አስደናቂ የሆነውን ማተሚያ ቤታችንን እንድትጎበኝ ተጋብዘሃል
አስደናቂ የሆነውን ማተሚያ ቤታችንን እንድትጎበኝ ተጋብዘሃል
አሁን እያነበብክ ያለኸውን መጽሔት የሚመስሉ ሌሎች መጽሔቶችን ከዚህ በፊት አይተህ ታውቅ ይሆናል። ምናልባትም የይሖዋ ምሥክሮች ቤትህ መጥተው መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ እንድትረዳ የሚያስችሉህን መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! የተባሉትን መጽሔቶች ሰጥተውህ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ በመንገድ ላይ አሊያም በገበያ ቦታ መጽሔቶቹን ለሰዎች ሲሰጡ ተመልክተህ ይሆናል። የሚገርምህ ነገር፣ የያዝከው መጽሔት በየወሩ ከ35 ሚሊዮን ቅጂዎች በላይ የሚሰራጭ በመሆኑ በዓለም ላይ የዚህን መጽሔት ያህል ሰፊ ስርጭት ያለው ሃይማኖታዊ ጽሑፍ የለም።
ይሁንና እነዚህ ሁሉ መጽሔቶች የሚታተሙት የትና እንዴት እንደሆነ ጠይቀህ ታውቃለህ? ለዚህ ጥያቄህ መልስ እንድታገኝ የይሖዋ ምሥክሮች በተለያዩ አገሮች ውስጥ ካሏቸው በርካታ ማተሚያ ቤቶች ውስጥ አንዱን ብቻ ይኸውም በዎልኪል፣ ኒው ዮርክ የሚገኘውን ማተሚያ ቤት እናስጎብኝህ። በዓለም ዙሪያ የሚገኙት አብዛኞቹ አንባቢዎቻችን በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች ማተሚያ ቤት ለመጎብኘት በቀላሉ መምጣት ስለማይችሉ፣ በቃላትና በፎቶግራፎች አማካኝነት የሚደረግልህ ይህ ጉብኝት ስለ ማተሚያ ቤታችን ይበልጥ እንድታውቅ እንደሚረዳህ እንተማመናለን።
የሕትመት ሥራ ከመጀመሩ በፊት ጽሑፉ መዘጋጀት እንዳለበት የታወቀ ነው። በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ የሚገኘው የጽሑፍ ዝግጅት ክፍል፣ ለሕትመት ዝግጁ የሆነውን ጽሑፍ በኤሌክትሮኒክ ፋይል መልክ ዎልኪል ለሚገኘው ግራፊክስ ክፍል ይልከዋል። ይህ ፋይል ለሕትመት የሚያገለግል ፕሌት (ጽሑፉንና ሥዕሉን የያዘ ስስ ብረት ነው) ለማዘጋጀት ይውላል። በየወሩ 1,400 ገደማ የወረቀት ጥቅልሎች በዎልኪል በሚገኘው ማተሚያ ቤት የሚራገፉ ሲሆን ይህ ማተሚያ ቤት በአንድ ቀን ብቻ ከ80 ሺህ እስከ 100 ሺህ ኩንታል ወረቀት ይጠቀማል። የወረቀት ጥቅልሎቹ (አንዳንዶቹ ከ1,300 ኪሎ ግራም በላይ ይመዝናሉ) ጽሑፉንና ሥዕሎቹን የያዙት ፕሌቶች በታሠሩባቸው አምስት ትላልቅ ማተሚያ ማሽኖች ውስጥ እንዲያልፉ ይደረጋል። ከዚያም በወረቀቱ ላይ ጽሑፉ ይታተምበታል፣ ቀጥሎም እየተቆረጠ ይተጣጠፋል፤ ተቆርጦ የተጣጠፈው እያንዳንዱ ወረቀት 32 ገጾችን የያዘ ነው። ለምሳሌ፣ እያነበብክ ያለኸው መጽሔት ገጾች በሙሉ በአንድ ወረቀት ላይ የታተሙ ናቸው። መጻሕፍትስ የሚዘጋጁት እንዴት ነው? እያንዳንዳቸው 32 ገጾችን የያዙትና የተጣጠፉት ወረቀቶች በመጠረዣ ክፍል ውስጥ አንድ ላይ ይጠረዛሉ። ካሉን ሁለት መጠረዣ ማሽኖች አንዱ በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ 50,000 ጠንካራ ሽፋን ያላቸውን ወይም 75,000 ለስላሳ ሽፋን ያላቸውን መጻሕፍት መጠረዝ ይችላል። ሌላኛው መጠረዣ ማሽን ደግሞ በቀን ወደ 100,000 የሚደርሱ ለስላሳ ሽፋን ያላቸውን መጻሕፍት መጠረዝ ይችላል።
በ2008 በዚህ ማተሚያ ቤት ከ28 ሚሊዮን በላይ መጻሕፍት የታተሙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 2.6 ሚሊዮን የሚሆኑት መጽሐፍ ቅዱሶች ናቸው። በዚሁ ዓመት 243,317,564 የሚያህሉ መጽሔቶች ታትመዋል። በዚህ ማተሚያ ቤት ውስጥ እነዚህን የመሰሉ በ380 ቋንቋዎች የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማግኘት ይቻላል። ጽሑፎች ከተዘጋጁ በኋላ ያለው ሥራስ ምንድን ነው?
ማተሚያ ቤቱ፣ በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኙ 12,754 የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች እንዲሁም በካሪቢያን ደሴቶችና በሃዋይ ከሚገኙ 1,369 ጉባኤዎች የጽሑፍ ትእዛዝ ይደርሰዋል። የጽሑፍ መላኪያ ክፍሉ፣ የተጠየቁትን ጽሑፎች
በሙሉ በትእዛዞቹ መሠረት አሰናድቶ ካሸገ በኋላ በየአድራሻቸው የሚላኩበትን መንገድ ያዘጋጃል። በየወሩ 14 ሚሊዮን ኪሎ ግራም ገደማ የሚመዝኑ ጽሑፎች በዩናይትድ ስቴትስ ወደሚገኙ ጉባኤዎች ይላካሉ።የዚህ ማተሚያ ቤት በጣም አስፈላጊ ክፍል ማሽኖቹ ሳይሆኑ በዚያ የሚሠሩት ሰዎች ናቸው። በማተሚያ ቤቱ ሥር ባሉት የግራፊክስ፣ የፕሮግራም ማውጫ፣ የማተሚያ፣ የመጠረዣና የጽሑፍ መላኪያ ክፍሎች ውስጥ የሚሠሩ ከ300 በላይ የሚሆኑ ሠራተኞች አሉ። ሁሉም ደሞዝ የማይከፈላቸው ፈቃደኛ ሠራተኞች ሲሆኑ ከ19 እስከ 92 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ይገኛሉ።
እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች ለሰዎች ከልብ ያስባሉ፤ ምክንያቱም ጽሑፎቹን በጉጉት የሚቀበሉት ግለሰቦች በጽሑፎቹ ውስጥ ከሠፈሩት የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ትምህርትና ማበረታቻ እንደሚያገኙ አልፎ ተርፎም ሕይወታቸውን ለመምራት እንደሚጠቀሙባቸው ያውቃሉ። አንተም ከእነዚህ አንባቢያን አንዱ እንደሆንክና በዎልኪልም ሆነ በሌሎች አገሮች በሚገኙ ማተሚያ ቤቶቻችን የሚታተሙት ጽሑፎች፣ ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገረውን የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ እውቀት መቅሰምህን እንድትቀጥል እንደሚረዱህ ተስፋ እናደርጋለን።—ዮሐንስ 17:3
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]