በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዳግመኛ መወለድ በእኛ ምርጫ ላይ የተመካ ነው?

ዳግመኛ መወለድ በእኛ ምርጫ ላይ የተመካ ነው?

ዳግመኛ መወለድ በእኛ ምርጫ ላይ የተመካ ነው?

አንድን ሰው ዳግመኛ እንዲወለድ የሚያደርገው ማን ነው? አንዳንድ ሰባኪዎች አድማጮቻቸው ዳግመኛ የተወለዱ ክርስቲያኖች እንዲሆኑ ለማሳሰብ ኢየሱስ “ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ” ሲል የተናገረውን ሐሳብ ይጠቅሳሉ። (ዮሐንስ 3:7) እነዚህ ሰባኪዎች ይህን ሐሳብ የሚናገሩት በትእዛዝ መልክ ስለሆነ “ዳግመኛ ተወለዱ!” የሚሉ ያህል ነው። በሌላ አነጋገር ኢየሱስን በመታዘዝ እንደ አዲስ ለመወለድ የሚያስፈልገውን እርምጃ መውሰድ ያለበት እያንዳንዱ አማኝ እንደሆነ ያስተምራሉ። እነዚህ ሰዎች እንደሚሉት ከሆነ ዳግመኛ መወለድ በግለሰቦች ምርጫ ላይ የተመካ ነው። ይሁንና ይህ አመለካከት ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ ከሰጠው ትምህርት ጋር ይስማማል?

ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ ልብ ብለን ካነበብን ዳግመኛ መወለድ፣ በግለሰቦች ምርጫ ላይ የተመካ መሆኑን እንዳላስተማረ መገንዘብ እንችላለን። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? “ዳግመኛ መወለድ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ሐረግ “ከላይ መወለድ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። * በዚህ አተረጓጎም መሠረት አንድ ሰው እንደ አዲስ መወለድን ማግኘት የሚችለው “ከላይ” ማለትም በሰማይ ከሚኖረው “አባት” ነው። (ዮሐንስ 19:11፤ ያዕቆብ 1:17) አዎን፣ አንድ ሰው ዳግመኛ እንዲወለድ የሚያደርገው አምላክ ነው።—1 ዮሐንስ 3:9

“ከላይ” የሚለው ቃል የሚያስተላልፈውን ሐሳብ ከተረዳን ዳግመኛ መወለድ አንድ ሰው በራሱ የሚያደርገው ምርጫ እንዳልሆነ ግልጽ ይሆንልናል። በተፈጥሮ የምንወለድበትን መንገድ እንደ ምሳሌ እንመልከት። የተወለድከው በራስህ ምርጫ ነው? አይደለም! እንድትወለድ ያደረገው ወይም ለመወለድህ ምክንያት የሆነው አባትህ ነው። በተመሳሳይም ዳግመኛ መወለድ የምንችለው በሰማይ የሚኖረው አባታችን እንደ አዲስ እንድንወለድ ካደረገን ብቻ ነው። (ዮሐንስ 1:13) በመሆኑም ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደሚከተለው ማለቱ የተገባ ነው፦ “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ ምክንያቱም እሱ በታላቅ ምሕረቱ . . . እንደ አዲስ ወልዶናል።”—1 ጴጥሮስ 1:3

ትእዛዝ ነው?

አንዳንዶች ‘ዳግመኛ መወለድ በግለሰቦች ምርጫ ላይ የተመካ ካልሆነ ኢየሱስ “ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ” የሚል ትእዛዝ የሰጠው ለምንድን ነው?’ በማለት ሊጠይቁ ይችላሉ። ደግሞም እንዲህ ብለው መጠየቃቸው ተገቢ ነው። ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ትእዛዝ ከሆነ ልናደርገው የማንችለውን ነገር እንድንፈጽም እየጠየቀን ነው ማለት ይሆናል። ይህ ደግሞ ምክንያታዊ አይደለም። ታዲያ “ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ” የሚለውን ሐሳብ መረዳት ያለብን እንዴት ነው?

ይህ ዓረፍተ ነገር፣ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ የተገለጸው ትእዛዝ በሚያስተላልፍ መንገድ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አንድን እውነታ የሚገልጽ ዓረፍተ ነገር ነው። በሌላ አነጋገር ኢየሱስ “ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ” ሲል አንድ ሐቅ እየገለጸ እንጂ ትእዛዝ እየሰጠ አልነበረም። “ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል” ማለቱ ነበር።—ዮሐንስ 3:7 የ1954 ትርጉም

ይህንን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ብዙ ትምህርት ቤቶች ያሉትን አንድ ከተማ አስብ። አንደኛው ትምህርት ቤት ከከተማው በጣም ርቆ በሚገኝ ቦታ ለሚኖሩ የአንድ አካባቢ ተወላጆች የተዘጋጀ ነው። አንድ ቀን፣ የዚያ አካባቢ ተወላጅ ያልሆነ አንድ ወጣት የትምህርት ቤቱን ዳይሬክተር “እዚህ ትምህርት ቤት መግባት እፈልጋለሁ” አለው። ዳይሬክተሩም “በትምህርት ቤቱ ለመማር የዚያ አካባቢ ተወላጅ መሆን አለብህ” በማለት መለሰለት። ዳይሬክተሩ የተናገረው ነገር ትእዛዝ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ወጣቱን የዚያ አካባቢ ተወላጅ እንዲሆን እያዘዘው አልነበረም። ዳይሬክተሩ፣ ወጣቱ እዚያ ትምህርት ቤቱ ለመግባት ማሟላት ያለበትን ብቃት እየተናገረ ነበር። በተመሳሳይም ኢየሱስ “ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ” ሲል ‘ወደ አምላክ መንግሥት ለመግባት’ መሟላት ያለበትን ብቃት መግለጹ ነበር።

ኢየሱስ ዳግመኛ ከመወለድ ጋር በተያያዘ ያነሳው ሌላው ጉዳይ የአምላክ መንግሥት ነው። ይህ ደግሞ ‘አንድ ሰው ዳግመኛ የሚወለድበት ዓላማ ምንድን ነው?’ ለሚለው ጥያቄ መልስ እንድናገኝ ይረዳናል። ለዚህ ጥያቄ የምናገኘው መልስ ዳግመኛ መወለድ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ትክክለኛ ግንዛቤ ለማግኘት ያስችለናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ዮሐንስ 3:3⁠ን በዚህ መንገድ ተርጉመውታል። ለምሳሌ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከማጥኛ ጽሑፍ ጋር ይህን ጥቅስ እንደሚከተለው በማለት አስቀምጦታል፦ “ማንም ዳግመኛ ካልተወለደ [‘ከላይ ካልተወለደ፣’ የግርጌ ማስታወሻ] በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም።”

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በተፈጥሮ በምንወለድበት መንገድና እንደ አዲስ በመወለድ መካከል ምን ተመሳሳይነት አለ?