በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ሕፃናትን በሰማይ መላእክት እንዲሆኑ ይወስዳል?

አምላክ ሕፃናትን በሰማይ መላእክት እንዲሆኑ ይወስዳል?

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ

አምላክ ሕፃናትን በሰማይ መላእክት እንዲሆኑ ይወስዳል?

አንድ ሕፃን ሲሞት ወዳጅ ዘመዶች ሐዘን የደረሰበትን ቤተሰብ ለማጽናናት “አምላክ ልጁን የወሰደው በሰማይ ሌላ መልአክ ስላስፈለገው ነው” በማለት ይናገሩ ይሆናል። ታዲያ ይህ አባባል ምክንያታዊ ይመስልሃል?

አምላክ በሰማይ ተጨማሪ መላእክት ስላስፈለጉት ልጆች እንዲሞቱ ያደርጋል የሚለው አመለካከት እውነት ቢሆን ኖሮ አምላክ ስለ ሌሎች የማያስብ እንዲያውም ጨካኝ ነው ማለት ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ሐሳብ ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። (ኢዮብ 34:10) አንድ ርኅሩኅ የሆነ አባት የራሱን ቤተሰብ ቁጥር ለማሳደግ ሲል ብቻ አንድን ልጅ ከወላጆቹ ነጥቆ አይወስድም። ይሁንና የትኛውም ሰብዓዊ ወላጅ ዋነኛ ባሕርይው ፍቅር ከሆነው ከይሖዋ ይበልጥ ርኅራኄ ሊኖረው አይችልም። (1 ዮሐንስ 4:8) ይሖዋ ያለው ታላቅ ፍቅር ደግነት የጎደለው ድርጊት እንዳይፈጽም ያግደዋል።

እስቲ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘አምላክ በሰማይ ተጨማሪ መላእክት ያስፈልጉታል?’ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ሥራዎች ሁሉ መልካምና ፍጹም እንደሆኑ ይገልጻል። (ዘዳግም 32:4) አምላክ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ መላእክትን በቀጥታ በፈጠረበት ወቅት ሥራው ፍጹም ነበረ፤ ቁጥራቸውም በቂ ነው። (ዳንኤል 7:10) አምላክ ምን ያህል መላእክት እንደሚያስፈልጉት ሲወስን ስህተት ሠርቶ ይሆን? በፍጹም! ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በጭራሽ እንዲህ ያለ ስህተት ሊሠራ እንደማይችል የተረጋገጠ ነው። ይሖዋ መንፈሳዊ ፍጥረታት በመሆን በሰማያዊ መንግሥቱ ውስጥ እንዲገዙ ከሰው ልጆች መካከል አንዳንዶቹን መምረጡ እውነት ነው፤ ሆኖም አምላክ ለዚህ ዓላማ የሚጠቀመው በሕፃንነታቸው የሚሞቱ ልጆችን አይደለም።—ራእይ 5:9, 10

አምላክ ልጆችን በሰማይ መላእክት እንዲሆኑ ከምድር አይወስድም እንድንል የሚያደርገን ሌላው ምክንያት ደግሞ ይህ አመለካከት አምላክ ለሕፃናት ከነበረው የመጀመሪያ ዓላማው ጋር የማይስማማ በመሆኑ ነው። አምላክ በኤደን ገነት ውስጥ አዳምና ሔዋንን “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም” ብሏቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:28) ልጆች የአምላክ ስጦታ ከመሆናቸውም ሌላ አምላክ ምድርን ጻድቅ በሆኑ ሰዎች ለመሙላት ያወጣው የመጀመሪያ ዓላማ ዳር እንዲደርስ የግድ መኖር አለባቸው። አምላክ ልጆች ሕይወታቸው በአጭር እንዲቀጭና ወደ መንፈሳዊ ፍጥረትነት እንዲለወጡ ዓላማው አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ልጆች “የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው” በማለት በግልጽ ይናገራል። (መዝሙር 127:3) የፍቅር አምላክ የሆነው ይሖዋ ለወላጆች የሰጠውን ስጦታ መልሶ ይወስዳል? በጭራሽ አያደርገውም!

አንድ ልጅ ያለ ዕድሜው መሞቱ ከፍተኛ ሐዘን፣ የስሜት ጉዳትና ሥቃይ ያስከትላል። ታዲያ ሐዘን ለደረሰባቸው ወላጆች የሚሆን ምን የሚያጽናና ተስፋ አለ? መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከሞት በማስነሳት ገነት በምትሆነው በዚህች ምድር ላይ እንደሚያኖራቸው ተስፋ ይሰጣል። ልጆች ጤናማ አካል ይዘው ከሞት ሲነሱና ከሚወዷቸው ሰዎች ጋር በድጋሚ ሲገናኙ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። (ዮሐንስ 5:28, 29) አምላክ ልጆች አድገው ደስተኛ ሕይወት እንዲኖራቸውና ስለ እሱም ሆነ ለምድር ስላለው ዓላማ እንዲማሩ ፈቃዱ ነው። በመሆኑም በሞት ያንቀላፉ ልጆች በሰማይ ላይ መላእክት ሆነው እየኖሩ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለመኖር ትንሣኤ የሚያገኙበትን ጊዜ ይጠብቃሉ። በዚያን ጊዜ ልጆችም ሆኑ አዋቂዎች አፍቃሪ በሆነው ፈጣሪያችን ጥበቃ ሥር ሆነው ይሖዋ አምላክን ለዘላለም በደስታ ያመልኩታል።