በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትክክል የሆነውን ነገር ከማድረግ ወደኋላ የማይል ዳኛ

ትክክል የሆነውን ነገር ከማድረግ ወደኋላ የማይል ዳኛ

ወደ አምላክ ቅረብ

ትክክል የሆነውን ነገር ከማድረግ ወደኋላ የማይል ዳኛ

ዘኍልቍ 20:2-13

ሰብዓዊ ዳኞች ፍትሕ የጎደለው ፍርድ ሊሰጡ አሊያም ከመጠን ያለፈ ቅጣት ሊበይኑ ይችላሉ፤ ‘ፍትሕን የሚወደው’ ይሖዋ አምላክ ግን ፈጽሞ እንዲህ አያደርግም። (መዝሙር 37:28) ይሖዋ ታጋሽ ቢሆንም ጥፋት የሚሠሩ ሰዎችን በቸልታ አይመለከትም። በተጨማሪም ትክክል የሆነውን ከማድረግ ወደኋላ አይልም። በዘኍልቍ ምዕራፍ 20 ላይ ተመዝግቦ እንደምናገኘው አንዳንዶች ባጉረመረሙና ባመፁ ጊዜ ይሖዋ የወሰደውን እርምጃ እስቲ እንመልከት።

እስራኤላውያን በምድረ በዳ ያደርጉት የነበረውን ጉዞ ሊያገባድዱ አካባቢ የውኃ እጥረት አጋጠማቸው። * በዚህ ጊዜ ሕዝቡ “የእግዚአብሔርን ማኅበረ ሰብ ወደዚህ ምድረ በዳ ያመጣችሁት ለምንድነው! ከነከብቶቻችን እዚሁ እንድናልቅ ነውን?” በማለት ሙሴንና አሮንን ተጣሏቸው። (ቁጥር 4) ሕዝቡ፣ ምድረ በዳው “የሚጠጣ ውሃ” የሌለበት እንዲሁም ‘በለስ፣ ወይንና ሮማን’ የማይገኝበት “ክፉ ቦታ” እንደሆነ በምሬት ተናግረዋል፤ እስራኤላውያን ሰላዮች ከዓመታት በፊት ከተስፋይቱ ምድር ይዘው የመጡት እነዚህን ፍራፍሬዎች ነበር። (ቁጥር 5ዘኍልቍ 13:23) እነዚህ ሰዎች ምድረ በዳው የቀድሞ አባቶቻቸው ሊወርሱት ፈቃደኛ ካልሆኑት ምድር የተለየ ሆኖባቸዋል፤ ለዚህ ደግሞ ተጠያቂዎቹ ሙሴና አሮን እንደሆኑ ተሰምቷቸዋል።

ይሖዋ ያጉረመረሙትን ሰዎች ከመቅጣት ይልቅ ምሕረት አሳይቷቸዋል። እንዲያውም ለሙሴ “በትሪቱን ውሰድ፤ አንተና ወንድምህ አሮን ማኅበሩን በአንድነት ሰብስቡ፤ እነርሱም እያዩ ዐለቱን ተናገሩት፤ ዐለቱም ውሃ ያወጣል” በማለት ሦስት ነገሮችን እንዲያደርግ አዞታል። (ቁጥር 8) ሙሴ የመጀመሪያዎቹን ሁለት መመሪያዎች ተግባራዊ ያደረገ ሲሆን ሦስተኛውን ግን ሳይፈጽም ቀርቷል። ሙሴ በእምነት ዐለቱን ከመናገር ይልቅ ወደ ሕዝቡ በመዞር እንዲህ ሲል በንዴት ተናገረ፦ “እናንት ዐመፀኞች አድምጡ፤ ከዚህ ዐለት እኛ ለእናንተ ውሃ ማውጣት አለብን?” (ቁጥር 10መዝሙር 106:32, 33) ከዚያም ሙሴ እጁን ዘርግቶ በበትሩ ዐለቱን ሁለት ጊዜ መታው፤ “ውሃውም ተንዶለዶለ።”—ቁጥር 11

ሙሴና አሮን በዚህ ጊዜ ከባድ ኃጢአት ፈጸሙ። አምላክ ‘ሁለታችሁም በትእዛዜ ላይ ዓምፃችኋል’ ብሏቸዋል። (ዘኍልቍ 20:24) ሙሴና አሮን ሕዝቡን ‘ዓመፀኛ’ ብለው ቢከሱም በዚህ ጊዜ የአምላክን ትእዛዝ በመጣሳቸው እነሱ ራሳቸው ዓመፀኞች ሆነዋል። አምላክ የማያሻማ ፍርድ በይኖባቸዋል፦ ሙሴና አሮን እስራኤላውያንን እየመሩ ወደ ተስፋይቱ ምድር አይገቡም። ታዲያ ይሖዋ የበየነባቸው ቅጣት ከልክ ያለፈ ነበር? በፍጹም! እንዲህ እንድንል የሚያደርጉን በርካታ ምክንያቶች አሉን።

በመጀመሪያ ደረጃ ሙሴ ዓመፀኞች ናችሁ ብሎ መፍረድ ይቅርና ሕዝቡን እንዲናገር እንኳ ትእዛዝ አልተሰጠውም ነበር። በሁለተኛ ደረጃ ሙሴና አሮን ለአምላክ ክብር ሳይሰጡ ቀርተዋል። አምላክ ‘እኔን ቅዱስ አድርጋችሁ አላከበራችሁኝም’ ብሏቸዋል። (ቁጥር 12) ሙሴ “እኛ ለእናንተ ውሃ ማውጣት አለብን?” በማለት ውኃውን በተአምራዊ መንገድ የሚሰጣቸው አምላክ ሳይሆን እሱና አሮን እንደሆኑ የሚያስመስል ሐሳብ ተናግሯል። በሦስተኛ ደረጃ በዚህ ጊዜ የተበየነው ፍርድ ይሖዋ ከዚህ ቀደም ከሰጠው ፍርድ ጋር የሚጣጣም ነው። አምላክ ዓመፀኛ የነበረውን የቀድሞውን ትውልድ ወደ ከነዓን እንዳይገባ እንደከለከለው ሁሉ ሙሴንና አሮንንም ከልክሏቸዋል። (ዘኍልቍ 14:22, 23) በአራተኛ ደረጃ ሙሴና አሮን የእስራኤል መሪዎች ነበሩ። ብዙ ኃላፊነት ከተሰጠው ሰው ደግሞ ብዙ ይጠበቅበታል።—ሉቃስ 12:48

ይሖዋ ትክክል የሆነውን ነገር ከማድረግ ወደኋላ አይልም። ይሖዋ ፍትሕን የሚወድ አምላክ ስለሆነ ፍትሕ የጎደለው ፍርድ መበየን አይችልም። ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደምንችለው በዚህ ዳኛ ላይ ልንተማመንበትና አክብሮት ልንሰጠው ይገባል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ በኋላ ወደ ከነዓን ማለትም አምላክ ለአብርሃም ቃል ወደገባለት ምድር ለመግባት ተቃርበው ነበር። አሥሩ ሰላዮች መጥፎ ሪፖርት ይዘው በመጡ ጊዜ ግን ሕዝቡ በሙሴ ላይ አጉረመረሙ። ይሖዋ ሕዝቡ ለ40 ዓመት በምድረ በዳ እንዲቆዩ የወሰነባቸው ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ ደግሞ ዓመፀኛው ትውልድ ሞቶ ያልቃል።