በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በማያንማር በደረሰው የተፈጥሮ አደጋ የተጎዱ ሰዎች እርዳታ አገኙ

በማያንማር በደረሰው የተፈጥሮ አደጋ የተጎዱ ሰዎች እርዳታ አገኙ

በማያንማር በደረሰው የተፈጥሮ አደጋ የተጎዱ ሰዎች እርዳታ አገኙ

ማያንማር፣ ግንቦት 2, 2008 ናርጊስ በተባለች አውሎ ነፋስ ክፉኛ የተመታች ሲሆን ይህ የተፈጥሮ አደጋ ወዲያውኑ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ርዕሰ ዜና ሆኖ ነበር። ኢራዋዲ የተባለው አካባቢ በኃይለኛ ጎርፍ ከተጥለቀለቀ በኋላ ወደ 140,000 የሚጠጉ ሰዎች እንደሞቱ ወይም የደረሱበት እንዳልታወቀ ተዘግቧል።

የሚገርመው ነገር፣ በዚያ አካባቢ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ቢኖሩም በሕይወታቸው ላይ የደረሰ ጉዳት የለም። ይህ ሊሆን የቻለበት ዋነኛው ምክንያት አውሎ ነፋሱ በተነሳበት ወቅት፣ በጥሩ ሁኔታ በተገነቡ የመሰብሰቢያ አዳራሾቻቸው በመጠለላቸው ነው። በአንድ አካባቢ ጎርፉ 5 ሜትር ያህል ከፍታ ስለነበረው 20 የይሖዋ ምሥክሮችና 80 የሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች በመሰብሰቢያው አዳራሽ ጣሪያ ላይ ለዘጠኝ ሰዓታት መቀመጥ ግድ ሆኖባቸዋል። እነዚህ ሰዎች በሙሉ በሕይወት መትረፍ ችለዋል። የሚያሳዝነው ግን በዚያ መንደር የሚኖሩ 300 ሰዎች ሞተዋል። በበርካታ መንደሮች፣ ሳይፈርስ የቀረው የይሖዋ ምሥክሮች የመሰብሰቢያ አዳራሽ ብቻ ነው።

አደጋው ከደረሰ ከሁለት ቀናት በኋላ በያንጎን የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ፣ አደጋው ከደረሰባቸው መንደሮች አንዷ በሆነችው በቦቲንጎን ወደሚገኘው ጉባኤ እርዳታ የሚሰጥ አንድ ቡድን ላከ። የዚህ ቡድን አባላት በቦቲንጎን ለሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ከፍተኛ መጠን ያለው ሩዝ፣ ፓስታ፣ ውኃና ሻማ ለማድረስ በአደጋው ክፉኛ የተጎዱ አካባቢዎችን ማቋረጥ፣ ከዘራፊዎች ራሳቸውን መጠበቅና በሞቱ ሰዎች አስከሬን መካከል አልፈው መሄድ ጠይቆባቸዋል። ወደዚህ አካባቢ የደረሰው የመጀመሪያው የእርዳታ ቡድን ይህ ነበር። የቡድኑ አባላት፣ በአካባቢው ለነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ይዘውት የመጡትን ምግብና የእርዳታ ቁሳቁስ የሰጧቸው ከመሆኑም ሌላ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ የሚያበረታቱ ንግግሮች አቀረቡ፤ በተጨማሪም በአደጋው የተነሳ ንብረታቸውን ሙሉ በሙሉ አጥተው ስለነበር መጽሐፍ ቅዱሶችንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ሰጧቸው።

በአደጋው ሳቢያ ንብረቶቻቸውን ያጡት የይሖዋ ምሥክሮች የነበራቸው አመለካከት በእጅጉ የሚያስደንቅ ነው። በዚህ አደጋ በጣም በተጎዳው ኢራዋዲ በተባለው አካባቢ ባለ ጉባኤ ውስጥ የሚገኝ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “የነበረን ነገር ሁሉ ጠፍቷል። ቤቶቻችን በሙሉ እንዳልነበሩ ሆነዋል። ሰብሎቻችን በሙሉ ወድመዋል። በጎርፉ ምክንያት የምንጠጣው ውኃ ሁሉ ተበክሏል። ይሁን እንጂ ወንድሞችና እህቶች የሌሎችን ያህል አልተጨነቁም። በይሖዋና በድርጅቱ ይተማመናሉ። የሚሰጠንን መመሪያ ሁሉ እንታዘዛለን፤ በመንደሩ እንድንቆይ ከታዘዝን እዚሁ እንቆያለን ወደ ሌላ ቦታ እንድንሄድ ከተነገረንም ከመሄድ ወደኋላ አንልም።”

ንብረቶቻቸውን በሙሉ ያጡ 30 የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ደግሞ የእርዳታ ቡድኖቹ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ወዳዘጋጁበት ቦታ ለመድረስ አሥር ሰዓት የሚወስድ ጉዞ ሲያደርጉ መንፈሳዊ መዝሙሮችን በደስታ ይዘምሩ ነበር። ይጓዙበት ወደነበረው ቦታ ከመድረሳቸው በፊት በአቅራቢያቸው በሚገኝ ከተማ የይሖዋ ምሥክሮች የወረዳ ስብሰባ እያደረጉ እንዳለ ሰሙ። በዚህ ጊዜ መንፈሳዊ ምግብ ለመመገብና ከክርስቲያን ወንድሞቻቸው ጋር ለመገናኘት ሲሉ በመጀመሪያ ወደ ስብሰባው ቦታ ለመሄድ ወሰኑ።

በአውሎ ነፋሱ በተመቱት አካባቢዎች ካሉት የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶች መካከል 35ቱ የወደሙ ሲሆን 125 የሚሆኑ ቤቶች ደግሞ በከፊል ተጎድተዋል፤ በተጨማሪም 8 የመሰብሰቢያ አዳራሾች አነስተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ደስ የሚለው ነገር የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ብዙ ጉዳት አልደረሰበትም።

በአውሎ ነፋሱ ምክንያት የወደቁት ትላልቅ ዛፎች መንገዶቹን ዘግተዋቸው ስለነበር መጀመሪያ ላይ ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው መግባትም ሆነ ከዚያ መውጣት አስቸጋሪ ሆኖ ነበር። አውሎ ነፋሱ ካቆመ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ከ30 የሚበልጡ የቅርንጫፍ ቢሮው አባላት የወደቁትን ዛፎች ምንም ዓይነት ትልቅ መሣሪያ ሳይጠቀሙ ከመንገዱ ላይ ለማንሳት የበኩላቸውን እርዳታ አበርክተዋል። ይህን ሥራ እያከናወኑ ሳለ ሰዎች በግርምት ተውጠው ቆመው ይመለከቷቸው ነበር። የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ሴቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ቀዝቃዛ መጠጦችንና ፍራፍሬዎችን ይዘው በመምጣት እየሠሩ ለነበሩትና ለአካባቢው ሰዎች የሰጧቸው ሲሆን ሰዎቹ የሚያዩትን ነገር ማመን አቅቷቸው ነበር። አንድ ጋዜጠኛ ሁኔታውን ከተመለከተ በኋላ “እንዲህ ቅልጥፍና በተሞላበት መንገድ የሚሠሩት እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው?” ሲል ጠይቋል። እነማን እንደሆኑ ከተነገረው በኋላ “ሌሎች ሰዎችም ልክ እንደ ይሖዋ ምሥክሮች ከልብ የመነጨ የትብብር መንፈስ ቢኖራቸው እንዴት ጥሩ ነበር!” በማለት አስተያየት ሰጥቷል።

የይሖዋ ምሥክሮች ከአደጋው ጋር በተያያዘ የእርዳታ ሥራውን የሚያስተባብሩ ሁለት ኮሚቴዎችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወዲያውኑ አቋቋሙ። በመቶዎች የሚቆጠሩ ፈቃደኛ ሠራተኞች እርዳታ በሚሰጡ ቡድኖች ውስጥ ታቅፈው መሥራት ጀመሩ። በአደጋው ምክንያት ቤታቸው የፈረሰባቸው የይሖዋ ምሥክሮች በጥቂት ቀናት ውስጥ አዳዲስ ቤቶች ተሠሩላቸው። እርዳታ ለመስጠት ከተቋቋሙት ቡድኖች መካከል አንዱ ለአንዲት የይሖዋ ምሥክር አዲስ ቤት ለመገንባት በመጣበት ጊዜ ጎረቤቶቿ ዓይናቸውን ማመን አልቻሉም። ከጎረቤቶቿ መካከል አንዷ እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ይህች የይሖዋ ምሥክር ቤተ ክርስቲያኗ ቤቷን እየሠራላት ነው። ቡዲስት ከሆኑት ወዳጆቼ መካከል ግን እኔን ለመርዳት አንድም ሰው አልመጣም። ይህች ሴት ከዚህ በኋላ ከሰበከችልኝ የይሖዋ ምሥክር መሆን አለብኝ!”

የግንባታ ሠራተኞችና እርዳታ ለመስጠት የተቋቋመው ኮሚቴ በታንሊን ከተማ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበትን አንድ ቤት ለመሥራት ሄደው ነበር። በዚህ ጊዜ፣ የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑት የቤተሰቡ አባላት የሰጧቸው የሚከተለው መልስ ልባቸውን በጣም ነክቶታል፦ “ያን ያህል ከባድ ጉዳት አልደረሰብንም። ቤታችን ብዙም አልተጎዳም። እዚህ መኖር እንችላለን፤ ምንም ችግር የለም! አንዳንዶቹ የይሖዋ ምሥክሮች እኮ ቤታቸው ሙሉ በሙሉ ወድሟል፤ በቅድሚያ እነሱን ብትረዷቸው ይሻላል!”

በያንጎን ከተማ በሚገኝ አንድ አካባቢ የሚኖሩ የተወሰኑ ሰዎች በአቅራቢያቸው ባለ አንድ ቤተ ክርስቲያን ለመጠለል ሄደው ነበር። ይሁንና ቤተ ክርስቲያኑ ተቆልፎ ስለነበር ማንም ሰው መግባት አልቻለም። ሰዎቹ በጣም ስለተናደዱ የቤተ ክርስቲያኑን በር ለመስበር ሞክረው ነበር። ከዚህ በተቃራኒ የይሖዋ ምሥክሮች አደጋው በደረሰበት ወቅት በርካታ ሰዎች በመሰብሰቢያ አዳራሾቻቸው ውስጥ እንዲጠለሉ አድርገዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በዳላ ከተማ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ አንድ ባልና ሚስት፣ በጭንቀት ተውጠው ከአደጋው ለማምለጥ ወደ መሰብሰቢያ አዳራሹ የመጡ 20 ሰዎችን ረድተዋል። በነጋታው ጠዋት፣ እነዚህ ሰዎች የሚመለሱበት ቤት ያልነበራቸው ከመሆኑም ሌላ ተርበው ነበር። ባልየው ሩዝ የሚሸጥ ሰው ፈልጎ ካገኘ በኋላ ለሁሉም ሰው የሚበቃ ሩዝ ገዛ።

በያንጎን ከሚኖሩ የአንድ ቤተሰብ አባላት መካከል የተወሰኑት የይሖዋ ምሥክሮች ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ የተለያየ እምነት ተከታዮች ነበሩ። አደጋው ከደረሰ በኋላ ግን መላው ቤተሰብ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ ተገኘ። ይህን ያደረጉት ለምን ነበር? ከቤተሰቡ አባላት መካከል አንዷ እንዲህ በማለት ገልጻለች፦ “አደጋው ከተከሰተ በኋላ የቤተ ክርስቲያናችን አባላት መጥተው እንደሚጠይቁን ነግረውን ነበር፤ ሆኖም አንዳቸውም ዝር አላሉም። መጥተው የጠየቁን የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው። ሩዝና ውኃ የሰጣችሁን እናንተ ናችሁ። እንደ ሌሎቹ ሃይማኖቶች አይደላችሁም!” የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑት የቤተሰቡ አባላት በአንድ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ላይ በወጣው “ይሖዋ ለእርዳታ የምናሰማውን ጩኸት ይሰማል” በሚለው ርዕስ ላይ የተደረገው ውይይት ያስደሰታቸው ከመሆኑም በላይ በስብሰባው ላይ በተደጋጋሚ ሐሳብ ሰጥተዋል።

መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ታጠና የነበረች አንዲት ሴት አደጋው ከተከሰተ በኋላ በነበረው ሳምንት ወደ ጉባኤ ስብሰባ መጣች። ሰዎችን ለመርዳት የተደረጉትን እንቅስቃሴዎች የሚገልጽና ከአደጋው ከተረፉ ሰዎች ጋር የተያያዙ ተሞክሮዎችን የያዘ ከቅርንጫፍ ቢሮው የተላከ ደብዳቤ በስብሰባው ላይ ተነቦ ነበር። ይህ ደብዳቤ እየተነበበ ሳለ ሴትየዋ ማልቀስ ጀመረች። ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ መገለጹ በጣም ያስገረማት ከመሆኑም ሌላ አስደስቷታል። በኋላ ላይ አስፈላጊ የሆኑ አንዳንድ ቁሳቁሶች የተሰጣት ሲሆን ከቤቷ አጠገብ ድንኳን ተተከለላት። የይሖዋ ምሥክሮች በጥሩ ሁኔታ እየተንከባከቧት እንዳለ ሆኖ እንደተሰማት ተናግራለች።

ኢየሱስ “በመካከላችሁ ፍቅር ካለ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። (ዮሐንስ 13:35) ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብም እውነተኛ እምነት በመልካም ሥራ የተደገፈ እንደሆነ ጎላ አድርጎ ገልጿል። (ያዕቆብ 2:14-17) የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህን ሐሳቦች በቁም ነገር ይመለከቷቸዋል፤ በመሆኑም የተቸገሩ ሰዎችን በመርዳትና ለእነሱ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ እንዲህ ያለውን ፍቅር ለማሳየት ጥረት ያደርጋሉ።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

መጽሐፍ ቅዱስ፣ እውነተኛ እምነት በመልካም ሥራ የተደገፈ እንደሆነ ይናገራል