በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሚስዮናውያን በስተ ምሥራቅ የት ድረስ ተጉዘው ሊሆን ይችላል?

ሚስዮናውያን በስተ ምሥራቅ የት ድረስ ተጉዘው ሊሆን ይችላል?

ሚስዮናውያን በስተ ምሥራቅ የት ድረስ ተጉዘው ሊሆን ይችላል?

ኢየሱስ ከሞተ በኋላ 30 ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ ምሥራቹ ከሰማይ በታች ባለ “ፍጥረት ሁሉ” ዘንድ እንደተሰበከ ጽፏል። (ቆላስይስ 1:23) የጳውሎስ አነጋገር ቃል በቃል መወሰድ የለበትም፤ ይህን ሲል በዚያን ዘመን የነበረ እያንዳንዱ ግለሰብ ምሥራቹን ሰምቷል ማለቱ አልነበረም። ጳውሎስ ሊያስተላልፍ የፈለገው ሐሳብ ግልጽ ነው፤ ክርስቲያን ሚስዮናውያን በዚያን ጊዜ በነበረው ዓለም ምሥራቹን በስፋት ሰብከው ነበር።

እነዚህ ሚስዮናውያን የት ድረስ ተጉዘው ሊሆን ይችላል? ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ጳውሎስ የንግድ መርከቦችን በመጠቀም በስተ ምዕራብ እስከ ጣሊያን ድረስ የስብከቱን ሥራ ማከናወን እንደቻለ ይናገራሉ። ይህ መንፈሰ ጠንካራ ሚስዮናዊ በስፔን የመስበክ ፍላጎትም ነበረው።—የሐዋርያት ሥራ 27:1፤ 28:30, 31፤ ሮም 15:28

የጥንቶቹ ወንጌላውያን በምሥራቅ አቅጣጫስ እስከ የት ድረስ ተጉዘዋል? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚገልጸው ነገር ስለሌለ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ይሁን እንጂ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የንግድ መርከቦች ከሜድትራንያን ተነስተው ወደ ሩቅ ምሥራቅ ምን ያህል ርቀት ይጓዙ እንደነበር ስታውቅ ሳትገረም አትቀርም። ክርስቲያን ሚስዮናውያን የት ድረስ እንደተጓዙ ባናውቅም እንኳ እንዲህ ያሉ የንግድ መስመሮች መኖራቸውን ማወቃችን በዚያ ዘመን ወደ ምሥራቅ ለመጓዝ የሚያስችሉ ጥሩ አጋጣሚዎች እንደነበሩ እንድንገነዘብ ያስችለናል።

እስክንድር ትቶት ያለፈው ነገር

ታላቁ እስክንድር የተለያዩ አገሮችን ድል እያደረገ በስተ ምሥራቅ በባቢሎንና በፋርስ በኩል አልፎ በሰሜን ሕንድ እስከምትገኘው እስከ ፑንጃብ ድረስ መጓዝ ችሎ ነበር። ግሪካውያን ይህን ጉዞ ባደረጉበት ወቅት የኤፍራጥስ ወንዝ ወደ ፋርስ ባሕረ ሰላጤ ከሚገባበት ቦታ አንስቶ የኢንደስ ወንዝ ከዓረቢያን ባሕር ጋር እስከሚቀላቀልበት ስፍራ ድረስ ያሉትን የባሕር ዳርቻዎች መመልከት ችለዋል።

ብዙም ሳይቆይ ቅመማ ቅመሞችና ዕጣን የጫኑ መርከቦች ሕንድ ውቅያኖስን አቋርጠው በቀይ ባሕር በኩል ወደ ግሪክ ግዛት መትመም ጀመሩ። ይህን ንግድ መጀመሪያ የተቆጣጠሩት የሕንድና የዓረብ ነጋዴዎች ነበሩ። ይሁንና ግብፅን ይገዙ የነበሩት የቶለሚ ነገሥታት፣ ከደቡብ እስያ አካባቢ ነፋሳት የሚነሱበትን ወቅት በማጥናት በሕንድ ውቅያኖስ ላይ በሚካሄደው ንግድ ውስጥ እነሱም መሳተፍ ጀመሩ።

ከግንቦት እስከ መስከረም ባሉት ወራት ከደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ያለማቋረጥ የሚነፍሱት ነፋሳት፣ መርከቦች ቀይ ባሕር ከሕንድ ውቅያኖስ ጋር ከሚገናኝበት ቦታ በመነሳት የዓረብን ምድር ደቡባዊ የባሕር ዳርቻ ተከትለው እንዲሄዱ አሊያም በቀጥታ ወደ ደቡብ ሕንድ እንዲጓዙ ይረዷቸው ነበር። ከኅዳር እስከ መጋቢት ባሉት ወራት ደግሞ ነፋሳቱ ወደ ተቃራኒው አቅጣጫ ስለሚነፍሱ መርከቦቹ ወደመጡበት ስፍራ በቀላሉ መመለስ ይችላሉ። የዓረብና የሕንድ ባሕረተኞች ስለ እነዚህ ነፋሳት ያላቸውን እውቀት በመጠቀም ለበርካታ መቶ ዓመታት ብርጉድ፣ ቀረፋ፣ ናርዶስና በርበሬ እየጫኑ ከሕንድ ወደ ቀይ ባሕር ሲያጓጉዙ ኖረዋል።

ወደ እስክንድርያና ወደ ሮም የሚወስዱ የባሕር መስመሮች

ሮማውያን፣ የእስክንድር ወራሾች ይገዟቸው የነበሩትን አገሮች ድል አድርገው ከያዙ በኋላ ሮም ከምሥራቁ ዓለም ለሚመጡ ውድ ሸቀጣ ሸቀጦች ዋነኛ የመገበያያ ስፍራ ሆነች፤ የዝሆን ጥርስ ከአፍሪካ፣ ዕጣንና ከርቤ ከዓረብ ምድር፣ ቅመማ ቅመሞችና የከበሩ ድንጋዮች ከሕንድ እንዲሁም ሐር ከቻይና ይጫን ነበር። እነዚህን ሸቀጣ ሸቀጦች የያዙ መርከቦች የግብፅ ግዛት በሆነው የቀይ ባሕር ዳርቻ የሚገኙትን በረናይሲና ሚኦስ ኦርሞስ የተባሉ ሁለት ዋና ዋና ወደቦችን ሳይረግጡ አያልፉም ነበር። ሁለቱም ወደቦች፣ በዓባይ ወንዝ አጠገብ ወደምትገኘው ወደ ኮፕቶስ በሚወስዱ የንግድ መስመሮች ይጠቀሙ ነበር።

ከኮፕቶስ የተጫኑ ሸቀጦች የግብፅ የደም ሥር በሆነው በዓባይ ወንዝ በኩል ወደ እስክንድርያ ከተጓጓዙ በኋላ በመርከብ ተጭነው ወደ ጣሊያንና ወደ ሌሎች አካባቢዎች ይወሰዳሉ። ወደ እስክንድርያ የሚወስደው ሌላው መስመር ደግሞ በዘመናዊው የሱዌዝ ወደብ አቅራቢያ የሚገኘውን የቀይ ባሕር የላይኛውን ክፍል ከዓባይ ጋር ያገናኝ የነበረው ቦይ ነው። በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ግብፅም ሆነች ወደቦቿ ኢየሱስ ሲሰብክባቸው ከነበሩት ቦታዎች ብዙም የማይርቁ በመሆናቸው አንድ ሰው በቀላሉ ወደ እነዚህ አካባቢዎች መሄድ ይችል ነበር።

በአንደኛው መቶ ዘመን ይኖር የነበረ ስትራቦ የተባለ ግሪካዊ የጂኦግራፊ ተመራማሪ እንደገለጸው ከሆነ በዚያን ዘመን በየዓመቱ 120 የንግድ መርከቦች ከሚኦስ ኦርሞስ ወደ ሕንድ ይሄዱ ነበር። በዚህ አካባቢ ይደረግ ስለነበረው የባሕር ጉዞ የሚገልጹ መረጃዎችን የያዘ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተዘጋጀ አንድ መጽሐፍ አሁንም ድረስ ይገኛል። ይህ መጽሐፍ፣ ግሪክኛ ቋንቋ የሚናገር ግብፃዊ ነጋዴ ሌሎች ነጋዴዎችን ለመርዳት ብሎ የጻፈው እንደሆነ ይገመታል። ከዚህ ጥንታዊ መጽሐፍ ምን መረጃዎችን ማግኘት ይቻላል?

ፐሪፕለስ ማረስ ኤሪትራኤ (በኤሪትሪያን ባሕር የሚደረግ ጉዞ) በተባለው የላቲን ስያሜው የሚታወቀው ይህ መጽሐፍ ከደቡባዊ ግብፅ አንስቶ እስከ ዛንዚባር ድረስ በሺህ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርዝማኔ ያላቸው የባሕር መስመሮች እንደነበሩ ይገልጻል። ይህን መጽሐፍ ያዘጋጀው ሰው፣ በስተ ምሥራቅ አቅጣጫ ከዓረብ ምድር ደቡባዊ ዳርቻ አንስቶ በሕንድ ምዕራባዊ ዳርቻ በኩል እስከ ስሪላንካ እንዲሁም ከሕንድ ምሥራቃዊ የባሕር ዳርቻ እስከ ጋንጀስ ያለውን ርቀት፣ መርከቦች መልሕቅ የሚጥሉባቸውን ስፍራዎች፣ የገበያ ቦታዎችን፣ ሸቀጣ ሸቀጦችን እንዲሁም በእነዚህ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችን ባሕርይ ዘርዝሯል። መጽሐፉ ትክክለኛና ግልጽ መረጃዎችን የያዘ መሆኑ ጸሐፊው ወደ እነዚህ ቦታዎች ሄዶ እንደነበር ይጠቁማል።

ወደ ሕንድ የሄዱ ምዕራባውያን

ሕንዳውያን፣ ምዕራባውያን ነጋዴዎችን ያቫናስ ብለው ይጠሯቸው ነበር። ፐሪፕለስ የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው ከሆነ ምዕራባውያን ነጋዴዎች በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ አዘውትረው ይጓዙባቸው ከነበሩት ቦታዎች አንዷ በሕንድ ደቡባዊ ጫፍ አቅራቢያ የምትገኘው የሙዚሪስ ወደብ ነች። * ከክርስቶስ ልደት በኋላ በመጀመሪያዎቹ መቶ ዘመናት በታሚል ቋንቋ የተጻፉ ግጥሞች ስለ እነዚህ ነጋዴዎች በተደጋጋሚ ይናገራሉ። ከእነዚህ ግጥሞች አንዱ እንዲህ ይላል፦ “ውብ የሆኑት የያቫናስ መርከቦች ወርቅ ይዘው ይመጡና በርበሬ ጭነው ይመለሳሉ፤ ሙዚሪስም በሰዎች ጫጫታ ትሞላለች።” ሌላ ግጥም ደግሞ በደቡባዊ ሕንድ የሚኖር አንድ ልዑል፣ ያቫናስ ያመጡትን ጥሩ መዓዛ ያለውን ወይን ጠጅ እንዲጠጣ ግብዣ ቀርቦለት እንደነበር ይገልጻል። በሕንድ ገበያ ተፈላጊ ከነበሩት የምዕራባውያን ሸቀጣ ሸቀጦች መካከል የብርጭቆ ዕቃዎች፣ ብረታ ብረት፣ ዛጎልና ጨርቃ ጨርቅ ይገኙበታል።

አርኪኦሎጂስቶች፣ ከምዕራቡ ዓለም ወደ ሕንድ የተለያዩ ሸቀጦች ይገቡ እንደነበር የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎችን አግኝተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በሕንድ ደቡባዊ ምሥራቅ ዳርቻ በምትገኘው በአሪካሜዱ የሮማውያን የወይን ጠጅ ማሰሮና የሳህን ስብርባሪዎች ተገኘተዋል፤ እነዚህ ስብርባሪዎች፣ ዕቃዎቹ በመካከለኛው ጣሊያን በምትገኘው በአሬትሶ ይኖሩ በነበሩት ሸክላ ሠሪዎች የተሠሩ እንደሆኑ የሚጠቁም ማኅተም አላቸው። አንድ ጸሐፊ እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ተመራማሪ፣ በአሬትሶ ከተማ ዳርቻ ይኖሩ የነበሩ የእጅ ባለሞያዎችን ስም የያዙ የሸክላ ስብርባሪዎችን በቤንጋል የባሕር ወሽመጥ ደለል ውስጥ ተቀብረው ሲያገኝ በዚያ ዘመን የነበረው ሁኔታ በዓይነ ሕሊናው ይታየዋል።” በደቡብ ሕንድ የተገኙ በርካታ የሮማውያን የወርቅ እንዲሁም የብር ሳንቲሞች በሜድትራንያን አካባቢ በነበሩ አገሮችና በሕንድ መካከል የንግድ ግንኙነት እንደነበር ተጨማሪ ማስረጃ ይሆናሉ። አብዛኞቹ ሳንቲሞች በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የተሠሩ ሲሆኑ የሮማውያን ነገሥታት የሆኑትን የአውግስጦስን፣ የጢባርዮስንና የኔሮን ምስል ይዘዋል።

በአሁኑ ጊዜ የሚገኝ በመካከለኛው መቶ ዘመን የተዘጋጀ አንድ ጥንታዊ ካርታ፣ ሮማውያን በደቡብ ሕንድ በቋሚነት የያዟቸው የንግድ ቦታዎች እንደነበሯቸው ይጠቁማል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የነበረውን የሮማውያን ግዛት እንደሚያሳይ የሚነገርለት ፖይቲንገር ቴብል በመባል የሚታወቀው ይህ ካርታ፣ በሙዚሪስ የአውግስጦስ ቤተ መቅደስ ይገኝ እንደነበር ያመለክታል። ሮምስ ኢስተርን ትሬድ፦ ኢንተርናሽናል ኮሜርስ ኤንድ ኢምፔርያል ፖሊሲ 31 ቢሲ–ኤዲ 305 የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል፦ “ይህን ሕንፃ ሊሠሩ የሚችሉት በሮም መንግሥት ቁጥጥር ሥር የነበሩ ሰዎች መሆን አለባቸው፤ እነዚህ ሰዎች ምናልባት በሙዚሪስ ይኖሩ የነበሩ ወይም በዚያ አካባቢ ለረጅም ጊዜ የቆዩ ሳይሆኑ አይቀሩም።”

የሮማውያን የታሪክ መዛግብት፣ ከ27 ከክርስቶስ ልደት በፊት እስከ 14 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ባለው በአውግስጦስ የግዛት ዘመን ሦስት የሕንድ ልዑካን ወደ ሮም ሄደው እንደነበር ይጠቁማሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ የተካሄደ አንድ ጥናት “እነዚህ ልዑካን” ወደ ሮም የሄዱት “ከበድ ያለ ዲፕሎማሲያዊ ድርድር” ለማድረግ እንደነበር ይገልጻል፤ ድርድሩ የተካሄደው በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች የሚገበያዩባቸውን፣ ቀረጥ የሚሰበሰብባቸውንና የውጭ አገር ሰዎች የሚኖሩባቸውን ቦታዎች ለመወሰን እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ነበር።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የንግድ መርከቦች በሜድትራንያን አካባቢዎች ካሉ አገሮች ወደ ሕንድ አዘውትረው ይመላለሱ ነበር። ከቀይ ባሕር በስተ ሰሜን ባለ አካባቢ የሚኖር አንድ ክርስቲያን ሚስዮናዊ በቀላሉ በመርከብ ወደ ሕንድ መሄድ ይችል ነበር።

ከሕንድ አልፈው ሄደዋል?

በሜድትራንያን አካባቢ የሚኖሩ ነጋዴዎችና ሌሎች ተጓዦች በስተ ምሥራቅ የት ድረስ እንደሄዱ እንዲሁም ጉዞ ማድረግ የጀመሩት ከመቼ ጀምሮ እንደሆነ በእርግጠኝነት ማወቅ አስቸጋሪ ነው። ይሁን እንጂ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ አንዳንድ ምዕራባውያን እስከ ታይላንድ፣ ካምቦዲያ፣ ሱማትራና ጃቫ ድረስ እንደተጓዙ ይታመናል።

ከ23 እስከ 220 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የነበረውን ሁኔታ የሚገልጸው ሆ ሃን ሾ (የኋለኛው የሃን ሥርወ መንግሥት ታሪካዊ ዘገባ) እንዲህ ያለ አንድ ጉዞ የተደረገበትን ጊዜ ይጠቁማል። በ166 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከዳቺን ንጉሥ የተላከ አንቶን የተባለ ልዑክ ለንጉሠ ነገሥት ህዋንዲ ገጸ በረከት ይዞ ወደ ቻይና ቤተ መንግሥት መጥቶ ነበር። ቻይናውያን የሮምን መንግሥት ዳቺን ብለው ይጠሩት የነበረ ሲሆን አንቶን ደግሞ ለአንቶኒነስ የሰጡት የቻይንኛ ስያሜ ሳይሆን አይቀርም፤ አንቶኒነስ በዚያን ዘመን የነበረው ማርከስ ኦሪልየስ የተባለ የሮም ንጉሠ ነገሥት የቤተሰብ ስም ነው። ታሪክ ጸሐፊዎች፣ ይህ ልዑክ ከመንግሥት የተላከ ሳይሆን ብልህ የሆኑ ምዕራባውያን ነጋዴዎች በደላላ አማካኝነት ከመገበያየት ይልቅ በቀጥታ ከቻይና ሐር ለመግዛት የሚችሉበትን ዘዴ ለመቀየስ ሲሉ የላኩት መልእክተኛ መሆን አለበት የሚል ጥርጣሬ አላቸው።

መጀመሪያ ላይ ያነሳነውን ጥያቄ እስቲ መለስ ብለን እንመልከት፤ በአንደኛው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያን ሚስዮናውያን በስተ ምሥራቅ እስከ የት ድረስ በመርከብ ተጉዘው ሊሆን ይችላል? እስከ ሕንድ ብሎም ከዚያ አልፈው ተጉዘው ይሆን? ምናልባት ተጉዘው ሊሆን ይችላል። ምሥራቹ በስፋት ተሰራጭቶ ስለነበር ሐዋርያው ጳውሎስ “በመላው ዓለምም ፍሬ እያፈራና እየጨመረ ነው” ለማለት ችሏል፤ ይህም ምሥራቹ በዚያን ጊዜ በነበረው ዓለም በጣም ርቀው ወደሚገኙ ቦታዎች ተዳርሶ እንደነበር ያሳያል።—ቆላስይስ 1:6

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.15 ሙዚሪስ ትገኝበት የነበረው ስፍራ በትክክል የማይታወቅ ቢሆንም ምሁራን በኬራላ ግዛት ይኸውም የፔሪያር ወንዝ ወደ ሕንድ ውቅያኖስ በሚገባበት ቦታ አቅራቢያ እንደነበረች ይገምታሉ።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አንድ ንጉሠ ነገሥት ያቀረበው ስሞታ

በ22 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የሮም ንጉሠ ነገሥት ጢባርዮስ የአገሩ ሰዎች አልጠግብ ባይ በመሆናቸው የተሰማውን ቅሬታ ገልጾ ነበር። ሕዝቡ የቅንጦት ሕይወት ለመኖር ይቋምጥ የነበረ ሲሆን ሴቶቹ ደግሞ ለጌጣ ጌጥ ከፍተኛ ፍቅር ነበራቸው፤ ይህም የአገሪቱ ሀብት እንዲባክንና “ባዕድ ወይም ጠላት ወደሆኑ አገሮች” እጅ እንዲገባ ምክንያት ሆኗል። የሮም ታሪክ ጸሐፊ የነበረው ትልቁ ፕሊኒ (23-79 ከክርስቶስ ልደት በኋላ) ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ተመሳሳይ ቅሬታ አሰምቷል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሕንድ፣ ሴሬስ እንዲሁም የዓረቢያ ባሕረ ገብ ምድር ከአገራችን በየዓመቱ አነሰ ቢባል አንድ መቶ ሚሊዮን ሴስተርስ ያገኛሉ፤ ይህን ያህል ከፍተኛ ገንዘብ የምናፈሰው ለቅንጦትና ለሴት እህቶቻችን ነው።” *

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.28 አንዳንድ ተንታኞች እንዳሉት ከሆነ 100 ሚሊዮን ሴስተርስ ከሮም መንግሥት ጠቅላላ ኢኮኖሚ 2 በመቶ ያህል ይሆናል።

[ምንጭ]

Museo della Civiltà Romana, Roma; Todd Bolen/Bible Places.com

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ነጋዴዎች የሚፈልጓቸውን ሸቀጦች የሚያገኙት ከየት ነበር?

ኢየሱስ ‘ጥሩ ዕንቁ ይፈልግ ስለነበረ ተጓዥ ነጋዴ’ ተናግሯል። (ማቴዎስ 13:45) በተመሳሳይም የራእይ መጽሐፍ ስለ “ተጓዥ ነጋዴዎች” የሚናገር ሲሆን እነዚህ ነጋዴዎች ከነበሯቸው ሸቀጣ ሸቀጦች መካከል የከበሩ ድንጋዮች፣ ሐር፣ ጥሩ መዓዛ ያለው እንጨት፣ የዝሆን ጥርስ፣ ቀረፋ፣ ዕጣንና የሕንድ ቅመም ይገኙበታል። (ራእይ 18:11-13) እነዚህ ሸቀጦች የሚገኙት ከፓለስቲና በስተ ምሥራቅ ባሉ የንግድ መስመሮች አካባቢ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ እንደ ሰንደል ያሉ ጥሩ መዓዛ ያላቸው እንጨቶች የሚመጡት ከሕንድ ነበር። ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን ዕንቁዎች ከፋርስ ባሕረ ሰላጤ፣ ከቀይ ባሕር እንዲሁም ፐሪፕለስ ማረስ ኤሪትራኤ የተባለው መጽሐፍ ጸሐፊ እንደገለጸው ከሆነ ከሙዚሪስና ከስሪላንካ አካባቢ ማግኘት ይቻል ነበር። ከሕንድ ውቅያኖስ ይገኙ የነበሩት ዕንቁዎች ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ከመሆናቸውም ሌላ እጅግ ውድ ነበሩ።

[በገጽ 20 እና 21 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

በመጀመሪያ መቶ ዘመን በሮምና በእስያ መካከል የነበሩ አንዳንድ የንግድ መስመሮች

አሬትሶ

ሮም

ሜድትራንያን ባሕር

አፍሪካ

እስክንድርያ

ግብፅ

ኮፕቶስ

ዓባይ ወንዝ

ሚኦስ ኦርሞስ

በረናይሲ

ዛንዚባር

ቀይ ባሕር

ኢየሩሳሌም

የዓረብ ምድር

ኤፍራጥስ ወንዝ

ባቢሎን

የፋርስ ባሕረ ሰላጤ

ፋርስ

ከሰሜን ምሥራቅ የሚነሳ ነፋስ

ደቡብ ምዕራብ የሚነሳ ነፋስ

ኢንደስ ወንዝ

ፑንጃብ

ጋንጀስ ወንዝ

የቤንጋል የባሕር ወሽመጥ

ሕንድ

አሪካሜዱ

ሙዚሪስ

ስሪላንካ

ሕንድ ውቅያኖስ (ኤሪትሪያን ባሕር)

ቻይና

የሃን ግዛት

ታይላንድ

ካምቦዲያ

ቬትናየም

ሱማትራ

ጃቫ

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሮም የጭነት መርከብ ሞዴል

[ምንጭ]

Ship: Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.