በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክርስትና ጦርነትን ይደግፋል?

ክርስትና ጦርነትን ይደግፋል?

ክርስትና ጦርነትን ይደግፋል?

“ጦርነት ወንጀል ወይም ኃጢአት የሚሆነው የትኛውን የሥነ ምግባር መሥፈርት ስለሚጥስ ነው? በእርግጥ ይህ እንቆቅልሽ ነው።”—የክርስትና ሥነ ምግባር ፕሮፌሰር የሆኑት ኦሊቨር ኦዶነቨን

በካናዳ የጦርነት ሙዚየም ውስጥ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የተከሰተውን ሁኔታ የሚያሳይ ሳክሪፋይስ ወይም መሥዋዕት የሚል ስያሜ የተሰጠው አንድ ሥዕል ይገኛል፤ በዚህ ሥዕል ላይ የሞቱ ወታደሮች፣ በጦርነቱ የተሰላቹ ወታደሮችና የእነሱን መምጣት የሚጠባበቁ ቤተሰቦቻቸው ይታያሉ። ከላይ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ይታያል። አንዳንድ ጎብኚዎች “የሰላም ልዑል” የሆነው የኢየሱስ ሥዕል ጦርነትን ከሚያሳዩ ሥዕሎች ጎን ተቀምጦ ማየታቸው በጣም አስደንግጧቸዋል። (ኢሳይያስ 9:6) የአገራቸው ሰዎች ለከፈሉት መሥዋዕትነት አድናቆት ያላቸው ሌሎች ሰዎች ደግሞ ክርስቲያኖች የአገራቸውን ዳር ድንበርና ነፃነት ለማስጠበቅ ሲሉ በጦርነት እንዲካፈሉ አምላክና ልጁ እንደሚጠብቁባቸው ይሰማቸዋል።

የሃይማኖት መሪዎች ለብዙ ዘመናት ጦርነትን የሚደግፍ መልእክት ሲሰብኩ ኖረዋል። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምሑር የነበረው ኦገስቲን በ417 ዓ.ም. እንደሚከተለው ሲል ጽፏል፦ “መሣሪያ ታጥቆ በወታደርነት የሚያገለግል ማንኛውም ሰው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የለውም ብላችሁ ማሰብ የለባችሁም። . . . ሌሎች ሰዎች ለእናንተ ሲሉ በጸሎት አማካኝነት ከማይታዩ ጠላቶች ጋር ሲዋጉ እናንተ ደግሞ እነሱን ለመጠበቅ በዓይን ከሚታዩ አረመኔዎች ጋር ትዋጋላችሁ።” በ13ኛው መቶ ዘመን የኖረው ቶማስ አኩዋይነስ “ጦርነቶች ምስኪኖችንና አገሪቱን ከጠላት ጥቃት ለመጠበቅ እስካስቻሉ ድረስ ተገቢና ተቀባይነት ያላቸው ናቸው” ብሎ ነበር።

አንተስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይሰማሃል? ሰዎች ጦርነት ውስጥ የሚገቡት ለተቀደሰ ዓላማ ይኸውም የአገራቸውን ነፃነት ለማስጠበቅ ወይም የተጨቆኑ ሰዎችን ነፃ ለማውጣት ከሆነ ጦርነት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል ብለህ ታስባለህ? ክርስቲያኖች ጦርነትን በተመለከተ የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ ለማወቅ የሚያስችላቸው “የሥነ ምግባር መሥፈርት” የትኛው ነው?

ኢየሱስ ክርስቶስ የተወው ምሳሌ

በዚህ ዘመን ስለሚደረጉ ጦርነቶችና ይህን ስለመሳሰሉ ከባድ ርዕሰ ጉዳዮች አምላክ ምን አመለካከት እንዳለው ማወቅ ይቻላል? ሐዋርያው ጳውሎስ “‘ያስተምረው ዘንድ የይሖዋን አስተሳሰብ ያወቀ ማን ነው?’ እኛ ግን የክርስቶስ አስተሳሰብ አለን” ማለቱ እንዲህ ብለን መጠየቃችን አግባብነት እንዳለው ያሳያል። (1 ቆሮንቶስ 2:16) ይሖዋ አምላክ አስተሳሰቡን እንድናውቅ ለመርዳት ኢየሱስን ወደ ምድር ልኮታል። ኢየሱስ የተናገረውም ሆነ ያደረገው ነገር የይሖዋን አስተሳሰብና መንገድ የሚያንጸባርቅ ነው። ታዲያ ኢየሱስ ስለ ጦርነት ምን ተናግሯል? ጦርነትን በሚመለከት ምን አቋም ነበረው?

የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወትና ደኅንነት ከመጠበቅ የተሻለ ለጦርነት ምክንያት ሊሆን የሚችል ምን ነገር ይኖራል? ከተከታዮቹ አንዱ እንዲህ ተሰምቶት ነበር። ኢየሱስ በአንድ ደቀ መዝሙሩ አልፎ በተሰጠና በውድቅት ሌሊት መሣሪያ በታጠቁ ሰዎች በተያዘ ጊዜ ወዳጁ ጴጥሮስ “እጁን ሰዶ ሰይፉን በመምዘዝ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ጆሮውን ቆረጠው።” ጴጥሮስ ሰይፍ መምዘዙ ተገቢ ነበር? በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ጴጥሮስን “ሰይፍህን ወደ ቦታው መልስ፤ ሰይፍ የሚመዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” አለው።—ማቴዎስ 26:47-52

ኢየሱስ እንዲህ ብሎ መናገሩ ምንም አያስደንቅም። ምክንያቱም ይህን ከመናገሩ ከሁለት ዓመት በፊት እንደሚከተለው ብሎ ነበር፦ “‘ባልንጀራህን ውደድ፣ ጠላትህን ጥላ’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ለጠላቶቻችሁ ፍቅር ማሳየታችሁን እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ መጸለያችሁን ቀጥሉ፤ ይህን ብታደርጉ በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ። ምክንያቱም እሱ በክፉና በጥሩ ሰዎች ላይ ፀሐዩን ያወጣል፤ ጻድቅ በሆኑና ጻድቅ ባልሆኑ ሰዎች ላይም ዝናብ ያዘንባል።” (ማቴዎስ 5:43-45) አንድ ክርስቲያን በጠላቶቹ ላይ ጦርነት ከፍቶ እያለ እነሱን ይወዳቸዋል እንዲሁም ይጸልይላቸዋል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ይሆናል?

ክርስቲያኖች ብዙ ጠላቶች እንደነበሯቸው ከታሪክ መመልከት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል፣ ሮማውያን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የፈረዱበት ከመሆኑም ሌላ እንዲገደል አድርገዋል። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ክርስቲያኖች የጥቃት ዒላማ ሆኑ። ኢየሱስ፣ አንዳንድ አይሁዳውያን እንዳደረጉት ሁሉ ክርስቲያኖችም ከሮማውያን የጭቆና ቀንበር ለመላቀቅ ሲሉ መሣሪያ በመታጠቅ ዓመፅ ለማስነሳት ሊፈተኑ እንደሚችሉ ተሰምቶት ነበር። በዚህም ምክንያት ተከታዮቹን አስመልክቶ ሲናገር “እኔ የዓለም ክፍል እንዳልሆንኩ ሁሉ እነሱም የዓለም ክፍል አይደሉም” ብሏል። (ዮሐንስ 17:16) ስለሆነም ክርስቲያኖች በፖለቲካ ጉዳዮች ረገድ ገለልተኞች ለመሆን መርጠዋል። በእነሱ ላይ የሚፈጸመው ግፍም ሆነ አገራቸው ላይ የተደቀነው ስጋት በጦርነት እንዲካፈሉ አላደረጋቸውም።

የአምላክ መንግሥት ደጋፊዎች

እውነተኛ ክርስቲያኖች የኢየሱስን ፈቃድ ለመፈጸም ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ገለልተኝነታቸውን ጠብቀዋል። በትንሿ እስያ ትገኝ በነበረችው ኢቆንዮን በተባለች የጥንት ከተማ ውስጥ ምን እንደተከሰተ እስቲ እንመልከት። “አሕዛብና አይሁዳውያን ከገዥዎቻቸው ጋር ሆነው ሊያንገላቷቸውና በድንጋይ ሊወግሯቸው ቆርጠው በተነሱ ጊዜ ጳውሎስና በርናባስ ይህን ስላወቁ ልስጥራና ደርቤ ወደሚባሉት የሊቃኦንያ ከተሞች እንዲሁም በዙሪያቸው ወዳለው አገር ሸሹ፤ በዚያም ምሥራቹን ማወጃቸውን ቀጠሉ።” (የሐዋርያት ሥራ 14:5-7) ክርስቲያኖች ከባድ ተቃውሞ በገጠማቸው ጊዜ ራሳቸውን ለመከላከልም ሆነ ለመበቀል መሣሪያ እንዳላነሱ ልብ በል። ከዚህ ይልቅ “ምሥራቹን” መስበካቸውን ቀጥለዋል። የሰበኩት ስለ ምን የሚናገር ምሥራች ነበር?  

ክርስቲያኖች የሰበኩት ኢየሱስ ይሰብክ የነበረውን መልእክት ነበር። ኢየሱስ “የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ” ሲል ተናግሯል። (ሉቃስ 4:43) ኢየሱስና ተከታዮቹ የአምላክ መንግሥት ደጋፊዎች ነበሩ። ክርስቶስ ይህን መንግሥት ለመጠበቅ ወታደራዊ ኃይል ተጠቅሞ አያውቅም። እንዲህ ብሎ ነበር፦ “መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም። መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል ቢሆን ኖሮ በአይሁዳውያን እጅ እንዳልወድቅ አገልጋዮቼ ይዋጉልኝ ነበር። አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለም።”—ዮሐንስ 18:36

‘በመካከላችሁ ፍቅር ይኑራችሁ’

በጦርነት ወቅት ገለልተኛ አቋም መያዝ የእውነተኛው አምልኮ መለያ ምልክት ነው። ኢየሱስ “በመካከላችሁ ፍቅር ካለ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። (ዮሐንስ 13:35) የጦር መሣሪያ ለማንሳት ፈቃደኛ አለመሆናቸው ፌዝ፣ እስርና ሞት ቢያስከትልባቸውም እንኳ እንዲህ ያለውን ፍቅር የሚያሳዩ በርካታ ሰዎች አሉ፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲህ ያለ ቡድን መኖሩን ማወቃቸው በጣም አስደስቷቸዋል።

በናዚ ቁጥጥር ሥር በነበሩ የአውሮፓ አገሮች ውስጥ ባለሥልጣናት፣ ገለልተኛ አቋም በመያዛቸው ምክንያት ወደ ማጎሪያ ካምፖች የተላኩትን ወደ 3,000 የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮች ጨምሮ 10,000 የሚያህሉ የይሖዋ ምሥክሮችን አስረው ነበር። በዚህ ወቅት በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ ከ4,300 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮችም የውትድርና አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ታስረው ነበር። በጀርመንም ሆነ በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያን ወንድሞቻቸውንም ሆነ ሌላ ማንኛውንም ሰው ለመውጋት ሲሉ የጦር መሣሪያ አላነሱም። በጦርነት ተካፍለው ቢሆን ኖሮ እርስ በርስ እንደሚዋደዱም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ፍቅር እንዳላቸው አፋቸውን ሞልተው መናገር ይችሉ ነበር?

በርካታ ሰዎች ራስን ከጥቃት ለመከላከል ጦርነት የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይሁንና እስቲ የሚከተለውን ልብ በል፦ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ጭካኔ የተሞላበት ስደት ሲደርስባቸው የአጸፋ እርምጃ ለመውሰድ ባይነሳሱም እንኳ ከምድር ገጽ አልጠፉም። ኃያል የነበረው የሮም አገዛዝ ክርስትናን ማጥፋት አልቻለም። እውነተኛ ክርስቲያኖች በዛሬው ጊዜም ቢሆን በቁጥር እየበዙ የመጡ ሲሆን በገለልተኝነት አቋማቸው ጸንተዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች የአጸፋ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ አምላክ እንደሚረዳቸው ይተማመናሉ። የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፤ ከዚህ ይልቅ ‘በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ ይላል ይሖዋ’ ተብሎ ስለተጻፈ ለአምላክ ቁጣ ዕድል ስጡ።”—ሮም 12:19

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የአምላክ ድጋፍ የነበራቸው ጦርነቶች

የክርስትና እምነት ከመመሥረቱ ከመቶ ዓመታት በፊት የአምላክ ምርጥ ሕዝብ የነበሩት የጥንቶቹ እስራኤላውያን ሠራዊት እንዲያደራጁና እንዲዋጉ የታዘዙባቸው ጊዜያት ነበሩ። እስራኤላውያን ለአብርሃም ቃል ወደተገባለት ወደ ከነዓን ምድር ከመግባታቸው በፊት እንዲህ የሚል ትእዛዝ ተሰጥቷቸው ነበር፦ “አምላክህ እግዚአብሔር [ሰባቱን ነገሥታት] በእጅህ አሳልፎ በሰጠህና አንተም ድል ባደረግሃቸው ጊዜ፣ ሁሉንም ፈጽመህ ደምስሳቸው፤ ከእነርሱ ጋር አትዋዋል፤ አትራራላቸውም።” (ዘዳግም 7:1, 2) የእስራኤል ጄኔራል የነበረው ኢያሱ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ባዘዘውም መሠረት” እነዚህን ብሔራት ድል አድርጓል።—ኢያሱ 10:40

ይህ ጦርነት እስራኤላውያን ባዕድ አገሮችን ለመበዝበዝ ሲሉ ያደረጉት ጭካኔ የተሞላበት ወረራ ነበር? በፍጹም። እነዚህ ብሔራት በጣዖት አምልኮ፣ በደም መፋሰስና ወራዳ በሆነ የጾታ ብልግና ተዘፍቀው ነበር። ሌላው ቀርቶ ልጆችን እንኳ በእሳት መሥዋዕት ያደርጉ ነበር። (ዘኍልቍ 33:52፤ ኤርምያስ 7:31) አምላክ ቅዱስ፣ ፍትሐዊና ሕዝቡን የሚወድ መሆኑ እንዲህ ያለውን ርኩስ ተግባር ከምድሪቱ እንዲያስወግድ ገፋፍቶታል። ያም ሆኖ ይሖዋ ከሰብዓዊ የጦር አዛዦች በተለየ መልኩ የእያንዳንዱን ሰው ልብ ስለሚመረምር ከክፉ መንገዳቸው ተመልሰው እሱን ለማገልገል ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ከጥፋቱ አድኗቸዋል።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ተከታዮቹ እሱንም ሆነ ሌሎች ክርስቲያኖችን ከጥቃት ለመጠበቅ ሲሉ እንዲዋጉ ይጠብቅባቸዋል?

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥቂት የይሖዋ ምሥክሮች በ1945 ከቡከንዋልድ የማጎሪያ ካምፕ ከተለቀቁ በኋላ