በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ዘይቤያዊ አነጋገሮችን ትረዳቸዋለህ?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ዘይቤያዊ አነጋገሮችን ትረዳቸዋለህ?
አንድ ሥዕል ከሺህ ቃላት የበለጠ የመግለጽ ኃይል ሊኖረው ይችላል፤ አንዳንድ ጊዜ ግን በአንድ ወይም በሁለት ቃላት ብቻ የተነገረ ሐሳብ አንባቢው መልእክቱን በዓይነ ሕሊናው እንዲስል ያደርገዋል። በአንባቢው አእምሮ ውስጥ አንድ ዓይነት ምስል እንዲፈጠር የሚያደርጉ አገላለጾች ወይም ዘይቤያዊ አነጋገሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በበርካታ ቦታዎች ላይ ይገኛሉ። * ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ብቻ እንኳ ከ50 በላይ ዘይቤያዊ አነጋገሮችን ተጠቅሟል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጠቀሱ ዘይቤያዊ አነጋገሮች ማወቅህ ምን ጥቅም አለው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ለአምላክ ቃል ያለህን አድናቆትና ግንዛቤ በመጨመር የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህ አስደሳች እንዲሆንልህ ያደርጋል። በተጨማሪም የምታነበው ነገር ምሳሌያዊ አገላለጽ መሆኑን ከተረዳህና ትርጉሙ ግልጽ ከሆነልህ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ይበልጥ ትረዳለህ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ዘይቤያዊ አነጋገሮችን ካልተረዳህ ግን ሐሳቡ ግራ የሚያጋባህ ከመሆኑም በላይ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ልትደርስ ትችላለህ።
ዘይቤያዊ አነጋገሮችን መረዳት የሚቻለው እንዴት ነው?
ዘይቤያዊ አነጋገር አንድን ሐሳብ ከሌላው ጋር ያነጻጽራል። ከሌላ ሐሳብ ጋር እንዲነጻጸር የተፈለገው ዋነኛው ሐሳብ ርዕሰ ጉዳይ ይባላል፤ ለማነጻጸሪያነት የገባው ሁለተኛው ሐሳብ ደግሞ ምስል ይባላል። በሁለቱ ሐሳቦች መካከል ያለው ንጽጽር ተመሳሳይነት ይባላል። በመሆኑም የአንድን ዘይቤያዊ አነጋገር ትክክለኛ ትርጉም መረዳትህ የተመካው እነዚህን ሦስት ክፍሎች ለይተህ በማወቅህ ላይ ነው።
አንዳንድ ጊዜ ርዕሰ ጉዳዩንና ምስሉን መለየት በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ቀላል ሊሆን ይችላል። ተመሳሳይ የሚያደርጋቸውን ነጥብ በተመለከተ ግን በርካታ አማራጮች ሊኖሩ ይችላሉ። ሁለቱን ሐሳቦች የሚያመሳስላቸውን ነጥብ በትክክል ለመረዳት ምን ማድረግ ትችላለህ? በአብዛኛው በአንድ ዘይቤያዊ አነጋገር ዙሪያ ያለውን ሐሳብ ማንበብህ ሊረዳህ ይችላል። *
ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ በሰርዴስ ላለው ጉባኤ “ካልነቃህ ግን እንደ ሌባ እመጣለሁ” ብሎት ነበር። እዚህ ላይ ኢየሱስ መምጣቱን (ርዕሰ ጉዳይ) ከሌባ መምጣት (ምስል) ጋር አነጻጽሮታል። በሁለቱ ሐሳቦች መካከል ያለው ተመሳሳይነት ምንድን ነው? በዙሪያው ያለው ሐሳብ ይህን ለመረዳት ያስችለናል። ኢየሱስ በመቀጠል ራእይ 3:3) ስለዚህ ንጽጽሩ ያስፈለገው የሚመጣበትን ዓላማ ለማጉላት አይደለም። ኢየሱስ ይህን የተናገረው አንድ ነገር ለመስረቅ እንደሚመጣ ለማመልከት አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ ይህን ዘይቤያዊ አነጋገር የተጠቀመው ድንገት ሳይጠበቅ እንደሚመጣ ለማጉላት ነው።
“በየትኛው ሰዓት ከተፍ እንደምልብህም ፈጽሞ አታውቅም” ብሏል። (አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ የሚገኝ ዘይቤያዊ አነጋገር ሌላ ቦታ ላይ የተጠቀሰን ተመሳሳይ ዘይቤያዊ አነጋገር ለመረዳት ያስችልሃል። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ “የይሖዋ ቀን የሚመጣው ልክ ሌባ በሌሊት በሚመጣበት ዓይነት መንገድ መሆኑን እናንተ ራሳችሁ በሚገባ ታውቃላችሁ” ሲል በጻፈበት ጊዜ ኢየሱስ የተጠቀመበትን ዘይቤያዊ አነጋገር ተጠቅሟል። (1 ተሰሎንቄ 5:2) ጳውሎስ በተናገራቸው ቃላት ዙሪያ የሚገኘው ሐሳብ የይሖዋን ቀን መምጣት ከሌባ መምጣት ጋር የሚያመሳስለው ነጥብ ምን እንደሆነ አይጠቁምም። ይሁንና ጳውሎስ የተጠቀመውን ዘይቤያዊ አነጋገር ኢየሱስ በራእይ 3:3 ላይ ከተናገረው ጋር ማወዳደርህ በሁለቱ ተነጻጻሪ ሐሳቦች መካከል ያለውን ተመሳሳይነት እንድትረዳ ያስችልሃል። ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ንቁ ሆነው መኖር እንዳለባቸው የሚያሳስብ ጠንካራ መልእክት ያዘለ ዘይቤያዊ አነጋገር ነው።
ስለ አምላክ የሚያስተምሩን ዘይቤያዊ አነጋገሮች
ሁሉን ቻይ ስለሆነው አምላክ ባሕርይና ማድረግ ስለሚችላቸው ነገሮች ማንም ሰው ቢሆን ሙሉ በሙሉ መረዳት አይችልም። ከብዙ ዘመናት በፊት ንጉሥ ዳዊት የይሖዋ ‘ታላቅነት አይመረመርም’ ሲል ጽፏል። (መዝሙር 145:3) ኢዮብም የአምላክን የፍጥረት ሥራዎች ከተመለከተ በኋላ “እነዚህ የሥራው ዳር ዳር ናቸው፤ ስለ እርሱ የሰማነው ምንኛ አነስተኛ ነው! የኀይሉንስ ነጐድጓድ ማን ሊያስተውል ይችላል?” ሲል በአድናቆት ተናግሯል።—ኢዮብ 26:14
ያም ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ በሰማይ ያለውን አምላካችንን ድንቅ ባሕርያት በተወሰነ መጠንም ቢሆን መረዳት እንድንችል ዘይቤያዊ አነጋገሮችን ይጠቀማል። ይሖዋ እንደ ንጉሥ፣ ሕግ ሰጪ፣ ዳኛና ተዋጊ ተደርጎ መገለጹ ክብር ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ያጎላል። ከዚህ በተጨማሪ እረኛ፣ መካሪ፣ አስተማሪ፣ አባት፣ ፈዋሽና አዳኝ እንደሆነ ተደርጎ መገለጹ ልትወደው እንደምትችል ያሳያል። (መዝሙር 16:7፤ 23:1፤ 32:8፤ 71:17፤ 89:26፤ 103:3፤ 106:21፤ ኢሳይያስ 33:22፤ 42:13፤ ዮሐንስ 6:45) እዚህ ላይ የተጠቀሰው እያንዳንዱ መግለጫ ቀላል ቢሆንም ስለ ይሖዋ ብዙ ነጥቦች ወደ አእምሮህ እንዲመጡ ያደርጋል። እነዚህን የመሰሉ ዘይቤያዊ አገላለጾች ብዙ ቃላት አንድ ላይ ተጣምረው ሊገልጹ ከሚችሉት የበለጠ ሐሳብ ያስተላልፋሉ።
በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን ከግዑዛን ነገሮች ጋር ያነጻጽረዋል። ይሖዋ ‘የእስራኤል ዐለት፣’ “መጠጊያ” እንዲሁም “ዐምባ” እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል። (2 ሳሙኤል 23:3፤ መዝሙር 18:2፤ ዘዳግም 32:4) ይሖዋን ከእነዚህ ግዑዛን ነገሮች ጋር የሚያመሳስለው ነጥብ ምንድን ነው? አንድ ትልቅ ዐለት ከቦታው ንቅንቅ እንደማይል ሁሉ ይሖዋ አምላክም አስተማማኝ ከለላ እንደሚሆንልህ ያሳያል።
የመዝሙር መጽሐፍ የይሖዋን ባሕርያት የተለያዩ ገጽታዎች ጎላ አድርገው በሚገልጹ ዘይቤያዊ አነጋገሮች የተሞላ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ የብርሃን፣ የሕይወትና የኃይል ምንጭ እንዲሁም ጥበቃ የሚገኝበት በመሆኑ መዝሙር 84:11 “ፀሓይና ጋሻ” እንደሆነ አድርጎ ይገልጸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ መዝሙር 121:5 ይሖዋ “በቀኝህ በኩል ይከልልሃል” ይላል። ጥላ ያለው ቦታ ከጠራራ ፀሐይ እንደሚከልል ሁሉ ይሖዋም አገልጋዮቹን ‘በእጁ’ ወይም “በክንፎቹ” ጥላ በመጋረድ ከመከራ ትኩሳት ይጠብቃቸዋል።—ኢሳይያስ 51:16፤ መዝሙር 17:8፤ 36:7
ኢየሱስን የሚገልጹ ዘይቤያዊ አነጋገሮች
መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን “የአምላክ ልጅ” በማለት በተደጋጋሚ ይገልጸዋል። (ዮሐንስ 1:34፤ 3:16-18) ከክርስትና ውጭ ያሉ አንዳንድ ሃይማኖቶች አምላክ ቃል በቃል ሚስት ስለሌለውና ሰው ስላልሆነ ይህንን አገላለጽ መረዳት ይከብዳቸዋል። አምላክ፣ ሰዎች ልጅ በሚወልዱበት መንገድ ልጅ ሊኖረው እንደማይችል ግልጽ ነው። በመሆኑም ይህ አገላለጽ ዘይቤያዊ አነጋገር ነው። ኢየሱስ ከአምላክ ጋር ያለው ዝምድና አንድ ሰብዓዊ ልጅ ከአባቱ ጋር ካለው ዝምድና ጋር የሚመሳሰል መሆኑን አንባቢው እንዲረዳ ለማድረግ የታቀደ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ይህ ዘይቤያዊ አነጋገር ኢየሱስ በይሖዋ የተፈጠረ በመሆኑ ሕይወቱን ያገኘው ከእሱ መሆኑን ያጎላል። የመጀመሪያው ሰው አዳምም በተመሳሳይ “የአምላክ ልጅ” እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል።—ሉቃስ 3:38
ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ አፈጻጸም ረገድ እሱ የሚጫወተውን የተለያየ ሚና ለመግለጽ ዘይቤያዊ አነጋገሮችን ተጠቅሟል። ለምሳሌ ያህል፣ “እኔ እውነተኛው የወይን ተክል ነኝ፤ ገበሬው ደግሞ አባቴ ነው” ብሏል። ቀጥሎም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ከወይን ተክል ቅርንጫፎች ጋር አመሳስሏቸዋል። (ዮሐንስ 15:1, 4) ይህ ዘይቤያዊ አነጋገር ምን ቁም ነገር ያስተምረናል? አንድ የወይን ቅርንጫፍ ሕያው ሆኖ እንዲቀጥልና ፍሬ እንዲያፈራ ከግንዱ ጋር ተጣብቆ መቆየት አለበት። በተመሳሳይም የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ከእሱ ጋር ያላቸውን አንድነት ጠብቀው መኖር አለባቸው። ኢየሱስ “ከእኔ ተለይታችሁ ምንም ነገር ልታደርጉ አትችሉም” ብሏል። (ዮሐንስ 15:5) አንድ ገበሬ የወይን ተክሉ ፍሬ እንዲያፈራለት እንደሚጠብቅ ሁሉ ይሖዋም ከክርስቶስ ጋር አንድነት ያላቸው ሁሉ መንፈሳዊ ፍሬ እንዲያፈሩ ይጠብቅባቸዋል።—ዮሐንስ 15:8
የሚነጻጸሩት ሐሳቦች ያላቸውን ተመሳሳይነት በትክክል ለመረዳት ሞክር
ሁለት ተነጻጻሪ ሐሳቦች ያላቸውን ተመሳሳይነት በትክክል ካልተረዳን የዘይቤያዊ አነጋገሩን መልእክት ልንስት እንችላለን። ሮም 12:20ን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ጥቅሱ “ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ የሚጠጣ ነገር ስጠው፤ ይህን በማድረግ በራሱ ላይ ፍም ትከምራለህ” ይላል። በአንድ ሰው ራስ ላይ ፍም መከመር የሚለው ሐሳብ መበቀልን ያመለክታል? አያመለክትም፤ ሁለቱ ተነጻጻሪ ሐሳቦች ያላቸውን ተመሳሳይነት በትክክል ከተረዳን እንዲህ የሚል መደምደሚያ ላይ አንደርስም። ይህ ዘይቤያዊ አነጋገር በጥንት ዘመን ከነበረው ብረት የማቅለጥ ዘዴ የተወሰደ ነው። ያልተጣራ ብረት፣ ምድጃ ውስጥ ይከተትና ከታች ብቻ ሳይሆን ከላይም ፍም ይደረግበታል። ይህ የማጣራት ዘዴ ብረቱ ቀልጦ ከቆሻሻው እንዲለይ ያደርገዋል። በተመሳሳይም ደግነት ማሳየት የአንድን ሰው ልብ ሊያለሰልስና መልካም ባሕርይው ጎልቶ እንዲወጣ ሊያደርግ ይችላል።
ዘይቤያዊ አነጋገሮችን በትክክል መረዳታችን ነጥቡ ይበልጥ ግልጽ እንዲሆንልን የሚረዳን ከመሆኑም በላይ ልባችን እንዲነካ ያደርጋል። ኃጢአት ‘ከዕዳ’ ጋር እንደተመሳሰለ ስናነብ ምን ያህል ባለዕዳዎች እንደሆንን ይሰማናል። (ሉቃስ 11:4 የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።) ይሖዋ እኛ መክፈል የነበረብንን ዕዳ በመሰረዝ ኃጢአታችንን ይቅር እንደሚለን ስናውቅ ትልቅ እፎይታ ይሰማናል! ይሖዋ ኃጢአታችንን ‘እንደሚሸፍንልንና’ ‘እንደሚደመስስልን’ ስንማር፣ በሰሌዳ ላይ የተጻፈ ጽሑፍ በዳስተር ሙልጭ ብሎ እንደሚጠፋ ሁሉ ኃጢአታችንን እንደገና እንደማያስብብን እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል። (መዝሙር 32:1, 2፤ የሐዋርያት ሥራ 3:19) እንደ ዐለላ እና እንደ ደም ጎልቶ ይታይ የነበረውን ኃጢአታችንን ይሖዋ እንደ በረዶ ነጭ እንደሚያደርግልን ማወቃችን እንዴት የሚያጽናና ነው!—ኢሳይያስ 1:18
እስከ አሁን የተመለከትነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዘይቤያዊ አነጋገሮች መካከል ጥቂቶቹን ብቻ ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ ለዘይቤያዊ አነጋገሮች ልዩ ትኩረት ስጥ። በሁለት ተነጻጻሪ ሐሳቦች መካከል ያለውን ተመሳሳይነት ለይተህ ለማወቅ ጥረት አድርግ፤ እንዲሁም አሰላስልበት። እንዲህ ማድረግህ ስለ ቅዱሳን ጽሑፎች ያለህን ግንዛቤ የሚያሰፋልህ ከመሆኑም ሌላ አድናቆትህ እንዲጨምር ያደርጋል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.2 በዚህ ርዕስ ውስጥ “ዘይቤያዊ አነጋገር” የሚለው አገላለጽ ሁሉንም ዓይነት ምሳሌያዊ አነጋገሮችን የሚያመለክት ሲሆን ከእነዚህ መካከል ተለዋጭ ዘይቤ፣ አነጻጻሪ ዘይቤ ወይም ሌሎች የአጻጻፍ ስልቶች ይገኙበታል።
^ አን.6 በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል በተባለው (እንግሊዝኛ) ባለ ሁለት ጥራዝ የመጽሐፍ ቅዱስ ኢንሳይክሎፒዲያ ላይ የሚገኘው ሰፋ ያለ ማብራሪያ፣ ብዙ ጊዜ ሁለት ተነጻጻሪ ሐሳቦችን የሚያመሳስላቸው ነጥብ ምን እንደሆነ ለይተህ ለማወቅ ይረዳሃል።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ዘይቤያዊ አነጋገሮች ያላቸው ጥቅም
ዘይቤያዊ አነጋገሮች በርካታ ጥቅሞች አሏቸው። አስቸጋሪ የሆነ ሐሳብ በቀላሉ ልንረዳው ከምንችለው ነገር ጋር ሊነጻጸር ይችላል። የአንድን ጉዳይ የተለያዩ ገጽታዎች ግልጽ ለማድረግ ከአንድ በላይ ዘይቤያዊ አነጋገሮች ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ። ዘይቤያዊ አነጋገሮችን በመጠቀም በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነጥቦችን አጉልቶ ወይም ማራኪ አድርጎ ማቅረብ ይቻላል።
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የዘይቤያዊ አነጋገርን ሦስት ክፍሎች ለይቶ ማውጣት
ዘይቤያዊ አነጋገር፦ “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ።” (ማቴዎስ 5:13)
ርዕሰ ጉዳይ፦ እናንተ (የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት)
ምስል፦ ጨው
ተመሳሳይነት፦ አንድን ነገር ሳይበላሽ የማቆየት ችሎታ
የሚያስተላልፈው ትምህርት፦ ደቀ መዛሙርቱ ሕይወት አድን የሆነ መልእክት አላቸው።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
‘ይሖዋ እረኛዬ ነው፤ አንዳች አይጐድልብኝም።’—መዝሙር 23:1