ማርያም ከተወችው ምሳሌ ምን ልንማር እንችላለን?
ማርያም ከተወችው ምሳሌ ምን ልንማር እንችላለን?
ያልታሰበ ችግር አጋጥሞህ ወይም ያልጠበቅከው ኃላፊነት ተጥሎብህ በጭንቀት የተዋጥክበት ጊዜ አለ? የዕለት ጉርስህን ለማሟላት የምታደርገው ሩጫ አሰልቺ ሆኖብሃል? ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በመሰደዳቸው ምክንያት ሕይወታቸው ከተመሰቃቀለባቸውና ስጋት ላይ ከወደቁት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል አንዱ ትሆን? ደግሞስ የሚወደውን ሰው በሞት በማጣቱ ምክንያት ከባድ ሐዘንና የባዶነት ስሜት ያልተሰማው ማን ይኖራል?
የኢየሱስ እናት የሆነችው ማርያም እነዚህ ሁሉ ችግሮች አጋጥመዋት እንደነበር ታውቃለህ? ይሁንና የደረሱባትን ችግሮች ሁሉ በተሳካ ሁኔታ መወጣት ችላለች! ታዲያ ማርያም ከተወችው ምሳሌ ምን ልንማር እንችላለን?
በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ በርካታ ሰዎች ስለ ማርያም ያውቃሉ። ማርያም ከአምላክ ዓላማ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ልዩ ሚና በመጫወቷ ይህ መሆኑ ምንም አያስገርምም። ከዚህም በላይ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለማርያም አምልኮታዊ አክብሮት አላቸው። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን፣ ማርያምን እመቤታችን ብለው በአክብሮት የሚጠሯት ሲሆን የእምነት፣ የተስፋና የልግስና ተምሳሌት አድርገው ይመለከቷታል። ብዙዎች ማርያም አማላጅ እንደሆነች ያምናሉ።
አንተስ ስለ ኢየሱስ እናት ያለህ አመለካከት ምንድን ነው? ከሁሉ በላይ ደግሞ አምላክ ስለ እሷ ያለው አመለካከት ምንድን ነው?
በዓይነቱ ልዩ የሆነ ኃላፊነት
የሄሊ ልጅ የሆነችው ማርያም የእስራኤል ነገድ ከሆነው ከይሁዳ ወገን ነበረች። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰችው ከአንድ አስደናቂ ክንውን ጋር በተያያዘ ነበር። አንድ መልአክ ወደ ማርያም ቀርቦ “እጅግ የተወደድሽ ሆይ፣ ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ ይሖዋ ከአንቺ ጋር ነው” አላት። ማርያምም በሁኔታው ግራ በመጋባት “‘ይህ ምን ዓይነት ሰላምታ ነው?’ በማለት በውስጧ ታስብ ጀመር።” መልአኩም የአምላክን ልጅ የመፀነስ፣ የመውለድና የማሳደግ አስደናቂ ብሎም በጣም ከባድ የሆነ ኃላፊነት እንደተጣለባት ነገራት።—ሉቃስ 1:26-33
በእርግጥም ይህች ያላገባች ወጣት የተጣለባት ኃላፊነት ከባድ ነበር! በዚህ ጊዜ ማርያም ምን ተሰማት? ምናልባት ማርያም ‘አሁን ይህን ለሰው ብናገር ማን ያምነኛል?’ ብላ አስባ ይሆናል። መፀነሷ ከእጮኛዋ ከዮሴፍ ያለያያት ወይም ለውርደት ይዳርጋት ይሆን? (ዘዳግም 22:20-24) ይሁንና ይህን ከባድ ኃላፊነት ለመቀበል አላቅማማችም።
ማርያም ጠንካራ እምነት ያላት መሆኑ ለአምላኳ ለይሖዋ እንድትገዛ አነሳስቷታል። ይሖዋ እንደሚንከባከባት እርግጠኛ ነበረች። ስለሆነም “እነሆ፣ እኔ የይሖዋ ባሪያ ነኝ! እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” አለች። ማርያም ያገኘችውን መንፈሳዊ መብት ከፍ አድርጋ ስለተመለከተች የሚያጋጥሟትን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለመጋፈጥ ፈቃደኛ ነበረች።—ሉቃስ 1:38
ማርያም ለዮሴፍ መፀነሷን ስትነግረው ሊተዋት አሰበ። በወቅቱ ሁለቱም በጣም ተጨንቀው መሆን አለበት። መጽሐፍ ቅዱስ፣ በዚህ አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ለምን ያህል ጊዜ እንደቆዩ የሚገልጸው ነገር የለም። ሆኖም የይሖዋ መልአክ ለዮሴፍ ከተገለጠለት ማቴዎስ 1:19-24
በኋላ ማርያምና ዮሴፍ እፎይታ እንደተሰማቸው ጥርጥር የለውም። መልአኩ፣ ማርያም የፀነሰችው በተአምራዊ ሁኔታ እንደሆነ በመግለጽ ዮሴፍ ማርያምን ሚስቱ አድርጎ እንዲወስዳት ነገረው።—አስቸጋሪ ጊዜያት
በዛሬው ጊዜ በርካታ ነፍሰ ጡር ሴቶች የመውለጃ ጊዜያቸው ከመድረሱ በፊት ለበርካታ ወራት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ያደርጋሉ። ማርያምም የበኩር ልጇን ልትወልድ በመሆኑ እንዲሁ አድርጋ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ያልተጠበቁ ሁኔታዎች እቅዶቿን አፋልሰውባታል። አውግስጦስ ቄሳር ሁሉም ሰው ወደ ትውልድ ከተማው ሄዶ እንዲመዘገብና የሕዝብ ቆጠራ እንዲካሄድ አዋጅ አወጣ። ስለሆነም ዮሴፍ የዘጠኝ ወር ነፍሰ ጡር የነበረችውን ማርያምን ይዞ 150 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ ወደሚገኝ ቦታ ተጓዘ። ማርያም የተጓዘችው በአህያ ሳይሆን አይቀርም! የምትወልድበት አመቺ ስፍራ ያስፈልጋት የነበረ ቢሆንም ቤተልሔም በሰው ተጨናንቃ ስለነበር ከጋጣ በስተቀር ሌላ ቦታ ማግኘት አልቻሉም። በጋጣ ውስጥ መውለድ በጣም አስቸጋሪ እንደሚሆን እሙን ነው። በወቅቱ ማርያም ሁኔታው በጣም አስጨንቋት ሊሆን ይችላል።
በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ይሖዋ እሷንም ሆነ ልጇን እንደሚንከባከባቸው በመተማመን የልቧን አውጥታ ወደ አምላክ ትጸልይ እንደነበር ምንም አያጠራጥርም። ማርያም ከወለደች በኋላ ሕፃኑን ለማየት የጓጉ አንዳንድ እረኞች ወደዚህ ስፍራ መጡ። እነዚህ እረኞች፣ መላእክት ይህን ሕፃን ‘አዳኝና ጌታ ክርስቶስ’ በማለት እንደጠሩት ነገሯቸው። “ማርያም ግን የሰማቻቸውን ነገሮች በውስጧ ይዛ በልቧ ታሰላስል ነበር።” በእነዚህ ነገሮች ላይ በማሰላሰል ብርታት ማግኘት ችላለች።—ሉቃስ 2:11, 16-19
እኛም በሕይወታችን ውስጥ አሳዛኝ ሁኔታ ሊያጋጥመን ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ማንኛችንም ብንሆን “መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች” ሊያጋጥሙን ብሎም ብዙ መከራዎችና ፈታኝ ሁኔታዎች ሊደርሱብን እንደሚችሉ ያሳያል። (መክብብ 9:11 NW) እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙን አምላክን እናማርራለን? ከዚህ ይልቅ የማርያምን አመለካከት መኮረጃችን እንዲሁም ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን በመማርና በተማርነው ነገር ላይ በማሰላሰል ወደ ይሖዋ አምላክ መቅረባችን የተሻለ አይሆንም? ይህን ማድረጋችን ፈተናዎችን ለመቋቋም ይረዳናል።
በድህነትና በስደት መኖር
ማርያም በድህነት መኖርና ከትውልድ አገሯ መሰደድን ጨምሮ ሌሎች ችግሮችም አጋጥመዋታል። እንዲህ ያለ ችግር ደርሶብህ ያውቃል? አንድ ሪፖርት እንደገለጸው ከሆነ “ከዓለም ሕዝብ መካከል ግማሽ ያህሉ ይኸውም ሦስት ቢሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች የዕለት ገቢያቸው ከሁለት ዶላር ያነሰ” ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ሀብታም በሚባሉ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ቢሆኑም የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ይዋትታሉ። አንተስ? ለቤተሰቦችህ ምግብና ልብስ ለማቅረብ እንዲሁም መጠለያ ለማግኘት የምታደርገው ጥረት አድካሚ ብሎም አንዳንድ ጊዜ ተስፋ አስቆራጭ ይሆንብሃል?
ዮሴፍና ማርያም በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ድሆች እንደነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቁማል። ይህን እንዴት እናውቃለን? የማቴዎስ፣ የማርቆስ፣ የሉቃስና የዮሐንስ ወንጌሎች ማርያምንና ዮሴፍን አስመልክተው ከሚናገሯቸው ጥቂት ታሪኮች መካከል፣ ማርያም ከወለደች ከ40 ቀን በኋላ ከዮሴፍ ጋር ወደ ቤተ መቅደሱ ሄደው የሚፈለግባቸውን መሥዋዕት ይኸውም “ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች” ማቅረባቸውን የሚገልጸው ሐሳብ ይገኝበታል። * (ሉቃስ 2:22-24) ይህን መሥዋዕት ያቀርቡ የነበሩት የበግ ጠቦት ለማቅረብ አቅም ያልነበራቸው ድሃ ሰዎች ነበሩ። ዮሴፍና ማርያም የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ብዙ መድከም ነበረባቸው። ያም ሆኖ ቤታቸው ፍቅር የሰፈነበት ነበር። ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ ይሰጡ እንደነበር ጥርጥር የለውም።—ዘዳግም 6:6, 7
ኢየሱስ ከተወለደ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በማርያም ሕይወት ውስጥ ዳግመኛ ትልቅ ለውጥ ተከሰተ። አንድ መልአክ፣ ዮሴፍ ቤተሰቡን ይዞ ወደ ግብፅ እንዲሸሽ ነገረው። (ማቴዎስ 2:13-15) ማርያም ለሁለተኛ ጊዜ ከቀዬዋ ለመፈናቀል ተገደደች፤ በዚህ ወቅት ግን የተሰደደችው ወደ ባዕድ አገር ነበር። በግብፅ በርካታ አይሁዳውያን ስለነበሩ ማርያምና ዮሴፍ ከወገኖቻቸው ጋር አብረው ለመኖር የሚያስችል አጋጣሚ ሳያገኙ አልቀሩም። ሆኖም በባዕድ አገር መኖር አስቸጋሪና ግራ የሚያጋባ ሊሆን ይችላል። አንተም ሆንክ ቤተሰብህ፣ ልጆቻቸው ጥሩ ኑሮ እንዲኖሩ ወይም ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ ሲሉ ከትውልድ አገራቸው ከተሰደዱት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ትገኙበት ይሆን? ከሆነ ማርያም በግብፅ ያጋጠሟትን አንዳንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚገባ መረዳት ትችላለህ።
ለአምላክ ያደረች ሚስትና እናት
ማርያም፣ ስለ ኢየሱስ መወለድና ስለ ልጅነት ሕይወቱ ከሚናገሩት ዘገባዎች ጋር በተያያዘ ካልሆነ በስተቀር በወንጌሎች ውስጥ እምብዛም አልተጠቀሰችም። ይሁንና ማርያምና ዮሴፍ ቢያንስ ስድስት ልጆች እንደነበሯቸው ማወቅ እንችላለን። ይህ ምናልባት ያስገርምህ ይሆናል። ወንጌሎች ምን እንደሚሉ እስቲ እንመልከት።
ዮሴፍ፣ ማርያም ላገኘችው የአምላክን ልጅ የመውለድ ልዩ መብት ከፍተኛ አክብሮት ነበረው። ስለሆነም ኢየሱስ እስኪወለድ ድረስ ከማርያም ጋር የጾታ ግንኙነት አልፈጸመም። ማቴዎስ 1:25 ዮሴፍ “ልጁን እስክትወልድ ድረስ አልተገናኛትም” በማለት ይናገራል። “እስክትወልድ ድረስ” የሚለው አነጋገር ኢየሱስ ከተወለደ በኋላ ዮሴፍና ማርያም እንደ ማንኛውም ባልና ሚስት የጾታ ግንኙነት ይፈጽሙ እንደነበር ያሳያል። በመሆኑም ማርያም ከዮሴፍ የወለደቻቸው ወንዶችና ሴቶች ልጆች እንዳሏት የወንጌል ዘገባዎች ይገልጻሉ። ያዕቆብ፣ ዮሴፍ፣ ስምዖንና ይሁዳ የኢየሱስ ወንድሞች ነበሩ። በተጨማሪም ማርያም ቢያንስ ሁለት ሴቶች ልጆች ወልዳለች። (ማቴዎስ 13:55, 56) ሆኖም እነዚህ ልጆች የተጸነሱት በተአምራዊ መንገድ አልነበረም። *
ሉቃስ 2:41) ይህ ደግሞ በቁጥር እየጨመረ የመጣውን ቤተሰብ ይዞ በየዓመቱ ወደ ኢየሩሳሌም መጓዝ የሚጠይቅ ሲሆን ጉዞው ደርሶ መልስ 300 ኪሎ ሜትር ያህል ይሆናል! ቤተሰቡ ይህን ጉዞ በሚያደርግበት ወቅት አስደሳች ጊዜ እንደሚያሳልፍ ጥርጥር የለውም።
ማርያም መንፈሳዊ ነገሮችን ከፍ አድርጋ ትመለከት ነበር። ሕጉ፣ ሴቶች የፋሲካ በዓል ላይ እንዲገኙ የሚያዝ ባይሆንም ማርያም በዓሉን ለማክበር ከዮሴፍ ጋር በየዓመቱ ወደ ኢየሩሳሌም ትሄድ ነበር። (በዛሬው ጊዜ የሚገኙ በርካታ ሴቶች የማርያምን ግሩም ምሳሌ ይከተላሉ። ያሉባቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነቶች ለመወጣት ራሳቸውን ሳይቆጥቡ በትጋት ይሠራሉ። እነዚህ ለአምላክ ያደሩ ሚስቶች በእጅጉ የሚደነቅ ትዕግሥት፣ ጽናትና ትሕትና ያሳያሉ! የማርያምን አመለካከት መኮረጃቸው ከራሳቸው ምቾትና ደስታ ይልቅ መንፈሳዊ ነገሮችን እንዲያስቀድሙ ረድቷቸዋል። ማርያም እንዳደረገችው ከትዳር ጓደኛቸውና ከልጆቻቸው ጋር ሆነው አምላክን ማምለካቸው የቤተሰባቸውን አንድነት እንደሚያጠናክር ይገነዘባሉ።
በአንድ ወቅት ማርያምና ዮሴፍ ከልጆቻቸው ጋር በዓል አክብረው ከኢየሩሳሌም ሲመለሱ የ12 ዓመቱ ልጃቸው ኢየሱስ አብሯቸው እንዳልነበረ ተገነዘቡ። ኢየሱስን ሲፈልጉ በቆዩባቸው ሦስት ቀናት ማርያም ምን ያህል ተጨንቃ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትህም! ከብዙ ፍለጋ በኋላ ማርያምና ዮሴፍ ልጃቸውን በቤተ መቅደሱ ሲያገኙት “በአባቴ ቤት መሆን እንደሚገባኝ አታውቁም?” አላቸው። ማርያም በዚህ ጊዜም ቢሆን “የተባሉትን ነገሮች ሁሉ በልቧ ትይዝ” እንደነበር ዘገባው ይናገራል። ይህም ማርያም መንፈሳዊ ነገሮችን ከፍ አድርጋ ትመለከት እንደነበር የሚያሳይ ሌላ ማስረጃ ነው። ከኢየሱስ ሉቃስ 2:41-52
ጋር በተያያዘ የተከናወኑትን ነገሮች በሙሉ በሚገባ ታሰላስልባቸው ነበር። ዓመታት ካለፉ በኋላ ማርያም ይህንንም ሆነ ከኢየሱስ የልጅነት ሕይወት ጋር የተያያዙ ክንውኖችን በማስታወስ ለወንጌል ጸሐፊዎች በዝርዝር ሳትነግራቸው አትቀርም።—መከራንና ሐዘንን መቋቋም
የኢየሱስ አሳዳጊ አባት ስለሆነው ስለ ዮሴፍስ ምን ማለት ይቻላል? ኢየሱስ ልጅ በነበረበት ጊዜ ከተፈጸመው ከዚያ ክንውን በኋላ ዮሴፍ በወንጌል ዘገባዎች ላይ አልተጠቀሰም። በዚህ ምክንያት አንዳንዶች፣ ኢየሱስ አገልግሎቱን ከመጀመሩ ከተወሰነ ጊዜ በፊት ዮሴፍ ሞቶ መሆን አለበት ይላሉ። * ያም ሆነ ይህ ማርያም፣ ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን እያገባደደ በነበረበት ወቅት መበለት የነበረች ይመስላል። ኢየሱስ በሞተበት ወቅት እናቱን እንዲንከባከብለት ለሐዋርያው ዮሐንስ አደራ ሰጥቶታል። (ዮሐንስ 19:26, 27) ዮሴፍ በሕይወት ቢኖር ኖሮ ኢየሱስ ይህን እንደማያደርግ የታወቀ ነው።
ማርያምና ዮሴፍ ብዙ ነገሮችን አንድ ላይ አሳልፈዋል። መላእክት አነጋግረዋቸዋል፣ አምባገነን ከሆነ መሪ ሸሽተዋል፣ በተደጋጋሚ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል እንዲሁም ብዙ ልጆችን አሳድገዋል። ከዚህም በተጨማሪ ‘ኢየሱስ ወደፊት ምን ነገር ያጋጥመው ይሆን? አስፈላጊውን ሥልጠና ሰጥተነዋል? ወደፊት ለሚጠብቀውስ ነገር በተገቢው መንገድ አዘጋጅተነዋል?’ በሚሉት ጉዳዮች ላይ በመወያየት በርካታ ምሽቶች አሳልፈው መሆን አለበት። ከዚያም ሳይታሰብ ዮሴፍ በሞት ተለያት።
አንተስ የትዳር ጓደኛህን በሞት ተነጥቀሃል? ይህ ከሆነ በርካታ ዓመታት ካለፉ በኋላም እንኳ የሐዘንና የባዶነት ስሜት ይሰማሃል? ማርያም ትንሣኤ እንዳለ ማወቋና በዚህ ተስፋ ላይ እምነት ማሳደሯ እንድትጽናና እንደረዳት ጥርጥር የለውም። * (ዮሐንስ 5:28, 29) ማርያም ልትጽናናባቸው የምትችልባቸው እንዲህ የመሰሉ ነገሮች ቢኖሩም ያሉባት ችግሮች በዚህ አላበቁም። በዛሬው ጊዜ የትዳር ጓደኛቸውን በሞት እንዳጡ በርካታ እናቶች ማርያምም ያለ ባለቤቷ እርዳታ ልጆቿን የማሳደግ ከባድ ኃላፊነት ወድቆባት ነበር።
ዮሴፍ ከሞተ በኋላ ቤተሰቡን የማስተዳደር ኃላፊነት በዋነኝነት የወደቀው በኢየሱስ ላይ ነበር ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው። የኢየሱስ ወንድሞች ካደጉ በኋላ ቤተሰቡን ሉቃስ 3:23) አብዛኞቹ ወላጆች፣ ልጃቸው ራሱን ችሎ ከቤት ሲወጣ የተዘበራረቀ ስሜት ይሰማቸዋል። ወላጆች ልጆቻቸውን ለማሳደግ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን መሥዋዕት ከማድረጋቸውም ሌላ በመካከላቸው የጠበቀ ግንኙነት ተመሥርቷል፤ በመሆኑም ልጆቻቸው ሲለዩአቸው የባዶነት ስሜት ሊሰማቸው ይችላል። የአንተስ ልጆች የራሳቸውን ኑሮ ለመምራት ከቤት ወጥተዋል? በልጆችህ ኩራት ቢሰማህም አንዳንድ ጊዜ ‘ምነው አጠገቤ በሆኑ’ ብለህ ትመኛለህ? ከሆነ ማርያም ኢየሱስ ሲለያት ምን ተሰምቷት ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትህም።
በመርዳት የበኩላቸውን ድርሻ እንዳበረከቱ ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ “ሠላሳ ዓመት ገደማ” ሲሆነው ከቤተሰቡ ተለይቶ አገልግሎቱን ማከናወን ጀመረ። (ያልተጠበቁ ፈተናዎች
ማርያም ያጋጠማት ሌላው ፈተና ደግሞ ፈጽሞ ያልጠበቀችው ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ሲሰብክ ብዙዎች የተከተሉት ቢሆንም ወንድሞቹ ግን አልተቀበሉትም። መጽሐፍ ቅዱስ “ወንድሞቹም ቢሆኑ አላመኑበትም ነበር” ይላል። (ዮሐንስ 7:5) ማርያም፣ ኢየሱስ “የአምላክ ልጅ” ነው ብሎ መልአኩ እንደነገራት ለወንድሞቹ ሳትነግራቸው አልቀረችም። (ሉቃስ 1:35) ሆኖም ያዕቆብ፣ ዮሴፍ፣ ስምዖንና ይሁዳ ኢየሱስን የሚመለከቱት እንደ ታላቅ ወንድማቸው ብቻ ነበር። በመሆኑም በማርያም ቤተሰብ ውስጥ የተለያየ ሃይማኖታዊ አመለካከት ነበር።
ማርያም በሁኔታው ተስፋ ቆርጣ የልጆቿን አመለካከት ለመለወጥ የምታደርገውን ጥረት እርግፍ አድርጋ ትታው ይሆን? በጭራሽ! በአንድ ወቅት ኢየሱስ በገሊላ ሲሰብክ ቆይቶ ምግብ ለመብላት ወደ አንድ ቤት ገባ፤ በዚያም ብዙ ሰዎች የሚናገረውን ለመስማት ተሰበሰቡ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ማርያምና ወንድሞቹ ኢየሱስን ለመፈለግ መጡ። ከዚህ ለመረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ ቤተሰቡ ወደሚኖርበት አካባቢ ሲመጣ ማርያም ልጆቿን ይዛ እሱ ወዳለበት ትሄድ ነበር፤ ይህን ታደርግ የነበረው ልጆቹ ለኢየሱስ ያላቸው አመለካከት ይለወጣል ብላ ተስፋ በማድረግ ሊሆን ይችላል።—ማቴዎስ 12:46, 47
አንተም የቤተሰቦችህ አባላት ኢየሱስን ባለመከተላቸው ምክንያት ተመሳሳይ የሆነ ፈተና አጋጥሞህ ይሆናል። ይህ ሁኔታ በጣም እንድታዝንና ተስፋ ቆርጠህ እነሱን ከመርዳት ወደኋላ እንድትል ሊያደርግህ አይገባም። ማርያም እንዳደረገችው ሁሉ ብዙዎች፣ ቤተሰቦቻቸው አመለካከታቸውን እንዲለውጡ ለበርካታ ዓመታት በትዕግሥት ረድተዋቸዋል። ሰዎቹ አመለካከታቸውን ለወጡም አልለወጡ አምላክ እንዲህ ያለውን ትዕግሥትና ጽናት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል።—1 ጴጥሮስ 3:1, 2
ከሁሉ የከፋው ፈተና
በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ተገልጾ የምናገኘው ማርያም የደረሰባት የመጨረሻ ፈተና ልቧን በሐዘን ሉቃስ 2:34, 35
ሰብሮት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። በጣም የምትወደው ልጇ የገዛ ወገኖቹ ሲቃወሙትና ተሠቃይቶ ሲሞት ተመልክታለች። የልጅ ሞት “ቅስም የሚሰብር” እንዲሁም “ከሁሉ የከፋው ሐዘን” ተብሎ ተገልጿል፤ በየትኛውም ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጅ ሲሞት እንዲህ ዓይነት ስሜት መሰማቱ አይቀርም። ከአሥርተ ዓመታት በፊት በተነገረው ትንቢት መሠረት ማርያም በነፍሷ ትልቅ ሰይፍ ያለፈ ያህል ሆኖ ተሰምቷት ነበር።—ማርያም የደረሰባት ይህ የመጨረሻ ፈተና ቅስሟን እንዲሰብረው ወይም በይሖዋ ላይ ያላትን እምነት እንዲያዳክምባት ፈቅዳለች? በፍጹም። ከዚህ በኋላ ማርያም የተጠቀሰችበት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ፣ ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ጋር አንድ ላይ ሆና ‘ተግታ ስትጸልይ’ እንደነበር ይገልጻል። በዚህ ጊዜ ግን ማርያም ብቻዋን አልነበረችም። ከዚህ ይልቅ በታላቅ ወንድማቸው በኢየሱስ ማመን የጀመሩት ወንዶች ልጆቿም ከእሷ ጋር ነበሩ። ይህ ማርያምን ምንኛ አጽናንቷት ይሆን! *—የሐዋርያት ሥራ 1:14
ማርያም አምላክ የጣለባትን የሚስትነትና የእናትነት ኃላፊነት በታማኝነት በመወጣት አርኪና አስደሳች ሕይወት አሳልፋለች። አምላክን በማገልገል በርካታ አስደሳች ተሞክሮዎች አግኝታለች። ብዙ ፈተናዎችንና መከራዎችን ተቋቁማለች። እኛም ያልጠበቅነው ፈታኝ ሁኔታ ሲያጋጥመን ወይም በቤተሰባችን ውስጥ የተፈጠሩ ችግሮች ሲያስጨንቁን ማርያም አምላክን በታማኝነት በማገልገል ከተወችው የጽናት ምሳሌ ብዙ ትምህርት ማግኘት እንደምንችል የተረጋገጠ ነው።—ዕብራውያን 10:36
ይሁን እንጂ ለማርያም ልዩ የሆነ አምልኮታዊ ክብር ስለመስጠትስ ምን ማለት ይቻላል? ማርያም ስለተጫወተችው ልዩ ሚና የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ መመለክ እንዳለባት ያሳያል?
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.17 ከሁለቱ ወፎች አንዱ የኃጢአት መሥዋዕት ሆኖ የቀረበ ነው። (ዘሌዋውያን 12:6, 8) ማርያም ይህን መሥዋዕት ማቅረቧ እንደ ማንኛውም ሰው እሷም የመጀመሪያው ሰው አዳም የሠራው ኃጢአት ያስከተላቸውን ውጤቶች በሙሉ መውረሷን አምና እንደተቀበለች ያሳያል።—ሮም 5:12
^ አን.21 “ኢየሱስ ወንድሞችና እህቶች ነበሩት?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
^ አን.26 ስለ ኢየሱስ አገልግሎት በሚገልጸው ዘገባ ውስጥ የቤተሰቡ አባላት ማለትም እናቱ፣ ወንድሞቹና እህቶቹ ሲጠቀሱ ስለ ዮሴፍ ግን ምንም የተገለጸ ነገር አለመኖሩን ልብ ልንለው ይገባል። ለምሳሌ ያህል፣ በቃና በተደረገው የሠርግ ድግስ ላይ ማርያም ስላደረገችው ተሳትፎና ቅድሚያውን ወስዳ ስላከናወነችው ነገር የተገለጸ ቢሆንም ዮሴፍ ግን ጨርሶ አልተጠቀሰም። (ዮሐንስ 2:1-11) በሌላ ወቅት ደግሞ በክርስቶስ የትውልድ ከተማ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ኢየሱስን የዮሴፍ ልጅ ከማለት ይልቅ “የማርያም ልጅ” በማለት ጠርተውታል።—ማርቆስ 6:3
^ አን.28 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትንሣኤ ተስፋ የሚሰጠውን ሐሳብ በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 7ን ተመልከት።
^ አን.36 “ሃይማኖቷን ለመለወጥ ድፍረቱ ነበራት” የሚለውን በገጽ 7 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ኢየሱስ ወንድሞችና እህቶች ነበሩት?
አዎን ነበሩት። የወንጌል ዘገባዎች፣ ኢየሱስ ወንድሞችና እህቶች እንደነበሩት በተለያዩ ቦታዎች ላይ በግልጽ የሚናገሩ ቢሆኑም አንዳንድ የሃይማኖት ምሁራን ከዚህ ሐቅ ለመሸሽ ሲሉ የመከራከሪያ ሐሳቦችን ለማቅረብ ይሞክራሉ። (ማቴዎስ 12:46, 47፤ 13:54-56፤ ማርቆስ 6:3) ይሁንና ማርያም ከኢየሱስ በቀር ሌላ ልጅ አልወለደችም የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ በተመለከተ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን በሁለት ጉዳዮች ላይ አስተያየት ሰጥተዋል። በመጀመሪያ ደረጃ እንዲህ ያሉ ጽንሰ ሐሳቦችን የሚያስፋፉት፣ ማርያም ሕይወቷን በሙሉ ድንግል ሆና ኖራለች የሚለውን ከጊዜ በኋላ የመጣ የቤተ ክርስቲያን መሠረተ ትምህርት ለመደገፍ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ጽንሰ ሐሳቦቹ ራሳቸው በጥልቀት ሲመረመሩ አሳማኝ አይደሉም።
ለምሳሌ ያህል አንዱ ጽንሰ ሐሳብ፣ የኢየሱስ “ወንድሞች” የተባሉት ዮሴፍ ከቀድሞ ሚስቱ የወለዳቸው ልጆች ናቸው የሚል ነው። ይህ ሐሳብ፣ ኢየሱስ በኩር በመሆኑ የዳዊትን ዙፋን ለመውረስ ካገኘው ሕጋዊ መብት ጋር የሚቃረን በመሆኑ ከእውነታው የራቀ ነው።—2 ሳሙኤል 7:12, 13
ሌላው ጽንሰ ሐሳብ ደግሞ የኢየሱስ ወንድሞች የተባሉት የአክስቱ ወይም የአጎቱ ልጆች ናቸው የሚለው ነው። ይሁን እንጂ የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት “ወንድም፣” “የአክስት ወይም የአጎት ልጅ” እና “ዘመድ” ለሚሉት መጠሪያዎች የሚጠቀሙት የተለያዩ ቃላትን ነው። በመሆኑም ፍራንክ ጌበላይን የተባሉ ምሁር፣ እነዚህ ሃይማኖታዊ ጽንሰ ሐሳቦች ተአማኒነት የሌላቸው እንደሆኑ ገልጸዋል። አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “[የኢየሱስ] ‘ወንድሞች’ የሚለው አገላለጽ . . . የማርያምንና የዮሴፍን ልጆች ማለትም በእናቱ በኩል ያሉትን የኢየሱስ የሥጋ ወንድሞች የሚያመለክት መሆን አለበት።”
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሃይማኖቷን ለመለወጥ ድፍረቱ ነበራት
ማርያም የተወለደችው በአይሁዳውያን ቤተሰብ ውስጥ ሲሆን የአይሁድ ሃይማኖት ተከታይ ነበረች። ምኩራብ ተብሎ በሚጠራው አይሁዳውያን ለአምልኮ በሚሰበሰቡበት ቦታ ትገኝ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ኢየሩሳሌም ውስጥ ወደሚገኘው ቤተ መቅደስ ትሄድ ነበር። ይሁን እንጂ ማርያም ስለ አምላክ ዓላማዎች ያላት እውቀት እየጨመረ ሲሄድ የአባቶቿ ወግና ልማድ በአምላክ ፊት ተቀባይነት እንደሌለው ተገነዘበች። የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች መሲሕ የሆነውን ልጇን ገደሉት። ኢየሱስ ከመገደሉ በፊት የሃይማኖት መሪዎቹን “እነሆ፣ ቤታችሁ ለእናንተ የተተወ ይሆናል” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 23:38) ማርያም ያደገችበት ሃይማኖታዊ ሥርዓት የአምላክ በረከት ርቆት ነበር።—ገላትያ 2:15, 16
የክርስትና ጉባኤ በተቋቋመበት ወቅት ማርያም 50 ዓመት ገደማ ሳይሆናት አይቀርም። ታዲያ ምን አደረገች? በአይሁድ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ውስጥ ያደገች በመሆኑ የአባቶቿን ወግና ልማድ የሙጥኝ ብላ ለመኖር ወስና ይሆን? ‘በዚህ ዕድሜዬ እንዴት ሃይማኖቴን እለውጣለሁ’ ብላ አስባ ይሆን? በጭራሽ! ማርያም በወቅቱ አምላክ በረከቱን በክርስቲያን ጉባኤ ላይ እያፈሰሰ መሆኑን ተገንዝባ ስለነበር ሃይማኖቷን ለመለወጥ እምነቱና ድፍረቱ ነበራት።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወደ ግብፅ ተሰደዱ
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዲት እናት በሕይወቷ ሊያጋጥሟት ከሚችሉ አሳዛኝ ሁኔታዎች ሁሉ የከፋው