ወደ “ምድር ጫፍ” ያደረግነው ጉዞ
ከሩሲያ የተላከ ደብዳቤ
ወደ “ምድር ጫፍ” ያደረግነው ጉዞ
ትንሿ አውሮፕላናችን ከያኩትስክ ተነስታ ቀስ በቀስ ወደ ላይ ከፍ እያለች ስትሄድ ቱይማዳ ሸለቆን ቁልቁል መመልከት ጀመርን። የተለያየ ቅርጽና ስፋት ያላቸውን ወደ በረዶነት የተለወጡ በርካታ ሐይቆች ካለፍን በኋላ የፀሐይ ብርሃን ሲያርፍባቸው በሚያንፀባርቁት በበረዶ የተሸፈኑ ቬርኮያንስኪ የተባሉ የተራራ ሰንሰለቶች ላይ መብረር ጀመርን። ዘጠኝ መቶ ኪሎ ሜትር ከተጓዝን በኋላ በመጨረሻ ዴፑታትስኪ በምትባል መንደር አረፍን።
ከመላው ምዕራብ አውሮፓ የሚበልጥ የቆዳ ስፋት ወዳላት ወደ ሳካ ሪፑብሊክ ካደረግኋቸው ጉዞዎች ይህ የመጀመሪያው ነበር፤ ሳካ ሪፑብሊክ፣ ያኪውሻ ተብላም የምትጠራ ሲሆን መልክዓ ምድሯ ውብ ሆኖም አስቸጋሪ ነው። ይህ አካባቢ በሞቃቱ ወራት ሙቀቱ እስከ 40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሚደርስ ሲሆን በቀዝቃዛው ወራት ደግሞ ቅዝቃዜው ከዜሮ በታች እስከ 70 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይደርሳል። በተጨማሪም በዚህ ቦታ ዝርያቸው ከረዥም ጊዜ በፊት ከምድር ገጽ የጠፋ እጅግ ብዙ እንስሳት ቅሪተ አካላትን ማየት የተለመደ ነው። ለመጨረሻ ጊዜ ወደዚህ አካባቢ ከሄድኩ በርካታ ዓመታት ቢያልፉም ያየኋቸው ነገሮች የትናንት ያህል ትዝ ይሉኛል፤ ጥቅጥቅ ባለ ጉም የተሸፈኑትን ትንንሽ ከተሞች፣ የሰሜኑን ውጋገን እንዲሁም ደስተኛ የሆኑትንና ችግር የማይበግራቸውን የአካባቢው ሰዎች በደንብ አስታውሳቸዋለሁ።
የጉዟችን መጨረሻ ዴፑታትስኪ አልነበርም። እኔና የጉዞ ጓደኛዬ ልንሄድባቸው ያሰብናቸው ሌሎች መንደሮችም ነበሩ። የመጀመሪያዋ ካይር ስትሆን በስተ ሰሜን በኩል 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሰሜን ሳይቤሪያ ውስጥ ላፕቲፍ በሚባለው ባሕር አጠገብ ትገኛለች። ይህን ጉዞ ለማድረግ የወሰንነው ለምን ነበር? ቀደም ሲል አንዲት የይሖዋ ምሥክር ወደ እነዚህ መንደሮች ሄዳ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ መማር የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች አግኝታ ነበር። እነዚህ መንደሮች እኛ ከምንኖርበት ከያኩትስክ 1,000 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ ቢሆንም ሰዎቹን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለማስተማር ቅርብ የሆንነው እኛ ብቻ ነበርን! እነዚህ ሰዎች ማበረታቻና እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተሰማን።
ዴፑታትስኪ ስንደርስ በመኪና ወደ ካይር እየሄደ የነበረ አንድ ሰው አገኘንና በአነስተኛ ክፍያ ወደዚያ ሊወስደን እንደሚችል ሐሳብ አቀረበልን። በሶቪየት ኅብረት ዘመን የተሠራችውን ክርክስ ያለችውን መኪና ስናያት ከእሱ ጋር ለመሄድ ትንሽ አቅማምተን ነበር። ይሁንና አጋጣሚውን ለመጠቀም ስለፈለግን በዚያ ምሽት ከእሱ ጋር ጉዞ ጀመርን። ምን እንደሚያጋጥመን የምናውቀው ነገር አልነበረም።
በመኪናዋ ውስጥ ያሉት መቀመጫዎች በውጭ እንዳለው ግግር በረዶ እጅግ ቀዝቃዛ ስለነበሩ መቼም እንደማይሞቁ ለመገንዘብ ጊዜ አልፈጀብንም። መኪናው እንዲቆምልን ከጠየቅን በኋላ የሚሞቁ የሱፍ ልብሶችን ከሻንጣችን ውስጥ በርብረን በማውጣት ደርበን ለበስናቸው። ይሁን እንጂ ብርዱ ሊለቀን አልቻለም።
የጉዞ ልምድ ያለውና የሰሜን ሰው የሆነው ሾፌራችን እኛን ለማጫወት የተቻለውን ጥረት ያደርግ ነበር። በድንገት
“የሰሜንን ውጋገን አይታችሁ ታውቃላችሁ?” ብሎ ጠየቀን። እኔ አይቼ ስለማላውቅ መኪናዋን አቆማት፤ በብርድ ተቆራምደን የነበረ ቢሆንም እንደምንም ብለን ከመኪናዋ ወረድን። ለአንድ አፍታ ሁሉም ነገር ተረሳ። ከፊት ለፊታችን በኅብረ ቀለማት ያሸበረቀው ብርሃን እንደ መጋረጃ ሲሰበሰብና ሲዘረጋ የሚፈጥረውን ልዩ ትዕይንት ስመለከት በአድናቆት ፍዝዝ ብዬ ቀረሁ። የብርሃኑ ርቀት እጃችንን ብንዘረጋ የምንነካው ይመስል ነበር።ማለዳ ገና ጎሕ ሳይቀድ በበረዶው ላይ እየተጓዝን ሳለ የመኪናዋ ጎማ በረዶ ውስጥ ተቀረቀረ። ሾፌሩን ረድተነው መኪናዋን እንደ ምንም አወጣናት፤ በበረዶ ሙሉ በሙሉ በተሸፈነው መንገድ ላይ እየነዳን ወደ ካይር ጉዟችንን ስንቀጥል እንዲህ ያለው አስቸጋሪ ሁኔታ በተደጋጋሚ ጊዜ አጋጥሞን ነበር። “መንገዶቹ” ወደ በረዶነት የተቀየሩ ወንዞች እንደሆኑ ያወቅሁት ረፋዱ ላይ ነበር! ከዴፑታትስኪ ከተነሳን ከ16 ሰዓት በኋላ እኩለ ቀን ላይ ካይር ደረስን። ለረዥም ሰዓታት ብርድ ላይ ስለቆየን እንታመማለን ብለን ፈርተን የነበረ ቢሆንም በማግስቱ ጠዋት ኃይላችን ታድሶ ተነሳን። ጣቶቼ ብቻ ትንሽ እንደ መደንዘዝ ብለው ነበር። የመንደሩ ሰዎች ጣቶቼን እንድቀባቸው ከድብ ሞራ የተሠራ ቅባት ሰጡኝ።
ለሰዎች ምሥራቹን ለመንገር ቤታቸው መሄዳችን የተለመደ ነገር ነው። በካይር ግን የተለየ ሁኔታ አጋጠመን። የመንደሩ ነዋሪዎች መምጣታችንን እንደሰሙ ሊያነጋግሩን ያረፍንበት ቦታ ድረስ መጡ! እዚያ በቆየንባቸው ሁለት ሳምንት ተኩል ጊዜያት በየዕለቱ የአካባቢውን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናን ሲሆን ከማለዳ አንስተን በጣም እስኪመሽ ድረስ የቆየንባቸው ቀናት ነበሩ። መንፈሳዊ ነገሮችን የማወቅ ጉጉት ያላቸው እንዲሁም ሰው ወዳድና እንግዳ ተቀባይ የሆኑ በርካታ ሰዎች ማግኘት እጅግ አስደሳች ነበር። አረጋውያን የሆኑ በርካታ የያኩት ሴቶች “በአምላክ እናምናለን። የምድር ጫፍ ወደሆነው ወደዚህ ቦታ መምጣታችሁ ብቻ እንኳ አምላክ እንዳለ ያሳያል!” ብለውናል።
የአካባቢው ባሕልም አስገርሞናል። ለምሳሌ ያህል፣ ሰዎች የበረዶ ግግሮችን በቤታቸው አጠገብ ይከምራሉ። ውኃ ሲፈልጉ አንዱን ግግር ያነሱና እንዲሟሟ እሳት ላይ በተጣደ ትልቅ ማንቆርቆሪያ ውስጥ ይከቱታል። የመንደሩ ነዋሪዎች ቺር ተብሎ ከሚጠራ ግሩም የአርክቲክ ዓሣ የሚዘጋጅ ስትሮጋኒና በመባል የሚታወቅ ምርጥ ምግብ አዘጋጅተው ጋብዘውን ነበር። ዓሣው ወዲያው እንደተጠመደ በረዶ ውስጥ ይከቱታል፤ ከዚያ በኋላ በስሱ ተከትፎ ከጨውና ከበርበሬ በተዘጋጀ ማባያ ውስጥ እየተጠቀሰ ይበላል። የመንደሩ ነዋሪዎች፣ በአካባቢው በብዛት ስለሚገኙት የጥንት የዝሆን ዝርያ ጥርሶች ቅሪተ አካላትና ወደ ቅሪተ አካልነት ስለ ተቀየሩ ዛፎች ለእኛ መንገር ያስደስታቸው ነበር።
በያኪውሻ በሚገኙ ሌሎች መንደሮች ውስጥ የሚኖሩ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የማወቅ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ለማነጋገር ከካይር ተነስቼ በመቶ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች የተጓዝኩ ሲሆን አብዛኛውን ጉዞዬን ያደረግኩት በአውሮፕላን ነው። በእነዚህ መንደሮች ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች ተግባቢና ሰው ወዳዶች ናቸው! በአንድ ወቅት የተዋወቅኩት ትንሽ ልጅ በአውሮፕላን መሄድ እንደሚያስፈራኝ ተገነዘበ። ልጁ እኔን ለማበረታታት አንድ ካርድ አዘጋጅቶ ሰጠኝ። በካርዱ ላይ ሁለት ድንቢጦችንና አንድ ትንሽ አውሮፕላን ሥሎ “ሳሻ፣ በአውሮፕላን ስትሄድ እወድቃለሁ ብለህ አትፍራ። ማቴዎስ 10:29” የሚል ሐሳብ ጽፎበታል። ጥቅሱን አውጥቼ ሳነበው ልቤ በጥልቅ ተነካ! በዚህ ጥቅስ ላይ ኢየሱስ “አንዷም እንኳ አባታችሁ ሳያውቅ መሬት ላይ አትወድቅም” በማለት ስለ ድንቢጦች የተናገረው ሐሳብ ይገኛል።
የተረክሁላችሁ በያኪውሻ ካጋጠሙኝ ብዙ አስደናቂ ነገሮች ጥቂቱን ብቻ ነው። ያ ቀዝቃዛና አስቸጋሪ ምድር በእርግጥም ‘በምድር ጫፍ’ የሚኖሩትን እነዚያን ተግባቢና ተወዳጅ ሰዎች ሲያስታውሰኝ ይኖራል።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የያኩት ሕዝብ ተግባቢና እንግዳ ተቀባይ ነው