በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ማን ነው?

አምላክ ማን ነው?

አምላክ ማን ነው?

ለዚህ ጥያቄ ምን መልስ ትሰጣለህ? አንዳንዶች አምላክን በደንብ እንደሚያውቁት እንዲያውም የቅርብ ወዳጃቸው እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሌሎች ደግሞ ልክ እንደ ሩቅ ዘመድ አድርገው ይመለከቱታል። አምላክ መኖሩን የሚያምኑ ቢሆኑም እንኳ ስለ እሱ የሚያውቁት ግን በጣም ጥቂት ነው። በአምላክ የምታምን ከሆነ ከዚህ በታች ለተዘረዘሩት ጥያቄዎች ምን መልስ ትሰጣለህ?

1. አምላክ አካል አለው?

2. አምላክ ስም አለው?

3. ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው?

4. አምላክ ስለ እኔ ያስባል?

5. አምላክ ሁሉንም የአምልኮ ዓይነቶች ይቀበላል?

እነዚህን ጥያቄዎች ለሌሎች ሰዎች ብታቀርብ በጣም የተለያዩ መልሶች እንደምታገኝ ምንም ጥርጥር የለውም። በመሆኑም አምላክን በተመለከተ የተሳሳቱ እምነቶችና አመለካከቶች መኖራቸው ምንም አያስገርምም።

የጥያቄዎቹን መልስ ማወቅ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ካገኛት በአምላክ የምታምን ሴት ጋር በተነጋገረበት ወቅት ስለ አምላክ እውነቱን የማወቁን አስፈላጊነት አበክሮ ገልጿል። ይህች ሳምራዊት ሴት ኢየሱስ ነቢይ መሆኑን ተቀብላ ነበር። ይሁንና አንድ የከነከናት ጉዳይ አለ። ኢየሱስ የአይሁድ እምነት ተከታይ ሲሆን እሷ የምትከተለው ሃይማኖት ግን የተለየ ነበር። ይህን የሚያሳስባትን ጉዳይ በገለጸችበት ወቅት ኢየሱስ “እናንተ የማታውቁትን ታመልካላችሁ” ሲል በግልጽ ነገራት። (ዮሐንስ 4:19-22) ኢየሱስ ሃይማኖተኛ የሆኑ ሰዎች በሙሉ አምላክን በትክክል ያውቃሉ የሚል እምነት እንዳልነበረው ከዚህ በግልጽ ማየት እንችላለን።

ኢየሱስ እንዲህ ሲል የትኛውም ሰው አምላክን በትክክል ማወቅ አይችልም ማለቱ ነበር? በጭራሽ። ኢየሱስ በመቀጠል ሴቲቱን እንዲህ አላት፦ ‘እውነተኛ አምላኪዎች አብን በመንፈስና በእውነት ያመልኩታል፤ ምክንያቱም አብ እንዲህ ዓይነት ሰዎች እንዲያመልኩት ይፈልጋል።’ (ዮሐንስ 4:23) አንተስ አምላክን “በመንፈስና በእውነት” ከሚያመልኩት ሰዎች መካከል ነህ?

የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቅህ በጣም አስፈላጊ ነው። ለምን? ኢየሱስ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ስለሆንከው ስለ አንተና ስለላክኸው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት መቅሰማቸውን መቀጠል አለባቸው” ብሎ በጸለየበት ጊዜ ትክክለኛ እውቀት የማግኘትን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። (ዮሐንስ 17:3) አዎን፣ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋህ ስለ አምላክ እውነቱን ከማወቅህ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው!

በእርግጥ ስለ አምላክ እውነቱን ማወቅ ይቻላል? አዎ፣ ይቻላል! ታዲያ ይህን እውነት ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ ስለ ራሱ ሲናገር “እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ። በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” ብሏል። (ዮሐንስ 14:6) በተጨማሪም “ከወልድና ወልድ ሊገልጥለት ከሚፈቅድለት በስተቀር አብ ማን እንደሆነ የሚያውቅ የለም” በማለት ተናግሯል።—ሉቃስ 10:22

ስለዚህ የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረው ትምህርት አምላክን ለማወቅ የሚያስችል ቁልፍ ነው። እንዲያውም ኢየሱስ “በትምህርቴ ብትጸኑ እናንተ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነጻ ያወጣችኋል” በማለት ቃል ገብቶልናል።—ዮሐንስ 8:31, 32 አ.መ.ት

ታዲያ ኢየሱስ ቀደም ሲል ለተነሱት አምስት ጥያቄዎች ምን መልስ ይሰጥ ይሆን?

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በትክክል የማታውቀውን አምላክ ታመልካለህ?