በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንድን ሰው ለማግኘት ያደረግኩት ከፍተኛ ጥረት

አንድን ሰው ለማግኘት ያደረግኩት ከፍተኛ ጥረት

ከአየርላንድ የተላከ ደብዳቤ

አንድን ሰው ለማግኘት ያደረግኩት ከፍተኛ ጥረት

ያለማቋረጥ ይጥል የነበረው ቀለል ያለ ካፊያ የመኪናዬን መስተዋት ስለሸፈነው በዙሪያዬ ያለውን ገጠራማ አካባቢ በደንብ ማየት አልቻልኩም። አሥራ ስድስት ኪሎ ሜትር ያህል ከተጓዝኩ በኋላ አንድ ኮረብታማ ቦታ ላይ ደረስኩ። እዚህ ቦታ ላይ ሆኖ በምዕራብ አየርላንድ በባሕር ዳርቻ አካባቢ የምትገኘውን ዌስትፖርት የተባለች አነስተኛ ከተማ ማየት ይቻላል። ፀሐይ ስትወጣ ጭጋጉ ስለተገፈፈ በባሕር ወሽመጡ ዙሪያ ያሉትን በርካታ ትናንሽ ደሴቶች ማየት ቻልኩ፤ እነዚህ ደሴቶች ከርቀት ሲታዩ በሰማያዊ ምንጣፍ ላይ ተበታትነው የሚገኙ ውብ ማዕድናት ይመስላሉ። በአብዛኞቹ ደሴቶች ላይ ሰው የማይኖር ቢሆንም የአካባቢው ገበሬዎች ከብቶቻቸውን በጀልባ ጭነው ወደ እነዚህ ደሴቶች በመውሰድ ሣር እንዲግጡ ያደርጋሉ።

በስተ ምዕራብ አቅጣጫ በባሕሩ ዳርቻ ረጅም የተራራ ሰንሰለት ይታያል። በተለያዩ ዕፅዋት የተሸፈኑት ተራሮች የቀትር ፀሐይ ሲያርፍባቸው የሚያብረቀርቅ መዳብ ይመስላሉ። የአካባቢው ነዋሪዎች ሪክ ብለው የሚጠሩት ክሮ ፓትሪክ የተባለው ሾጠጥ ያለ ተራራ ከሌሎቹ ጎላ ብሎ ይታያል። በተጨናነቁትና ጠባብ በሆኑት የዌስትፖርት ጎዳናዎች በመጓዝ ሪክ የተባለውን ተራራ አልፌ የይሖዋ ምሥክሮች እምብዛም ወደማይሄዱበት አንድ አካባቢ ደረስኩ።

እየተጓዝኩ ያለሁት አንድ ሰው ለማግኘት ነው፤ ይህ ሰው ዛሬ ወደ እሱ እንደምመጣ አያውቅም። ግለሰቡ ወደዚህ አካባቢ የመጣው በቅርቡ እንደሆነና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የሚያደርገውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት መቀጠል እንደሚፈልግ የሚገልጽ አንድ ደብዳቤ ደርሶኝ ነበር። ‘የስንት ዓመት ሰው ይሆን? አግብቷል ወይስ አላገባም? የሚያስደስተው ነገር ምንድን ነው?’ እያልኩ ራሴን መጠየቅ ጀመርኩ። ከዚያም ቦርሳዬን አየት በማድረግ የያዝኳቸውን ጽሑፎች መለስ ብዬ ለማስታወስ ሞከርኩ፤ መጽሐፍ ቅዱስና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ይዣለሁ። ሰውየው ለመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ያለው ፍላጎት እያደገ እንዲሄድ ለማድረግ ምን ልለው እንደምችል አሰብኩ።

አሁን ሪክ የተባለውን ተራራ አልፌው ሄጃለሁ። ባዶ በሆኑት ሜዳዎች ላይ ድንጋይ በማነባበር ብቻ የተሠሩ እስከ ባሕሩ ዳርቻ የሚደርሱ አስገራሚ አጥሮች ይታያሉ፤ ከእነዚህ አጥሮች መካከል አብዛኞቹ በ19ኛው መቶ ዘመን በተከሰተው ታላቅ ረሃብ ወቅት የተሠሩ ናቸው። ሲገል የተባለ አንድ የወፍ ዝርያ ብቻውን አየር ላይ ይንሳፈፋል። የተጣመሙና እንዳረጀ ሰው የጎበጡ ዛፎች ጀርባቸውን ለነፋስ ሰጥተውና እርስ በርስ ተደጋግፈው ቆመው በርቀት ይታያሉ።

በዚህ ገጠራማ አካባቢ የቤት ቁጥርም ሆነ የጎዳና ስም የሚባል ነገር የለም። የተሰጠኝ አድራሻ የቤቱን ስምና ቀበሌውን ይገልጻል። ይሁን እንጂ በመጀመሪያ፣ የእያንዳንዱን ሰው መኖሪያ ቤት የሚያውቀውን የፖስታ ቤት ሠራተኛ ባገኝ የተሻለ እንደሚሆን አሰብኩ። ከግማሽ ሰዓት በኋላ ፖስታ ቤቱን አገኘሁት፤ ፖስታ ቤቱ ተያይዘው በተሠሩ ቤቶች መካከል የሚገኝ ሲሆን ቀደም ሲል ለሌላ ዓላማ የሚያገለግል ቤት ነበር። በሩ ላይ “ዝግ ነው” የሚል ምልክት ተንጠልጥሏል። በዚህ ተስፋ ሳልቆርጥ በአካባቢው ወደሚገኝ አንድ ሱቅ ጎራ ብዬ ባለሱቁን ጠየቅኩት፤ እሱም ቀበሌው የሚገኝበትን አካባቢ ጠቆመኝ።

ስምንት ኪሎ ሜትር ያህል ከተጓዝኩ በኋላ ስፈልገው የነበረውን ምልክት አገኘሁ፤ ወደ ቀኝ ከታጠፍኩ በኋላ በስተ ግራ በኩል ያለውን ጠባብ መንገድ ተከትዬ ሄድኩ። ከዚያም በአቅራቢያው ያለውን አንድ ቤት አንኳኳሁ። አንዲት አረጋዊት ሴት በሩን ከፍተው ያነጋገሩኝ ሲሆን ዕድሜያቸውን ሙሉ የኖሩት በዚህ አካባቢ እንደሆነ በኩራት መንፈስ ነገሩኝ፤ ሆኖም የምፈልገውን ሰው እንደማያውቁት በአዘኔታ ገለጹልኝ። ወደ ቤት እንድገባ ከጋበዙኝ በኋላ ስልክ ደውለው እንደሚያጠያይቁልኝ ነገሩኝ።

ሴትየዋ በስልክ እያወሩ በየመሃሉ አየት ያደርጉኝ ነበር፤ ‘ይህ ሰው ማን ይሆን? ምን ፈልጎ ነው የመጣው?’ የሚል ጥያቄ ሳይፈጠርባቸው አልቀረም። የድንግል ማርያም ምስል በትንሹ ተቀርጾ በሩ አጠገብ የተቀመጠ ሲሆን ግድግዳው ላይ ደግሞ የክርስቶስ ሥዕል በትልቁ ተሰቅሏል። ወጥ ቤት ውስጥ በሚገኘው ጠረጴዛ ላይ ለጸሎት የሚያገለግል መቁጠሪያ ተቀምጧል። ሴትየዋ አላስፈላጊ ጥርጣሬ እንዳያድርባቸው ለማድረግ ስል “ከጓደኞቹ የተላከ አስፈላጊ መልእክት ይዤለት መጥቻለሁ” በማለት ነገርኳቸው።

በዚህ መሃል የሴትየዋ ባለቤት የአካባቢውን ታሪክ ያጫውቱኝ ጀመር። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሴትየዋ መጀመሪያ ከደወሉለት ሰው ምንም ፍንጭ ባለማግኘታቸው ሌሎች ሰዎች ጋር እስኪደውሉ ድረስ እንድታገሳቸው ጠየቁኝ። ሰውየውንም ሆነ ቤቱን የሚያውቅ ሰው ሊገኝ አልቻለም። ሰዓቴን ስመለከት እየመሸ መሆኑን ተረዳሁ። ሰውየውን ለማግኘት ሌላ ጊዜ ተመልሼ ብመጣ ሳይሻል አይቀርም ብዬ አሰብኩ። ላደረጉልኝ ትብብር ሁለቱንም ካመሰገንኩ በኋላ መኪናዬን አስነስቼ ወደ ቤት ለመመለስ ረጅሙን ጉዞ ተያያዝኩት።

በቀጣዩ ሳምንት ተመልሼ ሄድኩ። በዚህ ጊዜ የፖስታ ቤቱን ሠራተኛ አገኘሁትና ቦታውን በግልጽ ጠቆመኝ። ከአሥራ አምስት ደቂቃ በኋላ ሰውየው ወደ ጠቆመኝ መስቀለኛ መንገድ ደረስኩ። ከዚያም በስተ ግራ በኩል ታጥፌ የተነገረኝን ሁለተኛ ምልክት ማለትም በድንጋይ የተሠራውን የድሮ ድልድይ ለማግኘት ጠባብ በሆነው መንገድ ላይ ተመላለስኩ። ሆኖም ላገኘው አልቻልኩም። በኋላ ላይ ግን የተነገረኝን የመጨረሻ ምልክት አገኘሁት። በዚያም በኮረብታው ጫፍ ላይ፣ ለረጅም ሰዓት ስፈልገው የነበረውንና ብዙ ያደከመኝን ቤት ተመለከትኩ።

ምሥራቹን እንዴት ብዬ ብነግረው የተሻለ እንደሚሆን ቆም ብዬ ለማሰብ ሞከርኩ። በሩን ሳንኳኳ አንድ አረጋዊ ሰው ከፈቱልኝ። “ተሳስተሃል፤ የምትፈልገው ቤት ይሄ ሳይሆን ያኛው ነው” ብለው በዛፎች የተከበበን አንድ ቤት አሳዩኝ። ሰውየውን እንደማገኘው ተስፋ በማድረግ ወዳሳዩኝ ቤት ሄድኩና በሩን አንኳኳሁ። በሩ እስኪከፈትልኝ ድረስ እየጠበቅኩ በጥቂት መቶ ሜትሮች ርቀት ላይ የሚገኘውን የአትላንቲክ ውቅያኖስ ተመለከትኩ። ኃይለኛ ነፋስ ይነፍስ ስለነበር ማዕበሉ በጣም ውብ ከሆነው የባሕር ዳርቻ ጋር ሲላተም አረፋ ይሠራል። በአካባቢውም ሆነ በቤቱ ውስጥ ማንም ሰው አልነበረም።

በድጋሚ ተመልሼ ብመጣም ቤት ውስጥ ሰው አልነበረም፤ ለሦስተኛ ጊዜ ስመጣ ግን አንድ ወጣት አገኘሁ። ወጣቱም እንዲህ አለኝ፦ “ቤቱ ይሄ ነው፤ አንተ የምትፈልገው ሰው እዚህ ተከራይቶ ይኖር የነበረ ቢሆንም አሁን ለቋል፤ ወዴት አካባቢ እንደሄደም አላውቅም።” ሰውየውን የፈለግኩት ለምን እንደነበር ከገለጽኩለት በኋላ ይህ ወጣት ከዚህ በፊት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተወያይቶ እንደማያውቅ ተገነዘብኩ። ቀደም ሲል ዝርፊያ ተፈጽሞበት የነበረ ሲሆን ‘አምላክ ይህም ሆነ ሌሎች ኢፍትሐዊ ድርጊቶች እንዲደርሱ የፈቀደው ለምንድን ነው?’ የሚለው ጥያቄ ያስጨንቀው ነበር። በመሆኑም በዚያው ወቅት የወጡ ይህን ርዕሰ ጉዳይ የሚያብራሩ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶችን በደስታ ተቀበለ።

ቅዱሳን መጻሕፍት ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ፈልገን ለማግኘት ትጋት የተሞላበት ጥረት እንድናደርግ ያበረታቱናል። የሚያሳዝነው ግን ስፈልገው የነበረውን ሰው አላገኘሁትም። ይሁንና ያደረግኩት ጥረት መና እንደቀረ አይሰማኝም። በአየርላንድ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለመማር ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። በዚያ ወጣት ልብ ውስጥ የተዘራውን የእውነት ዘር ይሖዋ ሊባርከውና አንድ ቀን ፍሬ ሊያፈራ ይችላል።