በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቫቲካን መለኮታዊው ስም ጥቅም ላይ እንዳይውል ትከላከላለች

ቫቲካን መለኮታዊው ስም ጥቅም ላይ እንዳይውል ትከላከላለች

ቫቲካን መለኮታዊው ስም ጥቅም ላይ እንዳይውል ትከላከላለች

የካቶሊክ ባለ ሥልጣናት፣ በቤተ ክርስቲያናቸው በሚከናወኑ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ላይ መለኮታዊው ስም ጥቅም ላይ እንዳይውል እየተከላከሉ ነው። አምልኮንና የሃይማኖት ሥነ ሥርዓቶችን በተመለከተ መመሪያ የሚያወጣው የቫቲካን ጉባኤ፣ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ያወጣቸው መመሪያዎች ባለፈው ዓመት በዓለም ዙሪያ በተደረጉ የካቶሊክ ጳጳሳትን ያሳተፉ ስብሰባዎች ላይ እንዲገለጹ አድርጎ ነበር። ይህ እርምጃ የተወሰደው በሊቀ ጳጳሱ “ትእዛዝ” መሠረት ነው።

በሰኔ 29, 2008 የወጡት እነዚህ መመሪያዎች የሰፈሩበት ሰነድ እንደገለጸው፣ በአምላክ ስም መጠቀም ተገቢ እንዳልሆነ የሚናገሩ መመሪያዎች ቢኖሩም “ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የእስራኤልን አምላክ ትክክለኛ ስም የመጥራት ልማድ እየታየ ነው፤ የአምላክ ስም፣ ቅዱስ ወይም መለኮታዊ ቴትራግራማተን ተብሎ የሚጠራ ሲሆን የሚጻፈውም የዕብራይስጥን አራት ተነባቢ ፊደላት በመጠቀም יהוה ወይም የሐወሐ ተብሎ ነው።” ይህ ሰነድ፣ መለኮታዊው ስም “ያዌ፣” “ጃዌ፣” “የሆቫ፣” ወዘተ እንደሚሉት ባሉ የተለያዩ መንገዶች ሲተረጎም እንደቆየ ገልጿል። * ከአሁን በኋላ ግን ቫቲካን፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቀደም ሲል የነበራትን አቋም ለማጠናከር ፈልጋለች። ይህም ሲባል መለኮታዊውን ስም የሚወክሉት የዕብራይስጥ ፊደላት “ጌታ” በሚለው ቃል ይተካሉ ማለት ነው። ከዚህም በተጨማሪ በካቶሊክ የሃይማኖት ሥነ ሥርዓቶች፣ መዝሙሮችና ጸሎቶች ላይ የአምላክን ስም የሚወክለው “የሐወሐ ሊጠራም ሆነ ሊሠራበት እንደማይገባ” ተገልጿል።

ቫቲካን የአምላክን ስም በተመለከተ ያላትን አቋም የገለጸችበት ሰነድ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን “የጥንት ወግ” እንደ ማስረጃ ይጠቅሳል። ይህ ሰነድ፣ ከክርስትና በፊት በተዘጋጀው የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ላይ እንኳ መለኮታዊው ስም በተደጋጋሚ ኪሪኦስ (በግሪክኛ “ጌታ”) ተብሎ እንደተቀመጠ ይገልጻል። በዚህም ምክንያት ሰነዱ “ክርስቲያኖችም ቢሆኑ ከመጀመሪያው ጀምሮ መለኮታዊውን ቴትራግራማተን ጠርተውት አያውቁም” የሚል የመከራከሪያ ሐሳብ ያቀርባል። ይሁን እንጂ ይህ ሐሳብ ግልጽ ከሆኑ ማስረጃዎች ጋር የሚጋጭ ነው። በመጀመሪያዎቹ የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ቅጂዎች ውስጥ የሚገኘው ኪሪኦስ ሳይሆን በአራቱ የዕብራይስጥ ፊደላት (יהוה) የሚወከለው መለኮታዊው ስም ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩት የክርስቶስ ተከታዮች የአምላክን ስም ያውቁት የነበረ ከመሆኑም ሌላ ይጠሩት ነበር። ኢየሱስ ራሱ ለአባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ “ስምህን . . . አሳውቄአለሁ” ብሏል። (ዮሐንስ 17:26) በተጨማሪም ታዋቂ በሆነው የናሙና ጸሎቱ ላይ “በሰማያት የምትኖር አባታችን፣ ስምህ ይቀደስ” ብለን እንድንጸልይ አስተምሮናል።—ማቴዎስ 6:9

ክርስቲያኖች በሙሉ የአምላክ ስም ሲቀደስ የማየት ፍላጎት ሊኖራቸው ይገባል። ቫቲካን የአምላክ ስም ጥቅም ላይ እንዳይውል የምታደርገው ጥረት “ስሜ ለዘላለም ይህ ነው፤ ወደፊት በሚነሳው ትውልድ ሁሉ የምታሰበው በዚህ ስም ነው” በማለት የተናገረውን ይሖዋን የሚያስከብር አይደለም።”—ዘፀአት 3:15 ዘ ጀሩሳሌም ባይብል

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 በእንግሊዝኛ “ጀሆቫ” (በአማርኛ “ይሖዋ”) የሚለው አጠራር ለዘመናት ሰፊ ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችም ተጠቅመውበታል።

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ስሜ ለዘላለም ይህ ነው።”—ዘፀአት 3:15 ዘ ጀሩሳሌም ባይብል

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የተጻፈ “የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም” ቁራጭ። በተለምዶ የሐወሐ ተብለው በሚቀመጡት በአራቱ የዕብራይስጥ ፊደላት የተወከለው መለኮታዊው ስም ተከቦበታል

[ምንጭ]

Courtesy of the Egypt Exploration Society