አምላክ ሀብታም እንደሚያደርግህ ቃል ገብቶልሃል?
አምላክ ሀብታም እንደሚያደርግህ ቃል ገብቶልሃል?
‘አምላክ ሀብታም እንድትሆኑ፣ ግቢያችሁ በመኪና እንዲሞላና የተትረፈረፈ ገቢ እንድታገኙ ይፈልጋል። እናንተ ብቻ በእሱ እመኑ፤ ቦርሳችሁን ከፍታችሁ የቻላችሁትን ያህል ስጡት።’
በብራዚል የሚታተም አንድ ጋዜጣ እንደዘገበው በአገሪቱ ያሉ አንዳንድ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ሰዎች ገንዘብ እንዲያዋጡ ለመቀስቀስ ከላይ ያለውን የስብከት ዘዴ ይጠቀማሉ። ብዙ ሰዎች የተባሉትን ካደረጉ ቃል የተገባላቸውን ነገር እንደሚያገኙ ይሰማቸዋል። ታይም መጽሔት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ክርስቲያን ነን በሚሉ ሰዎች ላይ የተደረገውን ጥናት አስመልክቶ እንዲህ በማለት ዘግቧል፦ “በጥናቱ ውስጥ ከተካተቱት ሰዎች መካከል 61 በመቶ የሚሆኑት አምላክ ሰዎች ሀብታም እንዲሆኑ እንደሚፈልግ ያምናሉ። እንዲሁም 31 በመቶ የሚሆኑት . . . ‘ገንዘብህን ለአምላክ ከሰጠህ እሱ ደግሞ አትረፍርፎ በመስጠት ይባርክሃል’ በሚለው ሐሳብ ይስማማሉ።”
ብዙውን ጊዜ ፕሮስፔሪቲ ቲኦሎጂ በመባል የሚታወቀው እንዲህ ያለው እምነት በተለይ እንደ ብራዚል ባሉ የላቲን አሜሪካ አገሮች እየተስፋፋ ሲሆን ሰዎችም ‘አምላክ ቁሳዊ ሀብት በመስጠት ይባርካል’ በማለት ወደሚሰብኩ አብያተ ክርስቲያናት በብዛት እየጎረፉ ነው። ይሁንና አምላክ እሱን ለሚያገለግሉት ሰዎች ሀብት በመስጠት እንደሚባርካቸው ቃል ገብቷል? በጥንት ዘመን የኖሩ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ ሀብታም ነበሩ?
በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የአምላክ በረከት አብዛኛውን ጊዜ ከቁሳዊ ብልጽግና ጋር ተያይዞ እንደተጠቀሰ ግልጽ ነው። ለምሳሌ ያህል ዘዳግም 8:18 እንዲህ ይላል፦ “ሀብት እንድታፈራ ችሎታ የሰጠህ . . . እርሱ ስለ ሆነ፣ አምላክህን እግዚአብሔርን አስበው።” አምላክ የገባው ይህ ቃል፣ እስራኤላውያን እሱን ከታዘዙ በብሔር ደረጃ ሀብታም እንደሚያደርጋቸው ማረጋገጫ ይሰጣቸዋል።
ግለሰቦችን በተመለከተስ ምን ለማለት ይቻላል? ታማኝ የአምላክ አገልጋይ የነበረው ኢዮብ በጣም ሀብታም ነበረ፤ ሰይጣን ለድህነት ከዳረገው በኋላም ይሖዋ ሀብቱን “ዕጥፍ አድርጎ” መልሶለታል። (ኢዮብ 1:3፤ 42:10) አብርሃምም ቢሆን ሀብታም ሰው ነበር። ዘፍጥረት 13:2 “በከብት፣ በብርና በወርቅ እጅግ በልጽጎ ነበር” ይላል። አራቱ የምሥራቅ ነገሥታት ሕብረት ፈጥረው የአብርሃም የወንድም ልጅ የሆነውን ሎጥን በማረኩት ጊዜ አብርሃም “በቤቱ ተወልደው አድገው የሠለጠኑ 318 ጦረኞች አሰልፎ” ነበር። (ዘፍጥረት 14:14) አብርሃም 318 “የሠለጠኑ” ጦረኞች ከነበሩት፣ የቤተሰቡ አባላት ቁጥር በርካታ እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም። አብርሃም እንዲህ ያለውን ሰፊ ቤተሰብ ማስተዳደር መቻሉ በርካታ ቁጥር ያለው የከብትና የበግ መንጋ የነበሩት በጣም ሀብታም ሰው እንደነበር ይጠቁማል።
አዎን፣ እንደ አብርሃምና ይስሐቅ እንዲሁም እንደ ያዕቆብ፣ ዳዊትና ሰለሞን ያሉ በርካታ የአምላክ አገልጋዮች ሀብታሞች ነበሩ። ታዲያ ይህ ሲባል አምላክ እሱን የሚያገለግሉ ሰዎችን በሙሉ ሀብታም ያደርጋቸዋል ማለት ነው? በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሰው ድሃ መሆኑ አምላክ እንዳልባረከው የሚያሳይ ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።