በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አዳም እና ሔዋን በሕይወት የኖሩ ሰዎች ነበሩ?

አዳም እና ሔዋን በሕይወት የኖሩ ሰዎች ነበሩ?

አዳም እና ሔዋን በሕይወት የኖሩ ሰዎች ነበሩ?

ብዙ ሰዎች በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ የሚገኘውን ስለ አዳምና ሔዋን የሚናገረውን ዘገባ ለጆሮ የሚጥም ተረት አድርገው ይመለከቱታል። ለታይም መጽሔት አዘጋጅ የተጻፈ አንድ ደብዳቤ “አብዛኞቹ ክርስቲያኖች በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ስለ አዳምና ሔዋን እንደሚናገሩት ያሉ ዘገባዎች ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ምሳሌያዊ እንደሆኑ አድርገው ይረዷቸዋል” የሚል ሐሳብ ይዟል። በርካታ የካቶሊክ፣ የፕሮቴስታንትና የአይሁድ ሃይማኖታዊ ምሑራን በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ። እነዚህ ምሑራን የዘፍጥረት መጽሐፍ አብዛኛው ክፍል ከታሪክ ወይም ከሳይንስ ጋር እንደማይስማማ ይናገራሉ።

አንተስ ምን ይሰማሃል? አዳምና ሔዋን በሕይወት የኖሩ ሰዎች እንደነበሩ ታምናለህ? እንዲህ ብሎ ለማመን የሚያስችል ማስረጃስ አለ? በሌላ በኩል ሰዎች የዘፍጥረት መጽሐፍ ዘገባን እንደ ተረት አድርገው መመልከታቸው ምን አንድምታ ይኖረዋል?

የዘፍጥረት መጽሐፍ ዘገባ ከሳይንስ ጋር ይስማማል?

በቅድሚያ ስለ መጀመሪያው ሰው አፈጣጠር ከሚናገረው ዘገባ ላይ ዋና ዋና የሆኑትን ነጥቦች እስቲ እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ አዳምን አስመልክቶ እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር አምላክ ከምድር ዐፈር ወስዶ ሰውን አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ።” (ዘፍጥረት 2:7) ይህ አባባል ሳይንሳዊ ድጋፍ አለው?

ናኖሜዲሲን የተባለው መጽሐፍ የሰው አካል ከ41 የተለያዩ ኬሚካላዊ ንጥረ ነገሮች እንደተሠራ ገልጿል። ካርቦንን፣ ብረትን፣ ኦክሲጅንን እና ሌሎች ንጥረ ነገሮችን ጨምሮ መሠረታዊ የሆኑት እነዚህ ንጥረ ነገሮች በሙሉ በምድር “ዐፈር” ውስጥ ይገኛሉ። በመሆኑም የዘፍጥረት መጽሐፍ እንደሚገልጸው የሰው ልጆች በእርግጥ የተሠሩት “ከምድር ዐፈር” ነው።

ሕይወት አልባ የሆኑት እነዚህ ንጥረ ነገሮች ሕይወት ያለው ሰው ሊያስገኙ የቻሉት እንዴት ነው? ሁኔታው ምን ያህል አስቸጋሪ መሆኑን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል እስከ ዛሬ ከተፈለሰፉት እጅግ ውስብስብ የሆኑ ማሽኖች አንዱ የሆነውን በብሔራዊ የበረራና የሕዋ አስተዳደር (NASA) የተሠራውን የጠፈር መንኮራኩር እንመልከት። እጅግ አስደናቂ የሆነው ይህ የቴክኖሎጂ ውጤት 2.5 ሚሊዮን የሚሆኑ የተለያዩ ክፍሎች አሉት። የዚህን ማሽን ንድፍ ለማውጣትም ሆነ ገጣጥሞ ለመጨረስ በርካታ ኢንጂኔሮች የተሳተፉ ከመሆኑም ሌላ ይህን ለማድረግ ረጅም ዓመት ወስዶባቸዋል። አሁን ደግሞ የሰውን አካል እንመልከት። የሰው አካል ከ7 ኦክቲሊዮን አቶሞች፣ ከ100 ትሪሊዮን ሴሎች እና ከበርካታ የአካል ክፍሎች የተገነባ ሲሆን የደም ዝውውር ሥርዓትን የመሰሉ 9 ዋና ዋና ሥርዓቶች አሉት። * ከማሰብ ችሎታ በላይ የሆነው ይህ ውስብስብና እንከን የማይወጣለት ሕያው ማሽን እንዴት ሊገኝ ቻለ? እንዲሁ በአጋጣሚ ወይስ የማሰብ ችሎታ ባለው ፈጣሪ?

ከዚህም በተጨማሪ ሰዎች ሕይወት ሊኖራቸው የቻለው እንዴት ነው? የሕይወት ምንጭ ምንድን ነው? ሳይንቲስቶች የዚህን ጥያቄ መልስ እንደማያውቁት ተናግረዋል። እንዲያውም ሕይወት ለሚለው ቃል በሚሰጡት ትርጉም እንኳ እርስ በርስ አይስማሙም። ፈጣሪ አለ ብለው ለሚያምኑ ሰዎች ግን መልሱ ግልጽ ነው። የሕይወት ምንጭ አምላክ ነው። *

ሔዋን ከአዳም የጎድን አጥንት እንደተሠራች በሚናገረው የዘፍጥረት መጽሐፍ ዘገባስ ታምናለህ? (ዘፍጥረት 2:21-23) ይህ ዘገባ ተረት ወይም ልብ ወለድ ነው ብለህ ከመደምደምህ በፊት የሚከተሉትን እውነታዎች ተመልከት፦ በጥር 2008 በካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ሳይንቲስቶች ከአንድ ጎልማሳ ሰው ቆዳ ላይ ሴሎችን ከወሰዱ በኋላ ክሎኒንግ በተባለው ዘዴ ተጠቅመው በዓለም ላይ የመጀመሪያዎቹን ሰብዓዊ ጽንሶች ማዳበር ችለዋል። እንዲያውም ሳይንቲስቶች ክሎኒንግ የተባለውን ይህን ዘዴ ተጠቅመው ቢያንስ 20 የሚያህሉ እንስሳትን በላብራቶሪ ውስጥ መሥራት ችለው ነበር። ከእነዚህ መካከል በሰፊው የምትታወቀው በ1996 ከአንድ በግ የወተት አመንጪ ዕጢዎች ላይ ከተወሰዱ ሴሎች በላብራቶሪ የተሠራችው ዶሊ የምትባለው በግ ናት። *

የእነዚህ ምርምሮች የመጨረሻ ውጤት ምን እንደሚሆን አናውቅም። ይሁንና ሰዎች ሕይወት ካለው አንድ እንስሳ ሴል ውስጥ አንድ ነገር ወስደው ያንኑ የሚመስል እንስሳ ማስገኘት ከቻሉ ሁሉን የሚችለው ፈጣሪ ሕያው ከሆነ ሰብዓዊ ፍጡር ላይ አንድ አካል ወስዶ ሌላ ሰው ማስገኘት ያቅተዋል? የጎድን አጥንት እንደገና የማደግና ራሱን የመተካት ችሎታ ስላለው የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች፣ የተጎዱ አጥንቶችን ለመተካት አብዛኛውን ጊዜ የጎድን አጥንትን የሚጠቀሙ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ የሚሰጠው ምሥክርነት

አንዳንድ ሰዎች አዳምና ሔዋን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜ እንደተጠቀሱ ሲያውቁ ይገረማሉ። ስለ አዳምና ሔዋን የሚናገሩት እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የዘፍጥረት መጽሐፍ ዘገባዎች ትክክለኛ መሆናቸውን የሚያረጋግጡት እንዴት ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በሆኑት በአንደኛ ዜና መዋዕል ከምዕራፍ 1 እስከ 9 እንዲሁም በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 3 ላይ የሚገኙትን የአይሁዳውያንን የዘር ሐረግ ዝርዝሮች እንደ ምሳሌ እንመልከት። በአንደኛ ዜና መዋዕል ላይ 48 ትውልዶች በሉቃስ ዘገባ ላይ ደግሞ 75 ትውልዶች ምንም ሳይጎድል በዝርዝር ተቀምጠዋል። የሉቃስ ዘገባ ያተኮረው በኢየሱስ ክርስቶስ የዘር ሐረግ ላይ ሲሆን በዜና መዋዕል ላይ የሰፈረው ዘገባ ያተኮረው ደግሞ በእስራኤል ብሔር ውስጥ ነገሥታትና ካህናት ሆነው ባገለገሉ ሰዎች የዘር ሐረግ ላይ ነው። በሁለቱም የዘር ሐረግ ዝርዝሮች ውስጥ አዳምን ጨምሮ እንደ ሰለሞን፣ ዳዊት፣ ያዕቆብ፣ ይስሐቅ፣ አብርሃምና ኖኅ ያሉ ታዋቂ ሰዎች ተጠቅሰዋል። በሁለቱም የዘር ሐረግ ዝርዝሮች ውስጥ የተጠቀሱት ሰዎች በሕይወት የነበሩ ናቸው፤ የእነዚህ ሰዎች መገኛ እንደሆነ የተጠቀሰው አዳምም በሕይወት የኖረ ሰው ነው።

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ አዳምንና ሔዋንን የሚገልጻቸው በልብ ወለድ ውስጥ እንዳሉ ገጸ ባሕርያት ሳይሆን በሕይወት እንደነበሩ ሰዎች አድርጎ ነው። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት፦

• “[አምላክ] የሰውን ወገኖች በሙሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ።”—የሐዋርያት ሥራ 17:26

• “በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ . . . ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ሞት በሁሉ ላይ ነገሠ።”—ሮም 5:12, 14

• “የመጀመሪያው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ።”—1 ቆሮንቶስ 15:45

• “በመጀመሪያ የተፈጠረው አዳም ነው፤ ከዚያም ሔዋን ተፈጠረች።”—1 ጢሞቴዎስ 2:13

• “ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ ትውልድ የሆነው ሄኖክ ስለ እነዚህ ሰዎች [ስለ ክፉዎች] . . . ተንብዮአል።”—ይሁዳ 14

ከዚህም በላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት ሰዎች መካከል ከፍተኛ ተዓማኒነት ያለው ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምና ሔዋን በሕይወት እንደነበሩ ያምን ነበር። ኢየሱስ ፍቺን በተመለከተ ለቀረበለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ እንዲህ ብሏል፦ “በፍጥረት መጀመሪያ ‘አምላክ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። ከዚህም የተነሳ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’፤ . . . ስለዚህ አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው።” (ማርቆስ 10:6-9) ኢየሱስ ሰዎች ሊከተሉት የሚገባ መመሪያ ለመስጠት ልብ ወለድ ታሪክ ይጠቀማል? በጭራሽ! ኢየሱስ በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን ዘገባ በእርግጥ የተፈጸመ ታሪክ እንደሆነ አድርጎ ጠቅሶታል።

ዘ ኒው ባይብል ዲክሽነሪ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎችን ከመረመረ በኋላ “አዲስ ኪዳን በዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፎች ውስጥ የሚገኘው ዘገባ ትክክል መሆኑን ያረጋግጣል” ወደሚል መደምደሚያ ደርሷል።

የዘፍጥረት መጽሐፍ ዘገባን አለማመን ያለው ጉዳት

ቤተ ክርስቲያን የሚያዘወትሩ ቅን ልብ ያላቸው በርካታ ሰዎች፣ ጥሩ ክርስቲያን ለመሆን አዳምና ሔዋን በሕይወት የኖሩ ሰዎች መሆናቸውን ማመን ያን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አይሰማቸውም። እንዲህ ያለው አመለካከት ላይ ላዩን ሲታይ እውነትነት ያለው ይመስላል። ይሁንና ከዚህ በታች የቀረበውን ማስረጃ እንመርምር፤ ከዚያም ይህ አመለካከት ወደ ምን ሊመራን እንደሚችል እንመልከት።

ቤተ ክርስቲያን የሚያዘወትሩ በርካታ ሰዎች በጣም አስፈላጊ እንደሆነ የሚሰማቸውን ስለ ቤዛው የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንደ ምሳሌ እንመልከት። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ከኃጢአት ለማንጻት ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ እንደሰጠ ይናገራል። (ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 3:16) ሁላችንም እንደምናውቀው ቤዛ የሚያመለክተው አንድ ሰው የጠፋበትን ወይም ያጣውን ነገር ለማስመለስ ወይም እንደገና ለመግዛት የሚከፍለውን ተመጣጣኝ ዋጋ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን “ተመጣጣኝ ቤዛ” እንደሆነ አድርጎ የሚገልጸው ለዚህ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:6) ኢየሱስ የሚመጣጠነው ከምን ነገር ጋር ነው ብለን እንጠይቅ ይሆናል? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት መልስ ይሰጣል፦ “ሁሉም በአዳም እንደሚሞቱ ልክ እንደዚሁም ሁሉም በክርስቶስ ሕያው ይሆናሉ።” (1 ቆሮንቶስ 15:22) ኢየሱስ ታዛዥ የሆኑትን የሰው ዘሮች ለመቤዠት የከፈለው ፍጹም ሕይወት አዳም በኤደን ገነት ኃጢአት በሠራ ጊዜ ካጣው ፍጹም ሕይወት ጋር ተመጣጣኝ ነው። (ሮም 5:12) አዳም በሕይወት የኖረ ሰው ካልነበረ የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ምንም ትርጉም እንደማይኖረው በግልጽ መመልከት ይቻላል።

አንድ ሰው ስለ አዳምና ሔዋን የሚናገረውን የዘፍጥረት መጽሐፍ ዘገባ አለመቀበሉ ወይም ችላ ብሎ ማለፉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት በአብዛኞቹ ዋና ዋና ትምህርቶች ላይ ጠንካራ እምነት እንዳይኖረው ያደርገዋል። * አንድ ሰው አዳምና ሔዋን በሕይወት የኖሩ ሰዎች አይደሉም ብሎ ማመኑ አእምሮው መልስ በማያገኙ በርካታ ጥያቄዎች እንዲሞላና ጠንካራ መሠረት ያለው እምነት እንዳያዳብር እንቅፋት ይሆንበታል።—ዕብራውያን 11:1

ሕይወት ትርጉም አለው?

በመጨረሻም ወሳኝ የሆነ አንድ ጥያቄ እናንሳ፦ በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን ዘገባ አለመቀበላችን ስለ ሕይወት ትርጉምና ዓላማ ለማወቅ ያለንን ፍላጎት ያረካልናል? የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ አራማጅ የሆኑትና በአምላክ መኖር የማያምኑት ሪቻርድ ዶከንዝ እንዳሉት ከሆነ አጽናፈ ዓለም “ንድፍና ዓላማ ብሎም መጥፎም ሆነ ጥሩ የሚባል ነገር የለውም፤ ከዚህ ይልቅ ምንም ትርጉም የሌለው ባዶና ጨለማ ነው።” ከሰው ልጆች ተፈጥሮ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጋጭ እንዴት ያለ ተስፋ አስቆራጭ አመለካከት ነው!

መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ በተለየ መልኩ ሕይወትን በተመለከተ ለሚነሱ እንደሚከተሉት ላሉ አንገብጋቢ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ይሰጣል፦ ‘ሕይወት ከየት ተገኘ? የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? በዓለም ላይ ክፋትና መከራ የበዛው ለምንድን ነው? ክፋት ይወገድ ይሆን?’ በተጨማሪም በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት ማሳደር በምድር ላይ በገነት የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ያስችለናል። በዚህች ገነት ውስጥ የሚኖረው ሁኔታ አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ሰዎች ማለትም ለአዳምና ለሔዋን መኖሪያ አድርጎ በሰጣቸው ኤደን ገነት ውስጥ ከሚኖረው ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል። (መዝሙር 37:29፤ ራእይ 21:3-5) እንዴት ያለ አስደሳች ተስፋ ነው! *

ስለ አዳምና ሔዋን የሚናገረው ዘገባ ከዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ጋር ባይጣጣምም ሳይንስ ከደረሰባቸው ነገሮች ጋር ግን ይስማማል። ከዚህም በላይ በአምላክ መንፈስ መሪነት በተጻፈው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት ከሌሎቹ ዘገባዎች ሁሉ ጋር ሙሉ በሙሉ ይስማማል፤ መጽሐፍ ቅዱስ የሕይወትን ትርጉምና ዓላማ በተመለከተ ለሚነሱ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ይሰጣል።

ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስን ለምን አትመረምርም? የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ረገድ ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.7 በዩናይትድ ስቴትስ ሥርዓተ አኃዝ መሠረት 7 ኦክቲሊዮን ከ7 በኋላ 27 ዜሮዎች ያሉት ቁጥር ሲሆን 100 ትሪሊዮን ደግሞ ከ100 በኋላ 12 ዜሮዎች አሉት።

^ አን.8 ስለዚህ ርዕሰ ጉዳይ ሰፊ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁትን ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? (እንግሊዝኛ) እንዲሁም ሕይወት—እንዴት ተገኘ? በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት? (እንግሊዝኛ) የተባሉትን መጻሕፍት ተመልከት።

^ አን.9 እርግጥ ነው፣ እነዚህ ሳይንቲስቶች ሕይወት አልፈጠሩም። ከዚህ ይልቅ ከላይ የተጠቀሱትን ሕያዋን ነገሮች የሠሩት ሕይወት ካላቸው ሴሎች የወሰዷቸውን አንዳንድ ንጥረ ነገሮች ተጠቅመው ነው።

^ አን.25 ከእነዚህ መካከል ስለ አምላክ ሉዓላዊ ገዥነት፣ ስለ ሰዎች ንጹሕ አቋም፣ መልካምና ክፉ ስለሆኑ ነገሮች፣ ስለ መምረጥ ነፃነት፣ ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ፣ ስለ ጋብቻ፣ ተስፋ ስለተደረገበት መሲሕ፣ ስለ ምድራዊ ገነት፣ ስለ አምላክ መንግሥት እና ስለተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች የሚናገሩ ትምህርቶች ይገኙበታል።

^ አን.28 ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች ከተዘጋጀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? ከተባለው መጽሐፍ “አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?” የሚለውን ምዕራፍ 3⁠ን እና “ቤዛው—ከሁሉ የላቀ የአምላክ ስጦታ” የሚለውን ምዕራፍ 5⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አዳም በሕይወት የኖረ ሰው ካልነበረ የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ምንም ትርጉም እንደማይኖረው በግልጽ መመልከት ይቻላል

[በገጽ 12, 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ የጠፈር መንኮራኩር በጥንቃቄ የተሠራ ንድፍ እንዳለው ሁሉ የሰው ልጆች አካልም እንዲሁ ነው

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ አዳምና ሔዋን በሕይወት የነበሩ ሰዎች መሆናቸውን ያምን ነበር