በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሕይወታችን ውስጥ መከራ የሚደርስብን አምላክ እየቀጣን ስለሆነ ነው?

በሕይወታችን ውስጥ መከራ የሚደርስብን አምላክ እየቀጣን ስለሆነ ነው?

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ

በሕይወታችን ውስጥ መከራ የሚደርስብን አምላክ እየቀጣን ስለሆነ ነው?

በሕይወትህ ውስጥ ያጋጠመህ አንድ አሳዛኝ ሁኔታ ‘አምላክ መከራ እንዲደርስብኝ ፈልጎ ይሆናል’ ብለህ እንድታስብ አድርጎሃል? ድንገተኛ ሕመም ሲያጋጥመን ወይም ከባድ የአካል ጉዳት የሚያስከትል አደጋ ሲደርስብን አሊያም ከቤተሰባችን አንዱ ያለ ዕድሜው በሞት ሲቀጭ አምላክ ከሌሎች በተለየ እኛን እየቀጣን እንዳለ ሊሰማን ይችላል።

ከዚህ በተቃራኒ፣ አምላክ ሰዎች እንዲደሰቱ እንጂ ጉዳት እንዲደርስባቸው የማይፈልግ በመሆኑ ልትጽናና ይገባሃል። አምላክ የመጀመሪያዎቹን ሰዎች በፈጠረበት ጊዜ ይህ እውነት መሆኑ ታይቷል፤ እነዚህ ባልና ሚስት ከማንኛውም ዓይነት መከራ ነፃ የሆነ ሕይወት እንዲመሩ ውብ በሆነች ገነት ውስጥ ይኸውም “በዔድን የአትክልት ስፍራ” እንዲኖሩ አድርጎ ነበር።—ዘፍጥረት 2:15

የሚያሳዝነው ግን የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ይህን የመሰለውን ግሩም ተስፋ አሽቀንጥረው በመጣል ሆነ ብለው የአምላክን ትእዛዝ ጣሱ። በዚህም ምክንያት እነሱ ብቻ ሳይሆኑ እኛን ጨምሮ ዘሮቻቸው በሙሉ ለመከራ ተዳረጉ። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ሁኔታውን አንድ የቤተሰብ ራስ የቤት ኪራይ ለመክፈል የገባውን ውል ለመፈጸም ፈቃደኛ ባይሆን ከሚከሰተው ነገር ጋር ማመሳሰል ይቻላል፤ በዚህ ወቅት መላው ቤተሰብ ከመኖሪያ ቤቱ ስለሚባረር ለችግርና ለእጦት ይጋለጣል። በተመሳሳይም የመጀመሪያው ዓመጽ ከተፈጸመበት ጊዜ አንስቶ ሁሉም የሰው ዘር ለመከራ ተዳርጓል። (ሮም 5:12) አዳምና ሔዋን ካመጹ ከብዙ ዓመታት በኋላ የኖረው ጻድቁ ኢዮብ በወቅቱ ያጋጠመውን ሁኔታ በተመለከተ ሲናገር ‘ሐዘኑና መከራው ሚዛን ላይ ቢቀመጥ ኖሮ ከባሕር አሸዋ ይልቅ እንደሚከብድ’ በምሬት ገልጿል።—ኢዮብ 6:2, 3

መከራ እንዲደርስብን ምክንያት የሚሆነው ሌላው ነገር ወደፊት የሚከሰቱ ነገሮችን አሻግረን የማየት ችሎታችን ውስን መሆኑ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ድርጅት ቤቶችን ሠርቶ እየሸጠ ነው እንበል፤ ሆኖም ቤቶቹ የተገነቡት ብዙ ጊዜ ሰደድ እሳት በሚነሳበት አካባቢ ነው። አንተም ይህን ሁኔታ ባለማወቅ ከእነዚህ ቤቶች ውስጥ አንዱን ገዝተህ እዚህ አካባቢ መኖር ጀመርክ። ይህ ውሳኔህ አንተም ሆንክ ቤተሰብህ ለአስከፊ መከራ እንድትጋለጡ የሚያደርግ አይሆንም? ይህን ቤት በመግዛትህ ምክንያት የሚደርስብህን ማንኛውንም መከራ ከአምላክ የመጣ ቅጣት እንደሆነ አድርገህ ማሰቡ ምክንያታዊ ይሆናል? መጽሐፍ ቅዱስ እውነታውን እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “ተላላ ሰው ሁሉን ያምናል፤ አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል።”—ምሳሌ 14:15

አሁን ሁላችንም መከራና ሥቃይ የሚደርስብን ቢሆንም አምላክ በቅርቡ ሰዎችን ከመከራ ለመገላገል ዓላማ እንዳለው ማወቁ በጣም የሚያጽናና ነው። ይህ ጊዜ ሲመጣ በራስህም ሆነ በሌሎች ላይ መከራ ሲደርስ አታይም፤ ሌላው ቀርቶ ስለ መከራ ወሬውን እንኳ አትሰማም። ሐዘን፣ ሥቃይ፣ ሞትና ለቅሶ ‘ያለፉ’ ነገሮች ይሆናሉ። (ራእይ 21:4) ሰዎች የሠሩት ቤትና ሠብላቸው በጦርነት ወይም በተፈጥሮ አደጋ ፈጽሞ እንደማይጠፋ የሚናገረው ተስፋም በጣም የሚያስደስት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰዎች በእጃቸው ሥራ “ለረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋል” በማለት ይናገራል።—ኢሳይያስ 65:21-25

አምላክ መከራን ሙሉ በሙሉ የሚያስወግድበት ጊዜ እስኪመጣ ድረስ ግን በአሁኑ ጊዜ የሚያጋጥምህ መከራ የሚያስከትልብህን ችግር መቀነስ የምትችለው እንዴት ነው? የመጀመሪያውና ዋነኛው ነገር ‘በራስህ ማስተዋል አለመደገፍ’ ነው፤ ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን” በማለት ይመክረናል። (ምሳሌ 3:5) የይሖዋን መመሪያና ማጽናኛ ለማግኘት ጥረት አድርግ። እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን አምላካዊ ጥበብ በትኩረት አዳምጥ። እንዲህ ማድረግህ ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ እንድታደርግ የሚረዳህ ከመሆኑም ሌላ ልታስቀራቸው ከምትችላቸው መከራዎች ይጠብቅሃል።—ምሳሌ 22:3