በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥቁሩ ቀበቶ የወለቀበት ዕለት

ጥቁሩ ቀበቶ የወለቀበት ዕለት

ከጋና የተላከ ደብዳቤ

ጥቁሩ ቀበቶ የወለቀበት ዕለት

ግለሰቡ እንደጠበቅኩት ዓይነት ሰው አልነበረም። ከጥጥ የተሠራ ያልተጨማደደ ነጭ ካባ ያደረገ ሲሆን አምስት ሴንቲ ሜትር ስፋት ያለው ጥቁር ቀበቶ በቀጭኑ ወገቡ ላይ ጠበቅ አድርጎ አስሯል። ባዶ እግሩን የነበረው ይህ ሰው አቋቋሙ ለድብድብ የተዘጋጀ ይመስላል። እጆቹን ለመሰንዘር ተዘጋጅቶ፣ እግሮቹን ደግሞ ከፈት አድርጎ ቆሟል። ዓይኖቹን ጠበብ አድርጎና ኮስተር ብሎ በትኩረት ሲመለከት ላየው ሰው አስተያየቱ ያስፈራል። ሰውየው ርኅራኄ የሚባል ነገር ያለው አይመስልም።

በድንገት “ሁያ!” የሚል ጩኸት በማሰማት እጆቹን በፍጥነት ካወናጨፈ በኋላ ጣውላውን ሲመታው ሁለት ቦታ እንክት አለ። ከዚያም በባላጋራው ላይ ጥቃት ለመሰንዘር በሚያስገርም ሁኔታ በአየር ላይ ተገለባበጠ። እውነት አሁን ይህ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፍላጎት ያለው ይመስላል?

እኔም ወደዚህ ሰው ጠጋ ብዬ ሰላምታ ለመስጠት እጄን ዘረጋሁ። “ኮጆ ማለት አንተ ነህ መሰለኝ። እንደገባኝ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ትፈልጋለህ” አልኩት። እሱም ፈገግ ብሎ ጨበጠኝ። ፊቱ ላይ የወዳጅነት መንፈስ ይነበብ ነበር። አስፈሪ የነበሩት ዓይኖቹ አሁን የማወቅ ጉጉት እንዳለው ይጠቁማሉ። “አዎ፣ በጣም እፈልጋለሁ። መቼ ነው የምንጀምረው?” በማለት መለሰልኝ።

ከዚያም መጽሐፍ ቅዱሶቻችንንና ለማጥኛ የምንጠቀምባቸውን ጽሑፎች ይዘን የቤቱ በረንዳ ላይ ቁጭ አልን። ቦታው ቀዝቀዝ ያለና ጸጥታ የሰፈነበት ከመሆኑም ሌላ ብቻችንን ለመሆን አመቺ ነበር። የኮጆ ጦጣም አብራን ነበረች። ሠላሳ አምስት ሴንቲ ሜትር ርዝመት ያላት ይህቺ ጦጣ አናቷ ላይ ቀላ ያለ ፀጉር፣ አገጯ ላይ ደግሞ ነጣ ያለ ጺም አላት። ጦጣዋ ስትታይ አስቂኝና ተንኮለኛ ትመስላለች። ደስ የምትልና ተጫዋች የሆነችው ይህቺ ጦጣ አንዴ ጽሑፎቻችን ላይ ትረማመዳለች፤ ሲያሻት ደግሞ እስክሪብቷችንን ትወስዳለች እንዲሁም የሆነ ነገር ለማግኘት የሸሚዛችንን ኪስ ትበረብራለች። ወላጆች የትንንሽ ልጆቻቸው ጫጫታና መቁነጥነጥ እንደማይረብሻቸው ሁሉ ኮጆም የጦጣዋን እንቅስቃሴ ከቁብ ሳይቆጥር ትምህርቱን በትኩረት ይከታተላል። የሚያነሳቸው በርካታ ጥያቄዎች በተማራቸው ነገሮች ላይ ቆም ብሎ እንደሚያስብና የማወቅ ጉጉት እንዳለው ያሳያሉ። ኮጆ ካላመነበትና ከመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ ካልቀረበለት በስተቀር አንድን ነገር እንዲሁ አይቀበልም። ይህ የሆነው የተማረው ካራቴ ንቁና ጠንቃቃ እንዲሆን ስላደረገው ሊሆን ይችላል።

ኮጆ በጥናቱ እየገፋ ሄደ። ይሁንና ከውስጡ ነቅሎ በማውጣት ሊያስወግደው የሚገባ የሚታገለው ነገር እንዳለ አስተዋልኩ። “በዚህ ዓለም ላይ እንደ ማርሻል አርት የምወደው ነገር የለም” አለኝ። ይህ ሰው መታገል የሚወድ ከመሆኑም ሌላ በሕይወቱ ውስጥ ትልቁን ቦታ የያዘው ማርሻል አርት ነበር፤ በዚህ ስፖርትም ተክኗል። ካራቴ በጣም ይወድ የነበረ ከመሆኑም በላይ ችሎታውም አለው፤ በመሆኑም በ26 ዓመቱ ጥቁር ቀበቶ ማግኘት ችሏል። እዚህ ደረጃ ላይ የደረሱት አሊያም መድረስ የሚችሉት ጥቂቶች ብቻ ናቸው።

ኮጆ ምን ውሳኔ ላይ እንደሚደርስ አላውቅም። የካራቴ ስፖርተኛ በመሆን ሰዎችን መጉዳት በእውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል የሚታየው ፍቅር መለያ ከሆኑት እንደ ርኅራኄ፣ አዘኔታና አሳቢነት ያሉ ባሕርያት ጋር የማይጣጣም መሆኑን እንደተገነዘበ ይሰማኛል። ደግሞም የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አስቸጋሪ ባሕርይ የነበራቸውን ሰዎች እንደለወጠ አውቃለሁ። ኮጆም ልቡ ቀና ከሆነ ውሎ አድሮ የአምላክ ቃል ሊለውጠው ይችላል። በመሆኑም መታገስ ይኖርብኛል።

አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ ጥናታችንን ልንጨርስ ስንል አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አነበብን፤ በዚህ ጊዜ ኮጆ ጠንከር ያለ ቡጢ ያረፈበት ያህል ደነገጠ። ያነበበው “እግዚአብሔር ጻድቁንና ኀጥኡን ይመረምራል፤ ዐመፃን የሚወዱትን ግን፣ ነፍሱ ትጠላቸዋለች” የሚለውን ጥቅስ ነበር። (መዝሙር 11:5) “ዐመፃን የሚወዱ” የሚለውን ሐሳብ በቀስታ ለራሱ ደገመው። በአንድ ወቅት ለስፖርቱ ያደረና ግትር የነበረው ሰው ልቡ መለስለስ ጀመረ። ፈገግ ብሎ ዓይን ዓይኔን እያየ “በቃ ቆርጫለሁ” አለኝ።

እኔና ኮጆ በአሁኑ ጊዜ የምንወደውን ሥራ እየሠራን ነው። ይኸውም ፍላጎት ላላቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ያለምንም ክፍያ በፈቃደኝነት እናስተምራለን። ዛሬ ጠዋት ሉክ ከተባለ ወጣት ጋር ለመወያየት ቀጠሮ አለን።

ወደ ሉክ ቤት የሄድነው በገበያ መሃል ሲሆን መንገዱም ጠባብና የተጨናነቀ ነው። በመንገዱ ዳርና ዳር ዕቃዎችን ዘርግተው የሚሸጡ በመቶ የሚቆጠሩ ነጋዴዎች አሉ። በገበያው ውስጥ ከሚታዩት ነገሮች መካከል ቃሪያና በርበሬ፣ በቲማቲም የተሞሉ ቅርጫቶች እንዲሁም ሬዲዮ፣ ጃንጥላ፣ ሳሙና፣ ዊግ፣ የወጥ ቤት ቁሳቁስ ብሎም ያገለገሉ ጫማዎችና ልብሶች ይገኙበታል። በቅመም የተዘጋጁ ትኩስ ምግቦችን በትልቅ ዕቃ አድርገው ያለምንም ችግር በጭንቅላታቸው የተሸከሙ ሴቶች ምግቦቹን ለመሸጥ ወዲያ ወዲህ ይላሉ። እነዚህ ሴቶች የሰዉን ፍላጎት ለመቀስቀስ አካባቢውን የሚያውድ ጣፋጭ ሾርባ እንዲሁም በተጠበሰ ዓሣ፣ በሸርጣንና በቀንድ አውጣ የተሠሩ ወጦችን ይዘው በሕዝቡ መካከል ይዘዋወራሉ። ውሾች፣ ፍየሎችና የሚያስካኩ ዶሮዎች በሰዉ እግር መሃል ይሹለከለካሉ። ሬዲዮና የመኪና ጥሩንባ ይጮኻል፤ ሕዝቡም ይንጫጫል።

ሁካታ የሞላበትን ይህን አካባቢ በመተው አቧራማውን መንገድ ተከትለን የተወሰነ ርቀት ከተጓዝን በኋላ ወደ አንድ ያረጀ ሕንፃ ደረስን። እዚያም በ20ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ የሚገኘውንና ቀጠን ያለ ቁመና ያለውን ሉክን አገኘነው፤ እሱም ፀሐይ ላይ ከምንቆም ወደ ቤት እንድንገባ ጋበዘን። በክፍሉ ውስጥ ለመድኃኒትነት በሚያገለግሉ የደረቁ ተክሎችና ሥራ ሥሮች፣ በገመድ በታሰሩ ቅጠሎችና በዛፍ ቅርፊቶች የተሞሉ ከረጢቶችና ሣጥኖች ይታያሉ። እነዚህ ሁሉ የባሕል ሐኪም የሆኑት አረጋዊ አክስቱ የሚጠቀሙባቸው ናቸው። ከአያት ከቅድመ አያቶቻቸው ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የሕክምና እውቀት በመጠቀም የተለያዩ ሕመሞችን ለመፈወስ የሚረዱ መድኃኒቶችን በዱቄትና በፈሳሽ መልክ ይቀምማሉ። ሉክ የተዝረከረኩትን ነገሮች ካስተካከለ በኋላ ሦስት በርጩማዎችን አዘጋጅቶ ይጠብቀን ነበር። ከቦታው ጥበት የተነሳ ተጠጋግተን ተቀመጥንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት ማድረግ ጀመርን።

ሉክን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ኮጆ ነው። ሁለቱ ወጣቶች በምድር ላይ ሥቃይና መከራ የበዛበትን ምክንያት በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ሐሳብ ሲወያዩ ዝም ብዬ አዳመጥኳቸው። ሉክ አንድ ጥቅስ ለማውጣት ሲቸገር ኮጆ ጥቅሱን ለማውጣት ሲል ጠንካራ በሆኑት እጆቹ ስስ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች በቀስታ ሲገልጥ ተመለከትኩት። በዚህ ጊዜ እነዚህን እጆቹን ለድብድብ ይጠቀምባቸው የነበሩትን ወቅቶች አስታወስኩ። የአምላክ ቃል ሥነ ምግባር በጎደለው በዚህ ዓለም ውስጥ በጣም የተለመዱትን ሥር የሰደዱ መጥፎ ባሕርያት የሚያንጸባርቁ ሰዎች ተለውጠው ርኅሩኅና አፍቃሪ እንዲሆኑ የማድረግ ኃይል አለው። ታዲያ ይህን ከማየት የበለጠ ምን የሚያስደስት ነገር ሊኖር ይችላል?

ወደ ቤታችን ስንመለስ በማንጎ ዛፍ ሥር የተቀመጠ አንድ ሰው አነጋገርን። ኮጆ መጽሐፍ ቅዱስ ገልጦ አንድ ጥቅስ ሲያነብለት በጥሞና አዳመጠው። ይሁንና ሰውየው የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን ሲያውቅ ፍንጥር ብሎ ከተቀመጠበት ተነሳ። “ከእናንተ ጋር መነጋገር አልፈልግም!” በማለት በቁጣ ጮኸ። ኮጆ ለትንሽ ጊዜም ቢሆን ስሜቱ ተናነቀው። በኋላ ግን ራሱን በማረጋጋት ከሰውየው ጋር በሰላም ተለያዩና መንገዳችንን ቀጠልን።

እየተጓዝን ሳለ ኮጆ ወደ እኔ ጠጋ ብሎ በቀስታ እንዲህ አለኝ፦ “ሰውየው እንደዚያ ሲናገረን ደሜ ፈልቶ ነበር። ምን ላደርገው እችል እንደነበር ታውቃለህ?” እኔም ፈገግ አልኩና “በሚገባ!” በማለት መለስኩለት። እሱም ፈገግ አለ፤ ከዚያም ጉዟችንን ቀጠልን።