ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
ለልጆች ተግሣጽ መስጠት
ጆን፦ * ወላጆቼ አንድ ጥፋት በምሠራበት ጊዜ እኔን ከመቅጣታቸው በፊት ለምን እንደዛ እንዳደረግሁና በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ለመረዳት ከልብ ጥረት ያደርጋሉ። እኔም ሴቶች ልጆቼን ስቀጣ እነሱ ይጠቀሙበት የነበረውን ዘዴ ለመኮረጅ እጥራለሁ። የባለቤቴ የአለሰን አስተዳደግ ደግሞ ከእኔ የተለየ ነው። የእሷ አባትና እናት ቁጣ የሚቀናቸው ሰዎች ነበሩ። አንድ ነገር በሚፈጠርበት ጊዜ በጉዳዩ ዙሪያ የነበሩትን ሁኔታዎች ሳያጤኑ ልጆቻቸውን የመቅጣት ልማድ የነበራቸው ይመስላል። አንዳንድ ጊዜ ባለቤቴ ልጆቻችንን፣ ወላጆቿ ይቀጧት በነበረው መንገድ በኃይል እንደምትቀጣቸው ይሰማኛል።
ካረል፦ ገና የአምስት ዓመት ልጅ እያለሁ አባቴ ቤተሰቡን ጥሎ ሄደ። ለእኔም ሆነ ለሦስቱ እህቶቼ ምንም ግድ አልነበረውም። እናቴ ለእኛ የሚያስፈልገውን ነገር ለማሟላት በጣም ትደክም ነበር፤ ታናናሽ እህቶቼን የመንከባከቡ ኃላፊነት ደግሞ በእኔ ትከሻ ላይ ወደቀ። አንድ ወላጅ የሚያደርገውን ነገር ለማድረግ ስለተገደድኩ እንደ ልጅ ተጫውቼ አላደግኩም። አሁንም ቢሆን ቁም ነገር እንጂ ቀልድ የሚባል ነገር አላውቅም። ልጆቼ አጥፍተው እርማት በሚያስፈልጋቸው ጊዜ የሠሩትን ስህተት መርሳት ይከብደኛል። አንድ ጥፋት በሚሠሩበት ጊዜ ምን አስበው እንደዚያ እንዳደረጉ ማወቅ እፈልጋለሁ። በአንጻሩ ደግሞ ባለቤቴ ማርክ አንድን ጉዳይ ሲያብሰለስል አይከርምም። አባቱ ጥብቅ ቢሆንም እንኳ አፍቃሪ ነበር፤ ደግሞም ምንጊዜም ለባለቤቱ የሚያስብ ሰው ነበር። ማርክ ሴቶች ልጆቻችን በሚያጠፉበት ጊዜ መፍትሔ ለማምጣት ፈጣን ነበር። ሁኔታውን አመዛዝኖ መፍትሔ ከሰጠ በኋላ ዳግመኛ ስለ ጉዳዩ አያስብም።
ጆንና ካረል ከተናገሩት ሐሳብ መመልከት እንደሚቻለው አስተዳደጋችሁ ለልጆቻችሁ ተግሣጽ በምትሰጡበት መንገድ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል። አንድ ባልና ሚስት አስተዳደጋቸው የተለያየ በሚሆንበት ጊዜ ልጆችን ከማሠልጠን ጋር በተያያዘ በጣም የተለያየ አመለካከት ሊኖራቸው ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ይህ ልዩነት በትዳራቸው ውስጥ ውጥረት እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል።
ወላጆች ኃይላቸው እየተሟጠጠ ሲሄድ በመካከላቸው ያለው ውጥረት ሊባባስ ይችላል። ወላጆች የመጀመሪያ ልጃቸውን ከወለዱ በኋላ ልጆችን ማሠልጠን አድካሚ የሆነ የሙሉ ጊዜ ሥራ እንደሆነ ለመረዳት ጊዜ አይወስድባቸውም። ከባለቤቷ ከዳረን ጋር በመሆን ሁለት ሴት ልጆችን ያሳደገችው ጆውን እንዲህ ትላለች፦ “ልጆቼን እወዳቸዋለሁ፤ ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ እኔ እንዲተኙ በምፈልግበት
ሰዓት እሺ ብለው አይተኙም። ደግሞም አጉል ሰዓት ላይ ከእንቅልፋቸው ይነቃሉ። ላናግራቸው ስፈልግ በሥርዓት አያዳምጡኝም። ጫማዎቻቸውን፣ ልብሶቻቸውንና አሻንጉሊቶቻቸውን በየቦታው አዝረክርከው ይተዋሉ፤ በልተው ከጨረሱ በኋላ የተረፈውን ምግብ አያነሱም።”ጃክ፣ ባለቤቱ ሁለተኛ ልጃቸውን ከወለደች በኋላ ከወሊድ ጋር ተያይዞ በሚመጣ ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ትሠቃይ የነበረ ሲሆን በወቅቱ የገጠመውን ሁኔታ እንዲህ ሲል ይገልጻል፦ “አብዛኛውን ጊዜ ከሥራ ደክሞኝ ወደ ቤት እመለሳለሁ፤ ከዚያ በኋላ ደግሞ ግማሹን ሌሊት ሕፃኗን በመንከባከብ አሳልፋለሁ። ይህ ሁኔታ ትልቋን ልጃችንን ቀጣይነት ባለው መንገድ ማሠልጠንና ማረም አስቸጋሪ እንዲሆንብን አደረገ። ትልቋ ልጃችን ለታናሽ እህቷ ትኩረት መስጠታችን ያስቀናት ነበር።”
በሥራ የዛሉ ወላጆች ልጆቻቸውን የሚያሠለጥኑበትን መንገድ በተመለከተ ሲነጋገሩ የሚፈጠሩ ጥቃቅን አለመግባባቶች መልካቸውን ቀይረው ከፍተኛ ውዝግብ ሊያስከትሉ ይችላሉ። እልባት ሳያገኙ የቀሩ አለመግባባቶች በባልና ሚስት መካከል ክፍተት እንዲፈጠር ሊያደርጉ ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ ልጆች የፈለጉትን ለማግኘት ወደ ማን መጠጋት እንዳለባቸው እንዲያውቁ ያስችላቸዋል። ባልና ሚስት የጋብቻ ጥምረታቸውን ለማጠንከርም ሆነ ልጆቻቸውን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማሠልጠን የሚረዷቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች የትኞቹ ናቸው?
ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ጊዜ አሳልፉ
አምላክ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጆች ከመውለዳቸው በፊት ተጋብተው እንዲኖሩና ልጆቹ ራሳቸውን ችለው ከወጡም በኋላ በጋብቻቸው እንዲቀጥሉ ዓላማው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ የጋብቻ ጥምረትን በተመለከተ “አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው” ይላል። (ማቴዎስ 19:6) በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ልጅ ውሎ አድሮ ‘ከአባትና ከእናቱ መለየቱ’ የአምላክ ዓላማ እንደሆነ ቃሉ ይናገራል። (ማቴዎስ 19:5) በእርግጥም ልጆችን ማሳደግ ለትዳር መሠረት ሳይሆን የትዳር ሕይወት አንድ ገጽታ ብቻ ነው። ወላጆች ልጆቻቸውን ለማሠልጠን ጊዜ መመደብ እንደሚያስፈልጋቸው ምንም ጥያቄ የለውም፤ ሆኖም ይህን ለማድረግ የሚያስችለው ወሳኝ ነገር ጠንካራ ትዳር መሆኑን ማስታወስ ይኖርባቸዋል።
ባልና ሚስት ልጆች በሚያሳድጉባቸው ዓመታት ግንኙነታቸው ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ከሚያስችሉት ነገሮች መካከል አንዱ ምንድን ነው? በተቻለ መጠን ልጆቹ በሌሉበት አብራችሁ የምታሳልፉት ቋሚ ጊዜ መድቡ። እንዲህ ማድረጋችሁ ቤተሰቡን የሚመለከቱ አስፈላጊ ጉዳዮችን አንስታችሁ ለመወያየትና አብራችሁ የምታሳልፉት ጊዜ ለማግኘት ያስችላችኋል። ሁለታችሁ ብቻ ሆናችሁ የምታሳልፉት ጊዜ ማግኘት ቀላል እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው አለሰን የተባለችው የሁለት ልጆች እናት እንዲህ ትላለች፦ “እኔና ባለቤቴ አብረን የምናሳልፈው ጥቂት ጊዜ አገኘን ብለን ስናስብ ድንገት ትንሿ ልጃችን አንድ ነገር እንድናደርግላት ትፈልጋለች፤ ወይም ደግሞ የስድስት ዓመቷ ልጃችን ምናልባት ከለሮቿ ጠፍተውባት አሊያም በሌላ ምክንያት ይሆናል ትልቅ ‘ቀውስ’ እንደገጠማት ሆና ወደ እኛ ትመጣለች።”
ቀደም ሲል የተጠቀሱት ጆውንና ዳረን ልጆቻቸው የሚተኙበት ቋሚ የሆነ ሰዓት በመመደብና ሰዓቱን እንዲያከብሩ በማድረግ አብረው የሚያሳልፉት ጊዜ ማግኘት ችለዋል። ጆውን እንዲህ ትላለች፦ “ልጆቻችን ምንጊዜም የመኝታ ቤታቸው መብራት ከመጥፋቱ በፊት በተወሰነላቸው ሰዓት አልጋቸው ውስጥ እንዲሆኑ ይጠበቅባቸው ነበር። በዚህ ወቅት እኔና ዳረን ዘና የምንልበትና የምናወራበት ጊዜ እናገኛለን።”
ባልና ሚስት ልጃቸው የሚተኛበት ቋሚ የሆነ ሰዓት መመደባቸው አብረው የሚያሳልፉት ጊዜ የሚያስገኝላቸው ከመሆኑም በላይ ልጁ “ከሚገባው በላይ ስለ ራሱ በማሰብ ራሱን ከፍ አድርጎ [እንዳይመለከት]” ይረዳዋል። (ሮም 12:3) የመኝታ ሰዓታቸውን እንዲያከብሩ ሥልጠና የተሰጣቸው ልጆች በቤተሰቡ ውስጥ አስፈላጊ ቢሆኑም የቤተሰቡ ሕልውና የተመካው በእነሱ ላይ አለመሆኑን ቀስ በቀስ መገንዘባቸው አይቀርም። ቤተሰቡ ከእነሱ ፍላጎት ጋር እንዲስማማ ከመጠበቅ ይልቅ እነሱ ቤተሰቡ ከሚከተለው ልማድ ጋር መስማማት ይኖርባቸዋል።
እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ቋሚ የመኝታ ሰዓት መድቡ፤ እንዲሁም ሰዓቱ ምንጊዜም እንዲከበር አድርጉ። ልጃችሁ ‘ውኃ ልጠጣ’ ብሎ ወይም ሌላ ምክንያት በማቅረብ ትንሽ መቆየት ቢፈልግ ጥያቄውን ለማስተናገድ ትፈቅዱ ይሆናል። ሆኖም ልጃችሁ ማለቂያ የሌለው ጥያቄ እያቀረበ የመኝታ ሰዓቱን ዝም ብሎ እንዲያራዝም አትፍቀዱለት። ልጃችሁ አምስት ደቂቃ እንዲጨመርለት ቢለምናችሁና በሐሳቡ ብትስማሙ ጊዜው እንዲከበር ለማድረግ ጥረት አድርጉ። ልክ ሰዓቱ ሲሞላ ያለምንም ጥያቄ ወደ መኝታው እንዲሄድ አድርጉ። “ቃላችሁ አዎ ከሆነ አዎ ይሁን፤ አይደለም ከሆነ አይደለም ይሁን።”—ማቴዎስ 5:37
ሁለታችሁም አንድ አቋም ይኑራችሁ
አንድ ጥበብ ያዘለ ምሳሌ “ልጄ ሆይ፤ የአባትህን ምክር አድምጥ፤ የእናትህንም ትምህርት አትተው” ይላል። (ምሳሌ 1:8) ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አባቶችም ሆኑ እናቶች በልጆቻቸው ላይ ሥልጣን እንዳላቸው ያሳያል። ይሁን እንጂ አንድ ዓይነት አስተዳደግ ያላቸው ባልና ሚስት እንኳ ልጃቸውን እንዴት መገሠጽ እንዳለባቸው እንዲሁም አንድ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥም ቤተሰቡ ያወጣቸውን የትኞቹን መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በሚወስኑበት ጊዜ ላይስማሙ ይችላሉ። ታዲያ ወላጆች እንዲህ ዓይነቱን አስቸጋሪ ሁኔታ መወጣት የሚችሉት እንዴት ነው?
ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጆን “በልጆች ፊት ከመጨቃጨቅ መቆጠብ አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማኛል” ብሏል። ይሁን እንጂ አንድ አቋም መያዝ እንደሚናገሩት ቀላል እንዳልሆነ ሳይሸሽግ ተናግሯል። ጆን እንዲህ ይላል፦ “ልጆች በጣም አስተዋዮች ናቸው። አለመግባባታችንን በቃላት ባንገልጽም እንኳ ልጃችን ስሜታችንን ማንበብ ትችላለች።”
ጆንና አለሰን ይህን አስቸጋሪ ሁኔታ የተወጡት እንዴት ነው? አለሰን እንዲህ ትላለች፦ “ባለቤቴ ልጃችንን የሚቀጣበት መንገድ ትክክል እንዳልሆነ በሚሰማኝ ጊዜ የእኔን ሐሳብ ከመግለጼ በፊት ልጃችን ራቅ ብላ እስክትሄድ ድረስ እጠብቃለሁ። በመካከላችን ባለው የአመለካከት ልዩነት ተጠቅማ እኛን እንደፈለገች ማሽከርከር እንደምትችል እንዲሰማት ማድረግ አልፈልግም። በመካከላችን ልዩነት መኖሩን ከተገነዘበች እያንዳንዱ የቤተሰቡ አባል የይሖዋን ዝግጅት ማክበር እንደሚኖርበትና እሷ ለወላጆቿ ሥልጣን መገዛት እንዳለባት ሁሉ እኔም ለአባቷ የራስነት ሥልጣን በፈቃደኝነት እንደምገዛ እነግራታለሁ።” (1 ቆሮንቶስ 11:3፤ ኤፌሶን 6:1-3) ጆን እንዲህ ይላል፦ “ቤተሰቡ አንድ ላይ በሚሆንበት ጊዜ በአብዛኛው ልጆቻችንን ለመቅጣት ኃላፊነቱን የምወስደው እኔ ነኝ። ይሁንና አለሰን ስለ ሁኔታው ይበልጥ የምታውቅ ከሆነ እሷ እንድትቀጣቸው አደርግና በቅጣቱ መስማማቴን እገልጻለሁ። በአንድ ጉዳይ ላይ ከእሷ ጋር ባልስማማ በሌላ ጊዜ ጉዳዩን አንስቼ አነጋግራታለሁ።”
ልጆችን ማሠልጠንን በተመለከተ በአንተና በትዳር ጓደኛህ መካከል የተፈጠረ አለመግባባት የቅሬታ ስሜት እንዳያስከትልና በዚህም ምክንያት ልጆቻችሁ ለእናንተ ያላቸው አክብሮት እንዳይቀንስ መከላከል የምትችሉት እንዴት ነው?
እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ልጆችን ማሠልጠንን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በየሳምንቱ ለመነጋገር ቋሚ ጊዜ መድቡ፤ በመካከላችሁ ያለውን የአመለካከት ልዩነት አንስታችሁም በግልጽ ተወያዩ። የትዳር ጓደኛችሁን አመለካከት ለመረዳት ጥረት አድርጉ፤ እንዲሁም የትዳር ጓደኛችሁና እናንተ ከልጁ ጋር ያላችሁ ዝምድና የተለያየ ሊሆን እንደሚችል አምናችሁ ተቀበሉ።
የወላጅነት ኃላፊነታችሁ እንዲያቀራርባችሁ አድርጉ
ልጆችን ማሠልጠን ከባድ ሥራ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። አንዳንድ ጊዜ ኃላፊነቱ ኃይላችሁን እንዳሟጠጠባችሁ ይሰማችሁ ይሆናል። ይዋል ይደር እንጂ ልጆቻችሁ ራሳቸውን ችለው መሄዳቸው አይቀርም፤ በዚህ ጊዜ እንደ አዲስ ባልና ሚስት እንደሆናችሁ ይሰማችኋል። ልጆች በማሳደግ ያሳለፋችሁት ጊዜ የጋብቻ ትስስራችሁን አጠናክሮታል ወይስ አዳክሞታል? የዚህ ጥያቄ መልስ በመክብብ 4:9, 10 ላይ የሚገኘውን “ለሥራቸው መልካም ውጤት ስለሚያገኙ፣ ከአንድ፣ ሁለት መሆን ይሻላል፤ አንዱ ቢወድቅ፣ ባልንጀራው ደግፎ ያነሣዋል” የሚለውን መመሪያ በተግባር በምታውሉበት መንገድ ላይ የተመካ ነው።
ወላጆች ተደጋግፈው በሚሠሩበት ጊዜ ውጤቱ እጅግ ያማረ ይሆናል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ካረል እንዲህ ስትል ስሜቷን ገልጻለች፦ “ባለቤቴ በጣም ግሩም ባሕርያት እንዳሉት አውቃለሁ፤ ይሁንና ልጆችን አብረን ማሳደጋችን ሌሎች ጥሩ ጎኖቹን ማየት እንድችል አድርጎኛል። ልጆቻችንን በፍቅር የሚንከባከብበትን መንገድ በማየት ለእሱ ያለኝ ፍቅርና አክብሮት አድጓል።” ጆን ደግሞ ስለ አለሰን ሲናገር “ባለቤቴ አሳቢ እናት መሆኗን ማየቴ ለእሷ ያለኝ ፍቅርና አድናቆት እንዲጨምር አድርጎኛል” ብሏል።
ልጆች በምታሳድጉባቸው ዓመታት ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር የምታሳልፉት ጊዜ የምትመድቡና ተደጋግፋችሁ የምትሠሩ ከሆነ ልጆቻችሁ እያደጉ ሲሄዱ ትዳራችሁም እየተጠናከረ ይሄዳል። ለልጆቻችሁ ከዚህ የተሻለ ምን ጥሩ ምሳሌ መተው ትችላላችሁ?
^ አን.3 ስሞቹ ተቀይረዋል።
ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ . . .
-
ልጆቻችን በሌሉበት ከትዳር ጓደኛዬ ጋር በየሳምንቱ ምን ያህል ጊዜ አሳልፋለሁ?
-
ባለቤቴ ልጆቻችንን በሚቀጣበት ወይም በምትቀጣበት ወቅት በቅጣቱ መስማማቴን ማሳየት የምችለው እንዴት ነው?