በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሙታንን ትፈራለህ?

ሙታንን ትፈራለህ?

ሙታንን ትፈራለህ?

በርካታ ሰዎች ለዚህ ጥያቄ “በፍጹም፤ ምን ያስፈራኛል?” የሚል መልስ ይሰጣሉ። እነዚህ ሰዎች፣ ሙታን ምንም የማያውቁ በድን እንደሆኑ ያምናሉ። ይሁን እንጂ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ሙታን፣ መናፍስት ሆነው በሕይወት መኖራቸውን ይቀጥላሉ የሚል ጠንካራ እምነት አላቸው።

በምዕራብ አፍሪካ በምትገኘው በቤኒን የሚኖሩ ብዙ ሰዎች፣ ሙታን ሌሎች የቤተሰቦቻቸውን አባላት ለመግደል ተመልሰው እንደሚመጡ ያምናሉ። በመሆኑም የእንስሳት መሥዋዕት በማቅረብና ከዚህ ጋር የተያያዙ ሥርዓቶችን በመፈጸም የሞተውን ዘመዳቸውን ለመለማመን ሲሉ ንብረታቸውን ይሸጣሉ አሊያም ዕዳ ውስጥ ይዘፈቃሉ። አንዳንዶች፣ መናፍስታዊ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ሲሆን አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ መንፈሱ በሕይወት መኖሩን ይቀጥላል እንዲሁም በሕይወት ካሉት ሰዎች ጋር ይገናኛል የሚል አመለካከት አላቸው። ሌሎች ደግሞ በሕይወታቸው የገጠሟቸውን አስፈሪ ሁኔታዎች ያመጡባቸው የሙታን መናፍስት እንደሆኑ አድርገው ያስባሉ።

በቤኒንና በናይጄሪያ ድንበር አቅራቢያ በሚገኝ አካባቢ የሚኖረው አግቡላ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “በአካባቢያችን መናፍስታዊ ድርጊት መፈጸም የተለመደ ነው። ሰዎች ሙታንን ለመንፈሳዊው ዓለም ለማዘጋጀት ሲሉ አስከሬናቸውን የማጠብ ሥነ ሥርዓት ይፈጽማሉ። ብዙውን ጊዜ አስከሬን የታጠበበትን ሳሙና ሰብስቤ ከቅጠል ጋር እለውሰዋለሁ። ከዚያም ጠመንጃዬን እየቀባሁ ማደን የምፈልገውን እንስሳ ስም ድምፄን ከፍ አድርጌ እጠራለሁ። እንዲህ ያሉ ድርጊቶች የተለመዱ ከመሆናቸውም ሌላ በጣም ውጤታማ ሊመስሉ ይችላሉ። ይሁንና አንዳንድ አስፈሪ የሆኑ መናፍስታዊ ድርጊቶች አሉ።

“ሁለቱ ወንዶች ልጆቼ ባልታወቀ ምክንያት ሲሞቱ የሆነ ሰው አስደግሞብኝ ይሆናል የሚል ጥርጣሬ አደረብኝ። ሁኔታውን ለማጣራት ስል በጥንቆላቸው በጣም ታዋቂ ወደሆኑ አንድ ሽማግሌ ሄድኩ። እሳቸውም ጥርጣሬዬ እውነት መሆኑን አረጋገጡልኝ። ይባስ ብሎ ደግሞ ልጆቼ ገዳያቸው ሲሞት እሱን ለማገልገል በመንፈሳዊው ዓለም እየተጠባበቁ መሆኑን ነገሩኝ። ሽማግሌው፣ ሦስተኛው ልጄም ቢሆን ተመሳሳይ ዕጣ እንደሚገጥመው አረዱኝ። እንዳሉትም ከጥቂት ቀናት በኋላ ልጄ ሞተ።”

ከጊዜ በኋላ አግቡላ ጎረቤት አገር በሆነችው በናይጄሪያ ከሚኖረው ጆን ከተባለ የይሖዋ ምሥክር ጋር ተገናኘ። ጆን መጽሐፍ ቅዱስን እየጠቀሰ ሙታን ያሉበትን ሁኔታ አስረዳው። ይህ ውይይት የአግቡላን መላ ሕይወት ለወጠው። ይህን ማወቅህ የአንተንም ሕይወት ሊለውጠው ይችላል።

ሙታን ሕያዋን ናቸው?

ለዚህ ጥያቄ ትክክለኛውን መልስ ሊሰጥ የሚችለው ማን ነው? የትኛውም ሰው ምንም ያህል የታወቀ ቢሆን ለዚህ ጥያቄ ትክክለኛ መልስ ሊሰጥ አይችልም። ከዚህ ይልቅ ይህን መልስ መስጠት የሚችለው ‘የሚታዩትንና የማይታዩትን ነገሮች ጨምሮ በሰማያትና በምድር ያሉትን’ ሕያዋን ነገሮች በሙሉ የፈጠረው ይሖዋ ነው። (ቆላስይስ 1:16) አምላክ መላእክትን በመንፈሳዊው ዓለም፣ ሰውንና እንስሳን ደግሞ በምድር ላይ እንዲኖሩ ፈጥሯል። (መዝሙር 104:4, 23, 24) ማንኛውም ሕይወት የተመካው በእሱ ላይ ነው። (ራእይ 4:11) እንግዲያው የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሞት ምን እንደሚል እንመርምር።

ሞትን አስመልክቶ ለመጀመሪያ ጊዜ የተናገረው ይሖዋ ነው። አዳምና ሔዋን ካልታዘዙት እንደሚሞቱ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸው ነበር። (ዘፍጥረት 2:17) ትሞታላችሁ ሲላቸው ምን ማለቱ ነበር? ይሖዋ ሁኔታውን ሲገልጽ “ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህ” ብሏል። (ዘፍጥረት 3:19) አንድ ሰው ሲሞት አካሉ ይበሰብስና ዐፈር ይሆናል። ሕይወቱ ያከትማል።

አዳምና ሔዋን ሆን ብለው የአምላክን ሕግ በመጣሳቸው ሞት ተበየነባቸው። ይሁንና ሞትን የቀመሱት የመጀመሪያዎቹ ሰዎች እነሱ አይደሉም። ከዚህ ይልቅ መጀመሪያ የሞተው ልጃቸው አቤል ሲሆን የገደለውም ታላቅ ወንድሙ ቃየን ነበር። (ዘፍጥረት 4:8) ቃየን፣ ‘የሞተው ወንድሜ ይበቀለኛል’ የሚል ፍራቻ አልነበረውም። ከዚህ ይልቅ ቃየን ያሳሰበው በሕይወት ያሉት ሰዎች ሊያደርሱበት የሚችሉት ጉዳት ነበር።—ዘፍጥረት 4:10-16

ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ ንጉሥ ሄሮድስ ኮከብ ቆጣሪዎች በእሱ ግዛት ውስጥ “የአይሁድ ንጉሥ” እንደተወለደ ሲነግሩት ተደናገጠ። ሄሮድስ ሥልጣኔን ሊቀናቀነኝ ይችላል ብሎ ያሰበውን ይህን ልጅ ለማጥፋት ቆርጦ በመነሳት በቤተልሔም የነበሩትን ሁለት ዓመት የሞላቸውንና ከዚያ በታች የሆኑ ሕፃናት በሙሉ ለመግደል ዕቅድ አወጣ። ሆኖም አንድ መልአክ ኢየሱስንና ማርያምን ‘ይዞ ወደ ግብፅ እንዲሸሽ’ ለዮሴፍ ማስጠንቀቂያ ሰጠው።—ማቴዎስ 2:1-16

ሄሮድስ ሲሞት መልአኩ “የሕፃኑን ነፍስ የሚፈልጉት ሰዎች ስለሞቱ” ወደ እስራኤል እንዲመለስ ለዮሴፍ ነገረው። (ማቴዎስ 2:19, 20) መንፈሳዊ ፍጡር የሆነው ይህ መልአክ፣ ሄሮድስ ከሞተ በኋላ ኢየሱስን ሊጎዳው እንደማይችል ያውቅ ነበር። ዮሴፍም ቢሆን በሞት ያንቀላፋውን ንጉሥ ሄሮድስን አልፈራም። ከዚህ ይልቅ ዮሴፍ የፈራው ጨካኝ የሆነውን የሄሮድስን ልጅ አርኬላዎስን ነበር። ስለሆነም ዮሴፍ ቤተሰቡን ይዞ ከአርኬላዎስ ግዛት ውጪ በምትገኘው በገሊላ መኖር ጀመረ።—ማቴዎስ 2:22

እነዚህ ዘገባዎች ሙታን ምንም ኃይል እንደሌላቸው እንድንገነዘብ ይረዱናል። ታዲያ አግቡላና ሌሎች ስለገጠሟቸው ሁኔታዎች ምን ማለት ይቻላል?

‘አጋንንት’ ወይም ርኩሳን መናፍስት

ኢየሱስ ካደገ በኋላ ክፉ መንፈሳዊ ፍጡራን አጋጥመውት ነበር። እነዚህ መንፈሳዊ ፍጡራን ማንነቱን ያወቁ ሲሆን “የአምላክ ልጅ” ሲሉ ጠርተውታል። ኢየሱስም ቢሆን ማንነታቸውን አውቆ ነበር። እነዚህ ፍጡራን የሙታን መናፍስት አልነበሩም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ ‘አጋንንት’ ወይም ርኩሳን መናፍስት መሆናቸውን ገልጿል።—ማቴዎስ 8:29-31፤ 10:8፤ ማርቆስ 5:8

መጽሐፍ ቅዱስ ለአምላክ ታማኝ ስለሆኑ እንዲሁም በእሱ ላይ ስላመጹ መንፈሳዊ ፍጥረታት ይናገራል። የዘፍጥረት መጽሐፍ ይሖዋ ታዛዥ ሳይሆኑ የቀሩትን አዳምንና ሔዋንን ከኤደን ገነት ሲያስወጣቸው ማንም ወደ ገነት እንዳይገባ ለማገድ ከኤደን በስተ ምሥራቅ ኪሩቦችን ወይም መላእክትን አቁሞ እንደነበር ይገልጻል። (ዘፍጥረት 3:24) ይህ ደግሞ መንፈሳዊ ፍጡራን ለሰው ልጆች ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለጡበት ወቅት ሳይሆን አይቀርም።

ይህ ከሆነ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው መላእክት የሰው አካል ለብሰው ወደ ምድር መጡ። እነዚህ መላእክት ወደ ምድር የመጡት ይሖዋ ልኳቸው ሳይሆን በመንፈሳዊው ዓለም የነበረውን ‘ትክክለኛ መኖሪያቸውን ትተው’ ነው። (ይሁዳ 6) ይህን ያደረጉት በራስ ወዳድነት ተነሳስተው ነው። ሚስት አግብተው ኔፊሊም የተባሉ ዲቃላ ልጆችን ወለዱ። ኔፊሊሞችና ዓመጸኞች የሆኑት አባቶቻቸው ምድር በዓመጽና በክፋት እንድትሞላ አደረጉ። (ዘፍጥረት 6:1-5) ይሖዋ በኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ በማምጣት ይህን አስከፊ ሁኔታ አስወገደው። የጥፋት ውኃው ክፉ ወንዶችንና ሴቶችን እንዲሁም ኔፊሊሞቹን ጠራርጎ አጠፋ። መላእክቱስ ምን ሆኑ?

የጥፋት ውኃው ወደ መንፈሳዊው ዓለም እንዲመለሱ አስገደዳቸው። ሆኖም ይሖዋ “መጀመሪያ የነበራቸውን ቦታ” መልሰው እንዲያገኙ አልፈቀደላቸውም። (ይሁዳ 6) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አምላክ ኃጢአት የሠሩትን መላእክት ከመቅጣት ወደኋላ አላለም፤ ከዚህ ይልቅ በድቅድቅ ጨለማ በተዋጠ ጉድጓድ ውስጥ ሆነው ፍርዳቸውን እንዲጠባበቁ ወደ እንጦሮጦስ ጣላቸው።”—2 ጴጥሮስ 2:4

እንጦሮጦስ የሚለው ቃል አንድን የተወሰነ ቦታ የሚያመለክት ሳይሆን የተባረሩት መላእክት ተዋርደውና እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ እንደ እስር ቤት ባለ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ የሚያሳይ ነው። በአሁኑ ጊዜ አጋንንት የሰው አካል መልበስ ባይችሉም ከፍተኛ ኃይል አላቸው፤ እንዲሁም በሰዎች አስተሳሰብና ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ሰዎችንና እንስሳትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ኃይል አላቸው። (ማቴዎስ 12:43-45፤ ሉቃስ 8:27-33) በተጨማሪም የሙታን መናፍስት መስለው በመቅረብ ሰዎችን ያታልላሉ። እንዲህ የሚያደርጉት ለምንድን ነው? ሰዎች፣ ይሖዋን እሱን በሚያስደስት መንገድ እንዳያመልኩትና ሙታን ያሉበትን ሁኔታ በትክክል እንዳይረዱ ለማድረግ ነው።

ፍርሃትን ማሸነፍ የሚቻለው እንዴት ነው?

አግቡላ ሞትንና የመናፍስትን ማንነት አስመልክቶ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተሰጠው ማብራሪያ አሳማኝ ሆኖ አገኘው። በመሆኑም ስለ ጉዳዩ ይበልጥ ማወቅ እንዳለበት ተሰማው። መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ከጆን ጋር ማጥናት ጀመረ። ገዳያቸውን ለማገልገል በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ሆነው በመጠባበቅ ላይ ናቸው የተባሉት ልጆቹ መቃብር ውስጥ በሞት አንቀላፍተው እንደሚገኙ ማወቁ አጽናናው።—ዮሐንስ 11:11-13

ከዚህም በተጨማሪ አግቡላ ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ሙሉ በሙሉ መራቅ እንዳለበት ተገነዘበ። ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር ንክኪ ያላቸውን ዕቃዎቹን በሙሉ አቃጠለ። (የሐዋርያት ሥራ 19:19) በአካባቢው ያሉ አንዳንድ ሰዎች መናፍስቱ ሊጎዱት እንደሚችሉ በመግለጽ አስጠነቀቁት። ይሁንና አግቡላ ፈጽሞ አልፈራም። በ⁠ኤፌሶን 6:11, 12 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ አድርጓል፦ “ከአምላክ የሚገኘውን ሙሉ የጦር ትጥቅ ልበሱ፤ . . . ምክንያቱም ትግል የምንገጥመው . . . ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር ነው።” ይህ መንፈሳዊ የጦር ትጥቅ እውነትን፣ ጽድቅን፣ የሰላምን ምሥራች፣ እምነትንና የአምላክ ቃል የሆነውን የመንፈስን ሰይፍ ያጠቃልላል። እንዲህ ያለው የጦር ትጥቅ የሚገኘው ከአምላክ ሲሆን ከፍተኛ ኃይል አለው!

አግቡላ ከመናፍስታዊ ድርጊቶች መራቅ ሲጀምር አንዳንድ ወዳጆቹና ዘመዶቹ አገለሉት። ይሁን እንጂ በአካባቢው በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ መሰብሰብ ከጀመረ በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚመሩ አዳዲስ ወዳጆች ማፍራት ቻለ።

አግቡላ፣ ይሖዋ በቅርቡ ምድርን ከክፋት እንደሚያጸዳትና ከአጋንንት ተጽዕኖ ነፃ እንደሚያደርጋት ተገንዝቧል። ውሎ አድሮም አምላክ፣ አጋንንትን ያጠፋቸዋል። (ራእይ 20:1, 2, 10) በተጨማሪም ‘በመታሰቢያ መቃብር ያሉትን ሁሉ’ በምድር ላይ እንዲኖሩ ከሞት ያስነሳቸዋል። (ዮሐንስ 5:28, 29) ከእነዚህም መካከል አቤል፣ ንጉሥ ሄሮድስ ያስገደላቸው ምንም የማያውቁ ሕፃናት እንዲሁም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ይገኙበታል። አግቡላ፣ ሦስት ልጆቹ ከሞት እንደሚነሱ ጠንካራ እምነት አለው። በሞት ያጣሃቸው ወዳጅ ዘመዶችህም ከእነዚህ መካከል ሊገኙ ይችላሉ። እነዚህ ሰዎች ትንሣኤ ሲያገኙ በሞት አንቀላፍተው በቆዩበት ወቅት ሁሉ በድን እንደነበሩና ከእነሱ ጋር በተያያዘ ስለተከናወኑት ሥነ ሥርዓቶች ምንም የሚያውቁት ነገር እንዳልነበር ያረጋግጡልናል።

የሞቱ ሰዎችን የምትፈራበት ምንም ምክንያት የለም። ከዚህ ይልቅ በሞት ያጣሃቸውን የምትወዳቸውን ሰዎች ዳግመኛ የምታገኝበትን ጊዜ በጉጉት ልትጠባበቅ ትችላለህ። እስከዚያው ድረስ ግን እምነትህን ለማጠናከር መጽሐፍ ቅዱስን ለምን አታጠናም? በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከሚመሩ ሰዎች ጋር ተቀራረብ። በጨዋታ መልክም ይሁን በማንኛውም ዓይነት መንገድ ከመናፍስታዊ ድርጊት ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ እንዳይኖርህ ቆራጥ እርምጃ ውሰድ። “ከአምላክ የሚገኘውን ሙሉ የጦር ትጥቅ” በመልበስ ከአጋንንት ጥቃት ራስህን ጠብቅ። (ኤፌሶን 6:11) የይሖዋ ምሥክሮች አንተን ለመርዳት ፈቃደኞች ናቸው። ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? * የተባለውን መጽሐፍ በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ሊያስጠኑህ ይችላሉ።

አግቡላ አጋንንትን መቋቋም የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ስለተማረ ሙታንን አይፈራም። እንዲህ ብሏል፦ “ሦስቱን ልጆቼን ማን እንደገደላቸው አላውቅም። ይሖዋን ማገልገል ከጀመርኩ በኋላ ሰባት ልጆችን የወለድኩ ሲሆን በመንፈሳዊው ዓለም ያለ ማንኛውም አካል በልጆቼ ላይ ጉዳት አድርሶ አያውቅም።”

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.25 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አግቡላ አጋንንትን መቋቋም የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ስለተማረ ሙታንን አይፈራም

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቃየን፣ ‘የሞተው ወንድሜ ይበቀለኛል’ የሚል ፍራቻ አልነበረውም