አምላክ ሁሉንም የአምልኮ ዓይነቶች ይቀበላል?
አምላክ ሁሉንም የአምልኮ ዓይነቶች ይቀበላል?
የተለመዱት መልሶች፦
▪ “ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ አምላክ የሚያደርሱ መንገዶች ናቸው።”
▪ “የምታምነው ምንም ይሁን ምን ዋናው ነገር ቅን መሆንህ ነው።”
ኢየሱስ ምን ብሏል?
▪ “በጠባቡ በር ግቡ፤ ምክንያቱም ወደ ጥፋት የሚወስደው መንገድ ትልቅና ሰፊ ነው፤ በዚያ የሚሄዱም ብዙዎች ናቸው። ወደ ሕይወት የሚያስገባው በር ግን ጠባብ መንገዱም ቀጭን ነው፤ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።” (ማቴዎስ 7:13, 14) ኢየሱስ ሁሉም መንገዶች ወደ አምላክ ያደርሳሉ የሚል እምነት አልነበረውም።
▪ “በዚያ ቀን ብዙዎች ‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ በስምህ ትንቢት አልተናገርንም? በስምህ አጋንንትን አላወጣንም? በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንም?’ ይሉኛል። እኔም በዚያ ጊዜ ‘ቀድሞውንም አላውቃችሁም! እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ’ እላቸዋለሁ።” (ማቴዎስ 7:22, 23) ኢየሱስ የእሱ ተከታይ እንደሆኑ የሚናገሩትን ሁሉ አልተቀበላቸውም።
ሃይማኖተኛ የሆኑ ብዙ ሰዎች ለሚያምኑባቸው ነገሮችና ለሚከተሏቸው ወጎች ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ። ይሁንና እነዚህ ትምህርቶች የአምላክ ቃል ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የማይስማሙ ቢሆኑስ? ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩትን የሃይማኖት መሪዎች “ለወጋችሁ ስትሉ የአምላክን ቃል ሽራችኋል” ባላቸው ጊዜ የሰውን ወግ መከተል አደገኛ መሆኑን ገልጿል። በመቀጠልም አምላክ የተናገራቸውን የሚከተሉትን ቃላት ጠቅሶ ተናግሯል፦ “ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ እጅግ የራቀ ነው። የሚያስተምሩት የሰውን ሥርዓት ስለሆነ እኔን የሚያመልኩት በከንቱ ነው።”—ማቴዎስ 15:1-9፤ ኢሳይያስ 29:13
የምናምንባቸው ነገሮች ብቻ ሳይሆኑ አኗኗራችንም ትልቅ ቦታ አለው። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን እናመልካለን ብለው ስለሚናገሩ አንዳንድ ሰዎች ሲገልጽ “አምላክን እንደሚያውቁ በይፋ ይናገራሉ፤ ሆኖም በሥራቸው ይክዱታል” ይላል። (ቲቶ 1:16) እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናችን ስላሉ ሰዎች ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “እግዚአብሔርን ከመውደድ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወድዱ ይሆናሉ። እንዲሁም ሃይማኖት ያላቸው ይመስላሉ፤ ነገር ግን የሃይማኖትን ኀይል ይክዳሉ፤ ከእነዚህም ሰዎች ራቅ።”—2 ጢሞቴዎስ 3:4, 5 የ1980 ትርጉም
ቅንነት ብቻውን በቂ አይደለም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አንድ ሰው ቅን ቢሆንም ሊሳሳት ይችላል። በመሆኑም ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ወሳኝ ነው። (ሮም 10:2, 3) ይህን እውቀት መቅሰምና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካለው ትምህርት ጋር ተስማምቶ መኖር አምላክን እንድናስደስት ያስችለናል። (ማቴዎስ 7:21) እንግዲያው ትክክለኛው ሃይማኖት ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ መያዝን፣ ትክክለኛ እምነት ማዳበርንና ትክክለኛ ድርጊት መፈጸምን ይጠይቃል። ትክክለኛ ድርጊት መፈጸም ሲባል ደግሞ በየዕለቱ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ማለት ነው።—1 ዮሐንስ 2:17
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ የሚያስተምረውን ትምህርት በተመለከተ ተጨማሪ እውቀት ማግኘት ከፈለግህ መጽሐፍ ቅዱስ በነፃ እንዲያስጠኑህ የይሖዋ ምሥክሮችን መጠየቅ ትችላለህ።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ትክክለኛው ሃይማኖት ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ መያዝን፣ ትክክለኛ እምነት ማዳበርንና ትክክለኛ ድርጊት መፈጸምን ይጠይቃል