4 ጥርጣሬህን ለማስወገድ ጥረት አድርግ
4 ጥርጣሬህን ለማስወገድ ጥረት አድርግ
“አንተ እምነት የጎደለህ፣ ለምን ተጠራጠርክ?”—ማቴዎስ 14:31
እንቅፋት የሚሆነው ነገር ምንድን ነው? የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንኳ የተጠራጠሩባቸው ጊዜያት ነበሩ። (ማቴዎስ 14:30፤ ሉቃስ 24:36-39፤ ዮሐንስ 20:24, 25) እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ እምነት ማጣትን ‘በቀላሉ ተብትቦ የሚይዘን ኃጢአት’ ሲል ገልጾታል። (ዕብራውያን 12:1) ሐዋርያው ጳውሎስም “እምነት ሁሉም ሰው የሚኖረው ነገር [እንዳልሆነ]” ተናግሯል። (2 ተሰሎንቄ 3:2) ጳውሎስ ይህን ሲል አንዳንዶች እምነትን በተግባር ሊያሳዩ አይችሉም ማለቱ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ብዙዎች እምነት እንዲኖራቸው ጥረት አያደርጉም ማለቱ ነበር። አምላክ እምነት እንዲኖራቸው ጥረት የሚያደርጉ ሰዎችን ይባርካል።
እንቅፋቱን እንዴት ልትወጣው ትችላለህ? እንድትጠራጠር የሚያደርጉህን ጉዳዮች ለይተህ እወቅ። ለምሳሌ ያህል፣ ደቀ መዝሙሩ ቶማስ ሌሎቹ ዮሐንስ 20:24-29
ኢየሱስን እንዳዩት ቢናገሩም እንኳ እሱ ኢየሱስ ትንሣኤ ማግኘቱን ተጠራጥሮ ነበር። ቶማስ ማስረጃ ማግኘት ፈልጎ ነበር። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ኢየሱስ፣ ቶማስ ጠንካራ እምነት እንዲኖረው የሚያስችለውን ማስረጃ ሰጠው።—ይሖዋ አምላክ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ጥርጣሬያችንን እንድናስወግድ የሚረዱን መልሶች ይሰጠናል። ለምሳሌ ያህል፣ ብዙዎች የሰውን ዘር ለሚያሠቃየው ጦርነት፣ ዓመፅና መከራ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አምላክ ተጠያቂ እንደሆነ ስለሚሰማቸው በእሱ ላይ ያላቸውን እምነት ያጣሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በሚመለከት ምን ይላል?
አምላክ በሰብዓዊ መንግሥታት አማካኝነት ምድርን እየገዛ አይደለም። ኢየሱስ፣ ሰይጣን የተባለውን በዓይን የማይታይ መንፈሳዊ ፍጡር “የዚህ ዓለም ገዥ” ሲል ጠርቶታል። (ዮሐንስ 14:30) ሰይጣን፣ ኢየሱስ አንዴ በፊቱ ተደፍቶ ቢያመልከው በመንግሥታት ሁሉ ላይ ሥልጣን እንደሚሰጠው የሚከተለውን በማለት ግብዣ አቅርቦለት ነበር፦ “ይህን ሁሉ ሥልጣንና የእነዚህን መንግሥታት ክብር ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ይህ ሁሉ ለእኔ ስለተሰጠ እኔ ደግሞ ለፈለግሁት እሰጠዋለሁ።” ኢየሱስ፣ ሰይጣን በመንግሥታት ላይ ሥልጣን እንዳለው አልካደም። ከዚህ ይልቅ “‘ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ፤ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ’ ተብሎ ተጽፏል” ሲል መለሰለት። (ሉቃስ 4:5-8) በዓለም ላይ ለሚደርሰው ሥቃይና መከራ ተጠያቂው አምላክ ሳይሆን ሰይጣንና ሰብዓዊ መንግሥታት ናቸው።—ራእይ 12:9, 12
በቅርቡ ይሖዋ አምላክ ለመከራ መንስኤ የሆኑትን ነገሮች ሁሉ ያስወግዳል። አምላክ የሰውን ዘር ለመግዛት በልጁ በክርስቶስ ኢየሱስ የሚመራ መንግሥት አቋቁሟል። (ማቴዎስ 6:9, 10፤ 1 ቆሮንቶስ 15:20-28) መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ በተነበየው መሠረት በአሁኑ ጊዜ የዚህ መንግሥት ምሥራች በመላው ምድር እየተሰበከ ነው። (ማቴዎስ 24:14) በቅርቡ ይህ መንግሥት ተቃዋሚዎቹን ሁሉ የሚያጠፋ ከመሆኑም በላይ ለሰው ልጆች ሥቃይ መንስኤ የሆኑትን ነገሮች ያስወግዳል።—ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 25:31-33, 46፤ ራእይ 21:3, 4
ምን በረከት ያስገኛል? ጥርጣሬያቸውን ለማስወገድ ጥረት የማያደርጉ ሰዎች ‘በማንኛውም የትምህርት ነፋስና በሰዎች የማታለያ ዘዴ’ ወዲያና ወዲህ እንደሚል ማዕበል ናቸው። (ኤፌሶን 4:14፤ 2 ጴጥሮስ 2:1) ለጥያቄዎቻቸው አጥጋቢ መልስ የሚያገኙ ሰዎች ግን ‘በእምነት ጸንተው መቆም’ ይችላሉ።—1 ቆሮንቶስ 16:13
የዚህ መጽሔት አዘጋጆች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች፣ እምነት እንዳታዳብር እንቅፋት ለሆኑብህ ጥያቄዎች መልስ እንድታገኝ አንተን ለመርዳት ፈቃደኞች ናቸው። ከእነሱ ጋር ተቀራርበህ ትምህርቶቻቸውን አንተው ራስህ እንድትመረምር ይጋብዙሃል። እንዲህ ማድረግህ በአምላክ ላይ ያለህን እምነት በእጅጉ ያጠናክርልሃል።
ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? * ከተባለው መጽሐፍ ላይ “የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?” የሚለውን ምዕራፍ 8ን እና “አምላክ በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው ለምንድን ነው?” የሚለውን ምዕራፍ 11ን ተመልከት።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.10 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለጥያቄዎቻቸው አጥጋቢ መልስ የሚያገኙ ሰዎች ጠንካራ መሠረት ያለው እምነት ይኖራቸዋል