አምላክ ስም አለው?
አምላክ ስም አለው?
የተለመዱት መልሶች፦
▪ “ስሙ ጌታ ነው።”
▪ “የግል መጠሪያ ስም የለውም።”
ኢየሱስ ምን ብሏል?
▪ “እንግዲያው እናንተ በዚህ መንገድ ጸልዩ:- ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን፣ ስምህ ይቀደስ።’” (ማቴዎስ 6:9) ኢየሱስ አምላክ ስም እንዳለው ያምን ነበር።
▪ “እኔን የወደድክበትን ፍቅር እነሱም እንዲያንጸባርቁ እንዲሁም እኔ ከእነሱ ጋር አንድነት እንዲኖረኝ ስምህን ለእነሱ አሳውቄአለሁ፤ ደግሞም አሳውቃለሁ።” (ዮሐንስ 17:26) ኢየሱስ የአምላክን ስም ለሌሎች አሳውቋል።
▪ “‘በይሖዋ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው!’ እስክትሉ ድረስ ፈጽሞ አታዩኝም።” (ሉቃስ 13:35፤ መዝሙር 118:26) ኢየሱስ በአምላክ ስም ይጠቀም ነበር።
አምላክ ራሱ ስሙ ማን እንደሆነ ነግሮናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “እኔ ይሖዋ ነኝ፤ ስሜም ይህ ነው” ብሎ መናገሩ ተጽፏል። * (ኢሳይያስ 42:8 አሜሪካን ስታንዳርድ ቨርዥን) አምላክ ለራሱ የሰጠው የዕብራይስጥ ስም በአማርኛ ይሖዋ የሚል ነው። ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የዕብራይስጥ ስም በጥንቶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ውስጥ በሺዎች በሚቆጠሩ ቦታዎች ላይ የሚገኝ መሆኑ ያስገርምህ ይሆናል። እንዲያውም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሰ ከሌላ ከማንኛውም ስም የበለጠ በብዛት ይገኛል።
አንዳንዶች “የአምላክ ስም ማን ነው?” ተብለው ሲጠየቁ “ጌታ ነው” ብለው ይመልሳሉ። ይሁንና እንዲህ ዓይነቱ መልስ “ምርጫውን ማን አሸነፈ?” ለሚለው ጥያቄ “ዕጩው” ብሎ ከመመለስ ያለፈ ትርጉም ያለው መልእክት አያስተላልፍም። በተጨማሪም “ጌታ” እና “ዕጩው” የሚሉት ቃላት ስም ስላልሆኑ ለጥያቄው ተገቢ መልስ ሊሆኑ አይችሉም።
አምላክ ስሙን የገለጠልን ለምንድን ነው? ይህን ያደረገው እሱን በተሻለ ሁኔታ ማወቅ እንድንችል ነው። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት አንድ ሰው እንደ ሁኔታው አቶ፣ አለቃ፣ አባዬ ወይም አያቴ ተብሎ ሊጠራ ይችላል። እነዚህ የማዕረግ ስሞች ስለ ግለሰቡ የሚገልጹት ነገር ይኖራል። የግለሰቡ መጠሪያ ስም ግን ስለ እሱ የምናውቀውን ነገር በሙሉ ያስታውሰናል። በተመሳሳይም ጌታ፣ ሁሉን ቻይ፣ አባት እና ፈጣሪ እንደሚሉት ያሉ የማዕረግ ስሞች አምላክ ያከናወናቸውን የተለያዩ ተግባራት ቆም ብለን እንድናስብ ያደርጉናል። ይሁንና ስለ እሱ የምናውቀውን ነገር በሙሉ እንድናስታውስ የሚያደርገን ይሖዋ የሚለው የግል ስሙ ብቻ ነው። ስሙን ሳታውቅ አምላክን እንዴት በትክክል ልታውቀው ትችላለህ?
የአምላክን ስም ማወቅ ብቻ ሳይሆን በስሙ መጠቀምም በጣም አስፈላጊ ነው። ለምን? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” ይላል።—ሮም 10:13፤ ኢዩኤል 2:32
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.9 የአምላክን ስም ትርጉም እንዲሁም በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ ስሙ የማይገኘው ለምን እንደሆነ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 195-197 መመልከት ትችላለህ።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አንድ ሰው እንደ ሁኔታው አቶ፣ አለቃ፣ አባዬ ወይም አያቴ ተብሎ ሊጠራ ይችላል። የሰውየው የግል ስም ግን ስለ እሱ የምናውቀውን ነገር በሙሉ ያስታውሰናል