረክት የቻለው እንዴት ነው? የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ጸሐፊዎችና ሚስዮናውያን መልእክታቸውን ግሪክኛ ተናጋሪ ለሆኑ ሰዎች በሚማርክ መንገድ ማቅረብ የቻሉትስ እንዴት ነበር? በዚያ ዘመን የተከናወኑት ነገሮች ትኩረታችንን የሚስቡት ለምንድን ነው?

የግሪካውያን ባሕል መስፋፋት

በአራተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ታላቁ እስክንድር የፋርስን መንግሥት ድል ካደረገ በኋላ አብዛኛውን የዓለም ክፍል ለመቆጣጠር ጥረት ማድረግ ጀመረ። ታላቁ እስክንድር በወረራ የያዛቸውን አገሮች አንድ ለማድረግ፣ እሱም ሆነ ከእሱ በኋላ የተነሱት ነገሥታት በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች የግሪክን ቋንቋና ባሕል እንዲከተሉ ጫና አድርገዋል።

ግሪክ፣ በሮም ድል ከተደረገችና ፖለቲካዊ ኃይሏን ካጣች በኋላም እንኳ የግሪክ ባሕል በዙሪያዋ በሚኖሩ አገሮች ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን ቀጥሎ ነበር። በሁለተኛውና በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበሩ የሮም ገዢዎች ሥነ ጥበብን፣ ሥነ ሕንፃን፣ ሥነ ጽሑፍንና ፍልስፍናን ጨምሮ የግሪካውያን ለሆነ ነገር ሁሉ ከፍተኛ አድናቆት ነበራቸው። በዚህም የተነሳ ባለቅኔው ሆራስ እንዲህ ለማለት ተገፋፍቷል፦ “የተማረከችው ግሪክ ድል ያደረጓትን ሕዝቦች ምርኮኛ አድርጋቸዋለች።”

በሮም የግዛት ዘመን በትንሿ እስያ፣ በሶርያና በግብፅ በሚገኙ ትላልቅ ከተሞች ውስጥ የግሪክ ባሕል በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍቶ ነበር። የግሪክን ባሕል ለማስፋፋት የተደረገው ጥረት ከመንግሥትና ከሕግ ተቋማት አንስቶ እስከ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ፋሽን ድረስ ተጽዕኖ ያላሳደረበት መስክ የለም ማለት ይቻላል። በአብዛኞቹ የግሪክ ከተሞች ውስጥ ወጣት ወንዶች የሚሠለጥኑባቸው የስፖርት ማዕከሎች እንዲሁም የግሪክ ድራማዎች የሚታዩባቸው ቲያትር ቤቶች ነበሩ።

የታሪክ ምሁር የሆኑት ኤሚል ሹረር “አይሁዳውያን ቀስ በቀስ ቢሆንም የግሪክን ቋንቋና ባሕል ለማስፋፋት በተደረገው ጥረት መነካታቸው አልቀረም” በማለት ተናግረዋል። መጀመሪያ ላይ፣ አይሁዳውያን ለአምልኳቸው ቅንዓት ስለነበራቸው ከአረማዊ ልማዶች ጋር ንክኪ ያለውን ማንኛውንም የግሪክ ባሕል ላለመከተል ቆርጠው ነበር፤ ውሎ አድሮ ግን የአይሁዳውያኑ አኗኗር እየተለወጠ መጣ። ሹረር እንዲህ በማለት ገልጸዋል፦ “አነስተኛ በሆነ ክልል ውስጥ ይኖሩ የነበሩት አይሁዳውያን የግሪክን ቋንቋና ባሕል በሚከተሉ ሰዎች ተከብበው ስለነበር የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለማካሄድ በየጊዜው ከእነዚህ ሰዎች ጋር መገናኘታቸው የግድ ነበር።”

የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም የተጫወተው ሚና

በርካታ አይሁዳውያን ተሰድደው የሄዱባቸው በሜድትራኒያን አካባቢ የሚገኙት ከተሞች የግሪክን ባሕል ይከተሉ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ነዋሪዎቹም ግሪክኛ ተናጋሪ ነበሩ። በስደት የመጡት እነዚህ አይሁዳውያን ሃይማኖታዊ ልማዶቻቸውን አልተዉም ነበር፤ እንዲሁም በዓመታዊ በዓላት ላይ ለመገኘት ወደ ኢየሩሳሌም ይጓዙ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን አብዛኞቹ የራሳቸውን ቋንቋ ማለትም ዕብራይስጥን እየረሱት መጡ። * በመሆኑም የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን በዘመኑ የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች በሚጠቀሙበት በግሪክኛ ቋንቋ መተርጎም አስፈላጊ ሆነ። በዚህም የተነሳ የግሪካውያን ባሕል ከፍተኛ ተጽዕኖ ባሳደረባት በእስክንድርያ፣ ግብፅ ውስጥ ይኖሩ እንደነበር የሚገመቱ የአይሁድ ምሁራን የትርጉም ሥራውን በ280 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ ጀመሩ። በመጨረሻም የሰብዓ ሊቃናት ትርጉምን ማዘጋጀት ቻሉ።

የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር አከናውኗል። በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙትን ውድ ሀብቶች ለምዕራቡ ዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል። ይህ ትርጉም ባይዘጋጅ ኖሮ አምላክ ከእስራኤላውያን ጋር ስለነበረው ግንኙነት የሚገልጸውን ታሪክ ማወቅ የሚቻልበት መንገድ አይኖርም ነበር። ምክንያቱም ታሪኩ የተጻፈው በዚያን ጊዜ የነበሩ አብዛኞቹ ሰዎች በማይጠቀሙበትና በወቅቱ ወንጌሉን በዓለም ዙሪያ ለማዳረስ ያን ያህል አስተዋጽኦ በሌለው ቋንቋ ነበር። በግሪክኛ የተዘጋጀው የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ግን በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘውን ስለ ይሖዋ አምላክ የሚናገረውን እውቀት የተለያየ ዘር ላላቸው ሰዎች ለማዳረስ አስችሏል። በወቅቱ ግሪክኛ በሰፊው የሚነገር ቋንቋ ስለነበር ስለ አምላክ የሚገልጸውን እውነት ለዓለም ሕዝብ በማሰራጨት ረገድ ከየትኛውም ቋንቋ የበለጠ ጠቀሜታ ነበረው።

ወደ ይሁዲነት የተለወጡና አምላክን የሚፈሩ ሰዎች

በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት፣ አይሁዳውያን ቀደም ሲል ያዘጋጇቸውን አብዛኞቹን ጽሑፎቻቸውን ወደ ግሪክኛ የተረጎሙ ሲሆን አዳዲስ ጽሑፎችን የሚጽፉት ደግሞ በግሪክኛ ነበር። እነዚህ ጽሑፎች የእስራኤልን ታሪክና ሃይማኖት ለአሕዛብ በማሳወቅ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። የታሪክ ምሁራን እንደገለጹት ከሆነ በዚያ ዘመን በርካታ አሕዛብ “ከአይሁዳውያን ጋር በተወሰነ ደረጃ ይገናኙ፣ በአይሁዳውያን የአምልኮ ሥነ ሥርዓቶች ይካፈሉ እንዲሁም የአይሁዳውያንን ሕጎች አንዳንድ ጊዜ በከፊል በሌላ ጊዜ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ይጠብቁ ነበር።”—ዘ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ጁዊሽ ፒፕል ኢን ዚ ኤጅ ኦቭ ጂሰስ ክራይስት

አንዳንድ አሕዛብ የአይሁዳውያንን ሃይማኖታዊ ትምህርቶች በመቀበልና በመገረዝ ወደ ይሁዲነት እስከ መለወጥ ደርሰው ነበር። ሌሎቹ ደግሞ ወደ ይሁዲነት ለመለወጥ እርምጃዎችን ባይወስዱም አንዳንዶቹን የአይሁድ ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ተቀብለዋል። እነዚህ ሰዎች በግሪክኛ ቋንቋ በተዘጋጁ ጽሑፎች ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ፣ “አምላክን የሚፈሩ” ተብለው ተጠቅሰዋል። ቆርኔሌዎስ “በመንፈሳዊ ነገር የተጋና እግዚአብሔርን የሚፈራ” ተብሎ ተጠርቷል። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ከአይሁዳውያን ጋር ከሚቀራረቡ በመላው ትንሿ እስያና ግሪክ ከሚገኙ አምላክን የሚፈሩ ብዙ ሰዎች ጋር ተገናኝቷል። ለምሳሌ በጵስድያ፣ አንጾኪያ በሚገኝ ምኩራብ ውስጥ የተሰበሰቡትን ሰዎች “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ ደግሞም እናንት እግዚአብሔርን የምትፈሩ” በማለት ጠርቷቸው ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 10:2፤ 13:16, 26፤ 17:4፤ 18:4

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ወንጌሉን ከሰበኩላቸው ከይሁዳ ውጪ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ የአይሁድ እምነት ተከታዮች መካከል አብዛኞቹ የግሪክ ባሕል ተጽዕኖ ያሳደረባቸው ነበሩ። በእነዚህ አካባቢዎች የነበረው ሁኔታ ክርስትናን ለማስፋፋት ምቹ ነበር። አምላክ የመዳንን ተስፋ ለአሕዛብ እንኳ ሳይቀር እንደዘረጋ በግልጽ ሲታወቅ ደቀ መዛሙርቱ፣ አምላክ “በአይሁድና በግሪክ” መካከል ልዩነት እንደማያደርግ ተገነዘቡ።—ገላትያ 3:28

ግሪክኛ በሚነገርባቸው አካባቢዎች መስበክ

የአሕዛብን ሃይማኖታዊና ሥነ ምግባራዊ ሁኔታ በሚገባ ያውቁ ስለነበር አንዳንድ የጥንት አይሁዳውያን ክርስቲያኖች፣ ወደ ክርስትና የተለወጡ አሕዛብን የክርስቲያን ጉባኤ አባላት አድርገው ለመቀበል መጀመሪያ ላይ ፈቃደኞች አልነበሩም። አምላክ፣ አሕዛብ የክርስቲያን ጉባኤ አባላት እንዲሆኑ መፍቀዱ ሲታወቅ ግን በኢየሩሳሌም የሚገኙት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ወደ ክርስትና የተለወጡት እነዚህ ሰዎች ከደም፣ ከዝሙትና ከጣዖት መራቅ እንደሚጠበቅባቸው ግልጽ አደረጉላቸው። (የሐዋርያት ሥራ 15:29) የግሪክና የሮም ሰዎች ‘አሳፋሪ በሆነ [የጾታ] ምኞት’ ያበዱና ግብረ ሰዶም በመፈጸም የታወቁ ስለነበሩ የግሪካውያንን የአኗኗር ዘይቤ ይከተል ለነበረ ለማንኛውም ሰው ይህ ትእዛዝ መሰጠቱ በጣም አስፈላጊ ነበር። እንዲህ ያሉት ድርጊቶች በክርስቲያኖች ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም።—ሮሜ 1:26, 27፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከኖሩት ክርስቲያን ሚስዮናውያን መካከል የሐዋርያው ጳውሎስን ያህል ግሪክኛ በሚነገርባቸው አገሮች ውስጥ የሰበከ የለም። በዛሬው ጊዜ ግሪክ ውስጥ ያለችውን አቴናን የሚጎበኙ ሰዎች በአርዮስፋጎስ ኮረብታ ሥር የሚገኝ በነሐስ ላይ የተቀረጸ አንድ ጽሑፍ ማየት ይችላሉ። ይህ ጽሑፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 17 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ጳውሎስ በአቴና ከተማ የሰጠውን ታዋቂ ንግግር ለማስታወስ ተብሎ የተዘጋጀ ነው። ጳውሎስ ንግግሩን የጀመረው በግሪኮች ዘንድ እንደተለመደው “የአቴና ሰዎች ሆይ” በማለት ሲሆን ይህ አባባል የኤፊቆሮስና የኢስጦኢክ ፈላስፎችን ጨምሮ የአድማጮቹን ትኩረት በቀላሉ እንዲያገኝ አስችሎታል። ጳውሎስ ባየው ነገር ከመበሳጨት ወይም የአድማጮቹን እምነት ከመንቀፍ ይልቅ ሰዎቹ ሃይማኖተኞች መሆናቸውን በመግለጽ ጥሩ ውይይት ለማድረግ የሚያስችለውን መንገድ ከፍቷል። “ለማይታወቅ አምላክ” የሚል ጽሑፍ ስላለበት መሠዊያቸው ከጠቀሰ በኋላ ሊነግራቸው የፈለገውም ስለዚህ አምላክ እንደሆነ በመግለጽ በጋራ የሚያስማማቸውን ነጥብ አንስቷል።—የሐዋርያት ሥራ 17:16-23

ጳውሎስ አድማጮቹ ሊቀበሉት የሚችሉትን ሐሳብ ጠቅሷል። ኢስጦኢኮች፣ አምላክ ሰውን እንደፈጠረ፣ የሰው ዘር በሙሉ ከአንድ ወገን እንደተገኘ፣ አምላክ ከእያንዳንዳችን የራቀ እንዳልሆነ እንዲሁም የሰው ሕይወት የተመካው በአምላክ ላይ እንደሆነ ጳውሎስ በተናገረው ሐሳብ ይስማማሉ። ይህ ሐዋርያ የኢስጦኢክ ባለቅኔ የሆኑት ኧራተስ (ፊኖሚና) እና ክሊያንቲዝ (ሂም ቱ ዙስ) ካዘጋጇቸው ጽሑፎች በመጥቀስ የሰው ሕይወት የተመካው በአምላክ ላይ እንደሆነ የተናገረውን ሐሳብ አጠናክሮታል። ኤፊቆሮሳውያንም ቢሆኑ ጳውሎስ ከተናገራቸው ሐሳቦች መካከል በብዙዎቹ ይስማማሉ፤ ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ እንዳለና ሊታወቅ የሚችል እንደሆነ፣ የሚጎድለው ነገር እንደሌለ፣ ከሰው ምንም እንደማይፈልግ እንዲሁም በእጅ በተሠራ መቅደስ ውስጥ እንደማይኖር በገለጸው ሐሳብ ያምናሉ።

ጳውሎስ የተጠቀመባቸው አገላለጾች ለአድማጮቹ እንግዳ አልነበሩም። እንዲያውም አንድ ጽሑፍ እንደተናገረው “ዓለም (ኮስሞስ)፣” “ልጆች” እና “አምላክ” የሚሉት አገላለጾች የግሪክ ፈላስፎች በአብዛኛው የሚጠቀሙባቸው ነበሩ። (የሐዋርያት ሥራ 17:24-29) ጳውሎስ እነዚህን ሰዎች ለመሳብ ሲል እውነት የሆነውን ነገር ከመናገር ወደኋላ አላለም። እንዲያውም ንግግሩን ሲደመድም ስለ ትንሣኤና ስለ ፍርድ የጠቀሳቸው ሐሳቦች ከእነሱ እምነት ጋር የሚጋጩ ነበሩ። ያም ቢሆን የመልእክቱ ይዘትና ንግግሩን ያቀረበበት መንገድ የፍልስፍና አመለካከት ያላቸውን ሰዎች የሚማርክ እንዲሆን ጥረት አድርጓል።

አብዛኞቹ የጳውሎስ ደብዳቤዎች በግሪክ ከተሞች አሊያም የግሪክ ባሕል ከፍተኛ ተጽዕኖ ባሳደረባቸው የሮም ቅኝ ግዛቶች ውስጥ ለሚገኙ ጉባኤዎች የተጻፉ ነበሩ። ጳውሎስ እነዚህን ደብዳቤዎች ሲጽፍ መልእክቱን ጥሩ አድርገው በሚያስተላልፉና ኃይል ባላቸው የግሪክኛ ቃላት የተጠቀመ ሲሆን በግሪካውያን ባሕል ውስጥ የተለመዱ አገላለጾችንና ምሳሌዎችንም ግሩም በሆነ መንገድ ተጠቅሞባቸዋል። ጳውሎስ የአትሌቲክስ ውድድሮችን፣ አሸናፊዎች የሚያገኙትን ሽልማትና አንድን ልጅ ወደ ትምህርት ቤት የሚያደርስን ሞግዚት ጨምሮ የግሪካውያንን የተለያዩ የሕይወት ዘርፎች የሚዳስሱ በርካታ ነገሮችን ጠቅሷል። (1 ቆሮንቶስ 9:24-27፤ ገላትያ 3:24, 25) ከግሪክ ቋንቋ የተወሰዱ አገላለጾችን ቢጠቀምም ግሪካውያን የሚከተሏቸውን የሥነ ምግባር ደንቦችና ሃይማኖታዊ ልማዶች ግን በጥብቅ አውግዟል።

ከሁሉም ጋር ሁሉን ነገር መሆን

ሐዋርያው ጳውሎስ ወንጌሉን ለሰዎች ለማካፈል ሲል ‘ከሁሉም ጋር ሁሉን ነገር መሆን’ እንዳለበት ተገንዝቧል። “አይሁድን እመልስ ዘንድ ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ” በማለት ጽፏል። እንዲሁም የአምላክን ዓላማ እንዲገነዘቡ ለመርዳት ሲል ከግሪካውያን ጋር እንደ ግሪካዊ ሆኖ ነበር። በእርግጥም ጳውሎስ የግሪካውያን ባሕል በገነነባት ከተማ ውስጥ የኖረ አይሁዳዊ እንደመሆኑ መጠን እንደ ግሪካዊ ሆኖ ግሪካውያንን ለመርዳት የተሻለ ብቃት ነበረው። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖችም ሌሎችን በመርዳት ረገድ የጳውሎስን ምሳሌ ለመከተል ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 9:20-23

በዛሬው ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር ተዛውረው ይኖራሉ። በዚህም የተነሳ ከእነሱ የተለየ ባሕል ካላቸው ሰዎች ጋር መኖር ግድ ይሆንባቸዋል። ይህም ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን ወንጌል ለመስበክና ኢየሱስ ‘ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው’ በማለት የሰጠውን ትእዛዝ ለመፈጸም ጥረት ለሚያደርጉ ክርስቲያኖች ሁኔታውን እጅግ ተፈታታኝ ያደርግባቸዋል። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19) እነዚህ ክርስቲያኖች፣ ሰዎች ወንጌሉ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሲነገራቸው ብዙውን ጊዜ ልባቸው እንደሚነካና ለመልእክቱ በጎ ምላሽ እንደሚሰጡ መገንዘብ ችለዋል።

በመሆኑም የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ የተባለው ይህ መጽሔት በየወሩ በ169 ቋንቋዎች የሚታተም ሲሆን ንቁ! መጽሔት ደግሞ በ81 ቋንቋዎች ይዘጋጃል። በተጨማሪም በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ እነሱ አካባቢ ለመጡ ሰዎች ወንጌሉን ለመስበክ ሲሉ የሩስያን ቋንቋ ጨምሮ እንደ አረብኛና ቻይንኛ የመሳሰሉ አስቸጋሪ የሚባሉ ቋንቋዎችን ለመማር ጥረት አድርገዋል። ይህን የሚያደርጉት በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ክርስቲያኖች ሁሉ ምሥራቹን ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ለማዳረስ ሲሉ ነው፤ ይህ ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስ “በሚቻለኝ ሁሉ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፣ ከሁሉም ጋር ሁሉን ነገር ሆንሁ” በማለት ከተናገረው ሐሳብ ጋር ይስማማል።—1 ቆሮንቶስ 9:22

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.10 በኢየሩሳሌም የሚኖሩ በርካታ አይሁዳውያን ግሪክኛ ተናጋሪዎች ነበሩ። ለምሳሌ ያህል፣ “‘የነጻ ወጪዎች’ ምኩራብ ተብሎ የሚጠራው ምኩራብ አባላት የሆኑ፣ ከቀሬናና ከእስክንድርያ እንዲሁም ከኪልቅያና ከእስያ አውራጃዎች የመጡ ሰዎች” የነበሩ ሲሆን የእነዚህ ሰዎች ቋንቋም ግሪክኛ ሳይሆን አይቀርም።—የሐዋርያት ሥራ 6:1, 9

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ሮም

ግሪክ

አቴና

እስያ

በጵስድያ የምትገኘው አንጾኪያ

ኪልቅያ

ይሁዳ

ኢየሩሳሌም

ግብፅ

እስክንድርያ

ቀሬና

የሜድትራኒያን ባሕር

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም” በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሰዎች ስለ ይሖዋ እንዲያውቁ ለመርዳት አስችሏል

[ምንጭ]

Israel Antiquities Authority

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጳውሎስን ንግግር ለማስታወስ ተብሎ የተዘጋጀው በአርዮስፋጎስ የሚገኝ የተቀረጸ ጽሑፍ