በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ውድ ሀብት ተገኘ

ውድ ሀብት ተገኘ

ውድ ሀብት ተገኘ

ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ለጽሕፈት የሚያገለግሉ መሣሪያዎችን ማግኘት የአሁኑን ያህል ቀላል አልነበረም። በመሆኑም ሰዎች ለጽሕፈት ይገለገሉባቸው የነበሩትን ብራናዎች ወይም ሌሎች ነገሮች እንደገና ለመጠቀም ሲሉ በላያቸው ላይ የተጻፈውን ጽሑፍ በመፋቅ ወይም በማጠብ ያስለቅቋቸው ነበር፤ እንዲህ የሚያደርጉት ጽሑፎቹ አስፈላጊ እንዳልሆኑ በሚሰማቸው ጊዜ ነበር። ሌላው ቀርቶ ሌሎች መረጃዎችን ለመመዝገብ ሲሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የተጻፉባቸውን ብራናዎች ፍቀዋል።

ትልቅ ግምት ከሚሰጣቸው የጥንት ብራናዎች መካከል አንዱ የሆነው ኮዴክስ ኢፍራይሚ ሱሪ ሬስክሪፕተስ ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ይሆነናል፤ ሬስክሪፕተስ የሚለው ቃል “አጥፍቶ መጻፍ” የሚል ትርጉም አለው። ይህ ኮዴክስ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን የተወሰኑ ክፍሎች ከያዙት በአሁኑ ጊዜ ከሚገኙት የጥንት ቅጂዎች መካከል አንዱ ነው። በመሆኑም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን ትክክለኝነት የሚያረጋግጥ መረጃ ሆኖ ያገለግላል። በዚህም ምክንያት ይህ ነው የማይባል ጥቅም አለው።

በአምስተኛው መቶ ዘመን በተዘጋጀው በዚህ ኮዴክስ ላይ ተጽፎ የነበረው የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል በ12ኛው መቶ ዘመን ጠፍቶ የሶርያዊው ምሑር የኢፍራይም 38 ስብከቶች የግሪክኛ ትርጉም ተጽፎበታል። ምሑራን ከዚህ ኮዴክስ ላይ የጠፋውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋሉት በ17ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ ነው። ከዚያ በኋላ በነበሩት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በብራናው ላይ የሚገኘውን የጠፋውን ጽሑፍ በተወሰነ መጠን ለማንበብ ተችሎ ነበር። ይሁን እንጂ የጠፋው ጽሑፍ ፈዛዛና ለማየት የሚያስቸግር በመሆኑ፣ አብዛኞቹ ገጾች ከማርጀታቸው የተነሳ በጣም በመጎዳታቸው እንዲሁም ቀደም ሲል የተጻፈውና በኋላ ላይ የሰፈሩት ቃላት በመደራረባቸው የጽሑፉን ሁሉንም ክፍል ማንበብ በጣም አስቸጋሪ ሆኖ ነበር። ምሑራን ቃላቱ ጎላ ብለው እንዲታዩ ለማድረግና ለማንበብ የተለያዩ ኬሚካሎችን ቢጠቀሙም ጥረታቸው አልተሳካም። በመሆኑም አብዛኞቹ ምሑራን የጠፋውን ጽሑፍ ማንበብ አይቻልም ወደሚል መደምደሚያ ደረሱ።

በ1840ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ፣ ጥሩ የቋንቋ ተሰጥኦ የነበረው ኮንስታንቲን ቮን ቲሸንዶርፍ የተባለ አንድ ጀርመናዊ ምሑር በዚህ ኮዴክስ ላይ የነበረውን ጽሑፍ ለማንበብ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ጀመረ። ቲሸንዶርፍ በኮዴክሱ ላይ ቀደም ሲል የተጻፈውን የእጅ ጽሑፍ አንብቦ ለመረዳት ሁለት ዓመት ፈጅቶበታል። ሌሎች ምሑራን ጽሑፉን ለማንበብ ቢቸገሩም ቲሸንዶርፍ በዚህ ረገድ ሊሳካለት የቻለው እንዴት ነው?

ቲሸንዶርፍ ቅጥልጥል ባልሆኑ ትልልቅ የግሪክኛ ፊደላት የተጻፉ ጽሑፎችን አንብቦ በመረዳት ረገድ ከፍተኛ እውቀት ነበረው። * ጥሩ የማየት ችሎታ የነበረው ቲሸንዶርፍ ብራናውን ከፍ አድርጎ ብርሃን ላይ በማየት ብቻ ቀደም ሲል የተጻፈውን ጽሑፍ ማንበብ ቻለ። በዛሬው ጊዜ ያሉ ምሑራን፣ ኢንፍራሬድ አሊያም የፀሐይ ጨረር በመጠቀም ወይም ደግሞ ብርሃን ከተለያየ አቅጣጫ በጽሑፉ ላይ እንዲያርፍ በማድረግ ተመሳሳይ ነገር ያከናውናሉ።

ቲሸንዶርፍ ከኮዴክስ ኢፍራይሚ ላይ ያነበበውን ጽሑፍ መጀመሪያ በ1843፣ ከዚያም በ1845 አሳተመ። ይህ ሥራው ቲሸንዶርፍ ጥንታዊ ግሪክኛ ጽሑፎችን አንብቦ በመረዳት ረገድ ቀዳሚውን ቦታ እንዲይዝ አስችሎታል።

የኮዴክስ ኢፍራይሚ መጠን 31 ሴንቲ ሜትር በ23 ሴንቲ ሜትር ገደማ ሲሆን በአንድ ገጽ ላይ አንድ አምድ ብቻ ካላቸው ጽሑፎች መካከል በጥንታዊነቱ እንደ ምሳሌ የሚጠቀስ ነው። ቲሸንዶርፍ ማንበብ ከቻላቸው 209 ገጾች ውስጥ 145 የሚሆኑት 2 ተሰሎንቄን እና 2 ዮሐንስን ሳይጨምር ሁሉንም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት የያዙ ናቸው። ቀሪዎቹ ገጾች ደግሞ የተወሰኑ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን ክፍል የግሪክኛ ትርጉም የያዙ ናቸው።

በዛሬው ጊዜ ይህ ኮዴክስ ፈረንሳይ አገር በፓሪስ ከተማ በሚገኘው ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ይገኛል። ይህ ጥንታዊ ጽሑፍ ከየት እንደተገኘ በግልጽ ባይታወቅም ቲሸንዶርፍ ከግብፅ ሊሆን እንደሚችል ገምቷል። ምሑራን ኮዴክስ ኢፍራይሚ፣ ቅጥልጥል ባልሆኑ ትላልቅ ፊደላት ከተጻፉ አራት ዋና ዋና የግሪክኛ መጽሐፍ ቅዱሶች መካከል እንደሚመደብ ተናግረዋል፤ የተቀሩት ሦስቱ የሳይናይቲክ፣ የአሌክሳንድራይን እና የቫቲካን 1209 ጽሑፎች ናቸው። ሁሉም የተጻፉት በአራተኛውና በአምስተኛው መቶ ዘመን እንደሆነ ይገመታል።

የቅዱሳን መጻሕፍት መልእክት፣ ሌሎች ነገሮች የተጻፈባቸውን ብራናዎች ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች በሚያስደንቅ ሁኔታ ለእኛ ደርሷል። በዚህ ርዕስ ላይ ከተመለከትነው አንጻር ግን እምብዛም አድናቆት የሌለው አንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ ከብራናው ላይ ለማጥፋት ቢሞክርም መልእክቱ እስከ ዘመናችን ድረስ ተጠብቆ ቆይቷል። ይህ ደግሞ “የይሖዋ ቃል . . . ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” የሚሉትን የሐዋርያው ጴጥሮስ ቃላት እውነተኝነት የሚያረጋግጥ ነው።—1 ጴጥሮስ 1:25

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 ቲሸንዶርፍ ይበልጥ የሚታወቀው በሲና ተራራ ግርጌ ካለው የሴይንት ካተሪና ገዳም የተገኘውን የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የግሪክኛ ትርጉም አንብቦ መረዳት በመቻሉ ነው። እስካሁን ከተገኙት እጅግ ጥንታዊ የሆኑ ጽሑፎች መካከል የሚመደበው ይህ ጽሑፍ ኮዴክስ ሳይናቲከስ በመባል ይታወቃል።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ኮዴክስ ኢፍራይሚ ሱሪ ሬስክሪፕተስ፣ ቲሸንዶርፍ (1815-1874) ማንበብ የቻለውና ትልቅ ግምት የሚሰጠው የጥንት ብራና

የመጀመሪያው ጽሑፍ

በላዩ ላይ የተጻፈው የግሪክኛ ስብከት

[የሥዕል ምንጭ]

© Bibliothèque nationale de France

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሴይንት ካተሪና ገዳም የተገኘው ኮዴክስ ሳይናቲከስ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቲሸንዶርፍ