በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምትመርጥበት ጊዜ አሁን ነው

የምትመርጥበት ጊዜ አሁን ነው

የምትመርጥበት ጊዜ አሁን ነው

“እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።”—ዘፍጥረት 1:27

በመጽሐፍ ቅዱስ የመክፈቻ ምዕራፎች ላይ የሚገኘው በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀው ይህ ሐሳብ፣ አምላክ ፍጹም የሆኑትን ባልና ሚስት ማለትም አዳምና ሔዋንን መፍጠሩን ይገልጻል፤ እነዚህ ፍጥረታት አምላክ “በጊዜው ውብ አድርጎ [ከሠራቸው]” እጅግ ድንቅ ነገሮች መካከል የሚመደቡ ናቸው። (መክብብ 3:11) ፈጣሪያቸው የሆነው ይሖዋ አምላክ ለእነዚህ ባልና ሚስት እንዲህ አላቸው፦ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም፤ የባሕርን ዓሦች፣ የሰማይን ወፎች፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ግዟቸው።”—ዘፍጥረት 1:28

አምላክ ከላይ ያለውን ሐሳብ በመናገር ለአዳምና ለሔዋን ዓላማውን አሳውቋቸዋል። ልጆችን መውለድ እንዲሁም ለራሳቸውም ሆነ ለልጆቻቸው መኖሪያ የሆነችውን ምድር ሙሉ በሙሉ ገነት እንድትሆን ማድረግ ነበረባቸው። ዕድሜያቸውም ሆነ የሚሞቱበት ጊዜ አስቀድሞ አልተወሰነም። ከዚህ ይልቅ አምላክ አስደናቂ የሆነ ተስፋ ሰጥቷቸው ነበር። ትክክለኛ ምርጫ ካደረጉና አምላክን መታዘዛቸውን ከቀጠሉ ሰላም በሰፈነበት ሁኔታ በደስታ ለዘላለም መኖር ይችሉ ነበር።

አዳምና ሔዋን የተሳሳተ ምርጫ አደረጉ፤ በመሆኑም የመላው የሰው ዘር ዕጣ እርጅናና ሞት ሆነ። የእምነት አባት የሆነው ኢዮብ “ከሴት የተወለደ ሰው፣ ዘመኑ አጭርና በመከራ የተሞላ ነው” ብሏል። (ኢዮብ 14:1) የሰው ልጆችን በሙሉ ለዚህ ችግር የዳረጋቸው ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጠናል፦ “በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።” (ሮም 5:12) “አንድ ሰው” የተባለው አዳም እንደሆነ ግልጽ ነው፤ አዳም፣ አምላክ የሰጠውን ቀላልና ግልጽ መመሪያ ሆን ብሎ ጥሷል። (ዘፍጥረት 2:17) አዳም የተሳሳተ ምርጫ በማድረጉ ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ አጥቷል። ለዘሮቹም እንዲህ ያለውን ውድ ውርስ ከማስተላለፍ ይልቅ ኃጢአትና ሞትን አወረሳቸው። በወቅቱ ሁሉም ነገር ተስፋ የሌለው ይመስል ነበር፤ ይሁንና ነገሩ እንደዚያ ይሆን?

የእድሳት ዘመን

አዳምና ሔዋን ካመፁ ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ አንድ መዝሙራዊ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ።” (መዝሙር 37:29) መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ በኤደን ገነት የገባውን ቃል በቅርቡ እንደሚፈጽም ማረጋገጫ ሲሰጥ እንደሚከተለው ብሏል፦ “እሱም እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።” አምላክ ራሱ “እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ” ብሏል።—ራእይ 21:4, 5

ታዲያ ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው ከተባለ፣ ‘አምላክ የሰጣቸው ድንቅ ተስፋዎች እውን የሚሆኑበት የእድሳት ዘመን የሚመጣው መቼ ነው?’ የሚል ጥያቄ መነሳቱ ተገቢ ይሆናል። የዚህ መጽሔት አዘጋጆች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች፣ የምንኖረው መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻዎቹ ቀኖች’ በማለት በሚጠራው ዘመን ውስጥ መሆኑንና አምላክ ‘ሁሉንም ነገር አዲስ ለማድረግ’ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ መቅረቡን ለሰዎች ለማሳወቅ ሲጥሩ ቆይተዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) መጽሐፍ ቅዱስን በመመርመር አምላክ አንተን ጨምሮ ለሰው ልጆች ሁሉ ስለሰጠው ግሩም ተስፋ እንድታጠና እናበረታታሃለን። “እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፤ ቀርቦም ሳለ ጥሩት” የሚለውን ግብዣ እንድትቀበልም እናበረታታሃለን። (ኢሳይያስ 55:6) የአሁኑም ሆነ የወደፊቱ ሕይወትህ የተመካው በዕድል ሳይሆን በምታደርጋቸው ምርጫዎች ላይ ነው!

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ”