በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ቅጠሉ የማይጠወልግ’ ዛፍ

‘ቅጠሉ የማይጠወልግ’ ዛፍ

‘ቅጠሉ የማይጠወልግ’ ዛፍ

ጥቅጥቅ ባሉ ዛፎች የተሸፈነ ገጠራማ አካባቢ አይተህ ታውቃለህ? እንዲህ ያለው ቦታ ለዓይን ማራኪ ነው ቢባል እንደምትስማማ ምንም ጥርጥር የለውም። ቅጠሎቻቸው የተንዠረገጉ በርካታ ትላልቅ ዛፎች ብታይ በዚያ ቦታ ድርቅ ይኖራል ብለህ ትገምታለህ? በፍጹም! ከዚህ ይልቅ ዛፎቹ ሊለመልሙ የቻሉት በቂ ውኃ በመኖሩ ምክንያት እንደሚሆን መገመት አያዳግትህም።

መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈሳዊ ጤናማ የሆኑ ሰዎችን ግዙፍና ለምለም ከሆኑ ዛፎች ጋር ያመሳስላቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በመጀመሪያው መዝሙር የመጀመሪያ ሦስት ቁጥሮች ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ግሩም ሐሳብ ተመልከት፦

“በክፉዎች ምክር የማይሄድ፣ በኀጢአተኞች መንገድ የማይቆም፣ በፌዘኞችም ወንበር የማይቀመጥ፣ ሰው ብፁዕ ነው። ነገር ግን ደስ የሚሰኘው በእግዚአብሔር ሕግ ነው፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያሰላስለዋል። እርሱም በወራጅ ውሃ [“በውኃ ጅረቶች፣” NW] ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ፣ ቅጠሏም እንደማይጠወልግ ዛፍ ነው፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።”

በተመሳሳይም ኤርምያስ 17:7, 8 እንዲህ ይላል፦ “በእግዚአብሔር የሚታመን፣ መታመኛውም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው። በውሃ [“በውኃ ፈሳሾች፣” NW] ዳር እንደ ተተከለ፣ ሥሩንም ወደ ወንዝ እንደ ሰደደ ዛፍ ነው፣ ሙቀት ሲመጣ አይፈራም፤ ቅጠሉም ዘወትር እንደለመለመ ነው፤ በድርቅ ዘመን አይሠጋም፤ ፍሬ ማፍራቱንም አያቋርጥም።”

በሁለቱም ጥቅሶች ላይ ዛፎች፣ ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርግን፣ በአምላክ ሕግ ደስ የሚሰኝንና በእሱ ላይ ሙሉ እምነት ያለውን ሰው ለማመልከት ተሠርቶባቸዋል። ይህ ደግሞ ‘እንዲህ ያለው ሰው በመንፈሳዊ ሁኔታ ለምለም ከሆነ ዛፍ ጋር የሚመሳሰለው በምን መንገድ ነው?’ ብለን እንድንጠይቅ ያነሳሳናል። እስቲ እነዚህን ጥቅሶች ጠለቅ ብለን እንመርምር።

“በውኃ ጅረቶች ዳር” የተተከሉ ዛፎች

ከላይ የተጠቀሱት ዛፎች በአንድ ወንዝ ወይም ጅረት አጠገብ ሳይሆን “በውኃ ጅረቶች ዳር” ወይም “በውኃ ፈሳሾች ዳር” እንደተተከሉ ተገልጿል። በ⁠ኢሳይያስ 44:3, 4 ላይ ተመሳሳይ የሆነ ምሳሌያዊ አገላለጽ ይገኛል። እዚህ ጥቅስ ላይ ይሖዋ አምላክ፣ ከባቢሎን ግዞት ለተመለሱ ንስሐ የገቡ አይሁዳውያን ስለሚያደርገው እንክብካቤ ተናግሯል። ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት እንዲህ ብሏል፦ “በተጠማ ምድር ላይ ውሃ፤ በደረቅ መሬት ላይ ወንዞችን አፈሳለሁና፤ . . . እነርሱም በለመለመ መስክ ላይ እንደ ሣር፣ በወንዝ ዳር እንደ አኻያ ዛፍ ይበቅላሉ።” እዚህ ላይ “ወንዞች” የአምላክን ጥበቃና መመሪያ የሚያገኙ ሰዎችን እንደ አኻያ ዛፎች እንደሚያለመልሟቸው ተገልጿል።

በዛሬው ጊዜም ግብርና በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ጥልቅ የሆነ ጉድጓድን፣ ወንዝን፣ ሐይቅን አሊያም ግድብን ከመሳሰሉ ትልልቅ የውኃ ምንጮች ጋር የተገናኙ የውኃ መውረጃ ቦዮችንና ጅረቶችን ማየት ትችላለህ። በአብዛኛው እነዚህ የውኃ መውረጃ ቦዮችና ጅረቶች፣ ሰብል ለሚበቅልባቸውና ለእርሻ ቦታዎች ተብሎ የሚዘጋጅ የመስኖ ልማት አንድ ክፍል ናቸው። አንዳንድ ጊዜ የውኃ መውረጃ ቦዮቹ የፍራፍሬ ዛፎች ወደተተከሉበት አካባቢ እንዲፈስሱ ይደረጋል። አልፎ አልፎ ደግሞ ጅረቶቹ በአንደኛው አቅጣጫ ለእርሻ ማሳዎች በተቃራኒው አቅጣጫ ደግሞ በረድፍ ለተተከሉ ዛፎች እንደ መስኖ ሆነው የሚያገለግሉ ከመሆኑም ሌላ የአንድን ሰው የእርሻ ቦታ ከሌላው ሰው ለመለየት እንደ ወሰን ሆነው ያገለግላሉ።

እንዲህ ባሉ ጅረቶች አጠገብ የተተከሉ ዛፎች ምን ያህል ጥሩ እድገት ያደርጋሉ? መዝሙር 1:3 ‘ፍሬውን በየወቅቱ ስለሚሰጥ’ ዛፍ ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጠቀሱ አገሮች በለስና ሮማን እንዲሁም የፖም፣ የተምርና የወይራ ዛፎች ይበቅላሉ። የበለስ ዛፍ እስከ 9 ሜትር የሚደርስ ርዝማኔና ትልልቅ ቅርንጫፎች ሊኖሩት ቢችልም ፍሬ የሚያፈሩ አብዛኞቹ ሌሎች ዛፎች ረጃጅም አይደሉም። ሆኖም በደንብ ሊለመልሙና በወቅቱ የተትረፈረፈ ፍሬ ሊሰጡ ይችላሉ።

በጥንት ዘመን በሶርያና በፓለስቲና ምድር ትልልቅ የአኻያ ዛፎች በወንዞችና በጅረቶች ዳርቻ ላይ ይበቅሉ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የአኻያ ዛፎች በአብዛኛው የተጠቀሱት ከጅረቶች ወይም ‘ከወንዞች’ ጋር በተያያዘ ነው። (ዘሌዋውያን 23:40 የ1954 ትርጉም) እነዚህ ዛፎች ውኃ እንደ ልብ ባለበት ቦታ በብዛት ሊገኙ ይችላሉ። (ሕዝቅኤል 17:5) ለምለም የሆኑት እነዚህ ትልልቅ ዛፎች መዝሙራዊውም ሆነ ኤርምያስ ሊያስተላልፉት የፈለጉትን የሚከተለውን መልእክት በሚገባ ይገልጻሉ፦ የአምላክን ሕግ የመከተል ፍላጎት ያላቸውና በእሱ ሙሉ በሙሉ የሚታመኑ ሰዎች በመንፈሳዊ ጤናማ ሆነው የሚኖሩ ከመሆኑም ሌላ ‘የሚሠሩት ሁሉ ይከናወንላቸዋል።’ ደግሞስ የምንፈልገው የምንሠራው ሁሉ እንዲከናወንልን ማለትም ሕይወታችን ስኬታማ እንዲሆን አይደለም?

በይሖዋ ሕግ ደስ መሰኘት

በዛሬው ጊዜ ሰዎች በብዙ መንገዶች ስኬትን ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ። ዝናና ሀብት ሊያስገኙ ይችላሉ ብለው በሚያስቧቸው ነገሮች ይጠመዳሉ፤ ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ነገሮች የማይጨበጡ ስለሚሆኑባቸው ለሐዘንና ለብስጭት ይዳረጋሉ። ታዲያ በሕይወት ውስጥ እውነተኛ እርካታና ዘላቂ ደስታ ሊያስገኝ የሚችለው ምንድን ነው? ኢየሱስ በተራራው ስብከት ወቅት የተናገራቸው ቃላት ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣሉ። እንዲህ ብሏል፦ “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ነውና።” (ማቴዎስ 5:3) በእርግጥም እውነተኛ ደስታ የሚገኘው በርካታ ቁሳዊ ነገሮችን በማካበት ሳይሆን መንፈሳዊ ፍላጎታችንን በማወቅና ይህን ፍላጎታችንን በማርካት ነው። ይህ ደግሞ በወቅቱ ፍሬ እንደሚሰጡ የለመለሙ ዛፎች በመንፈሳዊ ጤናማ እንድንሆን ያደርገናል። ታዲያ በመንፈሳዊ ሁኔታ እንደ ለመለመ ዛፍ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

በመጀመሪያ ደረጃ፣ መዝሙራዊው እንደተናገረው ልንርቃቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮች አሉ። ዳዊት ‘የክፉዎችን ምክር፣’ ‘የኃጢአተኞችን መንገድ’ እና ‘የፌዘኞችን ወንበር’ ጠቅሷል። ደስተኛ መሆን ከፈለግን በአምላክ ሕግ ከሚያፌዙ አልፎ ተርፎም ሕጉን ችላ ከሚሉ ሰዎች መራቅ ይኖርብናል።

በሁለተኛ ደረጃ፣ በይሖዋ ሕግ ደስ መሰኘት ይኖርብናል። አንድ ነገር ወይም አንድ ሥራ የሚያስደስተን ከሆነ ያን ነገር ለማድረግ እንደምንጓጓ የታወቀ ነው። በመሆኑም በአምላክ ሕግ ደስ መሰኘት ሲባል ለአምላክ ቃል ከፍተኛ አድናቆት ማሳየት እንዲሁም ቃሉን ይበልጥ ለመማርና ለመረዳት መጓጓት ማለት ነው።

በሦስተኛ ደረጃ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ‘በቀንና በሌሊት ድምፃችንን አውጥተን’ (NW) ማንበብ ይኖርብናል። ይህም ሲባል መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን ማንበብና ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል ማለት ነው። የአምላክን ቃል በተመለከተ “አቤቱ፤ ሕግህን ምንኛ ወደድሁ! ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ” በማለት የዘመረው መዝሙራዊ የነበረው ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል።—መዝሙር 119:97

አዎን፣ ስለ ይሖዋ አምላክ ትክክለኛ እውቀትና ማስተዋል ስናገኝ እንዲሁም በእሱም ሆነ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ሙሉ በሙሉ የመታመን ዝንባሌ እያዳበርን ስንሄድ በመንፈሳዊ ጤናማ እንደምንሆን ምንም ጥርጥር የለውም። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ መዝሙራዊው “የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል” በማለት እንደገለጸው ደስተኛ ሰው እንሆናለን።