በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከሠራው ስህተት ተምሯል

ከሠራው ስህተት ተምሯል

በእምነታቸው ምሰሏቸው

ከሠራው ስህተት ተምሯል

ዮናስ፣ የሚሰማውን የሚረብሽ ድምፅ ዝም ማሰኘት ቢችል ደስ ባለው ነበር። ዮናስን የረበሸው የመርከቧን ሸራ የሚያርገበግበው ነፋስና ከመርከቧ ጋር እየተላተመ ጣውላዋንና ሳንቃዋን የሚያንቃቃው ኃይለኛ ማዕበል ብቻ አልነበረም። ከዚህ ይበልጥ ያስጨነቀው የመርከቧ አዛዥና ሠራተኞች መርከቧ እንዳትሰምጥ ሲታገሉ የሚያሰሙት ጩኸትና ጫጫታ ነበር። ዮናስ እነዚህ ሁሉ ሰዎች በእሱ ምክንያት ሊያልቁ እንደሆነ ተሰምቶታል።

ዮናስ እንዲህ ያለ አጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ እንዲገባ ያደረገው ምንድን ነው? ከአምላኩ ከይሖዋ ጋር ካለው ግንኙነት ጋር በተያያዘ አንድ ከባድ ስህተት ሠርቶ ነበር። የሠራው ስህተት ምን ነበር? ከይሖዋ ጋር የነበረው ግንኙነት ሊታደስ በማይችል ሁኔታ ተበላሽቶ ነበር? ለእነዚህ ጥያቄዎች የምናገኘው መልስ ብዙ የሚያስተምረን ነገር አለ። ለምሳሌ ያህል፣ የዮናስ ታሪክ ጠንካራ እምነት ያላቸው ሰዎችም እንኳ እንዴት ስህተት ሊሠሩና ከስህተታቸው ሊማሩ እንደሚችሉ እንድናስተውል ይረዳናል።

ከገሊላ የተነሳ ነቢይ

ሰዎች ስለ ዮናስ ሲያስቡ ብዙውን ጊዜ የሚታያቸው ደካማ ጎኑ ይኸውም ሳይታዘዝ መቅረቱ ወይም ግትርነቱ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ስለዚህ ሰው ልናውቀው የሚገባ ብዙ ነገር አለ። የይሖዋ አምላክ ነቢይ ሆኖ እንዲያገለግል መመረጡን ልብ ልንለው ይገባል። ታማኝ ወይም ጻድቅ ባይሆን ኖሮ ይሖዋ እንዲህ ላለው ከባድ ኃላፊነት አይመርጠውም ነበር።

ሁለተኛ ነገሥት 14:25 ስለ ዮናስ የሚጠቁመን ነገር አለ። ዮናስ፣ የጋትሔፌር ከተማ ሰው ሲሆን ይህች ከተማ ከ800 ዓመታት ገደማ በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ ካደገባት ከናዝሬት 4 ኪሎ ሜትር ያህል ብቻ ርቃ ትገኛለች። * ዮናስ ነቢይ ሆኖ ያገለግል የነበረው አሥሩን ነገዶች ያቀፈውን የእስራኤል መንግሥት ይገዛ በነበረው በዳግማዊ ኢዮርብዓም የግዛት ዘመን ነበር። ኤልያስ ከኖረ ረጅም ጊዜ ያለፈ ሲሆን በእሱ እግር የተተካው ኤልሳዕም ቢሆን በኢዮርብዓም አባት የግዛት ዘመን ሞቷል። ይሖዋ በእነዚህ ነቢያት በኩል የበኣልን አምልኮ ያስወገደ ቢሆንም እስራኤላውያን ዳግመኛ ሆን ብለው የአምላክን ትእዛዝ መጣስ ጀምረው ነበር። በዚያን ዘመን ምድሪቱን ያስተዳድር የነበረው ንጉሥ ‘በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር ያደርግ’ ነበር። (2 ነገሥት 14:24) ስለሆነም ዮናስ አገልግሎቱን ማከናወን ከባድና አስቸጋሪ እንደሚሆንበት ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ኃላፊነቱን በታማኝነት ተወጥቷል።

ይሁንና አንድ ቀን በዮናስ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ለውጥ ተከሰተ። ዮናስ ከይሖዋ አንድ ተልዕኮ የተቀበለ ሲሆን ይህን ሥራ መፈጸም በጣም ከባድ ሆኖበት ነበር። የተሰጠው ተልዕኮ ምን ነበር?

‘ወደ ነነዌ ሂድ’

ይሖዋ ዮናስን “ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሄደህ፣ በእርሷ ላይ ስበክ፤ ክፋቷ በእኔ ፊት ወጥቶአልና” አለው። (ዮናስ 1:2) ይህ ተልዕኮ አስቸጋሪ ሊሆን የሚችልበትን ምክንያት መረዳት አያዳግትም። የነነዌ ከተማ በስተ ምሥራቅ 800 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ የምትገኝ ሲሆን ወደዚች ከተማ በእግር ተጉዞ ለመድረስ አንድ ወር ገደማ ይፈጅ ነበር። ይሁን እንጂ የተሰጠው ሥራ ጉዞው ከሚያስከትለው ውጣ ውረድ ይበልጥ ከባድ ነበር። ዮናስ በነነዌ ለሚኖሩት በጣም ክፉና አረመኔ የሆኑ አሦራውያን የይሖዋን የፍርድ መልእክት ማወጅ ነበረበት። ዮናስ፣ የአምላክ ሕዝቦች እንኳ ለመልእክቱ ጥሩ ምላሽ ካልሰጡ ከእነዚህ አረማውያን ምን ደህና ነገር ሊጠብቅ ይችላል? አንድ የይሖዋ አገልጋይ ብቻውን በጣም ሰፊ በሆነችውና ‘የደም ከተማ’ ተብላ በተጠራችው በነነዌ እንዴት የተሳካ ሥራ ሊያከናውን ይችላል?—ናሆም 3:1, 7

ዮናስ እነዚህ ነገሮች ሳያሳስቡት አልቀሩም። በእርግጠኝነት የምናውቀው ነገር ቢኖር ሸሽቶ መሄዱን ነው። ይሖዋ ያዘዘው ወደ ምሥራቅ እንዲሄድ ቢሆንም እሱ ግን ወደ ምዕራብ አቅጣጫ የቻለውን ያህል ተጓዘ። ኢዮጴ ወደተባለች የወደብ ከተማ ካመራ በኋላ መርከብ ተሳፍሮ ወደ ተርሴስ አቀና። አንዳንድ ምሁራን ተርሴስ በስፔን ትገኝ እንደነበር ይገልጻሉ። ከሆነ ዮናስ ጉዞ የጀመረው ከነነዌ 3,500 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኝ ስፍራ ነበር ማለት ነው። በአሁኑ ጊዜ ሜድትራንያን ባሕር በመባል ከሚታወቀው ከታላቁ ባሕር ጫፍ ተነስቶ ወደ ሌላኛው ጫፍ የሚደረገው እንዲህ ያለ ጉዞ አንድ ዓመት ያህል ሊፈጅ ይችል ነበር! ዮናስ ይሖዋ ከሰጠው ተልዕኮ ለመሸሽ ያን ያህል ቆርጦ ነበር!

ታዲያ ዮናስ ፈሪ ነበር ሊባል ይችላል? እንዲህ ብለን ለመደምደም መቸኮል የለብንም። ቀጥለን እንደምንመለከተው ዮናስ አስደናቂ ድፍረት ማሳየት ችሎ ነበር። ይሁንና ልክ እንደ እኛው፣ ያሉበትን በርካታ ድክመቶች ለማሸነፍ የሚታገል ፍጹም ያልሆነ ሰው ነበር። (መዝሙር 51:5) ከእኛ መካከል ፍርሃት የሚባል ነገር ጨርሶ ተሰምቶት የማያውቅ ማን አለ?

አንዳንድ ጊዜ አምላክ፣ አስቸጋሪ ብሎም ፈጽሞ የማይቻል የሚመስል ነገር እንድናደርግ ሊጠይቀን ይችላል። ከሁሉም ክርስቲያኖች የሚጠበቀው የአምላክን መንግሥት ምሥራች የመስበኩ ሥራ በጣም ከባድ ሆኖ ይታየን ይሆናል። (ማቴዎስ 24:14) ኢየሱስ “በአምላክ ዘንድ ሁሉ ነገር ይቻላል” በማለት የተናገረውን ሐቅ በቀላሉ ልንዘነጋ እንችላለን። (ማርቆስ 10:27) ይህን ሐቅ የዘነጋንባቸው አጋጣሚዎች ካሉ ዮናስ የገጠመውን ችግር መረዳት አያዳግተንም። ይሁን እንጂ ዮናስ መሸሹ ምን መዘዝ አስከተለበት?

ይሖዋ ያልታዘዘውን ነቢይ ገሠጸው

ዮናስ መርከቧ ውስጥ ገብቶ ተደላድሎ ሲቀመጥ በዓይነ ሕሊናችን ይታየን ይሆናል፤ ይህች መርከብ የፊንቄያውያን የጭነት መርከብ ሳትሆን አትቀርም። የመርከቧ አዛዥና ሠራተኞች መርከቧን አስነስተው ለመሄድ ሲሯሯጡ ዮናስ በአንክሮ ይመለከት ጀመር። የባሕሩ ዳርቻ ቀስ በቀስ እየራቀና ከዓይን እየጠፋ ሲሄድ ዮናስ በጣም ሲያስጨንቀው ከነበረው አደገኛ ሁኔታ እንዳመለጠ ሆኖ ሳይሰማው አልቀረም። ሆኖም በድንገት የአየሩ ሁኔታ መቀያየር ጀመረ።

ባሕሩ እጅግ አስፈሪ በሆነ ዐውሎ ነፋስ መናወጥ የጀመረ ሲሆን የተነሳው ማዕበል በአሁኑ ጊዜ ያሉ መርከቦችን እንኳ ሊያሰምጥ የሚችል ነበር። በማዕበል በሚናወጠው በዚያ ሰፊ ባሕር ላይ ኢምንት ሆና የምትታየው ይህች ከእንጨት የተሠራች መርከብ ይህን አደገኛ ሁኔታ ምን ያህል ተቋቁማ መቆየት ትችል ይሆን? ዮናስ ከጊዜ በኋላ እንደጻፈው ‘አምላክ በባሕሩ ላይ ታላቅ ነፋስን እንደላከ’ በወቅቱ ተረድቶ ነበር? ይህን በእርግጠኝነት ማወቅ አይቻልም። ይሁንና መርከበኞቹ ወደየአምላኮቻቸው መጮኽ ሲጀምሩ ተመልክቷል፤ እነዚህ የሐሰት አማልክት ምንም ሊረዷቸው እንደማይችሉ ደግሞ ያውቃል። ዘገባው ‘መርከቢቱ ልትሰበር ተቃረበች’ በማለት ይገልጻል። (ዮናስ 1:4፤ ዘሌዋውያን 19:4) ሆኖም ዮናስ እየሸሸው ወዳለው አምላክ እንዴት ሊጸልይ ይችላል?

ምንም ነገር ማድረግ እንደማይችል የተሰማው ዮናስ ወደ ታችኛው የመርከቧ ክፍል ሄዶ ተኛ። ከዚያም ከባድ እንቅልፍ ወሰደው። * የመርከቧ አዛዥ፣ ዮናስ ወደተኛበት ሄዶ ከቀሰቀሰው በኋላ እንደ ሌሎቹ ሰዎች አምላኩን እንዲማጸን ነገረው። መርከበኞቹ ይህን ኃይለኛ ማዕበል ያመጣባቸው አንድ መለኮታዊ ኃይል እንደሆነ ስለተሰማቸው ከተሳፋሪዎቹ መካከል ለዚህ ችግር የዳረጋቸውን ሰው ለማወቅ ሲሉ ዕጣ ተጣጣሉ። ዕጣው አንድ በአንድ ሲወጣ ዮናስ ልቡ በፍርሃት ሳይቀልጥ አይቀርም። ብዙም ሳይቆይ እውነታው ገሃድ ወጣ። ማዕበሉ እንዲነሳም ሆነ ዕጣው በዮናስ ላይ እንዲወጣ ያደረገው ይሖዋ ነበር!—ዮናስ 1:5-7

ዮናስ ለመርከበኞቹ ሁሉንም ነገር ግልጽልጽ አድርጎ ነገራቸው። ሁሉን ቻይ የሆነው የይሖዋ አምላክ አገልጋይ መሆኑን ገለጸላቸው። ይህ ሁሉ ችግር የመጣባቸው አምላክ የሰጠውን ትእዛዝ ባለመፈጸሙ ምክንያት እንደሆነ ነገራቸው። ሰዎቹ በጣም እንደደነገጡ ፊታቸው ላይ ይነበብ ነበር። መርከቧንም ሆነ የራሳቸውን ሕይወት ለማዳን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ጠየቁት። ዮናስ ምን ምላሽ ይሰጣቸው ይሆን? እየተናወጠ ባለው በዚያ ቀዝቃዛ ባሕር ውስጥ ሲሰምጥ ታይቶት በፍርሃት ሳይሸበር አልቀረም። ይሁን እንጂ ሊያድናቸው እንደሚችል እያወቀ እነዚህ ሁሉ ሰዎች ሲያልቁ እንዴት ዝም ብሎ ሊመለከት ይችላል? ስለሆነም ዮናስ “ይህ ታላቅ ማዕበል በእኔ ምክንያት እንደ መጣባችሁ ዐውቃለሁ፤ አንሥታችሁ ወደ ባሕሩ ጣሉኝ፤ ባሕሩም ጸጥ ይላል” አላቸው።—ዮናስ 1:12

ፈሪ የሆነ ሰው እንዲህ ሊናገር እንደማይችል የታወቀ ነው። በዚህ በጣም አስፈሪ ሁኔታ ውስጥ ዮናስ እንዲህ ያለ ድፍረትና የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ማሳየቱ ይሖዋን በእጅጉ አስደስቶት መሆን አለበት። ዮናስ ምን ያህል ጠንካራ እምነት እንዳለው በግልጽ ማየት ይቻላል። በዛሬው ጊዜ ከራሳችን ይልቅ ለሌሎች ሰዎች ደኅንነት ቅድሚያ በመስጠት ዮናስን መኮረጅ እንችላለን። (ዮሐንስ 13:34, 35) አንድ ሰው ቁሳዊ፣ ስሜታዊ ወይም መንፈሳዊ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ካስተዋልን እሱን ለመርዳት የተቻለንን ያህል ጥረት እናደርጋለን? እንዲህ ስናደርግ ይሖዋ በጣም ይደሰታል።

መርከበኞቹ መጀመሪያ ላይ ዮናስን መጣል አለመፈለጋቸው አዝነውለት እንደነበር ያሳያል። ማዕበሉን ተቋቁመው ለመጓዝ የተቻላቸውን ያህል ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም። ጭራሽ ነፋሱና ማዕበሉ ይበልጥ ኃይለኛ እየሆነ ሄደ። በመጨረሻም ዮናስን ወደ ባሕሩ ከመጣል ሌላ ምንም አማራጭ እንደሌላቸው ተገነዘቡ። የዮናስ አምላክ የሆነው ይሖዋ ምሕረት እንዲያደርግላቸው በመማጸን ዮናስን አንስተው ወደ ባሕሩ ወረወሩት።—ዮናስ 1:13-15

ዮናስ ምሕረት አግኝቶ ከሞት ተረፈ

ዮናስ እየተናወጠ ወዳለው ባሕር ገባ። ባሕሩ ላይ ለመንሳፈፍ የተቻለውን ያህል ጥረት እያደረገ ሳለ መርከቧ ባሕሩን እየሰነጠቀች በፍጥነት ስትጓዝ ሳይመለከት አልቀረም። ይሁንና ኃይለኛው ማዕበል ወደ ታች ደፈቀው። ከዚያም እየሰመጠ፣ እየሰመጠ ሲሄድ ተስፋው እንደተሟጠጠ ተሰማው።

ዮናስ ይህ ከሆነ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በወቅቱ ምን ተሰምቶት እንደነበር ገልጿል። በአእምሮው ውስጥ ብዙ ሐሳብ ሳይመላለስበት አልቀረም። በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የይሖዋን ውብ ቤተ መቅደስ ዳግመኛ እንደማይመለከት ሲያስበው በሐዘን ተውጦ መሆን አለበት። የተራሮች መሠረት ወደሚገኝበት ወደ ባሕሩ የታችኛው ወለል እንደሰመጠ ተገነዘበ፤ በዚያም የባሕር አረም ተብትቦ ያዘው። ሁኔታው ሲታይ እዚያው ተቀብሮ የሚቀር ይመስል ነበር።—ዮናስ 2:2-6

ሆኖም እዚያው ተቀብሮ አልቀረም! በአቅራቢያው አንድ ጠቆር ያለና በጣም ግዙፍ የሆነ ሕይወት ያለው ነገር ሲንቀሳቀስ ተመለከተ። ይህ ፍጡር በፍጥነት ወደ እሱ እየቀረበ መጣ። ከዚያም አንድ ትልቅ አፍ ተከፍቶ ዋጠው!

ዮናስ ያበቃለት ይመስል ነበር። ይሁንና ምንም አለመሆኑ በግርምት እንዲዋጥ አደረገው። በሰውነቱ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰም፤ ሌላው ቢቀር አየር አጥቶ እንኳ አልታፈነም። ሕይወቱን ሊያሳጣውና መቀበሪያው ሊሆን በሚችል ቦታ ውስጥ የነበረ ቢሆንም በሕይወት መቀጠል ችሏል! ይህም ለአምላክ አክብሮታዊ ፍርሃት እንዲያድርበት አደረገው። “ዮናስን የሚውጥ ትልቅ ዓሣ [ያዘጋጀው]” አምላኩ ይሖዋ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። *ዮናስ 1:17

ደቂቃዎች አልፈው በሰዓታት ተተኩ። ዮናስ አይቶት በማያውቅ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሆኖ የተለያዩ ነገሮችን ሲያውጠነጥን ከቆየ በኋላ ወደ ይሖዋ አምላክ ጸለየ። በዮናስ መጽሐፍ ሁለተኛ ምዕራፍ ላይ ሙሉ በሙሉ ተመዝግቦ የሚገኘው ጸሎቱ ብዙ የሚገልጸው ነገር አለ። ዮናስ በተደጋጋሚ ጊዜ ከመዝሙር መጽሐፍ ይጠቅስ ስለነበር ጥልቅ የሆነ የቅዱሳን ጽሑፎች እውቀት እንደነበረው ያሳያል። በተጨማሪም ግሩም የሆነ የአመስጋኝነት ባሕርይ እንደነበረው ይጠቁማል። ዮናስ “እኔ ግን በምስጋና መዝሙር፣ መሥዋዕት እሠዋልሃለሁ፤ የተሳልሁትንም እሰጣለሁ፤ ድነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው” በማለት ጸሎቱን ደምድሟል።—ዮናስ 2:9

ዮናስ፣ ይሖዋ ማንኛውንም ሰው በየትኛውም ጊዜና ቦታ ማዳን እንደሚችል ከደረሰበት ሁኔታ መማር ችሏል። ይሖዋ “በዓሣው ሆድ ውስጥ” የነበረውን አገልጋዩን እንኳ ታድጎታል። (ዮናስ 1:17) የአንድን ሰው ሕይወት በዓሣ ሆድ ውስጥ ለሦስት ቀንና ሌሊት ጠብቆ ማቆየት የሚችለው እሱ ብቻ ነው። ‘ሕይወታችን በአምላክ እጅ’ እንደሆነ ማስታወሳችን በጣም አስፈላጊ ነው። (ዳንኤል 5:23) እስትንፋሳችንም ሆነ ሕልውናችን ሙሉ በሙሉ በእሱ ላይ የተመካ ነው። ታዲያ ለዚህ ነገር አመስጋኞች ነን? ይሖዋን ልንታዘዘውስ አይገባም?

ስለ ዮናስስ ምን ማለት ይቻላል? ይሖዋን በመታዘዝ አመስጋኝነቱን በተግባር አሳይቷል? አዎን፣ አሳይቷል። ከሦስት ቀንና ሌሊት በኋላ ዓሣው ዮናስን ወደ ባሕሩ ዳርቻ ወስዶ “በደረቅ ምድር ላይ ተፋው።” (ዮናስ 2:10) እስቲ አስበው፣ ይህ ሁሉ ከሆነም በኋላ እንኳ ዮናስ ከባሕር ውስጥ ለመውጣት መዋኘት አላስፈለገውም! እርግጥ ነው፣ ዓሣው የተፋው የትም ይሁን የት ከባሕሩ ዳርቻ ተነስቶ መጓዝ ነበረበት። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ምን ያህል አመስጋኝ እንደሆነ የሚፈተንበት ጊዜ ደረሰ። ዮናስ 3:1, 2 እንዲህ ይላል፦ “የእግዚአብሔርም ቃል ለሁለተኛ ጊዜ እንዲህ ሲል ወደ ዮናስ መጣ፤ ‘ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሄደህ የምነግርህን መልእክት ስበክላት።’” ታዲያ ዮናስ ምን ያደርግ ይሆን?

በዚህ ጊዜ ዮናስ አላቅማማም። መጽሐፍ ቅዱስ “ዮናስም የእግዚአብሔርን ቃል ታዘዘ፤ ወደ ነነዌም ሄደ” ይላል። (ዮናስ 3:3) በእርግጥም ዮናስ ታዟል። ከሠራው ስህተት እንደተማረ በግልጽ መረዳት ይቻላል። በዚህም ረገድ ቢሆን የዮናስን እምነት መኮረጅ ይኖርብናል። ሁላችንም ኃጢአተኞች ነን፤ ስለሆነም ሁላችንም ስህተት እንሠራለን። (ሮም 3:23) ይሁን እንጂ ተስፋ ቆርጠን ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርገን እንተወዋለን? ወይስ ከስህተታችን ተምረን አምላክን ለመታዘዝ ጥረት እናደርጋለን?

ይሖዋ ዮናስ ላሳየው ታዛዥነት ወሮታ ከፍሎታል? እንዴታ! አንደኛ ነገር፣ ዮናስ እነዚያ መርከበኞች መትረፋቸውን ሳይሰማ አይቀርም። ዮናስ እነሱን ለማዳን ሲል እርምጃ ሲወስድ ማዕበሉ ወዲያውኑ ቆመ፤ በዚህ ጊዜ መርከበኞቹ “እግዚአብሔርን እጅግ ፈሩ፤” እንዲሁም ለሐሰት አማልክታቸው ሳይሆን ለይሖዋ መሥዋዕት አቀረቡ።—ዮናስ 1:15, 16

ከጊዜ በኋላ ደግሞ ከዚህ በላቀ መንገድ ተክሷል። ኢየሱስ፣ ዮናስ በትልቅ ዓሣ ሆድ ውስጥ ያሳለፈው ጊዜ እሱ በመቃብር ወይም በሲኦል ውስጥ ለሚያሳልፈው ጊዜ ትንቢታዊ ጥላ እንደሆነ ገልጾ ነበር። (ማቴዎስ 12:38-40) ዮናስ በምድር ላይ ትንሣኤ አግኝቶ በሚኖርበት ጊዜ እንዲህ ያለ በረከት ማግኘቱን ሲያውቅ ምንኛ ይደሰት ይሆን! (ዮሐንስ 5:28, 29) ይሖዋ አንተንም መባረክ ይፈልጋል። ታዲያ አንተም እንደ ዮናስ ከስህተትህ ለመማር እንዲሁም ታዛዥ ለመሆንና የራስህን ጥቅም መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ ነህ?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.7 ዮናስ የተወለደው በገሊላ በምትገኝ ከተማ ውስጥ መሆኑ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፤ ምክንያቱም ፈሪሳውያን በአንድ ወቅት ስለ ኢየሱስ ሲናገሩ በእብሪተኝነት መንፈስ “ከገሊላ አንድም ነቢይ እንደማይነሳ መርምረህ ተረዳ” ብለው ነበር። (ዮሐንስ 7:52) በርካታ ተርጓሚዎችና ተመራማሪዎች፣ ፈሪሳውያን ዝቅ ተደርጋ ከምትታየው ከገሊላ ነቢይ ተነስቶ አያውቅም፣ ወደፊትም አይነሳም የሚል ጭፍን አመለካከት እንደነበራቸው ገልጸዋል። እነዚህ ሰዎች እንዲህ ዓይነት አመለካከት ከነበራቸው ታሪክንም ሆነ ትንቢትን ወደ ጎን ገሸሽ አድርገው ነበር ማለት ነው።—ኢሳይያስ 9:1, 2

^ አን.17 ሰብዓ ሊቃናት፣ ዮናስ በተኛበት ወቅት እንዳንኮራፋ በመግለጽ ምን ያህል ከባድ እንቅልፍ ወስዶት እንደነበር ይጠቁማል። ይሁንና ዮናስ መተኛቱ ግዴለሽ እንደነበር የሚያሳይ ምልክት ነው ብለን መደምደም የለብንም፤ ከዚህ ይልቅ አንዳንዶች ስሜታቸው በጣም በሚደቆስበት ጊዜ በእንቅልፍ ሊሸነፉ እንደሚችሉ ማስታወስ ይኖርብናል። ኢየሱስ በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ በጣም ተጨንቆ በነበረበት ወቅት ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ “ከሐዘን የተነሳ ሲያንቀላፉ” ነበር።—ሉቃስ 22:45

^ አን.25 “ዓሣ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል በግሪክኛ “አስፈሪ የባሕር እንስሳ” ወይም “ግዙፍ ዓሣ” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። ይህ ዓሣ በትክክል ምን ዓይነት የባሕር እንስሳ እንደሆነ ማወቅ ባይቻልም በሜድትራንያን ሰውን ሙሉ በሙሉ መዋጥ የሚችሉ ሻርኮች እንዳሉ ማስተዋል ተችሏል። በሌሎች ቦታዎች ከእነዚህ በጣም የሚበልጡ ሻርኮች ይገኛሉ፤ ዌል ሻርክ የተባለው የዓሣ ዝርያ 15 ሜትር ወይም ከዚያ የሚበልጥ ርዝማኔ ሊኖረው ይችላል!

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በዮናስ መጽሐፍ ላይ የተሰነዘሩ ትችቶች

▪ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በዮናስ መጽሐፍ ላይ ተመዝግበው የምናገኛቸው ታሪኮች በእርግጥ የተፈጸሙ ናቸው? ከጥንት ዘመን ጀምሮ መጽሐፉ የተለያዩ ትችቶች ሲሰነዘሩበት ቆይቷል። በዘመናችን ያሉ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ሃያሲያን የዮናስን መጽሐፍ እንደ ተረት፣ አፈ ታሪክ ወይም ልብ ወለድ አድርገው ስለሚመለከቱት አይቀበሉትም። በ19ኛው መቶ ዘመን የነበረ ደራሲ፣ አንድ ቄስ ስለ ዮናስና ስለ ትልቁ ዓሣ የሚናገረው ታሪክ በዓይነቱ ለየት ያለ ምሳሌያዊ አነጋገር ነው በሚል የሰጡትን ማብራሪያ እንዲህ ሲል ገልጾታል፦ ዮናስ በኢዮጴ በሚገኝ ዓሣ ነባሪ ተብሎ በሚጠራ ሆቴል ውስጥ አርፎ ነበር። ሒሳቡን መክፈል ሳይችል ሲቀር የሆቴሉ ባለቤት አስወጣው። ዮናስ በዓሣ ነባሪ “የተዋጠው” ከዚያም “የተተፋው” በዚህ መንገድ ነው! እንደ እውነቱ ከሆነ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ሃያሲያን ከትልቁ ዓሣ ይበልጥ እነሱ ዮናስን ለመዋጥ ቆርጠው የተነሱ ይመስላሉ!

ብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በዮናስ መጽሐፍ ላይ ጥርጣሬ የሚያድርባቸው ለምንድን ነው? የተለያዩ ተአምራትን የያዘ መጽሐፍ በመሆኑ ነው። በርካታ ሃያሲያን፣ ተአምር የሚባል ነገር የለም የሚል ግትር አመለካከት ያላቸው ይመስላል። ይሁን እንጂ ይህ አመለካከት ምክንያታዊ ነው? እስቲ እንዲህ ብለህ ራስህን ጠይቅ፦ ‘በመጽሐፍ ቅዱስ መግቢያ ላይ የሚገኘውን “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” የሚለውን ሐሳብ አምንበታለሁ?’ (ዘፍጥረት 1:1) በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አስተዋይ ሰዎች ይህን ግልጽና የማያሻማ እውነት አምነው ይቀበላሉ። ይህ እውነታ ደግሞ ከጊዜ በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገለጹት ሌሎች ተአምራት ሁሉ የላቀ ተአምር ነው።

እስቲ አስበው፦ በከዋክብት የተሞላውን ሰማይና በምድር ላይ የሚገኙትን እጅግ አስደናቂ የሆኑ ነገሮች ሁሉ የፈጠረው አምላክ፣ በዮናስ መጽሐፍ ውስጥ ከተገለጹት ክንውኖች መካከል የትኛው ሊሳነው ይችላል? ማዕበል ማስነሳት? አንድ ትልቅ ዓሣ አንድን ሰው እንዲውጥ ማድረግ? ወይስ ይኸው ዓሣ የዋጠውን ሰው መልሶ እንዲተፋ ማድረግ? ገደብ የለሽ ኃይል ያለው አምላክ እንዲህ ያሉ ነገሮችን መፈጸም አያቅተውም።—ኢሳይያስ 40:26

ሌላው ቀርቶ ያለ ምንም መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት በጣም አስደናቂ የሆኑ ነገሮች የሚፈጸሙባቸው ጊዜያት አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በ1758 አንድ መርከበኛ በሜድትራንያን ባሕር ላይ እየተጓዘ ሳለ ከመርከቡ ላይ በመውደቁ አንድ ሻርክ ውጦት እንደነበር ይነገራል። ይሁንና ሻርኩ በመድፍ በመመታቱ መርከበኛውን መልሶ ተፋው፤ ሰውየው ይህ ነው የሚባል ጉዳት ሳይደርስበት መትረፍ ችሏል። ይህ እውነት ከሆነ፣ ታሪኩ አጀብ የሚያሰኝ ነው፤ ተአምር ግን አይደለም። ታዲያ አምላክ ኃይሉን ተጠቅሞ ከዚህ የበለጠ ነገር መፈጸም አይችልም?

በዮናስ መጽሐፍ ላይ ጥርጣሬ ያላቸው ሰዎች፣ ማንኛውም ሰው ቢሆን አየር ስለሚያጥረው በዓሣ ሆድ ውስጥ ለሦስት ቀናት ሊቆይ አይችልም ብለው ይከራከራሉ። ሆኖም ሰዎች እንኳ በዕቃ ውስጥ የታመቀ አየር ይዘው ባሕር ውስጥ በመግባት በውኃ ውስጥ ለረጅም ሰዓት መቆየት ችለዋል። ታዲያ አምላክ ይህ ነው የማይባለውን ታላቅ ኃይሉንና ጥበቡን በመጠቀም ዮናስ ለሦስት ቀናት በሕይወት እንዲቆይ ማድረግ ይሳነዋል? አንድ የይሖዋ መልአክ በአንድ ወቅት የኢየሱስ እናት ለሆነችው ለማርያም እንደገለጸው ‘ለአምላክ የሚሳነው ነገር የለም።’—ሉቃስ 1:37 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

የዮናስ መጽሐፍ ትክክለኛ ታሪክ መሆኑን የሚያሳይ ምን ተጨማሪ ማስረጃ አለ? ዮናስ ስለ መርከቧና ስለ ሠራተኞቹ የሰጠው መግለጫ እያንዳንዱን ዝርዝር ጉዳይ የሚገልጽ ከመሆኑም በላይ በእውነታ ላይ የተመሠረተ ነው። በ⁠ዮናስ 1:5 ላይ መርከበኞቹ የመርከቧን ክብደት ለመቀነስ በውስጧ የነበረውን ዕቃ እንደጣሉ ተገልጿል። በጥንት ጊዜ የነበሩ ታሪክ ጸሐፊዎችም ሆኑ የረቢዎች ሕግ እንደሚያመለክቱት መጥፎ የአየር ጠባይ በሚከሰትበት ጊዜ እንዲህ ማድረግ የተለመደ ነበር። ዮናስ ስለ ነነዌ የሰጠው መግለጫም ቢሆን ከታሪካዊና አርኪኦሎጂያዊ ማስረጃዎች ጋር ይስማማል። ከሁሉ በላይ ግን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ዮናስ በትልቅ ዓሣ ሆድ ውስጥ ለሦስት ቀናት መቆየቱ እሱ በመቃብር ውስጥ የሚቆይበትን ጊዜ የሚያመለክት ትንቢታዊ ጥላ እንደሆነ ገልጿል። (ማቴዎስ 12:38-40) ኢየሱስ የሰጠው ምሥክርነት የዮናስ ታሪክ እውነት መሆኑን ያረጋግጣል።

‘ለአምላክ የሚሳነው ነገር የለም።’—ሉቃስ 1:37 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መርከበኞቹ ዮናስን ወደ ባሕሩ ጣሉት