በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአፍሪካ የተገኙ ተሞክሮዎች

ከአፍሪካ የተገኙ ተሞክሮዎች

ከአፍሪካ የተገኙ ተሞክሮዎች

አገሮች 57

የሕዝብ ብዛት 848,582,269

አስፋፊዎች 1,122,493

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች 2,202,217

ሩዋንዳ አንዲት የዘጠኝ ዓመት ልጅ ከትምህርት ቤት ስትመለስ ብዙ ገንዘብ የያዘ አነስ ያለ ቦርሳ መንገድ ላይ ወድቆ አገኘች። በወቅቱ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ያጠኑ የነበሩት ቤተሰቦቿ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማሩትን ነገር በተግባር ለማዋል ወሰኑ። በመሆኑም የቦርሳውን ባለቤት ፈልገው ካገኙት በኋላ ገንዘቡን መለሱለት። የቦርሳው ባለቤት ልጅቷን እንዲህ ሲል ጠየቃት፦ “ለሐቀኝነትሽ ወሮታ እንዲሆን የተወሰነ ገንዘብ ብሰጥሽ ምን ታደርጊበታለሽ?”

ልጅቷም “መጽሐፍ ቅዱስ እገዛበታለሁ” ስትል መለሰች።

ሰውየውም በመገረም “የለበስሽው ልብስና ያደረግሽው ጫማ ያለቀ ስለሆነ ልብስ ወይም ጫማ ትገዢበታልሽ ብዬ አስቤ ነበር” አላት። ልጅቷ ግን ከልብስ ወይም ከጫማ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ እንደምትፈልግ በአጽንኦት ተናገረች። ሰውየው የልጅቷ ቤተሰቦች ገንዘቡን ያልወሰዱት ለምን እንደሆነ ማወቅ ፈልጎ ነበር። የልጅቷ ቤተሰቦች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እያጠኑ መሆኑን ሲገነዘብ ለልጅቷና ለራሱ ቤተሰብ ሁለት መጽሐፍ ቅዱስ ገዛ። በተጨማሪም የቤተሰቡ አባላት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ ዝግጅት አደረገ። አሁን ሁለቱም ቤተሰቦች ጥሩ መንፈሳዊ እድገት እያደረጉ ነው።

መካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ ከመጠን በላይ ዓይን አፋር የነበረችው ቲኦዶራ ይህን ችግሯን በይሖዋ እርዳታ ማሸነፍ ችላለች። ያደገችው በይሖዋ ምሥክር ቤተሰብ ውስጥ ቢሆንም በጣም ዓይን አፋር ከመሆኗ የተነሳ በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ የምትገኘው አልፎ አልፎ ነበር። ቲኦዶራ በስብሰባዎቹ ላይ መገኘት ስትጀምር ትቀመጥ የነበረው ብቻዋን ሲሆን ማንኛውንም ሰው አታነጋግርም ነበር። በተጨማሪም የመደምደሚያው መዝሙርና ጸሎት እንዳበቃ ከስብሰባው ወጥታ ትሄዳለች። ብዙም ሳይቆይ ቲኦዶራ በቋሚነት መሰብሰብ የጀመረች ቢሆንም ሰላምታ ሊሰጧት የመጡትን ሰዎች የምትጨብጣቸው ከስንት አንዴ ነበር። ከጊዜ በኋላ በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ መስጠት ብሎም ሰዎችን ቀርባ ሰላም ማለት ጀመረች። በስብከቱ ሥራ በመካፈል በሕይወቷ ውስጥ ትልቅ ለውጥ አደረገች። በአካባቢዋ የሚገኙት ልጆች ሲያፌዙባት በስብከቱ ሥራ መካፈሏን ለማቆም አስባ ነበር፤ ይሁን እንጂ ይሖዋ ኃይል እንዲሰጣት ጸለየች። ቲኦዶራ አሁን የተጠመቀች የይሖዋ ምሥክር ስትሆን ረዳት አቅኚ ሆና ታገለግላለች፤ እንዲሁም በስብሰባዎች ላይ ግሩም ሐሳቦችን ትሰጣለች። በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ሲያፌዝባት የነበረን አንድ ልጅ ጨምሮ አራት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ትመራለች።

ማዳጋስካር አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካችና ባለቤቱ ራቅ ባለ አካባቢ የሚገኝን ጉባኤ ለመጎብኘት እየተጓዙ ሳለ መጥረቢያና ጦር የያዙ የከብት ዘራፊዎች አጋጠሟቸው። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ባለቤት በልቧ ከጸለየች በኋላ ሰላም በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ የሚገኝ ሕይወት የተባለውን ትራክት አሳየቻቸው። ከዚያም እንዲህ አለቻቸው፦ “በዛሬው ጊዜ የምንኖረው በፍርሃት ነው። ይሁንና አምላክ በቅርቡ ክፉዎችን በማጥፋት ሰላም የሰፈነበት አዲስ ዓለም ያቋቁማል።” ከዘራፊዎቹ መካከል አንዱ በጥሞና ሲያዳምጣት ከቆየ በኋላ ትራክቱን ተቀበላት።

ከአንድ ዓመት በኋላ በተካሄደ ትልቅ ስብሰባ ላይ አንድ ሰው ወደ ወረዳ የበላይ ተመልካቹ ሚስት ቀርቦ ታስታውሰው እንደሆነ ጠየቃት። ወደ ገጠር ስትጓዝ መንገድ ላይ ካገኘቻቸው ዘራፊዎች መካከል እንደነበርና ትራክቱን የተቀበላት እሱ እንደሆነ ነገራት። ከዚያም እንዲህ አላት፦ “እናንተን ስናገኛችሁ ከዘረፋ እየተመለስን ነበር። የተናገርሽው ነገር ቆም ብዬ እንዳስብ አደረገኝ። ‘ፖሊሶችንም ሆነ ወታደሮችን ማምለጥ ስለምንችል እነሱን አንፈራቸውም። ይሁን እንጂ አምላክ ክፉዎችን የሚያጠፋ ከሆነ ከእሱ ማን ሊያመልጥ ይችላል?’ በማለት ራሴን ጠየቅኩ። በመሆኑም ይበልጥ ለማወቅ ወሰንኩ። ወደ ቤት ስመለስ ከአንድ ልዩ አቅኚ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ወደሚያጠና ጎረቤቴ ጋ ሄድኩ። እኔም ከልዩ አቅኚው ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የተስማማሁ ሲሆን አሁን በዚህ ስብሰባ ላይ እጠመቃለሁ።”

ሞዛምቢክ በ1992 ማዳሌና ገና በ30ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ እያለች በደረሰባት የመኪና አደጋ ምክንያት ከወገቧ በታች ሽባ ሆነች። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እምብዛም ከቤት ወጥታ አታውቅም። ከሦስት ዓመታት በኋላ ቤታቸው ደጃፍ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች አባቷን አነጋገሩት። የማዳሌና አባት በግቢያቸው ውስጥ ይሰበሰብ የነበረው የባሕል አምልኮ ቡድን መሪ ነበር። ማዳሌና ከአባቷ ጋር ይወያዩ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ስለ እሷ ደህንነት ሲጠይቁ ስትሰማ ወደ ቤት እንዲገቡ ጋበዘቻቸው። የይሖዋ ምሥክሮቹ ስለ እሷ በጥልቅ ማሰባቸው ልቧን ነካው! መጽሐፍ ቅዱስ እንድታጠና የቀረበላትን ግብዣ የተቀበለች ከመሆኑም ሌላ የምትማረው ነገር በጣም አስደሰታት። የይሖዋ ምሥክሮቹ የነበራትን ጉጉት ሲመለከቱ በስብሰባዎች ላይ እንድትገኝ ዝግጅት ማድረግን ጨምሮ በብዙ መንገዶች እርዳታ አደረጉላት። ማዳሌና የተደረገላት እገዛ በ2002 ራሷን ለይሖዋ መወሰኗን በጥምቀት ማሳየት እንድትችል ረድቷታል።

የማዳሌና ወላጆች፣ የይሖዋ ምሥክሮቹ ለልጃቸው ባደረጉላት እንክብካቤ ልባቸው በጥልቅ ተነካ። እናቷ የባለቤቷን ሃይማኖት በመተው በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ መገኘት ጀመረች። መጀመሪያ ላይ የማዳሌና አባት ሃይማኖቱን መቼም እንደማይተው ይናገር ነበር፤ ይሁንና ከጊዜ በኋላ እሱም በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ መገኘት ጀመረ። እሱ ቤት ይሰበሰቡ የነበሩት የባሕል አምልኮ ተከታዮች ይህ ሰው መሪያቸው በመሆኑ ወደ ስብሰባ መሄዱን እንዲያቆም ጫና አሳደሩበት። ይሁንና ለአምልኮ ይጠቀምባቸው የነበሩትን ዕቃዎቹን በማቃጠል የቀድሞ ሃይማኖቱን ለመተው ወሰነ። በ2007 እሱና ባለቤቱ ተጠመቁ። አሁን መላው ቤተሰብ ጥሩ መንፈሳዊ እድገት እያደረገ ነው።

ዚምባብዌ የዘጠኝ ዓመቷ ዴሲቤል አብረዋት ለሚማሩት ልጆችና ለመምህሮቿ ትመሰክራለች። አንድ ቀን ዴሲቤል መምህሯ በሐዘን እንደተዋጠች ተመለከተች፤ በመሆኑም ያሳዘናት ነገር ምን እንደሆነ ጠየቀቻት። መምህሯም የእህቷ ልጅ እንደሞተ ነገረቻት። ዴሲቤል መምህሯን የሚያጽናናት ነገር እንደምታመጣላት ገለጸችላት። በቀጣዩ ቀን የምትወዱት ሰው ሲሞት የተባለውን ብሮሹር ከወላጆቿ ተቀብላ ለመምህሯ ወሰደችላት። መምህሯ ከብሮሹሩ ላይ የተወሰኑ አንቀጾችን ካነበበች በኋላ በጣም ተደሰተች። ከጊዜ በኋላ ይህች ሴት፣ የዴሲቤል ወላጆች ልጃቸውን ጥሩ አድርገው ስላሠለጠኗትና ዴሲቤል በጭንቀቷ ጊዜ ስለሰጠቻት ማጽናኛ ምስጋናዋን በመግለጽ ደብዳቤ ጻፈችላቸው።

ጋና አቢጋኤል የምትኖረው ከአያቶቿ ጋር በደቡብ ጋና ሲሆን የፕሪስባይቴሪያን ሃይማኖት ተከታዮች የሆኑት አያቶቿ የይሖዋ ምሥክሮች ሐሰተኛ ነቢያት እንደሆኑ አስተምረዋት ነበር። በመሆኑም በሌላ የአገሪቱ ክፍል የሚኖሩት ወላጆቿ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት እንደጀመሩ ስትሰማ ጉዳዩ በጣም ስላሳሰባት ወላጆቿ ጥናታቸውን እንዲያቆሙ ለማሳመን ደብዳቤ ጻፈችላቸው። ሆኖም ደብዳቤው የፈለገችውን ውጤት ስላላስገኘ በአካል ልታነጋግራቸው በማሰብ ከ1,000 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዛ ወላጆቿ ወዳሉበት ቦታ ሄደች። አቢጋኤል፣ ሲኦል ክፉ ሰዎች የሚሠቃዩበት ቦታ እንዳልሆነ ከራሷ መጽሐፍ ቅዱስ ስትመለከት በጣም ደነገጠች። እሷ ራሷ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ ከወላጆቿ ጋር መገኘት ጀመረች፤ ከዚያም ያልተጠመቀች አስፋፊ ሆነች። አቢጋኤል በቅርቡ በተደረገ የወረዳ ስብሰባ ላይ ተጠምቃለች።

“ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ!” የሚል ርዕስ ያለው የ2009 አውራጃ ስብሰባ ፕሮግራም

መስከረም 22-24, 2002/ጥቅምት 2-4, 2009

በአዲስ አበባ የስብሰባ አዳራሽ፣ አማርኛ

መስከረም 29ጥቅምት 1, 2002/ጥቅምት 9-11, 2009

በአዲስ አበባ የስብሰባ አዳራሽ፣ አማርኛ እና የምልክት ቋንቋ

ድሬዳዋ፣ አማርኛ

ሶዶ፣ አማርኛ

ነቀምቴ፣ አማርኛ

ጥቅምት 6-8, 2002/ጥቅምት 16-18, 2009

በአዲስ አበባ የስብሰባ አዳራሽ፣ አማርኛ

ጊምቢ፣ ኦሮምኛ

ደሴ፣ አማርኛ

ናዝሬት፣ አማርኛ

ይርጋለም፣ ሲዳምኛ

ጥቅምት 13-15, 2002/ጥቅምት 23-25, 2009

በአዲስ አበባ የስብሰባ አዳራሽ፣ አማርኛ

በነፋስ ስልክ የመንግሥት አዳራሽ፣ እንግሊዝኛ

አምቦ፣ ኦሮምኛ

ሻሸመኔ፣ አማርኛ

አለታወንዶ፣ አማርኛ

ጥቅምት 20-22, 2002/ጥቅምት 30ኅዳር 1, 2009

በአዲስ አበባ የስብሰባ አዳራሽ፣ አማርኛ

መቀሌ፣ ትግርኛ

ሶዶ፣ ወላይትኛ

ጅማ፣ አማርኛ

ባሕር ዳር፣ አማርኛ