በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የቆሮንቶስ ከተማ​—“የሁለት ወደቦች ባለቤት”

የቆሮንቶስ ከተማ​—“የሁለት ወደቦች ባለቤት”

የቆሮንቶስ ከተማ​—“የሁለት ወደቦች ባለቤት”

የግሪክን ካርታ በምታይበት ጊዜ ባሕረ ገብ የሆነው መሬትና በስተ ደቡብ በኩል የሚገኘው ትልቅ ደሴት የሚመስል ምድር አብዛኛውን የአገሪቱን የቆዳ ሽፋን መያዛቸውን ማስተዋል ትችላለህ። ሁለቱን የሚያገናኝ ሾጠጥ ብሎ የሚታይ መሬት አለ። የቆሮንቶስ ወሽመጥ ተብሎ የሚጠራው ይህ ምድር ጠባብ በሆነው ቦታ ላይ ስፋቱ 6 ኪሎ ሜትር ገደማ ሲሆን በስተ ደቡብ ያለውን የፔሎፖኔዥያን ባሕረ ገብ መሬት በስተ ሰሜን ከሚገኘው የአገሪቱ ዋና ክፍል ጋር ያገናኛል።

የቆሮንቶስ ወሽመጥ ቁልፍ ቦታ የሆነበት ሌላም ምክንያት አለ። ይህ ቦታ የባሕር ድልድይ ተብሎ ይጠራል፤ ይህን ስያሜ ሊያገኝ የቻለው በስተ ምሥራቅ በኩል ወደ ኤጅያን ባሕርና ወደ ምሥራቃዊው ሜድትራኒያን የሚወስደው የሳሮኒክ ባሕረ ሰላጤ በመኖሩ፣ በስተ ምዕራብ በኩል ደግሞ ወደ አዮንያንና አድሪያቲክ ባሕር እንዲሁም ወደ ምዕራባዊው ሜድትራኒያን የሚያመራው የቆሮንቶስ ባሕረ ሰላጤ የሚገኝ በመሆኑ ነው። በዚህ ሁሉ መሃል የቆሮንቶስ ከተማ ትገኛለች። ቆሮንቶስ ሐዋርያው ጳውሎስ ባደረጋቸው ሚስዮናዊ ጉዞዎች ወቅት ቆይታ ካደረገባቸው ወሳኝ ቦታዎች አንዷ ስትሆን በጥንቱ ዓለም በብልጽግናዋ እንዲሁም በውስጧ በሚታየው የቅንጦት ኑሮና ልቅ የሆነ ሕይወት የታወቀች ነበረች።

ስትራቴጂያዊ ቦታ ላይ የምትገኝ ከተማ

የቆሮንቶስ ከተማ የምትገኘው ቁልፍ ቦታ በሆነው ሾጣጣ ምድር ምዕራባዊ ጫፍ አካባቢ ነው። ከተማዋ ሾጣጣ በሆነው ወሽመጥ ጫፍና ጫፍ ላይ በሚገኙ ሁለት ወደቦች ትጠቀም ነበር፤ እነሱም በምዕራብ በኩል የሚገኘው የሌካኦን ወደብና በምሥራቅ በኩል ያለው የክንክራኦስ ወደብ ናቸው። በዚህም ምክንያት ግሪካዊው የጂኦግራፊ ምሑር ስትሬቦ ቆሮንቶስን “የሁለት ወደቦች ባለቤት” ሲል ጠርቷታል። ከተማዋ ስትራቴጂያዊ ቦታ ላይ የምትገኝ በመሆኗ ከሰሜን እስከ ደቡብ ያለውን በየብስ የሚደረገውን የንግድ እንቅስቃሴም ሆነ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የሚካሄደውን የባሕር ላይ ንግድ መቆጣጠር ችላለች፤ በዚህም ምክንያት ዓለም አቀፋዊ መሸጋገሪያ ድልድይ ለመሆን በቅታለች።

ከጥንት ዘመን ጀምሮ ከምሥራቅ (ትንሿ እስያ፣ ሶርያ፣ ፊንቄና ግብፅ) እንዲሁም ከምዕራብ (ጣሊያንና ስፔን) የሚመጡ መርከቦች ጭነታቸውን በአንደኛው ወደብ ላይ ያራግፋሉ፤ ከዚያም ጭነቱ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቆ ወደሚገኘው ወደ ሌላኛው ወደብ በየብስ ላይ ይጓጓዛል። ጭነቱ እዚያ እንደደረሰ በሌሎች መርከቦች ላይ ተጭኖ ወደሚፈለግበት ቦታ ይወሰዳል። መርከቦቹ ትንንሽ ከሆኑ ደግሞ ዲዮልኮስ ተብሎ በሚጠራው ለዚሁ ዓላማ በተዘጋጀ መንገድ ላይ እየተገፉ ወሽመጡን ያቋርጣሉ።— ገጽ 27 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።

መርከበኞች የቆሮንቶስ ወሽመጥ በሚባለው ደረቅ ምድር ላይ ማቋረጥ የሚመርጡት ለምንድን ነው? ምክንያቱም በደቡባዊው የፔሎፖኒስ ምድር ዙሪያ የሚገኘው ባሕር እጅግ አደገኛና ማዕበል የሚያጠቃው በመሆኑ 320 ኪሎ ሜትር የሚፈጀውን ይህን የባሕር መስመር ተከትለው ቢሄዱ ሕይወታቸው አደጋ ላይ ይወድቅ ስለነበር ነው። በተለይ መርከበኞች ኬፕ መሊየ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ዞረው መሄድ ፈጽሞ አይፈልጉም፤ ይህ ቦታ “በኬፕ መሊየ ዞሬ እሄዳለሁ የምትል ከሆነ ወደ ቤት መመለስህ ዘበት ነው” ተብሎ ይነገርለት ነበር።

ክንክራኦስ—ሰጥሞ የተገኘው ወደብ

ከቆሮንቶስ በስተ ምሥራቅ 11 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የክንክራኦስ ወደብ ከእስያ አቅጣጫ ለሚመጡ መርከቦች የመጨረሻው ማረፊያ ነበር። በአራተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ መገባደጃ አካባቢ በተከሰተ አውዳሚ የመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ በዛሬው ጊዜ የወደቡ ግማሽ ክፍል ውኃ ውስጥ ሰጥሞ ይገኛል። ስትሬቦ፣ ክንክራኦስ ከፍተኛ እንቅስቃሴ የሚካሄድበትና የበለጸገ ወደብ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን ሮማዊው ፈላስፋ ሉክየስ አፑሊየስ ደግሞ “ከብዙ የተለያዩ አገሮች የሚመጡ መርከቦች የማይጠፉበት ታላቅና ኃያል ወደብ” ሲል ጠርቶታል።

በሮማውያን ዘመን ይህ ወደብ ወደ ባሕሩ ገባ ያሉ ሁለት ማራገፊያዎች የነበሩት ሲሆን በመካከላቸው ያለው ክፍተት ከ150 እስከ 200 ሜትር ስፋት ያለው መግቢያ እንዲፈጠር አድርጓል፤ ከዚህም የተነሳ ወደቡ የፈረስ ጫማ ዓይነት ቅርጽ ነበረው። ወደቡ እስከ 40 ሜትር ርዝመት ያላቸውን መርከቦች የማስተናገድ አቅም ነበረው። በወደቡ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ በሚገኝ አካባቢ ላይ በተደረገ የመሬት ቁፋሮ አይሲስ የተባለች ሴት አምላክ ማደሪያ እንደሆነ የሚታሰብ የአንድ ቤተ መቅደስ የተወሰነ ክፍል ተገኝቷል። በተቃራኒ አቅጣጫ ባለው የወደቡ ክፍል ላይ ደግሞ በርካታ ሕንፃዎች የተገኙ ሲሆን እነዚህም የአፍሮዳይት ቤተ መቅደስ እንደሆኑ ይገመታል። እነዚህ ሁለት እንስት አማልክት የመርከበኞች ጠባቂዎች እንደሆኑ ተደርገው ይታዩ ነበር።

ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ድንኳን በመስፋት ሥራ ሊሰማራ የቻለው በወደቡ አካባቢ ይካሄድ በነበረው የንግድ መርከቦች እንቅስቃሴ የተነሳ ሊሆን ይችላል። (የሐዋርያት ሥራ 18:1-3) ኢን ዘ ስቴፕስ ኦቭ ሴይንት ፖል የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ድንኳን በመስፋትም ሆነ መርከብ በመሥራት ይተዳደሩ የነበሩ በቆሮንቶስ የሚኖሩ ሰዎች ክረምት ሊገባ ሲል መጨረስ ከሚችሉት በላይ ብዙ ሥራ ያገኙ ነበር። የባሕር ላይ ጉዞ በሚቋረጥበት እንዲሁም ብዙ መርከቦች ክረምቱን ለማሳለፍና ጥገና እንዲደረግላቸው በሁለቱ ወደቦች ላይ በሚቆሙበት ወቅት በሌካኦንና በክንክራኦስ የሚገኙ የመርከብ መለዋወጫ ነጋዴዎች የመርከብ ሸራ መስፋት የሚችል ማንኛውንም ሰው ቀጥረው ያሠሩ ነበር።”

ጳውሎስ በቆሮንቶስ ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በላይ ከቆየ በኋላ በ52 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ከክንክራኦስ ወደ ኤፌሶን በመርከብ ተጓዘ። (የሐዋርያት ሥራ 18:18, 19) በቀጣዮቹ አራት ዓመታት ውስጥ በክንክራኦስ የክርስቲያን ጉባኤ ተቋቁሟል። ጳውሎስ በሮም ያሉ ክርስቲያኖችን “በክንክራኦስ ጉባኤ” የነበረችውን ፌበን የተባለችን አንዲት ክርስቲያን እንዲረዱ መጠየቁን መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል።—ሮም 16:1, 2

በዛሬው ጊዜ የክንክራኦስን ከተማ ለመጎብኘት የሚመጡ ሰዎች ጥርት ባለው ውኃ ውስጥ በሚዋኙበት ጊዜ የሰጠመውን ወደብ ፍርስራሽ ከሥራቸው ያያሉ። ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ይህ ቦታ ክርስቲያኖች ይሰብኩበትና ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ይካሄድበት እንደነበር አብዛኞቹ ጎብኚዎች አያውቁም። በቆሮንቶስ ወሽመጥ በስተ ምዕራብ በሚገኘው በሌካኦን ወደብ የነበረው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው።

ሌካኦን—ወደ ምዕራብ አቅጣጫ የሚያስወጣ የባሕር በር

በቆሮንቶስ ከሚገኘው የገበያ ቦታ አንስቶ በስተ ምዕራብ ወዳለው ወደ ሌካኦን ወደብ የሚወስድ 2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የሌካኦን ጎዳና ተብሎ የሚጠራ ድንጋይ የተነጠፈበት ጎዳና አለ። መሐንዲሶች ወደቡን ለመገንባት ወደ ባሕሩ ጫፍ አካባቢ የሚገኘውን የተወሰነ ቦታ ቆፍረው ካጎደጎዱት በኋላ ከዚያ የወጣውን አፈር መልሕቃቸውን የጣሉ መርከቦችን ከባሕሩ ከሚመጣው ኃይለኛ ነፋስ ለመከለል በባሕሩ ዳር ላይ ቆለሉት። በአንድ ወቅት ይህ ወደብ በሜድትራኒያን አካባቢ ከነበሩ ግዙፍ ወደቦች መካከል አንዱ ነበር። አርኪኦሎጂስቶች፣ ፖሳይደን ችቦ ይዞ በሚያሳይ ሐውልት መልክ የተሠራ የወደብ መብራት ቤት በቁፋሮ አግኝተዋል።

በድርብ ቅጥሮች ይከለል በነበረው በሌካኦን ጎዳና ግራና ቀኝ የእግረኛ መንገዶች፣ የመንግሥት ሕንፃዎች፣ ቤተ መቅደሶችና በረንዳ ላይ ያሉ ሱቆች ይገኙ ነበር። በዚህ አካባቢ ጳውሎስ ከገበያተኞች፣ ጊዜያቸውን በወሬ ከሚያሳልፉ ሰዎች፣ ከባለ ሱቆች፣ ከባሪያዎች፣ ከነጋዴዎችና ከሌሎች ሰዎችም ጋር የመገናኘት አጋጣሚ የነበረው ሲሆን ይህም የስብከት ሥራውን ለማከናወን ምቹ ሁኔታ ፈጥሮለታል።

ሌካኦን ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚደረግባት ወደብ ብቻ ሳትሆን የጦር መርከቦች የሚያርፉባት ቁልፍ ቦታም ነበረች። አንዳንዶች በጥንት ዘመን ከፍተኛ ብቃት ከነበራቸው የጦር መርከቦች አንዱ የሆነውና በሁለቱም ወገን ባለ ሦስት ረድፍ መቅዘፊያዎች ያሉት መርከብ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሠራው በሌካኦን በሚገኙ የመርከብ ግንባታ በሚካሄድባቸው ቦታዎች እንደሆነና ግንባታው የተከናወነውም በ700 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ የቆሮንቶስ ተወላጅ በሆነው በአሚኖክሊስ አማካኝነት እንደሆነ ይናገራሉ። አቴናውያን በ480 ከክርስቶስ ልደት በፊት ሳላሚስ ላይ ከፋርሳውያን የባሕር ኃይል ጋር ውጊያ በገጠሙበት ጊዜ ወሳኝ ድል እንዲቀዳጁ ያደረጋቸው ባለ ሦስት ረድፍ መቅዘፊያዎች ባሉት መርከብ መጠቀማቸው ነበር።

በአንድ ወቅት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ይካሄድበት የነበረው ይህ ወደብ በአሁኑ ጊዜ “ጥቁር መልክ ያለውና በረጃጅም ሣር የተሸፈነ የባሕር ዳርቻ ሆኗል።” ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት በሜድትራኒያን ከነበሩት ግዙፍ ወደቦች አንዱ በዚህ ቦታ ይገኝ እንደነበር የሚጠቁም ምንም ነገር የለም።

ለክርስቲያኖች ፈታኝ ቦታ የነበረችው ቆሮንቶስ

የቆሮንቶስ ወደቦች የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድባቸው ቦታዎች ከመሆናቸውም በተጨማሪ የከተማዋ ሕዝብ ከፍተኛ ተጽዕኖ ለሚያሳድሩ የተለያዩ ልማዶች እንዲጋለጥ መንገድ ከፍተው ነበር። እነዚህ ወደቦች ከተማይቱ የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችን ማስገባት የምትችልበት መንገድ ሆነው ያገለግሉ ስለነበር ለብልጽግናዋ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ቆሮንቶስ ለወደብ አገልግሎት ከሚሰበሰበው ከፍተኛ ክፍያም ሆነ ዕቃዎችንና መርከቦችን ዲዮልኮስ ተብሎ በሚጠራው መንገድ ላይ በማጓጓዝ ከምታገኘው ገቢ ብዙ ገንዘብ ታጋብስ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ከተማዋ የየብሱን የንግድ መስመር ከሚጠቀሙ ሰዎች ቀረጥ ትሰበስብ ነበር። በሰባተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት መገባደጃ ላይ መንግሥት በከተማዋ ውስጥ ካሉት ገበያዎችና በወደቦቹ ከሚጠቀሙ ሰዎች ቀረጥ በመሰብሰብ ከፍተኛ ገቢ ያገኝ ስለነበር የከተማዋ ነዋሪዎች ከቀረጥ ክፍያ ነፃ መሆን ችለዋል።

ቆሮንቶስ በዚያ ከሚቆዩ ነጋዴዎች ተጨማሪ ገቢ ታገኝ ነበር። አብዛኞቹ ነጋዴዎች የቅንጦት ኑሮ ይወዱና መረን የለቀቀ ፈንጠዝያ በሚታይባቸው ዝግጅቶች ላይ ይካፈሉ ነበር። መርከበኞችም ወደ ቆሮንቶስ በብዛት ይመጡ ስለነበረ ለከተማዋ ብልጽግና የራሳቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል። ስትሬቦ እንደገለጸው ከሆነ መርከበኞቹ ብዙ ገንዘብ ያጠፉ ነበር። የከተማዋ ነዋሪዎች መርከብ መጠገንን ጨምሮ በርካታ አገልግሎቶች ይሰጡ ነበር።

በጳውሎስ ዘመን የከተማዋ ነዋሪዎች ቁጥር 400,000 ገደማ እንደነበረ ይገመታል፤ በመሆኑም በሕዝብ ብዛት የሚበልጧት ሮም፣ እስክንድርያና የሶሪያዋ አንጾኪያ ብቻ ነበሩ። ግሪካውያን፣ ሮማውያን፣ ሶርያውያን፣ ግብፃውያንና አይሁዶች በቆሮንቶስ ውስጥ ይኖሩ ነበር። በወደቦቹ በኩል መንገደኞች፣ ስፖርታዊ ጨዋታዎችን ለማየት የሚመጡ ጎብኚዎች፣ አርቲስቶች፣ ፈላስፋዎች፣ ነጋዴዎችና ሌሎችም ያለማቋረጥ ወደ ከተማዋ ይመጡ ነበር። እነዚህ እንግዶች በዚያ ለሚገኙት ቤተ መቅደሶች ስጦታ ያመጡ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ለአማልክቱ መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር። ይህ ሁሉ ቆሮንቶስ የበለጸገችና ሞቅ ያለች ከተማ እንድትሆን አስችሏታል፤ ይሁንና ይህ ሁኔታ የራሱ መዘዝ ነበረው።

ኢን ዘ ስቴፕስ ኦቭ ሴይንት ፖል የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “እንዲህ ባሉ ሁለት ወደቦች መካከል የምትገኘው ቆሮንቶስ፣ በወደቦቿ ላይ መርከባቸውን የሚያቆሙ የባዕድ አገር ሕዝቦች የሚከተሏቸው ከሥነ ምግባር ውጪ የሆኑ የተለያዩ ልማዶች በሰፊው ተቀባይነት ያገኙባት ከተማ ለመሆን በቅታ ነበር።” ከምሥራቅም ሆነ ከምዕራብ የሚመጡ ሰዎች አልባሌ ልማዶቻቸውንና መጥፎ ድርጊቶቻቸውን ይዘው ወደ ከተማዋ ይገባሉ። በዚህም ምክንያት ቆሮንቶስ በሥነ ምግባር ያዘቀጠ ሕይወትና ከፍተኛ የቅንጦት ኑሮ የሚታይባት እንዲሁም በጥንቷ ግሪክ ከነበሩት ከተሞች ሁሉ እጅግ አስጸያፊ የብልግና ድርጊት የሚካሄድባት ከተማ ለመሆን በቅታለች። የቆሮንቶስ ሰዎችን የአኗኗር መንገድ መከተልና ቆሮንቶሳዊ መሆን ልቅና ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት ከመኖር ተለይቶ አይታይም ነበር።

እንዲህ ያለው ፍቅረ ንዋይና የሥነ ምግባር ብልግና የተንሰራፋበት ከተማ ለክርስቲያኖች መንፈሳዊ ደህንነት አስጊ ነበር። በቆሮንቶስ የሚኖሩ የኢየሱስ ተከታዮች በአምላክ ፊት ተቀባይነት ያለው አቋም ይዘው እንዲቀጥሉ ምክር ሊሰጣቸው ያስፈልግ ነበር። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፋቸው ደብዳቤዎች ላይ ስግብግብነትን፣ ቀማኛነትንና የሥነ ምግባር ርኩሰትን በጥብቅ ማውገዙ ተገቢ ነበር። በመንፈስ መሪነት የተጻፉትን እነዚህን ደብዳቤዎች ስታነብ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በካይ ተጽዕኖዎችን መቋቋም እንደነበረባቸው መገንዘብ ትችላለህ።—1 ቆሮንቶስ 5:9, 10፤ 6:9-11, 18፤ 2 ቆሮንቶስ 7:1

ሆኖም ቆሮንቶስ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለሚመጡ ሰዎች መናኸሪያ መሆኗ ራሱን የቻለ ጥቅሞች ነበሩት። ከተማዋ በየጊዜው የሚመጡ አዳዲስ ሐሳቦች ይስተናገዱባት ነበር። የከተማዋ ነዋሪዎች ጳውሎስ በሄደባቸው ሌሎች ከተሞች ውስጥ ከሚኖሩ ሕዝቦች በተለየ ሰፋ ያለ አስተሳሰብ ነበራቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ትንታኔ የሚሰጡ አንድ ሰው እንዲህ ብለዋል፦ “ከምሥራቅና ከምዕራብ የሚመጡ ሕዝቦች በሚገናኙባት በዚህች ጥንታዊ የወደብ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ይህ ዓለም ለሚያቀርባቸው የተለያዩ አዳዲስ ሐሳቦች፣ ፍልስፍናዎችና ሃይማኖቶች የተጋለጡ ነበሩ።” ከዚህም የተነሳ በከተማዋ ውስጥ የተለያዩ ሃይማኖቶች ሊኖሩ ችለዋል፤ ይህም ለጳውሎስ የስብከት ሥራ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረ ግልጽ ነው።

ክንክራኦስና ሌካኦን የተባሉት ሁለቱ የቆሮንቶስ ወደቦች ለከተማዋ ብልጽግናና ገናናነት አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በተጨማሪም እነዚሁ ወደቦች በቆሮንቶስ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ለተለያዩ ፈተናዎች እንዲጋለጡ አድርገዋል። ዛሬ በምንኖርበት ዓለም ውስጥ ያለው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። እንደ ፍቅረ ንዋይና የሥነ ምግባር ብልግና ያሉ በካይ ተጽዕኖዎች አምላክን በሚፈሩ ሰዎች መንፈሳዊነት ላይ አደጋ ይጋርጣሉ። በመሆኑም እኛም ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በመንፈስ መሪነት የሰጣቸውን ምክሮች ልብ ማለታችን ተገቢ ነው።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

 ዲዮልኮስ—በደረቅ ምድር ላይ ማጓጓዝ

በሰባተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት መገባደጃ ላይ፣ ቦይ ለመገንባት ተይዞ የነበረው እቅድ ሳይሳካ በመቅረቱ የቆሮንቶስ ገዥ የነበረው ፔሪአንደር በቆሮንቶስ ወሽመጥ ላይ ዕቃ ማጓጓዝ የሚቻልበት ላቅ ያለ ጥበብ የተንጸባረቀበት መንገድ ገነባ። * ይህ መንገድ ዲዮልኮስ ተብሎ የተጠራ ሲሆን ቃሉ “እየገፉ ማሻገር” የሚል ትርጉም አለው። ትላልቅ ጥርብ ድንጋዮች የተነጠፉበትና በውስጡ ሞራ የተቀቡ የእንጨት ሃዲዶች የተቀበሩበት መንገድ ነው። በአንደኛው ወደብ ላይ ከቆሙ መርከቦች የተራገፉ ዕቃዎች ጎማ ባላቸው ጋሪዎች ላይ ከተጫኑ በኋላ ባሪያዎች በመንገዱ ላይ እየገፉ ወደ ሌላኛው ወደብ ይወስዷቸዋል። መርከቦቹ ትንንሽ ከሆኑ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ከነጭነታቸው እየተገፉ ይወሰዳሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.29 ዘመናዊው ቦይ ስለተገነባበት መንገድ የሚገልጽ ታሪክ ማንበብ ከፈለግክ በታኅሣሥ 22, 1984 ንቁ! ገጽ 25-27 (እንግሊዝኛ) ላይ ያለውን “የቆሮንቶስ ቦይና በዚያ ዙሪያ ያለው ታሪክ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ግሪክ

የቆሮንቶስ ወሽመጥ

የሌካኦን ወደብ

የቆሮንቶስ ባሕረ ሰላጤ

የጥንቷ ቆሮንቶስ

ክንክራኦስ

የሳሮኒክ ባሕረ ሰላጤ

ፔሎፖኒስ

የአዮንያን ባሕር

ኬፕ መሊየ

የኤጅያን ባሕር

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዛሬው ጊዜ ዕቃ ጫኝ መርከቦች የቆሮንቶስን ቦይ አቋርጠው ሲያልፉ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሌካኦን ወደብ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክንክራኦስ ወደብ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Todd Bolen/Bible Places.com