ድሃ ብትሆንም ደስተኛና ብሩህ ተስፋ ያላት ሴት
ከቦሊቪያ የተላከ ደብዳቤ
ድሃ ብትሆንም ደስተኛና ብሩህ ተስፋ ያላት ሴት
በማደግ ላይ በምትገኝ አንዲት አገር ሚስዮናዊ ሆኜ እንዳገለግል እስከተመደብኩበት ጊዜ ድረስ ሰዎች በድህነት ሲማቅቁና በከፍተኛ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሲዋጡ አይቼ አላውቅም። እያንዳንዱ ሰው ከዚያ ሥቃይ ወዲያውኑ ተላቅቆ ብመለከት ደስ ይለኝ ነበር። ይሁንና እነዚህን ሁሉ ችግሮች የሚያስወግደው የአምላክ መንግሥት ብቻ መሆኑን አውቃለሁ። ያም ሆኖ የአምላክን ቃል ተግባራዊ የሚያደርጉ ሰዎች አስከፊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ቢኖሩም እንኳ ደስተኞች እንደሚሆኑ ለብዙ ጊዜያት ተመልክቻለሁ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ሳቢና ትገኝበታለች።
ከዓመታት በፊት ሳቢና፣ ባሏ የተሻለ ደሞዝ ፍለጋ ወደ ሌላ አገር ለመሄድ አሮጌ አውቶቡስ ላይ ሲሳፈር ሁለት ሴቶች ልጆቿን አቅፋ ትመለከተው ነበር። ከዛሬ ነገ ይመለሳል እያለች ስትጠብቅ ወራት ወራትን ወልደው ዓመታት ተቆጠሩ፤ ይሁንና ባሏ የውኃ ሽታ ሆኖ ቀረ። ባሏ ከሄደበት ጊዜ ጀምሮ ሳቢና የራሷንም ሆነ ሚሌና እና ጊልያን የተባሉ ልጆቿን ጉሮሮ ለመድፈን ከኑሮ ጋር ግብ ግብ ገጠመች።
ለመጀመሪያ ጊዜ ከሳቢና ጋር የተገናኘነው በእህቷ ሱቅ ውስጥ ተጨቃጫቂ ደንበኞችን በትዕግሥት ስታስተናግድ ነበር። ድክም ያሉት የሳቢና ዓይኖች ቀኑን ሙሉ ስትለፋ እንደዋለች ያሳብቁባታል። እኔም እሷንና ልጆቿን መጽሐፍ ቅዱስ እንዳስጠናቸው ጠየቅኳት። እሷም “ባጠና ደስ ይለኝ ነበር፤ ግን ምንም ጊዜ የለኝም። ልጆቼን ብታስጠኛቸው ግን ደስ ይለኛል” አለችኝ። እኔም በሐሳቧ ተስማማሁ። ልጆቹ በጥናታቸው እየገፉ ሲሄዱ ሳቢናን ይበልጥ ያወቅኳት ከመሆኑም ሌላ ምን ያህል አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደምትኖር ተረዳሁ።
ሳቢና፣ ልጆቿ ገና እንቅልፍ ላይ ሳሉ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ተነስታ አንድ ትልቅ አሮጌ ብረት ድስት እሳት ላይ ትጥዳለች። ከዚያም የዕለት ጉርስ ለማግኘት የምትሸጠውን ኢምፐናደ የተባለ እንደ ሳንቡሳ ያለ ምግብ ለመሥራት የሚያስፈልጋትን ሥጋ ታበስላለች። የሥጋ ኢምፐናደ ለማዘጋጀት የሚያስፈልጋትን ሊጥ አቡክታ የምታሳድረው ግን ማታ ላይ ነው።
ሳቢና ለዕለት ሥራዋ የሚያስፈልጋትን ዕቃ በሙሉ ማለትም ጃንጥላ፣ የጋዝ ምድጃ፣ ነጭ ጋዝ የያዘ ጠርሙስ፣ ጠረጴዛና በርጩማዎች፣ ድስቶችና ዘይት እንዲሁም ሥጋውንና ሊጡን ጨምሮ ከፍራፍሬ ያዘጋጀችውን መጠጥ በተዋሰችው በእጅ የሚገፋ ጋሪ ላይ በጥንቃቄ ትጭናለች።
ከጠዋቱ 12 ሰዓት ላይ ሳቢና እና ሁለቱ ልጆቿ ጉዞ ለመጀመር ይዘጋጃሉ። ከዚያም አንድ ክፍል ቤታቸውን ቆልፈው ጉዟቸውን ይጀምራሉ። ፊታቸው ላይ ምንም ዓይነት ስሜት የማይነበብ ሲሆን ከመካከላቸው የሚያወራም ሆነ የሚስቅ የለም። ልባቸው ያለው በሚጠብቃቸው ሥራ ላይ ነው። እንዲህ ያለው ሁኔታ፣ በሚስዮናዊ ቤታችን ሆኜ በመስኮት የምመለከተው የዕለት ተዕለት ትዕይንት ነው። ሳቢና፣ በቦሊቪያ ጎዳናዎች ላይ ምግብና መጠጥ ለመሸጥ ወፍ ሲንጫጫ ከቤታቸው ከሚወጡ በርካታ ሴቶች መካከል አንዷ ናት።
ማለዳ 12:30 ላይ ፀሐይዋ ከተራራው ጀርባ ብቅ ስትል ሳቢና እና ልጆቿ ኢምፐናደ የሚሸጡበት ቦታ ይደርሳሉ።
አንዳቸውም ምንም ቃል ሳይተነፍሱ ዕቃቸውን ከጋሪው ላይ ያወርዱና ጊዜያዊ ኩሽናቸውን ያዘጋጃሉ። ሳቢና የመጀመሪያውን ኢምፐናደ በሚንተከተከው ዘይት ላይ ስትጨምረው መንቻቻት ይጀምራል። ቀዝቃዛው የጠዋት አየር በአስደሳች መዓዛ ሲታወድ ረሃብ የሞረሞራቸው ሰዎች ከየአቅጣጫው ብቅ ብቅ ይላሉ።ሳቢና መጀመሪያ ሊገዛት የመጣውን ሰው “ስንት ልስጥህ?” በማለት ትጠይቀዋለች። ከእንቅልፉ በደንብ ያልነቃው ይህ ሰው እንዳቀረቀረ ሁለት ጣቱን ያሳያታል፤ በዚህ ጊዜ ሳቢና ቀላ ቀላ ያሉ ሁለት ትኩስ ኢምፐናደዎችን ትሰጠውና ጥቂት ሳንቲሞች ትቀበለዋለች። እንዲህ ያለው ግብይት ከዚያ በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥ ከመቶ ለሚበልጡ ጊዜያት ይካሄዳል። ሳቢና እና ልጆቿ የመጨረሻውን ኢምፐናደ ከሸጡ በኋላ ዕቃቸውን ሰብስበው ወደ ቤታቸው ያቀናሉ። ሳቢና በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ባከናወነችው ሥራ ምክንያት እግሮቿ የዛሉ ቢሆንም ሁለተኛ ሥራዋን ለመጀመር ወደ እህቷ ሱቅ ትሄዳለች።
የሳቢናን ልጆች ለመጀመሪያ ጊዜ ለማስጠናት እህቷ ሱቅ ስደርስ አንድ ጥግ ላይ ሁለት ትናንሽ በርጩማዎችን አዘጋጅተው ጠበቁኝ። የ9 ዓመቷ ሚሌና እና የ7 ዓመቷ ጊልያን ገና ከመጀመሪያው አንስቶ ለጥናቱ ከፍተኛ ጉጉት የነበራቸው ሲሆን ሁልጊዜም ተዘጋጅተው ይጠብቁኝ ነበር። ዓይን አፋር የነበሩት እነዚህ ልጆች ከጊዜ በኋላ ከእኔ ጋር በነፃነት ማውራት የጀመሩ ከመሆኑም ሌላ እንደ ጓደኛቸው ይመለከቱኝ ጀመር። ሳቢና ይህን ስትመለከት ልቧ ተነካ። ሳቢና ሥራዋ አድካሚ የነበረ ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ ከእኔ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ወሰነች።
ሳቢና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያላት እውቀት እያደገ ሲሄድ ለይሖዋ አምላክ ያላት ፍቅርም የዛኑ ያህል እየጨመረ መጣ። ሳቢና ከዚያ በፊት ተሰምቷት የማያውቅ አንድ ስሜት ማለትም ደስታ ይሰማት ጀመር! በአንድ ወቅት ድካም ይጫጫናትና ፊቷ ላይ የሐዘን ስሜት ይነበብባት የነበረችው ይህች ጎዳና ላይ የምትነግድ ሴት አሁን ተለውጣለች። ጎብጣና አቀርቅራ ትሄድ የነበረችው ሳቢና አሁን ቀና ብላ መሄድ የጀመረች ሲሆን ዓይኗ ላይ ብሩህ ተስፋ ይነበባል። እህቷ እንዲህ ብላለች፦ “ከሳቢና ፊት ላይ ፈገግታ አይጠፋም። ከዚህ በፊት እንዲህ ያለ ነገር አይቼባት አላውቅም።” ሌሎችም ቢሆኑ በእሷም ሆነ በልጆቿ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ተመልክተዋል። ሳቢና ከረጅም ጊዜ በፊት አንስቶ የነበረባትን መንፈሳዊ ጥማት ማርካት ችላለች።
ሳቢና በጥናቷ ደስተኛ ብትሆንም ካለባት የሥራ ጫና የተነሳ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት አልቻለችም ነበር። አንድ ቀን በጉባኤ ስብሰባ ላይ እንድትገኝ ያቀረብኩላትን ግብዣ ተቀበለች። ከዚያ በኋላ ከስብሰባ ቀርታ አታውቅም። ሳቢና በጉባኤ ውስጥ እውነተኛ ጓደኞችን አፍርታለች። በተጨማሪም ይሖዋ ለሚወዱትና እሱን ለማገልገል ሲሉ መሥዋዕትነት ለሚከፍሉ ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር በእርግጥ እንደሚያሟላላቸው ማስተዋል ችላለች።—ሉቃስ 12:22-24፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:8
ሳቢና የተማረችውን ነገር ስለወደደችው ለሌሎች ለማካፈል ፍላጎት አደረባት። ይሁንና “አደባባይ ወጥቶ ስለመስበክ ሳስብ እግሬ ይብረከረክ ነበር” ስትል ተናግራለች። ‘እንደ እኔ ያለች ፈሪና ብዙም ያልተማረች ሴት እንዴት ሌላ ሰው ልታስተምር ትችላለች?’ ብላ ታስብ ነበር። ያም ሆኖ ሌሎች ያሳዩዋት ደግነትና እሷ ራሷ በሕይወቷ ውስጥ ያደረገችው አስደናቂ ለውጥ ይኼንን አስፈላጊ እርምጃ እንድትወስድ አነሳስቷታል። በተጨማሪም ልጆቿ የሚከተሉት የእሷን ምሳሌ እንደሆነ ተገነዘበች። በመሆኑም ምሥራቹን ለሌሎች ማካፈል የጀመረች ሲሆን ልጆቿም በደስታ በስብከቱ ሥራ መካፈል ጀመሩ።
በአሁኑ ጊዜ ሳቢና አድካሚ በሆነ ሥራ ዕለት ዕለት የምትዳክር ድሃና ደስታ የራቃት ሴት አይደለችም። እርግጥ ኑሮዋ ብዙም አልተሻሻለም። የተለወጠው ነገር ለሕይወት ያላት አመለካከት ነው። ሳቢና በአሁኑ ጊዜ የተጠመቀች ክርስቲያን እንደመሆኗ መጠን በዓለም ላይ የሚታየውን ድህነትና የተስፋ መቁረጥ ስሜት ለዘለቄታው የሚያስወግደው የአምላክ መንግሥት መሆኑን ለሌሎች ትሰብካለች።—ማቴዎስ 6:10
አሁን ከሌሊቱ 11 ሰዓት ነው፤ ሳቢና እንደተለመደው ከመኖሪያ ቤቷ ለመውጣት ተዘጋጅታለች። ዛሬ ግን የምትወጣው ኢምፐናደ ለመሸጥ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከክርስቲያን ወንድሞቿና እህቶቿ ጋር ሆና ለመስበክ ቀጠሮ ስላላት ነው። በመንፈሳዊ ሌሎችን ለመርዳት በሳምንት ውስጥ የተወሰነ ሰዓት መመደቧ ተጨማሪ ደስታ አስገኝቶላታል። በሯን ቆልፋ መንገድ ስትጀምር ፊቷ ላይ ደስታ ይነበባል። በዚህ ጊዜ ከቤት የምትወጣው ጋሪ እየገፋች ሳይሆን ትልቅ ቦርሣ ይዛ ነው። በቦርሣዋ ውስጥ የያዘችው ለሰዎች ተስፋ ያዘለ መልእክት ለመናገር የሚረዷትን መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ነው። ሳቢና ፈገግ ብላ “ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እሰብካለሁ ብዬ አስቤም አልሜም አላውቅም። ሥራውን በጣም ወድጄዋለሁ!” በማለት በልበ ሙሉነት ተናግራለች።