ዳግመኛ መወለድ ምን ዓይነት ለውጥ ያስከትላል?
ዳግመኛ መወለድ—ምን ዓይነት ለውጥ ያስከትላል?
ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ስለ መጠመቅ ሲናገር ‘ከመንፈስ መወለድ’ የሚል አገላለጽ የተጠቀመው ለምንድን ነው? (ዮሐንስ 3:5) “መወለድ” የሚለው ቃል በምሳሌያዊ አነጋገር ሲሠራበት “መጀመሪያ” የሚል ፍቺ ይኖረዋል። በመሆኑም “ዳግመኛ መወለድ” ወይም “እንደ አዲስ መወለድ” የሚለው ሐረግ “አዲስ ጅምርን” የሚያመለክት ነው። “መወለድ” እና “እንደ አዲስ መወለድ” የሚሉት ምሳሌያዊ አነጋገሮች በመንፈስ ቅዱስ የተጠመቁት ክርስቲያኖች ከአምላክ ጋር የነበራቸው ዝምድና አዲስ መልክ እንደሚኖረው የሚጠቁሙ ናቸው። ዝምድናቸው አዲስ መልክ ሊኖረው የቻለው እንዴት ነው?
ሐዋርያው ጳውሎስ፣ አምላክ የተወሰኑ ሰዎችን በሰማይ ነገሥታት እንዲሆኑ የሚያዘጋጃቸው እንዴት እንደሆነ ሲያብራራ ከቤተሰብ ሕይወት ጋር ተዛማጅነት ያለው ምሳሌ ተጠቅሟል። ጳውሎስ በዘመኑ ለነበሩት ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ አምላክ እነሱን ‘እንደ ልጆቹ አድርጎ እንደወሰዳቸው’ ገልጿል፤ በዚህም ምክንያት አምላክ “እንደ ልጆቹ አድርጎ” እንደሚይዛቸው ጽፎላቸዋል። (ገላትያ 4:5፤ ዕብራውያን 12:7) ጳውሎስ የተጠቀመው ምሳሌ አንድ ሰው በመንፈስ ቅዱስ ሲጠመቅ የሚከናወነውን ለውጥ ለመረዳት የሚያስችለን እንዴት እንደሆነ ለማየት፣ የአንድ አካባቢ ተወላጅ የሆኑ ተማሪዎች ብቻ በሚማሩበት ትምህርት ቤት ለመግባት ስለፈለገው ወጣት የሚናገረውን ምሳሌ መለስ ብለን እንመልከት።
እንደ ልጅ ተደርጎ መወሰድ የሚያስከትለው ለውጥ
ቀደም ሲል ባየነው ምሳሌ ላይ፣ ወጣቱ የአንድ አካባቢ ተወላጅ ለሆኑ ተማሪዎች ብቻ በተከፈተው ትምህርት ቤት መግባት ያልቻለው የዚያ አካባቢ ተወላጅ ስላልሆነ ነበር። ሆኖም አንድ ቀን ትልቅ ለውጥ ተከሰተ። የዚያ አካባቢ ተወላጅ የሆነ አንድ የቤተሰብ ኃላፊ፣ ይህን ወጣት ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንደ ራሱ ልጅ አድርጎ ወሰደው። ታዲያ ይህ በወጣቱ ሁኔታ ላይ ምን ለውጥ ያመጣል? ይህ ወጣት በትምህርት ቤቱ ውስጥ መግባትን ጨምሮ የዚያ አካባቢ ተወላጅ የሆኑት ተማሪዎች የሚያገኟቸው መብቶች ሁሉ ሊያገኝ ይችል ይሆናል። የዚያ አካባቢ ተወላጅ የሆነ ሰው እንደ ልጁ አድርጎ የወሰደው መሆኑ የወጣቱን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ለውጦታል።
ይህ ምሳሌ ዳግመኛ መወለድ በአንድ ሰው ላይ የሚያስከትለውን ጉልህ ለውጥ ለመረዳት ያስችላል። በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ወጣት እና ዳግመኛ የሚወለዱት ክርስቲያኖች ባላቸው ሁኔታ መካከል የሚታየውን ተመሳሳይነት እንመልከት። በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ወጣት በትምህርት ቤቱ መመዝገብ የሚችለው አስፈላጊውን ብቃት ካሟላ ማለትም ራቅ ብሎ የሚገኘው አካባቢ ተወላጅ ከሆነ ብቻ ነው። ሆኖም ይህንን ብቃት በራሱ ማሟላት አይችልም። በተመሳሳይም የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በአምላክ መንግሥት ወይም በሰማይ በሚገኘው መስተዳድር ውስጥ መግዛት የሚችሉት የሚያስፈልገውን ብቃት ካሟሉ ይኸውም ‘ዳግመኛ ከተወለዱ’ ብቻ ነው። ሆኖም እንደ አዲስ
መወለድ በአምላክ ምርጫ ላይ የተመካ ስለሆነ እነዚህ ሰዎች ብቃቱን በራሳቸው ማሟላት አይችሉም።የወጣቱ ሁኔታ እንዲቀየር ያደረገው ምንድን ነው? ራቅ ያለው አካባቢ ተወላጅ የሆነ ሰው እንደ ልጁ አድርጎ የወሰደው መሆኑ ነው። እርግጥ ነው፣ ወጣቱ የሌላ ቤተሰብ አባል መሆኑ ማንነቱን አይቀይረውም። ያም ቢሆን የዚያ አካባቢ ተወላጅ የሆነው ሰው ይህን ወጣት ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንደ ራሱ ልጅ አድርጎ ከወሰደው በኋላ የወጣቱ ሁኔታ ተቀይሯል። በሌላ አባባል፣ ወጣቱ እንደገና የተወለደ ያህል አዲስ የሕይወት ጎዳና ጀምሯል። ሰውየው እንደ ልጁ አድርጎ ስለወሰደው በትምህርት ቤቱ የመመዝገብና የዚህ ሰው ቤተሰብ አባል የመሆን መብት አግኝቷል።
በተመሳሳይም ይሖዋ፣ ሕጋዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ፍጹማን ያልሆኑ የተወሰነ ቁጥር ያላቸው የሰው ልጆችን እንደ ልጆቹ አድርጎ ተቀብሏቸዋል፤ ይህም ሁኔታቸው እንዲቀየር አድርጓል። የዚህ ቡድን አባል የሆነው ሐዋርያው ጳውሎስ ለእምነት ባልንጀሮቹ እንዲህ ሲል ጽፎላቸዋል፦ “እንደ ልጅ የመቆጠር መብት የሚያስገኝ መንፈስ ተቀብላችኋል፤ ይህም መንፈስ ‘አባ፣ አባት!’ ብለን እንድንጣራ ይገፋፋናል። የአምላክ ልጆች መሆናችንን ይህ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ሆኖ ይመሠክራል።” (ሮም 8:15, 16) አዎን፣ አምላክ እነዚህን ክርስቲያኖች እንደ ልጆቹ አድርጎ ስለተቀበላቸው የእሱ ቤተሰብ አባላት ወይም “የአምላክ ልጆች” መሆን ችለዋል።—1 ዮሐንስ 3:1፤ 2 ቆሮንቶስ 6:18
እርግጥ ነው፣ እነዚህ ክርስቲያኖች አምላክ እንደ ልጆቹ አድርጎ ስለተቀበላቸው ማንነታቸው ተቀይሯል ማለት አይደለም፤ አሁንም ቢሆን ፍጹማን አይደሉም። (1 ዮሐንስ 1:8) ያም ቢሆን፣ ጳውሎስ እንዳብራራው አምላክ ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንደ ልጆቹ አድርጎ ከወሰዳቸው በኋላ ሁኔታቸው ተቀይሯል። አምላክ እንደ ልጆቹ አድርጎ ሲቀበላቸው፣ የአምላክ መንፈስ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ እንደሚኖሩ እርግጠኛ የሆነ እምነት እንዲያድርባቸው ያደርጋል። (1 ዮሐንስ 3:2) መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ያለ እርግጠኛ እምነት እንዲያድርባቸው ስላደረገ ለሕይወት ያላቸው አመለካከት በእጅጉ ይለወጣል። (2 ቆሮንቶስ 1:21, 22) አዎን፣ እነዚህ ክርስቲያኖች እንደ አዲስ የተወለዱ ያህል አዲስ የሕይወት ጎዳና ጀምረዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ እንደ ልጆቹ አድርጎ ስለወሰዳቸው ክርስቲያኖች ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “የአምላክና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፤ እንዲሁም ከእሱ ጋር ነገሥታት ሆነው ለአንድ ሺህ ዓመት ይገዛሉ።” (ራእይ 20:6) አምላክ እንደ ልጆቹ አድርጎ የተቀበላቸው ክርስቲያኖች ከክርስቶስ ጋር በአምላክ መንግሥት ወይም በሰማይ በሚገኘው መስተዳድር ውስጥ ነገሥታት የመሆን መብት ያገኛሉ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ለእምነት ባልንጀሮቹ እንደጻፈው ‘በሰማይ ለእነሱ የተጠበቀላቸው’ ይህ የመግዛት መብት ‘የማይበሰብስ፣ የማይረክስና የማይጠፋ ርስት ነው።’ (1 ጴጥሮስ 1:3, 4) ይህ በእርግጥም የላቀ ርስት ነው!
ይሁን እንጂ እነዚህ ክርስቲያኖች ያገኙት የመግዛት መብት አንድ ጥያቄ ያስነሳል። ዳግመኛ የተወለዱት ሰዎች በሰማይ ነገሥታት የሚሆኑ ከሆነ የሚገዙት በእነማን ላይ ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ለዚህ ጥያቄ ማብራሪያ ይሰጣል።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጳውሎስ፣ አንድን ሰው እንደ ራስ ልጅ አድርጎ መውሰድን በተመለከተ ምን ብሏል?