በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

“የቤተ መቅደሱ ሹም” ማን ነበር? ምንስ ኃላፊነት ነበረው?

ሐዋርያው ጴጥሮስና ሐዋርያው ዮሐንስ ሲሰብኩ ከያዟቸው የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች መካከል “የቤተ መቅደሱ ሹም” ይገኝበታል። (የሐዋርያት ሥራ 4:1-3) መጽሐፍ ቅዱስ የቤተ መቅደሱን ሹም ኃላፊነት በተመለከተ የሚናገረው ነገር የለም፤ ሆኖም አንዳንድ ታሪካዊ መረጃዎች አስገራሚ ፍንጭ ይሰጡናል።

ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ፣ እንዲህ ያለው ሹመት የሚሰጠው ከሊቀ ካህናቱ ቀጥሎ ሁለተኛውን የሥልጣን ደረጃ ለሚይዘው ካህን ሳይሆን አይቀርም። የቤተ መቅደሱ ሹም በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስም ሆነ በአካባቢው ሥርዓት እንዲጠበቅ ያደርጋል። በተጨማሪም በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚከናወነውን አምልኮ አልፎ ተርፎም የቤተ መቅደሱን የጥበቃ ኃይል በበላይነት ይቆጣጠራል። በእሱ ሥር ያሉት የበታች ሹሞች ደግሞ የቤተ መቅደሱን በር ማለዳ ላይ የሚከፍቱትንና ማታ ላይ የሚዘጉትን ጠባቂዎች ይቆጣጠራሉ፣ ሰዎች ወደተከለከሉ ቦታዎች እንዳይገቡ ይከላከላሉ እንዲሁም የቤተ መቅደሱን ግምጃ ቤት ይጠብቃሉ።

በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚሠሩት ካህናትና ሌዋውያን በ24 ምድብ ተደራጅተው ነበር፤ እያንዳንዱ ምድብ ለአንድ ሳምንት የሚሠራ ሲሆን በዓመት ሁለት ጊዜ ተራ ይደርሰዋል ማለት ነው። እያንዳንዱ ምድብ የራሱ የሆነ የቤተ መቅደስ ሹም ሳይኖረው አይቀርም።—1 ዜና መዋዕል 24:1-18

እነዚህ የቤተ መቅደስ ሹሞች ሥልጣን ነበራቸው። እነዚህ ሰዎች ኢየሱስን ለመግደል ካሴሩት የካህናት አለቆች ጋር አብረው የተጠቀሱ ሲሆን ኢየሱስን ለመያዝ በእነሱ ሥር ያለውን የጥበቃ ኃይል ተጠቅመዋል።—ሉቃስ 22:4, 52

ማቴዎስ 3:4 አጥማቂው ዮሐንስ “አንበጣና የዱር ማር” እንደበላ ይናገራል። ይሁንና በዚያን ዘመን ይኖሩ የነበሩ ሰዎች አንበጣ ይመገቡ ነበር?

አንዳንዶች ዮሐንስ ቃል በቃል አንበጣ መብላቱን ይጠራጠራሉ፤ እዚህ ላይ ማቴዎስ እየተናገረ ያለው አንበጦ ስለተባለው ዛፍ ፍሬ ወይም ከጫካ ስለሚለቀም አንድ የፍሬ ዓይነት አሊያም ስለተለያየ የዓሣ ዝርያ እንደሆነ ይናገራሉ። ይሁንና ማቴዎስ የተጠቀመው ግሪክኛ ቃል የሚያመለክተው በአሁኑ ጊዜ አክሪዲዴ የሚል ሳይንሳዊ መጠሪያ የተሰጠውን የፌንጣ ዝርያ ነው። በመንጋ ሆነው ሰብልን በማጥፋት የሚታወቁት የበረሃ አንበጦች በእስራኤል በብዛት ይገኙ ነበር።—ኢዩኤል 1:4, 7፤ ናሆም 3:15

በጥንት ጊዜ አንበጣ በአሦራውያንና በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተወዳጅ ምግብ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜም አንዳንድ የአረብ ዘላኖችና የመናውያን አይሁዶች አንበጣ ይበላሉ። በእስራኤላውያን ዘንድ አንበጣ የድሆች ምግብ ተደርጎ ይታይ ነበር። የአንበጣው ራስ፣ እግሩና ሆዱ ከተወገዱ በኋላ ቀሪው ክፍል ይኸውም ደረቱ ጥሬውን አሊያም ተቆልቶ ወይም በፀሐይ ደርቆ ይበላል። አንዳንድ ጊዜ አንበጣው በጨው ይታሻል አሊያም በኮምጣጤ ይዘፈዘፋል ወይም በማር ይለወሳል።

ዮሐንስ ይሰብክ የነበረው በምድረ በዳ በመሆኑ እንደ ልብ ማግኘት የሚችለው ምግብ አንበጣ ነበር። (ማርቆስ 1:4) አንበጦች 75 በመቶ የሚያህል ፕሮቲን ስላላቸው አንድ ሰው አንበጦችን ከዱር ማር ጋር ቢበላ የተመጣጠነ ምግብ ያገኛል።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አሦራውያን አገልጋዮች አንበጣና ሮማን ይዘው

[የሥዕል ምንጭ]

From the book Discoveries Among the Ruins of Nineveh and Babylon (1853)