በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች ምስሎችን ለአምልኮ የማይጠቀሙት ለምንድን ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች ምስሎችን ለአምልኮ የማይጠቀሙት ለምንድን ነው?

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ

የይሖዋ ምሥክሮች ምስሎችን ለአምልኮ የማይጠቀሙት ለምንድን ነው?

በምድር ዙሪያ የሚገኙ ሂንዱዎች፣ ቡድሂስቶች፣ ካቶሊኮችና የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባላት ምስሎች ወይም ቅርጻ ቅርጾች የአምልኳቸው ወሳኝ ክፍል እንደሆኑ አድርገው ያስባሉ። በአንዳንድ የአፍሪካ ክፍሎች የሚኖሩ ሰዎች ደግሞ አምላክ ወይም የአማልክት መንፈስ ይኖርባቸዋል ብለው የሚያስቧቸውን ከእንጨት ወይም ከድንጋይ የተሠሩ ቅርጻ ቅርጾች ለአምልኮ ይጠቀሙባቸዋል።

በአንጻሩ የይሖዋ ምሥክሮች ለአምልኮ በምስሎችና በቅርጻ ቅርጾች አይጠቀሙም። የመንግሥት አዳራሽ ብለው የሚጠሩትን የመሰብሰቢያ ቦታቸውን ሄደህ ብታይ “የቅዱሳንን” ምስሎችም ሆነ የኢየሱስን ወይም የማርያምን ሐውልት አታገኝም። * ለምን? ይህን ጉዳይ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ልብ በል።

አምላክ እስራኤላውያን ምን እንዲያደርጉ ይጠብቅባቸው ነበር?

ይሖዋ አምላክ እስራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት ነፃ ካወጣቸው በኋላ እንዴት መመለክ እንደሚፈልግ ግልጽ የሆነ መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር። ከአሥርቱ ትእዛዛት መካከል ሁለተኛው ሕግ እንዲህ ይላል፦ “በላይ በሰማይ ወይም በታች በምድር ካለው ወይም በውሃ ውስጥ ከሚኖሩት ነገሮች በማናቸውም ምስል ለራስህ ጣዖትን አታብጅ። አትስገድላቸው፤ አታምልካቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ . . . ቀናተኛ አምላክ ነኝ።”—ዘፀአት 20:4, 5

አምላክ ለሙሴ እነዚህን ትእዛዛት እየሰጠው በነበረበት በዚያው ወቅት እስራኤላውያን የወርቅ ጥጃ እየሠሩ ነበር፤ ይህን ያደረጉት የግብፃውያንን የእንስሳ አምልኮ በመኮረጅ ሊሆን ይችላል። ለሠሩት ምስል ከግብፃውያን አማልክት የአንዱን ስም አልሰጡትም። ከዚህ ይልቅ ምስሉን ለይሖዋ ከሚቀርብ አምልኮ ጋር አያይዘውታል። (ዘፀአት 32:5, 6) በዚህ ጊዜ አምላክ ምን ተሰማው? ለምስሉ ክብር በሰጡት ሰዎች ላይ ቁጣው ነደደ፤ ሙሴም ምስሉን ወስዶ አቃጠለው።—ዘፀአት 32:9, 10, 19, 20

ከጊዜ በኋላ ይሖዋ አምላክ ሁለተኛውን ሕግ በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጠ። በሙሴ አማካኝነት እስራኤላውያንን እንዲህ በማለት አሳሰባቸው፦ “በወንድ ወይም በሴት መልክ በማናቸውም ዐይነት ምስል የተቀረጸ ጣዖት ለራሳችሁ [አታብጁ]፣ ወይም በምድር ላይ የሚኖር የማናቸውንም እንስሳ ወይም በአየር ላይ የሚበር የማናቸውንም ወፍ፣ ወይም በደረቱ የሚሳብ የማናቸውንም ፍጡር ወይም በውሃ ውስጥ የሚኖር የማናቸውንም ዓሣ ምስል [አታድርጉ]።” (ዘዳግም 4:15-18) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው እስራኤላውያን አምላክን ለማምለክ በማንኛውም ዓይነት ቅርጽ ወይም መልክ የተሠራ ምስል መጠቀም አልነበረባቸውም።

ይሁንና እስራኤላውያን ከጊዜ በኋላ በጣዖት አምልኮ ተዘፈቁ። ይሖዋ እነሱን ለማረም ሲል ጣዖት አምላኪ በመሆናቸው ምክንያት የሚመጣባቸውን ቅጣት በተመለከተ ማስጠንቀቂያ የሚነግሯቸውን ነቢያት ይልክ ነበር። (ኤርምያስ 19:3-5፤ አሞጽ 2:8) እስራኤላውያን በብሔር ደረጃ አምላክ የሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ችላ አሉ። በመሆኑም ይሖዋ በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን እንዲያጠፉና ብሔሩን ማርከው እንዲወስዱ ፈቀደ።—2 ዜና መዋዕል 36:20, 21፤ ኤርምያስ 25:11, 12

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ምን ብለው ያምኑ ነበር?

በመጀመሪያው መቶ ዘመን አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች ክርስትናን በሚቀበሉበት ጊዜ ለአምላክ በሚያቀርቡት አምልኮ በምስሎች መጠቀማቸውን ያቆሙ ነበር። በኤፌሶን ምስሎችን ይሠራ የነበረው ብር አንጥረኛው ድሜጥሮስ የሐዋርያው ጳውሎስን ስብከት በተመለከተ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ሰዎች፣ መቼም ብልጽግናችን የተመካው በዚህ ሥራ ላይ እንደሆነ ታውቃላችሁ። በተጨማሪም ይህ ጳውሎስ የተባለ ሰው በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን በመላው የእስያ አውራጃ ማለት ይቻላል፣ በእጅ የተሠሩ አማልክት ሁሉ አማልክት አይደሉም እያለ ብዙ ሰዎችን አሳምኖ አመለካከታቸውን እንዳስለወጠ ያያችሁትና የሰማችሁት ጉዳይ ነው።”—የሐዋርያት ሥራ 19:25, 26

ጳውሎስ ራሱ የተናገራቸው ቃላት የድሜጥሮስ ክስ ትክክል መሆኑን ያረጋግጣሉ። ጳውሎስ በአቴና ለሚገኙ ግሪካውያን እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “አምላክ በሰው ጥበብና የፈጠራ ችሎታ ከወርቅ ወይም ከብር ወይም ከድንጋይ የተቀረጸን ነገር ይመስላል ብለን ልናስብ አይገባም። እርግጥ አምላክ ሰዎች ባለማወቅ የኖሩበትን ጊዜ ቸል ብሎ አልፎታል፤ አሁን ግን የሰው ልጆች ሁሉ በያሉበት ቦታ ንስሐ መግባት አለባቸው ብሎ እየተናገረ ነው።” (የሐዋርያት ሥራ 17:29, 30) በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ‘ጣዖቶቻችሁን በመተው ወደ አምላክ ተመልሳችኋል’ በማለት አመስግኗቸዋል።—1 ተሰሎንቄ 1:9

ጳውሎስ ብቻ ሳይሆን ሐዋርያው ዮሐንስም ክርስቲያኖች ለአምልኮ ምስሎችን መጠቀም እንደሌለባቸው አስጠንቅቋል። ዮሐንስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ ክርስቲያኖችን “ራሳችሁን ከጣዖቶች ጠብቁ” ሲል በጥብቅ አሳስቧቸዋል።—1 ዮሐንስ 5:21

የይሖዋ ምሥክሮች፣ አምላክ ለእሱ አምልኮ በሚያቀርቡበት ወቅት ማንኛውንም ዓይነት ምስል እንዳይጠቀሙ የሰጠውን ግልጽ መመሪያ ያከብራሉ። ይሖዋ አምላክ “እኔ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ነኝ፤ ስሜም ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፣ ምስጋናዬንም ለጣዖት አልሰጥም” ሲል የተናገረውን ሙሉ በሙሉ አምነው ይቀበላሉ።—ኢሳይያስ 42:8

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 በአንዳንድ የመንግሥት አዳራሾች ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱ ሰዎችን የሚያሳዩ ሥዕሎች ይገኛሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ሥዕሎች አዳራሹን ለማስዋብ የተሰቀሉ እንጂ እንደ ሃይማኖታዊ ምስሎች ተቆጥረው ለአምልኮ የሚያገለግሉ አይደሉም። የይሖዋ ምሥክሮች ለእነዚህ ሥዕሎች አይጸልዩም እንዲሁም በእነሱ ፊት አይሰግዱም።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“እኔ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ነኝ፤ ስሜም ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፣ ምስጋናዬንም ለጣዖት አልሰጥም።”—ኢሳይያስ 42:8