በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቫቲካን ኮዴክስ—እንደ ውድ ሀብት የሚታየው ለምንድን ነው?

ቫቲካን ኮዴክስ—እንደ ውድ ሀብት የሚታየው ለምንድን ነው?

ቫቲካን ኮዴክስ​—እንደ ውድ ሀብት የሚታየው ለምንድን ነው?

በቫቲካን በርካታ ቅርሶች ይገኛሉ። የቫቲካን ሥዕሎች፣ ቅርጻ ቅርጾችና ሕንፃዎች ልዩ ውበትና ግርማ እንዳላቸው ይነገርላቸዋል። ያም ሆኖ በቫቲካን ከሚገኙት እጅግ ውድ የሆኑ ቅርሶች መካከል አንዱ ለበርካታ መቶ ዓመታት ከሰዎች እይታ እንዲሰወር ተደርጎ ነበር። በቫቲካን ቤተ መጻሕፍት ውስጥ፣ ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት የተጻፈውን የአምላክ ቃል አንዳንድ ክፍሎች በተሻለ መንገድ እንድንረዳ የሚያስችል በእጅ የተገለበጠ ውድ ጽሑፍ ይገኛል። ይህ ጽሑፍ ቫቲካን ኮዴክስ በመባል ይታወቃል። *

ምሑራን ከፍተኛ ግምት የሚሰጧቸው አሌክሳንድራይን ኮዴክስ እና ሳይናይቲክ ኮዴክስ የተባሉ ሁለት ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ግልባጮች ስለተገኙበትም ሆነ ከጥፋት ስለተረፉበት መንገድ የሚናገረው ታሪክ በጣም አስገራሚ ነው። በሌላ በኩል ግን ስለ ቫቲካን ኮዴክስ አመጣጥ እምብዛም የሚታወቅ ነገር የለም።

የተደበቀ ውድ ሀብት

ቫቲካን ኮዴክስ ምንጩ የት ነው? ይህ ኮዴክስ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው በ15ኛው መቶ ዘመን በቫቲካን ቤተ መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ ነው። ምሑራን ይህ ኮዴክስ የተጻፈው በግብፅ፣ በቂሳርያ ሌላው ቀርቶ በሮም ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ። ይሁንና በእንግሊዝ የሚገኘው የበርሚንግሃም ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ጄምስ ኔቨል በርድዞል፣ እነዚህን ግምታዊ ሐሳቦች ከገመገሙ በኋላ የሚከተለው ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል፦ “በአጭር አነጋገር ኮዴክስ ቫቲካኑስ የተጻፈበትን ትክክለኛ ቀንም ሆነ ቦታ በእርግጠኝነት መናገር አንችልም፤ ምሑራን ምንም ያህል ጥረት ቢያደርጉ ይህ ኮዴክስ ከአሥራ አምስተኛው መቶ ዘመን በፊት ስለነበረበት ሁኔታ ምንም ዓይነት መረጃ ማግኘት አልቻሉም።” ያም ሆኖ ቫቲካን ኮዴክስ በጣም ጠቃሚ ከሆኑትና ሁሉንም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከያዙት የጥንት ቅጂዎች መካከል አንዱ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

ላለፉት መቶ ዓመታት አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ገልባጮች በሥራቸው ላይ የተወሰኑ ስህተቶችን ሠርተዋል። በዚህም ምክንያት ታማኝ መሆን የሚፈልጉ ተርጓሚዎች ከሚያጋጥሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች አንዱ መጀመሪያ ከተጻፉት የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ጋር የሚስማሙ አስተማማኝ ቅጂዎችን ማግኘት ነበር። ከዚህ የተነሳ ምሑራን በአራተኛው መቶ ዘመን ማለትም ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ከተጠናቀቀ 300 ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንደተዘጋጀ የሚታመነውን ቫቲካን ኮዴክስ የተባለውን ይህን ግሪክኛ ቅጂ ለመመርመር ምን ያህል ጓጉተው እንደነበር መገመት አያዳግትም! ይህ ኮዴክስ በጊዜ ሂደት ከጎደሉት ጥቂት ገጾች በስተቀር የዕብራይስጥ እና የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን በሙሉ የያዘ ነው።

የቫቲካን ባለሥልጣናት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን በዚህ ኮዴክስ እንዲጠቀሙ ለበርካታ ዓመታት ፈቃደኛ አልነበሩም። ሰር ፍሬድሪክ ኬንዮን የተባሉ ታዋቂ የሥነ ጽሑፍ ምሑር እንደሚከተለው ሲሉ ተናግረዋል፦ “በ1843 [የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር የሆነው ኮንስታንቲን ቮን] ቲሸንዶርፍ ለብዙ ወራት ከታገሠ በኋላ ኮዴክሱን ለስድስት ሰዓታት እንዲያይ ተፈቀደለት። . . . በ1845 ደግሞ ትሬጌለስ የተባለው ታላቁ እንግሊዛዊ ምሑር አንዲትም ቃል እንኳ ሳይገለብጥ ኮዴክሱን እንዲያይ ተፈቀደለት።” ቲሸንዶርፍ ኮዴክሱን እንደገና እንዲያይ እንዲፈቀድለት ጠየቀ፤ ሆኖም 20 ገጾችን ከገለበጠ በኋላ ተከለከለ። ኬንዮን እንደሚከተለው በማለት ሪፖርት አድርገዋል፦ “ቲሸንዶርፍ ለሁለተኛ ጊዜ ይግባኝ ማለቱ ለስድስት ቀን ጥናት ማድረግ የሚያስችል ፈቃድ አስገኘለት፤ ይህ ደግሞ ኮዴክሱን በጠቅላላው ለአሥራ አራት ቀን ለሦስት ለሦስት ሰዓት እንዲያጠና አስችሎታል። ቲሸንዶርፍ የተፈቀደለትን ጊዜ በሚገባ ስለተጠቀመበት በ1867 ፈጽሞ ተወዳዳሪ የሌለው ቅጂ ማሳተም ችሏል።” ከጊዜ በኋላ ቫቲካን ይህን ኮዴክስ በመገልበጥ የተሻለ ቅጂ አዘጋጅታለች።

“በከፍተኛ ጥንቃቄ የተገለበጠ”

ቫቲካን ኮዴክስ ምን ነገሮችን ግልጽ ለማድረግ አስችሏል? ዚ ኦክስፎርድ ኢለስትሬትድ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ባይብል እንደገለጸው ቫቲካን ኮዴክስ “ሆሄያቱ አቀማመጣቸው ወጥነት እንዳለውና ሲገለበጥ ስህተት እንዳልተሠራ ለማረጋገጥ አስችሏል፤ ይህ ደግሞ ጥራት ባለው መንገድ በጥንቃቄ እንደተገለበጠ ያሳያል።” ይኸው ጽሑፍ አክሎ “ኮዴክሱ በጣም ጥሩ ችሎታ ባለው ገልባጭ የተዘጋጀ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል” ብሏል።

ቫቲካን ኮዴክስ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ከተገነዘቡት ታዋቂ ምሑራን መካከል ብሩክ ፎስ ዌስትኮት እና ፌንተን ጆን አንቶኒ ሆርት ይገኙበታል። በቫቲካን ኮዴክስና በሳይናይቲክ ማኑስክሪፕት ላይ ተመሥርቶ የተዘጋጀውና በ1881 የታተመው ኒው ቴስታመንት ኢን ዚ ኦሪጅናል ግሪክ የተሰኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉማቸው፣ አዲስ ዓለም ትርጉምን እና በጆሴፍ ብራያንት ሮተርሃም የተዘጋጀው ዚ ኤምፈሳይዝድ ባይብልን ጨምሮ በዘመናችን ለተዘጋጁ በርካታ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት (አዲስ ኪዳን) ትርጉሞች ዋነኛ ምንጭ ሆኖ አገልግሏል።

ይሁንና አንዳንድ ሐያሲያን ዌስትኮት እና ሆርት ትርጉማቸውን በቫቲካን ኮዴክስ ላይ ተመሥርተው ማዘጋጀታቸው ትክክል እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። ይሁንና ይህ ኮዴክስ መጀመሪያ የተጻፉትን የቅዱሳን መጻሕፍት ሐሳብ በትክክል ያስተላልፋል? ከ1956 እስከ 1961 ባሉት ዓመታት ውስጥ የታተመው ቦድመር ፓፒሪ የተባለው ጽሑፍ፣ በሦስተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ የተዘጋጀ የሉቃስንና የዮሐንስን ወንጌል የተወሰነ ክፍል አካትቶ ስለያዘ ምሑራንን በእጅጉ አስደንቆ ነበር። ይሁንና ይህ ጽሑፍ በኋላ ላይ ከተዘጋጀው ከቫቲካን ኮዴክስ ጋር ይስማማል?

ፊለፕ ፔን እና ፖል ካናርት ኖቨም ቴስታመንተም በተሰኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉማቸው ላይ “ቫቲካኑስ ኮዴክስና ቦድመር ፓፒሪ የሚያስገርም ተመሳሳይነት አላቸው” ብለው ነበር። “ከዚህ በመነሳት ቫቲካኑስ ኮዴክስን የጻፈው የመጀመሪያው ግለሰብ የተጠቀመበት ምንጭ ከቦድመር ፓፒሪ ጋር ተመሳሳይ ነው ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው። በመሆኑም ይህ ግለሰብ የገለበጠው እጅግ ጥንታዊ ከሆነ አሊያም ከጥንታዊው በቀጥታ ከተገለበጠ ጽሑፍ ላይ መሆን አለበት።” ፕሮፌሰር በርድዞል እንዲህ ብለዋል፦ “ሁለቱ ጥንታዊ ጽሑፎች እርስ በርሳቸው በጣም ይመሳሰላሉ። . . . [ቫቲካን ኮዴክስ] በጥንቃቄ የተገለበጠ ነው፦ ምንጩ ራሱ ትክክለኛ መሆኑን ለማረጋገጥ በጥንቃቄ ተገምግሞ በከፍተኛ ጥንቃቄ የተገለበጠ ነው።”

ተርጓሚዎችን በጣም ይጠቅማል

እርግጥ ነው፣ በጣም ጥንታዊ የሚባለው ግልባጭ መጀመሪያ ከተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት ጋር ተመሳሳይ የማይሆንበት ጊዜ አለ። ይሁን እንጂ ምሑራን ቫቲካን ኮዴክስን ከሌሎች ጥንታዊ ግልባጮች ጋር ማወዳደራቸው መጀመሪያ የተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት ይዘት ምን እንደሚመስል ለማወቅ በጣም ረድቷቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በአራተኛው መቶ ዘመን የተዘጋጀው ሳይናይቲክ ማኑስክሪፕት ከዘፍጥረት እስከ 1 ዜና መዋዕል ያሉት የታሪክ መጻሕፍት አብዛኛው ክፍል ጎድሎታል። ይሁን እንጂ እነዚህ መጻሕፍት በቫቲካን ኮዴክስ ውስጥ መገኘታቸው በእርግጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መሆናቸውን ለማረጋገጥ አስችሏል።

ዚ ኦክስፎርድ ኢለስትሬትድ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ባይብል እንደገለጸው ከሆነ “ስለ ክርስቶስ ማንነት እና ስለ ቅዱስ ሥላሴ የሚናገሩ ጥቅሶች” ምሑራንን በጣም የሚያወዛግቡ ናቸው። ቫቲካን ኮዴክስ እነዚህን ጥቅሶች ግልጽ የሚያደርገው እንዴት ነው?

እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። በ⁠ዮሐንስ 3:13 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ኢየሱስ “ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም” ሲል ተናግሯል። አንዳንድ ተርጓሚዎች እዚህ ጥቅስ ላይ “እርሱም የሰው ልጅ በሰማይ የሚኖር” የሚል ሐሳብ ጨምረዋል። ይህ ሐሳብ የተጨመረው ኢየሱስ ምድር በነበረበት ጊዜም ሰማይ ላይም ነበረ የሚል ስሜት በመፍጠር የሥላሴ ትምህርት ትክክል እንደሆነ ለማስተማር ነው። ይህ ተጨማሪ ሐሳብ የሚገኘው በአምስተኛውና በአሥረኛው መቶ ዘመን በተዘጋጁ ጥቂት የጥንት የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ላይ ነው። ይሁንና ይህ ሐሳብ በቫቲካን ኮዴክስና በሳይናይቲክ ማኑስክሪፕት ውስጥ አለመኖሩ በዘመናችን የሚገኙ በርካታ ተርጓሚዎች ከትርጉማቸው ውስጥ እንዲያወጡት አድርጓቸዋል። ይህ ሐሳብ መውጣቱ የክርስቶስን ማንነት በተመለከተ የተፈጠረውን ውዝግብ የሚፈታ ከመሆኑም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርስ ስምም እንዲሆን ያደርጋል። ኢየሱስ በአንድ ጊዜ በሰማይም በምድርም አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ ከሰማይ የመጣ ሲሆን ወደ አባቱ ‘በማረግ’ እንደገና ወደ ሰማይ ይመለሳል።ዮሐንስ 20:17

በተጨማሪም ቫቲካን ኮዴክስ አምላክ ለምድር ስላለው ዓላማ የሚናገሩ ጥቅሶችን በግልጽ እንድንረዳ ያስችለናል። እስቲ ይህን ምሳሌ ተመልከት። ኪንግ ጄምስ ቨርሽን ሐዋርያው ጴጥሮስ የተናገረውን ትንቢት “ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል” በማለት ተርጉሞታል። (2 ጴጥሮስ 3:10) በአምስተኛው መቶ ዘመን በተዘጋጀው አሌክሳንድሪን ኮዴክስና ከዚያ በኋላ በተዘጋጁ የጥንት ቅጂዎች ላይ የተመሠረቱ ሌሎች ትርጉሞችም ይህን ጥቅስ የተረጎሙት በተመሳሳይ መንገድ ነው። በመሆኑም እንዲህ ያለው ትርጉም ቅን ልብ ያላቸው በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢያን አምላክ ምድርን ያጠፋታል የሚል መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል።

ይሁን እንጂ አሌክሳንድሪን ኮዴክስ ከመዘጋጀቱ ከአንድ መቶ ዓመት ገደማ በፊት፣ ቫቲካን ኮዴክስ (እንዲሁም በዚያው ዘመን የተዘጋጀው ሳይናይቲክ ማኑስክሪፕት) ጴጥሮስ የተናገረውን ትንቢት “ምድርና በላይዋ የተሠሩ ነገሮችም ይጋለጣሉ” በማለት ተርጉመውታል። የዚህ ትርጉም ሐሳብ ከተቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ጋር ይስማማል? እንዴታ! ቅዱሳን መጻሕፍት በሌላ ቦታ ላይ ግዑዟ ምድር ‘ለዘላለም እንደማትናወጥ’ ይናገራሉ። (መዝሙር 104:5) ታዲያ ምድር ‘የምትጋለጠው’ እንዴት ነው? ሌሎች ጥቅሶች “ምድር” የሚለው ቃል ምሳሌያዊ ትርጉም ሊኖረው እንደሚችል ያሳያሉ። ለምሳሌ ያህል፣ “ምድር” መናገርም ሆነ መዘመር እንደምትችል ተደርጋ ተገልጻለች። (ዘፍጥረት 11:1 የ1954 ትርጉም፤ መዝሙር 96:1) በመሆኑም “ምድር” የሰው ልጆችን አሊያም ሕዝብን ልታመለክት ትችላለች። አምላክ ፕላኔቷ ምድራችንን እንደማያጠፋ ከዚህ ይልቅ ክፋትና ክፉ አድራጊዎች እንዲጋለጡ ብሎም ከምድር ገጽ እንዲጠፉ እንደሚያደርግ ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና ነው!

“ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል”

የሚያሳዝነው ነገር ቫቲካን ኮዴክስ ለበርካታ መቶ ዓመታት ከሰዎች እይታ ተሰውሮ በመቆየቱ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢያን አንዳንድ ጥቅሶችን በአብዛኛው በተሳሳተ መንገድ እንዲረዱት ምክንያት ሆኗል። ይሁንና ቫቲካን ኮዴክስ ከታተመበት ጊዜ ጀምሮ ይህ ጥንታዊ ቅጂም ሆነ በዘመናችን የሚገኙ አስተማማኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች፣ እውነትን የሚፈልጉ ሰዎች ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንዲማሩ ረድተዋል።

በጥንት ዘመን የኖሩ ገልባጮች “[ይህን] የጻፉ እጆች መቃብር ውስጥ ይበሰብሳሉ፤ ጽሑፉ ግን ለዘመናት ይኖራል” የሚለውን ሐሳብ አብዛኛውን ጊዜ በጽሑፎቻቸው ላይ ያሰፍሩ ነበር። ሁላችንም ስማቸው ያልተጠቀሱት እነዚህ ገልባጮች ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ያከናወኑትን ተግባር እናደንቃለን። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ እስከ አሁን ድረስ በመቆየቱ ሊመሰገን የሚገባው ከብዙ ዘመናት በፊት የሚከተለውን ሐሳብ ያስጻፈው ፈጣሪ ነው፦ “ሣሩ ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”—ኢሳይያስ 40:8

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 ቫቲካን ኮዴክስ አንዳንድ ጊዜም ቫቲካን ማኑስክሪፕት ቁ. 1209 ወይም ኮዴክስ ቫቲካኑስ ተብሎም የሚጠራ ሲሆን አብዛኞቹ ምሑራን “B” የሚል ስያሜ ሰጥተውታል። ጽሑፎች በመጻሕፍት መልክ መጠረዝ በጀመሩበት ዘመን ‘ኮዴክስ’ ተብለው ይጠሩ ነበር። በሰኔ 1, 2007 መጠበቂያ ግንብ ላይ የሚገኘውን “ከጥቅልል ወደ ኮዴክስ—መጽሐፍ ቅዱስ በመጽሐፍ መልክ የተዘጋጀበት መንገድ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ ጽሑፎች የተጻፉበት ጊዜ የሚታወቀው እንዴት ነው?

አንዳንድ ገልባጮች ጽሑፉን ገልብጠው ያጠናቀቁበትን ቀን የመዘገቡ ቢሆንም በግሪክኛ የተዘጋጁ አብዛኞቹ የጥንት ግልባጮች እንዲህ ያለው መረጃ የላቸውም። ታዲያ ምሑራን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥንታዊ ግልባጮች የተጻፉበትን ጊዜ የሚገምቱት እንዴት ነው? እንደ ቋንቋና የሥነ ጥበብ ሥራዎች ሁሉ የእጅ ጽሑፍም ከትውልድ ትውልድ ይለያያል። ለምሳሌ ያህል፣ በትላልቅ ፊደላት (ካፒታል ሌተር) የሚጻፈውና አንሺያል ተብሎ የሚታወቀው የፊደል አጣጣል በአራተኛው መቶ ዘመንም ሆነ ከዚያ በኋላ ባሉ በርካታ መቶ ዓመታት ጥቅም ላይ ውሎ ነበር። ጠንቃቃ ምሑራን ቀን የሌላቸውን በአንሺያል የአጻጻፍ ስልት የተጻፉ የጥንት ግልባጮችን ቀናቸው ከተገለጸና ተመሳሳይ የአጻጻፍ ስልት ከተጠቀሙ ግልባጮች ጋር በማወዳደር የተጻፉበትን ጊዜ በተመለከተ የተሻለ ግምት መስጠት ችለዋል።

እርግጥ ነው፣ ይህ ዘዴ የራሱ የሆነ ችግር ይኖረዋል። የፕሪንስተን መንፈሳዊ ኮሌጅ ፕሮፌሰር የሆኑት ብሩስ ሜትስገር እንዲህ ብለዋል፦ “አንድ ሰው የእጅ ጽሑፉ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ አንድ ዓይነት ሊሆን ስለሚችል አንድ ጽሑፍ የተጻፈበትን ጊዜ ከሃምሳ ዓመት ባነሰ ክልል ውስጥ ለመገመት መጣር ምክንያታዊ አይደለም።” በርካታ ምሑራን ሁኔታውን በጥንቃቄ ካመዛዘኑ በኋላ ቫቲካን ኮዴክስ በአራተኛው መቶ ዘመን ተጽፏል ወደሚል ስምምነት ደርሰዋል።