በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመካከለኛው አሜሪካ ትልቁ ሐይቅ ያለው ውድ ሀብት

የመካከለኛው አሜሪካ ትልቁ ሐይቅ ያለው ውድ ሀብት

የመካከለኛው አሜሪካ ትልቁ ሐይቅ ያለው ውድ ሀብት

ኒካራጓ ትንሽ አገር ብትሆንም እንኳ በመካከለኛው አሜሪካ ከሚገኙት ሐይቆች ሁሉ ትልቁ የሆነው የኒካራጓ ሐይቅ የሚገኘው በዚህች አገር ነው። የሚያስገርመው የኒካራጓ ሐይቅ እንደ ሻርክ፣ ሶርድ ፊሽና ታርፐን ያሉ በውቅያኖስ ውስጥ ብቻ የሚኖሩ የዓሣ ዝርያዎች የሚገኙበት ጨዋማ ያልሆነ ብቸኛው ሐይቅ ሳይሆን አይቀርም። ሳይንቲስቶች በአንድ ወቅት ይህ ሐይቅ ከፓስፊክ ውቅያኖስ ጋር የተያያዘ የባሕር ወሽመጥ እንደነበረና በእሳተ ገሞራ ፍንዳታ የተነሳ ከውቅያኖሱ ተገንጥሎ ራሱን የቻለ ሐይቅ እንደሆነ ይናገራሉ። የውኃው ጨዋማነት እየቀነሰ ሲመጣም ዓሣዎቹ አዲሱ መኖሪያቸውን ጋር ተላመዱት።

ይህ ሐይቅ ወደ 160 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ርዝመትና ሰፊ በሆነው ቦታ ላይ ሲለካ ወደ 70 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ስፋት ያለው ሲሆን ከባሕር ወለል በላይ ወደ 30 ሜትር ከፍ ይላል። በኒካራጓ ሐይቅ ላይ ከሚገኙት ከ400 የሚበልጡ ደሴቶች መካከል 300 የሚያህሉት አሴሴ በሚባለው ባሕረ ገብ መሬት ዙሪያ እጅብ ብለው ይታያሉ። አሴሴ በሐይቁ ሰሜናዊ ጫፍ ላይ ባለው በግራናዳ ከተማ አቅራቢያ ይገኛል። እነዚህ ደሴቶች የግራናዳ ደሴቶች ተብለው ይጠራሉ።

በሐይቁ መሃል ላይ የሚገኘው ኦሜቴፔ የተባለው ደሴት ትልቁ ደሴት ነው። ወደ 25 ኪሎ ሜትር ርዝመትና ወደ 13 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው የኦሜቴፔ ደሴት በሁለት የእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎች ምክንያት የተገኘ ሲሆን ሁለቱ እሳተ ገሞራዎች በጠባብ መሬት ተያይዘዋል። ከንሰፕሲዮን ተብሎ የሚጠራው ትልቁ እሳተ ገሞራ ከሐይቁ በላይ 1,610 ሜትር ከፍታ አለው። በደሴቲቱ ሰሜናዊ ክፍል ጎላ ብሎ የሚታየው ይህ እሳተ ገሞራ ንቅ እሳተ ገሞራ ነው። ማዴራ የተባለው ሌላኛው እሳተ ገሞራ ደግሞ 1,394 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን ምንም እንቅስቃሴ የማይታይበት እሳተ ገሞራ ነው። ማዴራ በዛፎችና በሌሎች ዕፅዋት የተሸፈነ ከመሆኑም በላይ አናቱ ላይ ጭጋግ የማያጣ ኩሬ አለው።

የኒካራጓ ሐይቅ በአካባቢው ከሚገኙት የቱሪስት መስህቦች መካከል አንዱ ነው። ቱሪስቶች የአካባቢውን ተፈጥሯዊ ውበትና የጥንቱን ዓለም ሥልጣኔ የሚያሳዩትን በርካታ የአርኪኦሎጂ ግኝቶች ለማየት ወደዚህ ቦታ ይጎርፋሉ። ይሁንና በኒካራጓ ሐይቅ ላይ የሚገኘው ሀብት ይህ ብቻ አይደለም፤ ምን ሌላ ነገር ማግኘት ይቻላል?

በውኃ ላይ ያለ መንደር

የግራናዳ ደሴቶች በሞቃታማ አካባቢዎች በሚበቅሉ ተክሎችና በዱር እንስሳት ሀብት የበለጸጉ ናቸው። በእሳተ ገሞራ የተፈጠሩት ለም የሆኑት እነዚህ ደሴቶች በአብዛኛው በደን የተሸፈኑ ሲሆን በሚያማምሩ አበቦች አሸብርቀዋል። በሐይቁ ዳርቻ ላይ እንደ ሳቢሳ፣ አዳኝ ወፎች፣ ለመሚት እና ዓሣ ወጊ ያሉ ውብ የውኃ ዳር ወፎች ይገኛሉ። ከሐይቁ የሚነፍሰው ነፋስ በጫካዎቹ ዳር ባሉት ትልልቅ ዛፎች ላይ የተንጠለጠሉትን የወፍ ጎጆዎች ወዲያና ወዲህ ሲያወዛውዛቸው ይታያል።

አንዳንዶቹ ደሴቶች ላይ ሰው ይኖርባቸዋል። አብዛኞቹ ነዋሪዎች የአካባቢው ዓሣ አጥማጆች ሲሆኑ ሀብታሞች የእረፍት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉባቸው ጎጆ ቤቶችም በእነዚህ ደሴቶች ላይ ይገኛሉ። በተጨማሪም ትምህርት ቤቶች፣ የመቃብር ቦታ፣ ምግብ ቤቶችና መጠጥ ቤቶች አሉ። አንድ ላይ እጅብ ያሉት እነዚህ ደሴቶች በውኃ ላይ ያለ መንደር ይመስላሉ።

ሰማያዊና ነጭ ቀለም የተቀባች አንዲት ጀልባ በየቀኑ ጠዋት ጠዋት ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት ለመውሰድ ከአንዱ ደሴት ወደ ሌላው ትሄዳለች። ተንሳፋፊ ሱቅ ሆና የምታገለግል አንዲት ታንኳ አትክልትና ፍራፍሬ ለመሸጥ ከአንዱ ደሴት ወደ ሌላው ደሴት ትዘዋወራለች። ወንዶች ዓሣ ለማጥመድ መረቦቻቸውን ሲያሰናዱ፣ ሴቶች ደግሞ ሐይቁ ዳር ልብስ ሲያጥቡ መመልከት በጣም የተለመደ ነው።

የይሖዋ ምሥክሮችም በእነዚህ ደሴቶች ላይ የሚሠሩት ብዙ ሥራ አላቸው። በጀልባ እየተዘዋወሩ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለደሴቶቹ ነዋሪዎች ይናገራሉ። (ማቴዎስ 24:14) የደሴቶቹ አቀማመጥ አስቸጋሪ በመሆኑ የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ለመማር የሚያስችሉ ስብሰባዎችን የት ማካሄድ ይቻላል? ‘አንድ ላይ መሰብሰባችንን ቸል እንዳንል’ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መመሪያ ለማክበር የይሖዋ ምሥክሮች አስደናቂ መፍትሔ አገኙ፤ ለኒካራጓ የመጀመሪያ የሆነውን ተንሳፋፊ የመንግሥት አዳራሽ ለመገንባት አቀዱ።—ዕብራውያን 10:25

ተንሳፋፊ የመንግሥት አዳራሽ

ሙሉ ጊዜያቸውን በስብከቱ ሥራ የሚያሳልፉ የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ አንድ ባልና ሚስት በኅዳር 2005 ወደ ግራናዳ ደሴቶች መጡ። ከጥቂት ወራት በኋላ እነዚህ ባልና ሚስት በዓመት አንድ ጊዜ በሚከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ እንዲገኙ የደሴቲቱን ነዋሪዎች ጋበዙ፤ በበዓሉ ላይ 76 ሰዎች መገኘታቸውን ሲመለከቱም በጣም ተገረሙ። ይህ ሁኔታ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን በየሳምንቱ ማካሄድ አስፈላጊ መሆኑን እንዲገነዘቡ አደረጋቸው። በደሴቶቹ ላይ ለስብሰባ የሚሆን ተስማሚ ቦታ ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ እነዚህ ባልና ሚስት ሌላ ዘዴ ቀየሱ። ለነዋሪዎቹ አመቺ ወደሆኑ ቦታዎች እንደልብ ሊወሰድ የሚችል ተንሳፋፊ የመንግሥት አዳራሽ ለመሥራት ወሰኑ።

ከዚያ ቀደም የሚንሳፈፍ ነገር ሠርተው የማያውቁት እነዚህ ታታሪ ባልና ሚስት የመንግሥት አዳራሽ የመገንባቱን ሥራ ተያያዙት። ከሌሎች ስድስት ሰዎች ጋር ሆነው ሥራውን በአንድ ወር ውስጥ አጠናቀቁ። አዲሱ ተንሳፋፊ መሰብሰቢያ ባልተወሳሰበ መንገድ የተሠራ ነው። መጀመሪያ የብረት ቧንቧዎችን በይደው መወጠሪያ አዘጋጁ፤ ከዚያም መወጠሪያውን ለመንሳፈፍ ከሚያስችሉ 150 ሊትር ከሚይዙ አየር የተሞሉ 12 በርሜሎች ጋር አያያዙት። ወለሉ ከተነባበረ ሳንቃ የተሠራ ሲሆን ጣሪያው ደግሞ ሸራ ለበሰ። እየሠሩ ያሉት መሰብሰቢያ መንሳፈፍ አለመንሳፈፉን እርግጠኛ ስላልነበሩ ሠራተኞቹ በየቀኑ ይጸልዩ ነበር። የሚያስደስተው የሠሩት መሰብሰቢያ ሐይቁ ላይ ተንሳፈፈ!

ሰኔ 10, 2006 በአዲሱ የመንግሥት አዳራሽ ለመጀመሪያ ጊዜ የሕዝብ ስብሰባ ተደረገ። ይህንኑ ስብሰባ በሌላኛው የደሴቶቹ ጫፍ ለሚኖሩ ሰዎች ለመድገም ሲባል በማግሥቱ የመንግሥት አዳራሹ ወደዚያ ተወሰደ። ስብሰባ ላይ ለመገኘት አንዳንዶች በጫካ ውስጥ ከግማሽ ሰዓት በላይ መጓዝ ቢጠይቅባቸውም በሁለቱ ቀናት በተደረጉት ስብሰባዎች ላይ 48 ሰዎች ተገኝተው ነበር። ሁሉም የራሳቸው የአምልኮ ቦታ በማግኘታቸው እጅግ ተደሰቱ!

በዚህ የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ስብሰባ ማድረግ ለየት ያለ ስሜት ይፈጥራል፤ ተሰብሳቢዎቹ ተናጋሪው ንግግሩን በሚያቀርብበት ጊዜ ውኃው ከዓለት ጋር ሲጋጭ የሚፈጥረውን ድምፅና አልፎ አልፎ ከርቀት የሚመጣውን የጦጣ ጩኸት መስማት ይችላሉ። ብዙም ሳይቆይ የመንግሥት አዳራሹ ለደሴቶቹ ነዋሪዎች አዲስ ነገር መሆኑ ቀረ። አዳራሹ ከአንድ ደሴት ወደ ሌላ ደሴት ሲወሰድ ሲመለከቱ እጃቸውን በማውለብለብ ሰላምታ ይሰጣሉ። በየሳምንቱ ከ20 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ከክርስቲያን ባልንጀሮቻቸው ጋር ለመተናነጽና መጽሐፍ ቅዱስ ለመማር ወደዚህ ተንሳፋፊ የመንግሥት አዳራሽ ይመጣሉ። በእርግጥም ይህ የመንግሥት አዳራሽ በኒካራጓ ሐይቅ ላይ የሚገኝ ውድ ሀብት ሆኗል!

ኦሜቴፔ ደሴት

ከግራናዳ ከተማ በስተ ደቡብ ወደ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ኦሜቴፔ ደሴት ይገኛል። በደሴቱ ላይ የሚታየው የተፈጥሮ ውበትና ለም የሆነው አፈሩ ለመኖሪያነት ተፈላጊ እንዲሆን አድርጎታል። እንዲያውም የኒካራጓ የግብርና ታሪክ የሚጀምረው በዚህ አካባቢ ነው። በዛሬው ጊዜ ኦሜቴፔ ወደ 42,000 የሚጠጉ ነዋሪዎች ያሏት ሲሆን የሚተዳደሩትም ዓሣ በማጥመድ እንዲሁም እንደ በቆሎ፣ ሙዝ፣ ቡና እና ሌሎች የእህል ዓይነቶችን በማልማት ነው። እዚህም ቢሆን እጅግ አስደናቂ የሆኑ የዱር እንስሳት ይገኛሉ። ኃይለኛ ድምፅ የሚያወጡ በጣም ብዙ በቀቀኖችን፣ ነጭና ሰማያዊ ላባ ያላቸውን የሚያማምሩ ወፎች እንዲሁም ብዙ ሰው የሚወዳቸውን ነጭ ፊት ያላቸው ጦጣዎች ማግኘት ይቻላል።

የአምላክ መንግሥት ምሥራች ሰባኪዎች ለኦሜቴፔ ነዋሪዎችም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራሉ። በ1966 በኦሜቴፔ የነበሩት የተጠመቁ የይሖዋ ምሥክሮች ስምንት ብቻ ነበሩ፤ አሁን ግን ቁጥራቸው 183 የደረሰ ሲሆን እድገት እያደረጉ ያሉ አራት ጉባኤዎችም ይገኛሉ። እያንዳንዱ ጉባኤ ለተሰብሳቢዎቹ አመቺ በሆነ አካባቢ የተሠራ የመንግሥት አዳራሽ አለው። በዛሬው ጊዜ በዚህ ደሴት ውስጥ 1 የይሖዋ ምሥክር ለ230 ሰዎች ይደርሳል።

በኦሜቴፔ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ባለፉት ዓመታት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን አሳልፈዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በ1980 ተቃዋሚዎች በሜሪታ የሚገኘውን የመንግሥት አዳራሽ አቃጥለዋል። በመሆኑም በ1984 ሌላ አዳራሽ ተገነባ። ይህ አዳራሽ እስከ 2003 ካገለገለ በኋላ ደግሞ 60 ለሚሆኑት የጉባኤው አባላት ከፍተኛ ደስታ ምክንያት የሆነ አዲስ የመንግሥት አዳራሽ ተገነባ።

በሞዮጋልፓ የሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ ለትልልቅ ስብሰባዎችም እንዲያገለግል ተደርጎ የተሠራ ነው። ከኋላ በኩል ጣራው መርዘም የሚችል ከመሆኑም ሌላ ከሥሩ መድረክ አለ። ከመድረኩ ፊት ለፊት ደግሞ ወንበሮች ይደረደራሉ፤ ተሰብሳቢዎቹ ጥላ እንዲያገኙም ሸራ ይዘረጋላቸዋል። በሞዮጋልፓና በአካባቢው ባሉ ደሴቶች የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ትልልቅ ስብሰባ በሚኖርበት ጊዜ ወደዚህ ይመጣሉ። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለመሆን ዝግጁ የሆኑ ሰዎች ኒካራጓ ሐይቅ ውስጥ ይጠመቃሉ።—ማቴዎስ 28:19

የሐይቁ ውድ ሀብቶች ተጠብቀው ይቆዩ ይሆን?

የኒካራጓ ሐይቅ በጣም ትልቅ ስለሆነ ሳይሆን አይቀርም የማይደፈር ይመስላል። ይሁንና ሐይቁ ጥበቃ ያስፈልገዋል። ምክንያቱም የሐይቁ ውኃ በግብርና እና በኢንዱስትሪ ዝቃጭ እንዲሁም ከተመነጠሩ ጫካዎች በሚመጡ ቆሻሻዎች እየተበከለ ነው።

የአካባቢው ነዋሪዎችም ሆኑ መንግሥት የሚያደርጉት ጥረት ሐይቁን ከተጋረጠበት አደጋ መታደግ ይችል እንደሆነ ጊዜ ያሳየናል። እነሱ ባይሳካላቸውም እንኳ ፈጣሪ የተንጣለሉትን ሐይቆች፣ የሚያማምሩትን ደሴቶችና ዕፁብ ድንቅ የሆኑትን የዱር እንስሳት ጨምሮ በምድር ላይ ያለው ሀብት በሙሉ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች ተጠብቆ እንዲቆይ ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” በማለት ይናገራል።—መዝሙር 37:29

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚሰጥበት ተንሳፋፊ የመንግሥት አዳራሽ