በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“መጨረሻው” ስለሚለው ቃል

“መጨረሻው” ስለሚለው ቃል

ከኢየሱስ ምን እንማራለን?

“መጨረሻው” ስለሚለው ቃል

የምን ‘መጨረሻ’ ነው?

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ወደ እሱ ቀርበው “የመገኘትህና የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክትስ ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። (ማቴዎስ 24:3) ኢየሱስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ስለ ምድር መጨረሻ ወይም ጥፋት አልተናገረም። ቀደም ሲል ኢየሱስ ‘ስለዚህ ሥርዓት’ የተናገረ ሲሆን ይህን ሐረግ የተጠቀመበት በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለውንና ሰዎች ያቋቋሙትን የፖለቲካ፣ የንግድና የሃይማኖት ሥርዓት በአጠቃላይ ለማመልከት ነበር። (ማቴዎስ 13:22, 40, 49) በመሆኑም “መጨረሻው ይመጣል” በማለት ሲናገር ይህንን ሥርዓት በአእምሮው ይዞ ነበር።—ማቴዎስ 24:14

ኢየሱስ ‘መጨረሻውን’ የገለጸው እንዴት ነው?

ይህ ፍትሕ የጎደለው ሥርዓት መጨረሻ እንዳለው ማወቅ ‘የምሥራች’ ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።” ኢየሱስ የዚህ ሥርዓት መጨረሻ ምን እንደሚመስል ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ድረስ ሆኖ የማያውቅ ዳግመኛም የማይሆን ታላቅ መከራ ይከሰታል። እንዲያውም ቀኖቹ ባያጥሩ ኖሮ ሥጋ ሁሉ ባልዳነ ነበር።”—ማቴዎስ 24:14, 21, 22

የሚጠፉት እነማን ናቸው?

የሚጠፉት ይሖዋንና ኢየሱስን የማያገለግሉ እንዲሁም ለእነሱ ፍቅር የሌላቸው ብቻ ናቸው። እንዲህ ያሉት ሰዎች አምላክን አይታዘዙም። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “በኖኅ ዘመን እንደነበረው ሁሉ የሰው ልጅ መገኘትም እንደዚሁ ይሆናል። ከጥፋት ውኃ በፊት በነበረው ዘመን . . . የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ እስከወሰዳቸው ጊዜ ድረስ ምንም አላስተዋሉም።” (ማቴዎስ 24:36-39) ኢየሱስ ብዙዎች ወደ ጥፋት በሚመራ መንገድ ላይ እየተጓዙ እንደሆነ ተናግሯል። ይሁንና “ወደ ሕይወት የሚያስገባ ቀጭን መንገድ” እንዳለም ገልጿል።—ማቴዎስ 7:13, 14

የዚህ ሥርዓት መጨረሻው መቼ ነው?

ኢየሱስ የመገኘቱና “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” ምልክት ምን እንደሚሆን በተጠየቀ ጊዜ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳል፤ . . . የምግብ እጥረትና የምድር ነውጥ ይከሰታል። . . . ክፋት እየበዛ ስለሚሄድ የብዙዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል።” (ማቴዎስ 24:3-12) በዛሬው ጊዜ የምንሰማቸው አሳዛኝ ዜናዎች ያላቸውን ትርጉም ስለምንረዳ እንጽናናለን፤ ምክንያቱም በቅርቡ የአምላክ መንግሥት ታዛዥ ለሆኑ ሰዎች ሰላም እንደሚያመጣ እናውቃለን። ኢየሱስ “እነዚህ ነገሮች ሲከሰቱ ስታዩ የአምላክ መንግሥት እንደቀረበ እወቁ” ሲል ተናግሯል።—ሉቃስ 21:31

ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

ኢየሱስ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል [አምላክ] አንድያ ልጁን ሰጥቷል።” (ዮሐንስ 3:16) በአምላክም ሆነ በልጁ እንደምታምን በተግባር ለማሳየት ሁለቱንም በደንብ ልታውቃቸው ያስፈልጋል። በመሆኑም ኢየሱስ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ስለሆንከው ስለ አንተና ስለላክኸው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት መቅሰማቸውን መቀጠል አለባቸው” በማለት ተናግሯል።—ዮሐንስ 17:3

የኑሮ ጭንቀቶችም ሆኑ ሌሎች ችግሮች ለአምላክ ያለህን ፍቅር በተግባር መግለጽ ስለምትችልበት መንገድ እንዳትማር እንቅፋት እንዲሆኑብህ አትፍቀድ። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ስለ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ ሸክም እንዳይበዛበት ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ አለዚያ ያ ቀን ድንገት ሳታስቡት እንደ ወጥመድ ይመጣባችኋል። ምክንያቱም ይህ በመላው ምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ይደርስባቸዋል።” የኢየሱስን ማስጠንቀቂያ ከሰማህ “መፈጸማቸው ከማይቀረው ከእነዚህ ሁሉ ነገሮች ማምለጥ” ትችላለህ።—ሉቃስ 21:34-36

ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?* ከተባለው መጽሐፍ ላይ “የምንኖረው ‘በመጨረሻው ዘመን’ ውስጥ ነው?” የሚል ርዕስ ያለውን ምዕራፍ 9⁠ን ተመልከት።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።