የአካል ጉዳተኛ ብሆንም ደስተኛ ነኝ
የአካል ጉዳተኛ ብሆንም ደስተኛ ነኝ
ፖሌት ጋስፐር እንደተናገረችው
በተወለድኩበት ጊዜ ሦስት ኪሎ ገደማ እመዝን የነበረ ቢሆንም ሐኪሙ ከባድ የጤና እክል እንዳለብኝ ተረድቶ ነበር። ሐኪሞቹ እናቴን ሲያዋልዷት አንዳንድ አጥንቶቼ ተሰብረው ነበር። ይህ የሆነው ኦስቲኦጄነሲስ ኢምፐርፌክታ የተባለ አጥንት በቀላሉ እንዲሰበር የሚያደርግ በሽታ ስለነበረብኝ ነው። ሐኪሞቹ ወዲያውኑ ቀዶ ሕክምና ያደረጉልኝ ቢሆንም ትተርፋለች ብለው አላሰቡም። በ24 ሰዓት ውስጥ እንደምሞት ገምተው ነበር።
የአውስትራሊያ ዋና ከተማ በሆነችው በካንቤራ ሰኔ 14, 1972 ተወለድኩ። ሁሉም ሰው በዚያኑ ዕለት እንደምሞት አስቦ የነበረ ቢሆንም አልሞትኩም። ብዙም ሳይቆይ ግን የሳንባ ምች ያዘኝ። ሐኪሞቹ መሞቴ እንደማይቀር ስለተሰማቸው ምንም ዓይነት ሕክምና አላደረጉልኝም። የሚገርመው ግን በሕይወት መትረፍ ቻልኩ።
በወቅቱ የነበረው ሁኔታ ለወላጆቼ ምን ያህል ከባድ እንደነበረ መገመት ያዳግተኛል። የመትረፍ ተስፋዬ በጣም የተመናመነ ስለነበር የሕክምና ባለሙያዎቹ ለወላጆቼ በማሰብ ከእኔ ጋር በጣም እንዳይቀራረቡ መከሯቸው። በሆስፒታል ውስጥ በቆየሁባቸው የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ውስጥ በቀላሉ ልጎዳ ስለምችል ወላጆቼ እንዲነኩኝ እንኳ አልተፈቀደላቸውም ነበር። በኋላ ላይ ግን ሐኪሞቹ እንደማልሞት ሲያረጋግጡ የአካል ጉዳተኛ ለሆኑ ልጆች እንክብካቤ ወደሚደረግበት ተቋም እንዲያስገቡኝ ለወላጆቼ ሐሳብ አቀረቡላቸው።
ወላጆቼ ግን ወደ ቤታቸው ቢወስዱኝ እንደሚሻል ወሰኑ። እናቴ በዚያ ወቅት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምራ ነበር። የተማረችው ነገር እኔን የመንከባከብ ኃላፊነቷን ይበልጥ አክብዳ እንድትመለከተው አደረጋት። ይሁንና እኔን ለመንከባከብ የምታደርገው ጥረት ኃይሏን ስለሚያሟጥጥባትና ስሜቷን ስለሚደቁሰው ለእኔ ፍቅር ማሳየት ከባድ ሳይሆንባት አልቀረም። ወላጆቼ በተደጋጋሚ ጊዜያት ሆስፒታል ይወስዱኝ ነበር። ገላዬን እንደመታጠብ ያለ ቀላል ነገር አጥንቶቼ እንዲሰበሩ ያደርግ ነበር። ሌላው ቀርቶ ሳስነጥስ እንኳ አጥንቴ ሊሰነጠቅ ይችላል።
በመንፈስ ጭንቀት ተዋጥኩ
እያደግኩ ስሄድ የተሽከርካሪ ወንበር ጥገኛ ሆንኩ። ለመራመድ መሞከር ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነበር። እኔን ማሳደግ ብዙ ውጣ ውረድ ቢጠይቅም ወላጆቼ በሚያስደንቅ መንገድ ተንከባክበውኛል።
ከዚህም በላይ እናቴ አጽናኝ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ለእኔ ለማስተማር የተቻላትን ሁሉ ታደርግ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ወደፊት ምድርን ገነት እንደሚያደርጋትና ሁሉም ሰዎች በመንፈሳዊ፣ በአእምሯዊና በአካላዊ ሁኔታ ፍጹም ጤንነት እንደሚኖራቸው አስተምራኛለች። (መዝሙር 37:10, 11፤ ኢሳይያስ 33:24) ያም ሆኖ እናቴ፣ አምላክ እንዲህ ያለውን ጊዜ እስኪያመጣ ድረስ ደስተኛ ሕይወት መምራት እንደምችል ማሰብ እንደሚከብዳት በግልጽ ትነግረኝ ነበር።
መጀመሪያ ላይ ለአካል ጉዳተኞች የተዘጋጀ ትምህርት ቤት ገባሁ። መምህሮቼ ወደፊት ላከናውናቸው ስለምችላቸው ነገሮች ምንም ዓይነት ግብ አላወጡልኝም፤ እኔም ለራሴ ያወጣሁት ግብ አልነበረም። ለነገሩ ትምህርት ቤት የሚያጋጥሙኝን ሁኔታዎች መቋቋም በራሱ ፈታኝ ነበር። አብረውኝ የሚማሩት አብዛኞቹ ልጆች ይጨክኑብኝ ነበር። በኋላ ላይ ግን ጤነኛ የሆኑ ልጆች ወደሚማሩበት ትምህርት ቤት ገባሁ። ከሌሎች ልጆች ጋር ለመግባባት የማደርገው ጥረት ኃይሌን ያሟጥጠው እንዲሁም ስሜቴን ይጎዳው ነበር። ያም ሆኖ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ለመማር ቆርጬ ነበር።
በተለይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በነበርኩበት ወቅት አብረውኝ የሚማሩት ልጆች ሕይወታቸው ምን ያህል ባዶና ተስፋ ቢስ እንደሆነ አስብ ነበር። እናቴ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባስተማረችኝ ነገሮችም ላይ አሰላስል ነበር። የተማርኩት ነገር እውነት መሆኑን ባውቅም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ልቤን አልነካውም ነበር። ለተወሰነ ጊዜ ያህል፣ ስለ ነገ ምንም ሳልጨነቅ ጊዜዬን በመዝናናት ለማሳለፍ ወሰንኩ።
አሥራ ስምንት ዓመት ሲሞላኝ ከወላጆቼ ቤት ወጥቼ ከሌሎች የአካል ጉዳተኞች ጋር መኖር ጀመርኩ። እንዲህ ማድረጌ ቢያስደስተኝም በተወሰነ መጠን ፍርሃት አድሮብኝ ነበር። ነፃነት ማግኘቴ፣ ራሴን ችዬ መኖሬ፣ ጓደኞች ማፍራቴና ከእነሱ ጋር ጊዜ ማሳለፌ በጣም አስደስቶኝ ነበር። ከጓደኞቼ መካከል አብዛኞቹ ትዳር መሠረቱ። እኔም ለማግባትና የሚወደኝ ሰው ለማግኘት እጓጓ ነበር። ይሁን እንጂ ባለብኝ የጤና እክል የተነሳ የትዳር ጓደኛ የማግኘት አጋጣሚዬ በጣም የመነመነ ነበር። ይህንን እውነታ መገንዘቤ በሐዘን እንድዋጥ አደረገኝ።
ይሁንና ስላለሁበት ሁኔታ አምላክን አማርሬ አላውቅም። ስለ አምላክ በሚገባ ስለተማርኩ በምንም ዓይነት ፍትሕ የጎደለው ነገር ወይም በደል እንደማይፈጽም አውቅ ነበር። (ኢዮብ 34:10) ያሉብኝን ችግሮች ተቀብዬ ለመኖር ብጥርም በከባድ የመንፈስ ጭንቀት ተዋጥኩ።
ካደረብኝ የመንፈስ ጭንቀት ቀስ በቀስ ተላቀቅሁ
የሚያስደስተው ነገር፣ እናቴ ያለሁበትን ሁኔታ ስለተረዳች እኔ ባለሁበት አካባቢ ለሚኖር አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ስለ እኔ ነገረችው። ይህ ወንድም ስልክ ደወለልኝና በአካባቢዬ ባለው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በሚደረገው ክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ እንድገኝ ጋበዘኝ። ከዚህም በተጨማሪ በዚያ ጉባኤ ውስጥ የምትገኝ አንዲት እህት በየሳምንቱ መጽሐፍ ቅዱስ ታስጠናኝ ጀመር።
በጥናቴ እየገፋሁ ስሄድ እናቴ ከዓመታት በፊት ያስተማረችኝን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ማስታወስ ጀመርኩ፤ ይህም ለሕይወት ያለኝ አመለካከት እንዲስተካከል አደረገ። ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ጊዜ ማሳለፌም ያስደስተኝ ነበር። ይሁን እንጂ ሰዎች ስሜቴን እንዳይጎዱት ስለምፈራ የልቤን አውጥቼ አልናገርም ነበር። እንዲህ ያለው አመለካከት ለአምላክ ጥልቅ ፍቅር እንዳላዳብር እንቅፋት እንደሆነብኝ ይሰማኛል። ያም ቢሆን ሕይወቴን ለአምላክ መወሰን ተገቢ እርምጃ እንደሆነ አውቅ ነበር። ስለሆነም ታኅሣሥ 1991 በመጠመቅ ራሴን ለአምላክ መወሰኔን አሳየሁ።
ከዚያም የአካል ጉዳተኛ ከሆኑ ጓደኞቼ ጋር ከምኖርበት ቤት ወጥቼ በአንድ አፓርታማ ውስጥ ብቻዬን መኖር ጀመርኩ። ይህን በማድረጌ ብጠቀምም የተወሰኑ ችግሮችም አጋጥመውኛል። ለምሳሌ ያህል፣ ከፍተኛ የሆነ የብቸኝነት ስሜት ይሰማኝ ነበር። ከዚህም በላይ ወንዶች ቤቴን ሰብረው እንዳይገቡ እፈራ ነበር። ብዙም ሳይቆይ እንደገና በከባድ የመንፈስ ጭንቀት ተዋጥኩ። ሳቂታና ደስተኛ ብመስልም እውነታው ግን ከዚህ የራቀ ነበር። ልተማመንበት የምችል ጥሩ ወዳጅ ለማግኘት በጣም እፈልግ ነበር።
ከጊዜ በኋላ ይሖዋ አምላክ እንደዚህ ዓይነት ወዳጅ ሰጠኝ። የጉባኤያችን ሽማግሌዎች ሱዚ ከተባለች አንዲት ባለትዳር እህት ጋር ጥናቴን እንድቀጥል በደግነት ተነሳስተው ዝግጅት አደረጉ። ሱዚ አስተማሪዬ ብቻ ሳትሆን በጣም የምወዳት የቅርብ ወዳጄም ሆነች።
ሱዚ የተማርኩትን ነገር ከቤት ወደ ቤትም ሆነ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለሌሎች እንዳካፍል አሠለጠነችኝ። በዚህ ጊዜ ስለ አምላክ ባሕርያት ያለኝ ግንዛቤ ይበልጥ እያደገ መጣ። ይሁንና የተጠመቅኩ ክርስቲያን ብሆንም ለአምላክ ጥልቅ ፍቅር አላዳበርኩም ነበር። እንዲያውም በአንድ ወቅት ይሖዋን ማገልገሌን የማቆም ሐሳብ ነበረኝ።
ስሜቴን ለሱዚ ያካፈልኳት ሲሆን እሷም ይህንን ችግር እንድወጣው ረዳችኝ።በተጨማሪም ሱዚ፣ ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር ከሌላቸው ሰዎች ጋር ጊዜ ማሳለፌ ደስታ እንዲርቀኝ ከሚያደርጉኝ ምክንያቶች ዋነኛው መሆኑን እንዳስተውል ረዳችኝ። ስለዚህ በመንፈሳዊ ከጎለመሱ ሰዎች በተለይም ከአረጋውያን ጋር ወዳጅነት መመሥረት ጀመርኩ። ከእናቴ ጋር የነበረኝ ግንኙነትም ሻክሮ ነበር፤ በመሆኑም ከእሷም ሆነ ከወንድሜ ጋር እንደቀድሞው ጥሩ ግንኙነት ለመፍጠር ጥረት አደረግሁ። ከዚያ ቀደም ተሰምቶኝ የማያውቅ ደስታ እንዳገኘሁ ስገነዘብ በጣም ተገረምኩ። መንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ እንዲሁም ቤተሰቦቼ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ የብርታትና የደስታ ምንጭ ሆነውልኛል።—መዝሙር 28:7
አዲስ የሥራ መስክ
በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ፣ ብዙ ክርስቲያኖች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመሰማራታቸው ምን ያህል ደስተኞች እንደሆኑ ጎላ አድርጎ የሚገልጽ ንግግር ቀርቦ ነበር፤ ከስብሰባው በኋላ እኔም ‘በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መሰማራት እችላለሁ!’ ብዬ አሰብኩ። በእርግጥ ካለብኝ የጤና ችግር አንጻር ይህንን ማድረግ ከባድ ሊሆን እንደሚችል አውቅ ነበር። ያም ሆኖ ጉዳዩን በጸሎት ካሰብኩበት በኋላ ሙሉ ጊዜዬን መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማር ለማሳለፍ ወሰንኩ፤ ከዚያም ሚያዝያ 1998 በዚህ የሥራ መስክ መካፈል ጀመርኩ።
ከባድ የጤና እክል እያለብኝም በስብከቱ ሥራ የምካፈለው እንዴት ነው? በተፈጥሮዬ የሌሎች ጥገኛ መሆን አልወድም፤ መጓጓዣንና ሌሎች ነገሮችን ጨምሮ በምንም መንገድ በሰዎች ላይ ሸክም መሆን አልፈልግም። በመሆኑም ሱዚና ባለቤቷ ማይክል፣ ሞተር ብስክሌት እንድገዛ ሐሳብ አቀረቡልኝ። ይሁን እንጂ ሞተር ብስክሌቱን እንዴት ልነዳው ነው? በሥዕሉ ላይ እንደሚታየው ሞተር ብስክሌቱ ለእኔ ተብሎ በልዩ ትእዛዝ የተሠራ ነው። ከተሽከርካሪ ወንበሬ ላይ መነሳት ሳያስፈልገኝ ሞተር ብስክሌቱን መንዳት እችላለሁ! ክብደቴ 19 ኪሎ ነው።
በዚህ ሞተር ብስክሌት መጠቀሜ የሌሎች እርዳታ ሳያስፈልገኝ ለመንቀሳቀስ ስላስቻለኝ ሰዎችን ሄጄ ማነጋገር እንዲሁም ለሰዎቹም ሆነ ለእኔ አመቺ በሆነ ሰዓት ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ማስጠናት ችያለሁ። ሞተር ብስክሌቴን መንዳት በጣም ያስደስተኛል፤ ነፋሱ ፊቴን እየገረፈው በብስክሌቱ መጓዝ በሕይወቴ ደስታ ከሚሰጡኝ ነገሮች አንዱ ነው!
መንገድ ላይ ከሰዎች ጋር ውይይት መጀመር ያስደስተኛል፤ ደግሞም አብዛኞቹ ሰዎች በትሕትናና በአክብሮት ያነጋግሩኛል። ሌሎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲማሩ መርዳት ደስታ ይሰጠኛል። በአንድ ወቅት ከአንድ ረጅም ወንድም ጋር ከቤት ወደ ቤት ሳገለግል ያጋጠመኝን የሚያስቅ ሁኔታ አልረሳውም። ወንድም የቤቱን ባለቤት ሰላም እያላት እያለ ሴትየዋ እኔን በመገረም ትኩር ብላ ከተመለከተችኝ በኋላ “መናገር ትችላለች?” በማለት ጠየቀችው። በዚህ ጊዜ ሁለታችንም ሳቃችንን ለቀቅነው። ከዚያም ለሴትየዋ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ስነግራት በእርግጥም መናገር እንደምችል ተረዳች!
አሁን በሕይወቴ ደስተኛ ከመሆኔም ሌላ ለይሖዋ አምላክ ፍቅር ማዳበር ችያለሁ። እናቴ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ስላስተማረችኝ በጣም አመሰግናታለሁ፤ እንዲሁም አምላክ የእኔን ትንሽ ሰውነት ጨምሮ ‘ሁሉንም ነገር አዲስ የሚያደርግበትን’ ጊዜ በሙሉ እምነት እጠባበቃለሁ።—ራእይ 21:4, 5
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ያሉብኝን ችግሮች ተቀብዬ ለመኖር ብጥርም በከባድ የመንፈስ ጭንቀት ተዋጥኩ”