በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዳግመኛ መወለድ የሚከናወነው እንዴት ነው?

ዳግመኛ መወለድ የሚከናወነው እንዴት ነው?

ዳግመኛ​—መወለድ የሚከናወነው እንዴት ነው?

ኢየሱስ ከኒቆዲሞስ ጋር ባደረገው ውይይት ላይ፣ እንደ አዲስ መወለድ አስፈላጊ መሆኑንና በአምላክ የሚወሰን ጉዳይ መሆኑን እንዲሁም ዳግመኛ የመወለድን ዓላማ በመጥቀስ ብቻ አልተወሰነም፤ አንድ ሰው ዳግመኛ የሚወለደው እንዴት እንደሆነም ጭምር ተናግሯል። ኢየሱስ “ማንም ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ አምላክ መንግሥት ሊገባ አይችልም” ብሏል። (ዮሐንስ 3:5) ስለዚህ አንድ ሰው ዳግመኛ የሚወለደው በውኃና በመንፈስ አማካኝነት ነው። ይሁንና ‘ውኃና መንፈስ’ የሚለው አገላለጽ ምን ያመለክታል?

‘ውኃና መንፈስ’—ምንድን ናቸው?

ኒቆዲሞስ የአይሁድ ሃይማኖት ምሑር ስለነበረ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ‘የአምላክ መንፈስ’ የሚለውን ሐረግ እንዴት እንደሚጠቀሙበት ያውቅ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ኒቆዲሞስ ‘የአምላክ መንፈስ’ የሚለው ሐረግ፣ ሰዎች አስደናቂ የሆኑ ነገሮችን እንዲያከናውኑ የሚያስችላቸውን በሥራ ላይ የዋለ የአምላክ ኃይል እንደሚያመለክት ያውቅ ነበር። (ዘፍጥረት 41:38፤ ዘፀአት 31:3፤ 1 ሳሙኤል 10:6) ስለሆነም ኢየሱስ “መንፈስ” ሲል በሥራ ላይ ስለዋለው የአምላክ ኃይል ማለትም ስለ መንፈስ ቅዱስ እየተናገረ መሆኑን ኒቆዲሞስ እንደሚረዳ ግልጽ ነው።

ኢየሱስ “ውኃ” ሲልስ ምን ማለቱ ነበር? ኢየሱስ ከኒቆዲሞስ ጋር ስላደረገው ውይይት ከተጻፈው ዘገባ በፊትና በኋላ ያሉትን ሐሳቦች እንመልከት። እነዚህ ዘገባዎች አጥማቂው ዮሐንስም ሆነ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በውኃ ያጠምቁ እንደነበረ ይገልጹልናል። (ዮሐንስ 1:19, 31፤ 3:22፤ 4:1-3) በውኃ ማጥመቅ በኢየሩሳሌም የታወቀ ነገር ሆኖ ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ ስለ ውኃ ሲጠቅስ፣ በአጠቃላይ ስለ ውኃ ሳይሆን በውኃ ስለ መጠመቅ እየተናገረ እንደነበረ ኒቆዲሞስ ለመረዳት አያስቸግረውም። *

“በመንፈስ ቅዱስ” መጠመቅ

‘ከውኃ መወለድ’ በውኃ ከመጠመቅ ጋር የተያያዘ ከሆነ ‘ከመንፈስ መወለድስ’ ምን ትርጉም አለው? ኢየሱስ ከኒቆዲሞስ ጋር ከመነጋገሩ በፊት፣ አጥማቂው ዮሐንስ ውኃ ብቻ ሳይሆን መንፈስም በጥምቀት ረገድ የሚጫወተው ሚና እንዳለ ገልጾ ነበር። ዮሐንስ “እኔ በውኃ አጠመቅኋችሁ፤ እሱ [ኢየሱስ] ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል” ብሏል። (ማርቆስ 1:7, 8) የወንጌል ጸሐፊ የሆነው ማርቆስ እንዲህ ዓይነት ጥምቀት ለመጀመሪያ ጊዜ የተከናወነበትን ሁኔታ ሲዘግብ እንዲህ ብሏል፦ “በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በገሊላ ከምትገኘው ከናዝሬት መጥቶ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ ተጠመቀ። ወዲያው ከውኃ እንደወጣ ሰማያት ተከፍተው መንፈስ እንደ ርግብ በእሱ ላይ ሲወርድ አየ።” (ማርቆስ 1:9, 10) ኢየሱስ ዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ በጠለቀ ጊዜ በውኃ የተጠመቀ ሲሆን መንፈስ ከሰማይ በወረደበት ጊዜ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቋል።

ኢየሱስ ከተጠመቀ ከሦስት ዓመት ገደማ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን “ከጥቂት ቀናት በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ” ብሏቸው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 1:5) ታዲያ ይህ ፍጻሜውን ያገኘው መቼ ነው?

በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በጴንጤቆስጤ ዕለት 120 የሚሆኑ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በኢየሩሳሌም በሚገኝ አንድ ቤት ውስጥ ተሰብስበው ነበር። “ድንገትም እንደ ኃይለኛ ነፋስ ያለ ድምፅ ከሰማይ መጣ፤ ተቀምጠውበት የነበረውንም ቤት ሞላው። የእሳት ነበልባል የሚመስሉ ምላሶች ታዩአቸው፤ . . . ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ።” (የሐዋርያት ሥራ 2:1-4) በዚያኑ ዕለት በኢየሩሳሌም የነበሩ ሌሎች ሰዎች በውኃ እንዲጠመቁ ማበረታቻ ተሰጣቸው። ሐዋርያው ጴጥሮስ ተሰብስቦ ለነበረው ሕዝብ እንዲህ አለ፦ “ንስሐ ግቡ፤ እያንዳንዳችሁም ለኃጢአታችሁ ይቅርታ እንድታገኙ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ነፃ ስጦታ ትቀበላላችሁ።” የሰዎቹስ ምላሽ ምን ነበር? “ቃሉን ከልባቸው የተቀበሉ ተጠመቁ፤ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ ገደማ የሚሆኑ ነፍሳት ተጨመሩ።”—የሐዋርያት ሥራ 2:38, 41

ዳግመኛ መወለድ የሚያካትታቸው ሁለት ነገሮች

እነዚህ ሁለት ጥምቀቶች ዳግመኛ ስለ መወለድ ምን እንድናስተውል ይረዱናል? ዳግመኛ መወለድ ሁለት ነገሮችን እንደሚያካትት ይጠቁሙናል። ኢየሱስ በመጀመሪያ በውኃ እንደተጠመቀ ልብ በል። ከዚያም መንፈስ ቅዱስ ወረደበት። በተመሳሳይም የጥንቶቹ ደቀ መዛሙርት መጀመሪያ በውኃ የተጠመቁ ሲሆን (አንዳንዶቹን ያጠመቃቸው አጥማቂው ዮሐንስ ነው) ከዚያ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ወርዶባቸዋል። (ዮሐንስ 1:26-36) አዲሶቹ 3,000 ደቀ መዛሙርትም መጀመሪያ በውኃ የተጠመቁ ሲሆን ከዚያም መንፈስ ቅዱስን ተቀብለዋል።

በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በጴንጤቆስጤ ዕለት ከተከናወኑት ጥምቀቶች አንጻር በዛሬው ጊዜ አንድ ሰው ዳግመኛ የሚወለደው እንዴት ነው? የኢየሱስ ሐዋርያትም ሆኑ የጥንቶቹ ደቀ መዛሙርት ዳግመኛ ከተወለዱበት ጋር በሚመሳሰል መንገድ ነው። በመጀመሪያ አንድ ሰው ከኃጢአቱ ንስሐ ይገባል፣ ከመጥፎ ምግባሩ ይመለሳል፣ አምላክን ለማምለክና ለማገልገል ራሱን ለይሖዋ ይወስናል፤ ከዚያም በውኃ በመጠመቅ ውሳኔውን በሕዝብ ፊት ያሳያል። ቀጥሎ ደግሞ አምላክ በመንግሥቱ ላይ ገዢ እንዲሆን ከመረጠው በመንፈስ ቅዱስ ይቀባል። ዳግመኛ መወለድ ከሚያካትታቸው ሁለት ነገሮች መካከል የመጀመሪያው (ይኸውም በውኃ መጠመቅ) በግለሰቡ ውሳኔ ላይ የተመካ ነው፤ ሁለተኛው (ይኸውም በመንፈስ መጠመቅ) ግን በአምላክ ምርጫ ላይ የተመካ ነው። አንድ ሰው በውኃና በመንፈስ ሲጠመቅ ዳግመኛ ተወልዷል ማለት ነው።

ይሁንና ኢየሱስ ከኒቆዲሞስ ጋር ባደረገው ውይይት ላይ ‘ከውኃና ከመንፈስ መወለድ’ የሚለውን አገላለጽ የተጠቀመው ለምንድን ነው? ይህን ያለው በውኃና በመንፈስ የሚጠመቁ ሰዎች አስገራሚ ለውጥ እንደሚያደርጉ ለማጉላት ነው። የሚቀጥለው ርዕስ ስለዚህ ጉዳይ ያብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 በተመሳሳይም ሐዋርያው ጴጥሮስ የጥምቀት ሥነ ሥርዓት በተከናወነበት አንድ አጋጣሚ “ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማን ነው?” ብሎ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 10:47 የ1954 ትርጉም

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አጥማቂው ዮሐንስ ንስሐ የገቡ እስራኤላውያንን በውኃ አጥምቋል