በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ድህነት የአምላክ ሞገስ እንደሌለህ የሚያሳይ ምልክት ነው?

ድህነት የአምላክ ሞገስ እንደሌለህ የሚያሳይ ምልክት ነው?

ድህነት የአምላክ ሞገስ እንደሌለህ የሚያሳይ ምልክት ነው?

አምላክ ለጥንቱ የእስራኤል ብሔር “በመካከልህ ድኻ አይኖርም” ብሎ ነበር። ይህ ሊሆን የቻለው አምላክ በሰጣቸው ሕግ ላይ ለድሆች ምን መደረግ እንዳለበት ሌላው ቀርቶ ከዕዳ ነፃ መሆን የሚችሉት እንዴት እንደሆነ የሚገልጽ መመሪያ በመኖሩ ነው። (ዘዳግም 15:1-4, 7-10) በመሆኑም ይሖዋ እንደሚባርካቸው ቃል ስለገባላቸው በእስራኤላውያን መካከል ድሃ አይኖርም ነበር። ይሁንና እስራኤላውያን ይህን በረከት ማግኘታቸው የተመካው ሕጉን በመታዘዛቸው ላይ ነው፤ እነሱ ግን ይህን ሳያደርጉ ቀርተዋል።

ይህ ሲባል ግን ሀብት የሌላቸው ሰዎች የአምላክን ሞገስ አጥተዋል ሀብታም የሆኑት ደግሞ ሞገሱን አግኝተዋል ማለት አይደለም። ታማኝ የሆኑ በርካታ የአምላክ አገልጋዮች ቁሳዊ ሀብት አልነበራቸውም። ነቢዩ አሞጽ የበግ እረኛና የጉልበት ሠራተኛ ነበር። (አሞጽ 1:1፤ 7:14) ነቢዩ ኤልያስ በኖረበት ዘመን እስራኤል በረሃብ ተመትታ የነበረ ሲሆን ኤልያስ ይህን ችግር ለማለፍ በአንዲት ድሃ መበለት ቤት በእንግድነት መቀመጥ ግድ ሆኖበት ነበር፤ ይህች ሴት የነበራት ጥቂት ዱቄትና ዘይት የረሃቡ ወቅት እስኪያልፍ ድረስ ተአምራዊ በሆነ መንገድ መበርከት ችሎ ነበር። ኤልያስም ሆነ መበለቷ ሀብታም አልሆኑም፤ ይሖዋ የሚያስፈልጓቸውን መሠረታዊ ነገሮች ብቻ አሟልቶላቸዋል።—1 ነገሥት 17:8-16

ያልተጠበቁ ክስተቶች፣ ሰዎች በድንገት ለድህነት እንዲዳረጉ ሊያደርጓቸው ይችላሉ። ድንገተኛ አደጋና ሕመም አንድን ሰው ለጊዜው አሊያም ለዘለቄታው ሥራ እንዳይሠራ ያግደው ይሆናል። በተጨማሪም ሞት ልጆችን ወላጅ አልባ፣ ሴቶችን ደግሞ መበለት ሊያደርግ ይችላል። እነዚህ አሳዛኝ ክስተቶች አንድ ሰው የአምላክ ሞገስ እንደሌለው የሚያሳዩ አይደሉም። ስለ ኑኃሚንና ስለ ሩት የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ይሖዋ ለድሆች ልባዊ አሳቢነት እንደሚያሳይ የሚጠቁም ግሩም ምሳሌ ነው። ኑኃሚንና ሩት ባሎቻቸውን በሞት በመነጠቃቸው ምክንያት ለከፋ ድህነት ቢዳረጉም ይሖዋ አምላክ የባረካቸው ሲሆን የሚያስፈልጋቸውን ቁሳዊ ነገር አሟልቶላቸዋል።—ሩት 1:1-6፤ 2:2-12፤ 4:13-17

ድህነት አንድ ሰው የአምላክን ሞገስ እንዳጣ የሚያሳይ ማስረጃ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ለይሖዋ አምላክ ታማኝ የሆኑ ሰዎች ንጉሥ ዳዊት እንደሚከተለው በማለት በተናገረው ሐሳብ ሊተማመኑ ይችላሉ፦ “ጐልማሳ ነበርሁ፤ አሁን አርጅቻለሁ፤ ነገር ግን ጻድቅ ሲጣል፣ ዘሩም እንጀራ ሲለምን አላየሁም።”—መዝሙር 37:25

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኑኃሚንና ሩት ለከፋ ድህነት ቢዳረጉም የአምላክ ፍቅራዊ እንክብካቤና በረከት አልተለያቸውም