በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፍርሃትንና ጥርጣሬን ለማሸነፍ ታግሏል

ፍርሃትንና ጥርጣሬን ለማሸነፍ ታግሏል

በእምነታቸው ምሰሏቸው

ፍርሃትንና ጥርጣሬን ለማሸነፍ ታግሏል

ጴጥሮስ በመቅዘፊያው እየቀዘፈ ጨለማው ውስጥ አሻግሮ ለማየት ጥረት አደረገ። በስተ ምሥራቅ በኩል ከአድማሱ ባሻገር ደብዛዛ ብርሃን ተመለከተ። ያየው ብርሃን ጎህ ሊቀድ መሆኑን የሚያበስር ምልክት ይሆን? ለረጅም ሰዓት ጀልባውን ሲቀዝፍ ስለቆየ ወገቡና ትከሻው ዝሏል። የጴጥሮስን ፀጉር የሚያመሰቃቅለው ነፋስ የገሊላን ባሕር እያናወጠው ነው። እየተከታተለ የሚመጣው ሞገድ ከጀልባዋ ጋር በሚላተምበት ጊዜ የሚረጨው ቀዝቃዛ ውኃ ጴጥሮስን አበስብሶታል። ያም ሆኖ ጴጥሮስ ዓሣ ማስገሪያ ጀልባውን መቅዘፉን ቀጥሏል።

ጴጥሮስና ጓደኞቹ ወደዚህ የመጡት ኢየሱስን በባሕሩ ዳርቻ ብቻውን ትተውት ነው። ያን ዕለት ቀን ላይ ኢየሱስ፣ ርቧቸው የነበሩ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን በጥቂት ዳቦና ዓሣ ሲመግብ አይተዋል። ሕዝቡ ይህን ሲመለከት ኢየሱስን ንጉሥ ለማድረግ አስቦ ነበር፤ እሱ ግን በፖለቲካ ውስጥ እጁን ማስገባት አልፈለገም። ተከታዮቹም በፖለቲካ ውስጥ የመግባት ምኞት እንዳይኖራቸው አበረታቷል። ኢየሱስ ከሕዝቡ ገለል ካለ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ በጀልባ ተሳፍረው በተቃራኒ አቅጣጫ ወዳለው የባሕር ዳርቻ ቀድመውት እንዲሄዱ ነገራቸው፤ ከዚያም እሱ ለመጸለይ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ።—ማርቆስ 6:35-45፤ ዮሐንስ 6:14, 15

ደቀ መዛሙርቱ ጉዞ ሲጀምሩ ሙሉዋ ጨረቃ በአናታቸው ትክክል ነበረች፤ አሁን ግን በስተ ምዕራብ በኩል አድማስ ውስጥ ገብታ ልትሰወር ትንሽ ቀርቷታል። ያም ሆኖ የተጓዙት ጥቂት ኪሎ ሜትር ብቻ ነበር። ነፋሱና ሞገዱ የሚፈጥሩት ፉጨት እርስ በርስ እንዳይሰማሙ እንቅፋት ሆኖባቸዋል። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ በሐሳብ ተውጦ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም።

ወደ ጴጥሮስ አእምሮ ሊመጡ የሚችሉ ብዙ ነገሮች ይኖራሉ! የናዝሬቱ ኢየሱስን መከተል ከጀመረ ሁለት ዓመት አልፎታል። ብዙ ነገሮች በተከሰቱባቸው በእነዚህ ሁለት ዓመታት በርካታ ነገሮችን የተማረ ቢሆንም ገና የሚያሻሽላቸው ብዙ ነገሮች ነበሩ። ጴጥሮስ ለመሻሻል ፈቃደኛ በመሆን ይኸውም እንደ ጥርጣሬና ፍርሃት ያሉ እንቅፋቶችን ለማሸነፍ ትግል በማድረግ ልንከተለው የሚገባ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። እስቲ ጴጥሮስ ምሳሌ የሚሆነን እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

“መሲሑን አገኘነው”!

ጴጥሮስ ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር የተገናኘበትን ቀን መቼም ቢሆን አይረሳውም። “መሲሑን አገኘነው” የሚለውን አስደሳች ዜና ለመጀመሪያ ጊዜ ያበሰረው ወንድሙ እንድርያስ ነበር። ጴጥሮስ እነዚህን ቃላት ከሰማ በኋላ ሕይወቱ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተለወጠ።—ዮሐንስ 1:41

ጴጥሮስ የሚኖረው የገሊላ ባሕር ተብሎ በሚጠራው ጨዋማ ያልሆነ ሐይቅ ዳርቻ ላይ በምትገኘው በቅፍርናሆም ነው። እሱና እንድርያስ የዘብድዮስ ልጆች ከሆኑት ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ዓሣ በማጥመድ ሥራ ላይ ተሠማርተዋል። ጴጥሮስ የሚኖረው ከሚስቱ ጋር ብቻ ሳይሆን ከአማቱና ከወንድሙ እንድርያስ ጋር ነበር። ዓሣ በማጥመድ ሥራ እንዲህ ያለውን ቤተሰብ ማስተዳደር ትጋት፣ ጉልበትና ብልሃት እንደሚጠይቅ እሙን ነው። በዚህ ሥራ ላይ የተሠማሩ ሰዎች በሁለት ጀልባዎች ላይ ሆነው መረባቸውን ወደ ባሕሩ ከጣሉ በኋላ ያጠመዱትን ዓሣ ሁሉ ወደ ጀልባቸው ይጎትታሉ፤ በዚህ መንገድ ዓሣ በማስገር ረጅም ሌሊቶችን ሲያሳልፉ በየቀኑ ምን ያህል እንደሚለፉ መገመት አያዳግትም። ቀኑንም ቢሆን የሚያሳልፉት ዓሦችን በመለየትና በመሸጥ እንዲሁም መረባቸውን በመጠገንና በማፅዳት ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው እንድርያስ የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ነበር። ጴጥሮስ፣ ወንድሙ የዮሐንስን መልእክት ሲነግረው በጉጉት ይሰማ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። አንድ ቀን ዮሐንስ ወደ ኢየሱስ እያመለከተ “የአምላክ በግ ይኸውላችሁ!” ብሎ ሲናገር እንድርያስ ተመለከተ። በዚህ ጊዜ እንድርያስ ኢየሱስን መከተል የጀመረ ሲሆን መሲሑ እንደመጣ የሚናገረውን አስደሳች ዜና ለጴጥሮስ አበሰረው። (ዮሐንስ 1:35-40) ከ4,000 ዓመታት በፊት በኤደን ዓመፅ ከተፈጸመ በኋላ ይሖዋ አምላክ ለሰው ዘሮች እውነተኛ ተስፋ የሚፈነጥቅ ልዩ ሰው ወደ ምድር እንደሚልክ ቃል ገብቶ ነበር። (ዘፍጥረት 3:15) እንድርያስ ይህን አዳኝ ማለትም መሲሑን በአካል አግኝቶት ነበር! ጴጥሮስ ይህን ሲሰማ በፍጥነት ወደ ኢየሱስ ሄደ።

እስከዚያች ቀን ድረስ ጴጥሮስ ይጠራ የነበረው ስምዖን በሚለው ስም ነበር። ይሁንና ኢየሱስ ጴጥሮስን ባየው ጊዜ “አንተ የዮሐንስ ልጅ ስምዖን ነህ፤ ኬፋ (ትርጉሙ ጴጥሮስ ማለት ነው) ተብለህ ትጠራለህ” አለው። (ዮሐንስ 1:42) “ኬፋ” የሚለው ቃል “ቋጥኝ” ወይም “ዐለት” የሚል ትርጉም አለው። ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ትንቢታዊ ፍጻሜ እንደሚኖረው ግልጽ ነው። ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ልክ እንደ ዐለት ጽኑ፣ ቆራጥና አስተማማኝ በመሆን በክርስቶስ ተከታዮች ላይ በጎ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር እየተናገረ ነበር። ጴጥሮስ ስለ ራሱ እንዲህ ይሰማው ነበር? ጴጥሮስ እንደዚያ ዓይነት ተጽዕኖ ማሳደር እንደሚችል የተጠራጠረ ይመስላል። በዛሬው ጊዜ ወንጌሎችን የሚያነቡ አንዳንድ ሰዎችም እንኳ ጴጥሮስ እንደ ዐለት ያለ ጽኑ ባሕርይ አለው ብሎ ማሰብ ይከብዳቸዋል። አንዳንዶች ጴጥሮስ ወላዋይ፣ ቆራጥነት የሚጎድለውና አቋሙ የሚዋዥቅ ሰው እንደሆነ ይናገራሉ።

ጴጥሮስ የራሱ ድክመቶች ነበሩት። ኢየሱስ የጴጥሮስን ድክመቶች ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። ይሁንና ኢየሱስ እንደ አባቱ እንደ ይሖዋ ሁልጊዜም የሚመለከተው የሰዎችን በጎ ጎን ነው። ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ጥሩ ባሕርያት እንዳሉት ያስተዋለ ሲሆን እነዚህን ባሕርያት በሚገባ እንዲጠቀምባቸው ሊረዳው ፈልጓል። በዛሬው ጊዜም ይሖዋና ልጁ ሊጠቀሙብን ስለሚፈልጉ ያሉንን ጥሩ ባሕርያት ይመለከታሉ። በውስጣችን ያን ያክል ጥሩ ነገር ያገኛሉ ብሎ ማሰብ ይከብደን ይሆናል። ይሁን እንጂ የእነሱን አመለካከት መቀበልና ጴጥሮስ እንዳደረገው በእነሱ ለመሠልጠንም ሆነ ለመቀረጽ ፈቃደኛ መሆን ይገባናል።—1 ዮሐንስ 3:19, 20

“አይዞህ አትፍራ”

ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ከዚያ በኋላ ለስብከት ባደረጋቸው ጉዞዎች ሁሉ አብሮት በመሆን ሳይከተለው እንዳልቀረ መገመት ይቻላል። ጴጥሮስ እንዲህ አድርጎ ከሆነ ኢየሱስ በቃና በተደረገው የሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ ውኃን ወደ ወይን በመለወጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ተአምር ሲፈጽም ተመልክቶ መሆን ይኖርበታል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት አስመልክቶ የተናገረውን አስደናቂና ተስፋ የሚፈነጥቅ መልእክት ሰምቷል። ያም ሆኖ ኢየሱስን መከተሉን በማቆም ዓሣ ወደ ማጥመድ ሥራው ተመለሰ። ከተወሰኑ ወራት በኋላ ግን ጴጥሮስና ኢየሱስ በድጋሚ ተገናኙ፤ በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ የእሱ ተከታይ እንዲሆን ግብዣ አቀረበለት።

ኢየሱስ ጴጥሮስ ወዳለበት ቦታ የደረሰው ዓሣ ለማጥመድ ሌሊቱን ሙሉ ሲለፋ አድሮ ተስፋ በቆረጠበት ጊዜ ላይ ነው። ዓሣ አጥማጆቹ በተደጋጋሚ ጊዜ መረባቸውን ወደ ባሕሩ ቢጥሉም ምንም ዓሣ አላገኙም። ጴጥሮስ ያለውን ችሎታም ሆነ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ዓሦች በብዛት የሚገኙበትን ቦታ ለማግኘት ያላደረገው ጥረት አልነበረም። ጴጥሮስ እንደ ሌሎቹ ዓሣ አጥማጆች ሁሉ ባሕሩን እስከ ታች ድረስ የማየትና ዓሦቹ ሰተት ብለው ወደ መረቡ እንዲገቡ የማድረግ ልዩ ችሎታ እንዲኖረው ተመኝቶ መሆን አለበት። እንዲህ ያለው ሐሳብ ሐዘኑን ከማባባስ በቀር ምንም እንደማይፈይድለት ግልጽ ነው። ጴጥሮስ ዓሣ የሚያጠምደው ለመዝናናት ሳይሆን እጁን ጠብቀው የሚያድሩ ሰዎች ስላሉ ነው። ሌሊቱን ሁሉ ቢለፋም ወደ ዳርቻው የተመለሰው ምንም ዓሣ ሳያገኝ ነው። ከዚህ በኋላ ደግሞ መረቦቹን የማጽዳት ሥራ ይጠብቀዋል። ኢየሱስ እሱ ጋ ሲደርስ ጴጥሮስ በዚህ ሥራ ተጠምዶ ነበር።

በዚህ ጊዜ ብዙ ሰዎች በኢየሱስ ዙሪያ ተሰብስበው እሱ የሚሰጠውን ትምህርት በጉጉት ያዳምጡ ነበር። ኢየሱስ ሰዎቹ እየተገፋፉ ስላጨናነቁት በጴጥሮስ ጀልባ ላይ ወጣና ከየብስ ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጋት ጠየቀው። ኢየሱስ በባሕሩ ላይ ሆኖ መናገሩ ድምፁ በሚገባ እንዲሰማ ስላስቻለው ሕዝቡን ያለ ምንም ችግር ማስተማር ጀመረ። በባሕሩ ዳርቻ ላይ እንዳሉት ሰዎች ሁሉ ጴጥሮስም የኢየሱስን ትምህርት በትኩረት አዳመጠ። ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ የስብከቱ ዋና ጭብጥ ስለሆነው ስለ አምላክ መንግሥት ሰፊ ማብራሪያ ሲሰጥ መስማት አላደከመውም። ክርስቶስ ተስፋ የሚፈነጥቀውን ይህንን መልእክት በመላው እስራኤል ሲያስፋፋ መርዳት መቻል እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! ታዲያ ጴጥሮስ እንደዚያ ማድረግ ይችል ይሆን? እንደዚያ ካደረገ በምን ይተዳደራሉ? ምናልባት ጴጥሮስ በዚህ ጊዜ ያለ ምንም ውጤት ያሳለፈው ረጅም ሌሊት ትዝ ብሎት ሊሆን ይችላል።—ሉቃስ 5:1-3

ኢየሱስ ንግግሩን ሲጨርስ ጴጥሮስን “ወደ ጥልቁ ውሃ ፈቀቅ በልና ዓሣ ለመያዝ መረባችሁን ጣሉ” አለው። ጴጥሮስ ግን ዓሣ ማግኘት መቻሉን ተጠራጥሮ ስለነበር “መምህር፣ ሌሊቱን ሙሉ ስንደክም አድረን ምንም አልያዝንም፤ አንተ ካልክ ግን መረቦቹን እጥላለሁ” አለው። በተለይ ዓሦቹ በዚህ ሰዓት በፍጹም ስለማይገኙ ጴጥሮስ መረቦቹን እንደገና መጣል እምብዛም አልፈለገም ነበር። ያም ሆኖ ኢየሱስ ያዘዘውን ለማድረግ ፈቃደኛ ሆነ፤ በዚህ ጊዜ በሁለተኛው ጀልባ ላይ ያሉት የሥራ ባልደረቦቹ እንዲከተሉት ምልክት ሳይሰጣቸው አልቀረም።—ሉቃስ 5:4, 5

ጴጥሮስ መረቦቹን መጎተት ሲጀምር ክብደቱ ከጠበቀው በላይ ሆነበት። ሁኔታውን ማመን አቅቶት ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሞ መረቦቹን ሲጎትት ከፍተኛ መጠን ያላቸው ዓሦች መረቡ ውስጥ ሲተራመሱ ተመለከተ! ከባድ እንደሆነ ስለተሰማው በሌላኛው ጀልባ ላይ ያሉት ባልንጀሮቻቸው መጥተው እንዲረዱት ምልክት ሰጣቸው። ባልንጀሮቻቸው መጥተው ከረዷቸው በኋላ ያንን ሁሉ ዓሣ አንድ ጀልባ ብቻ እንደማይችለው ተገነዘቡ። ሁለቱንም ጀልባዎች ከሞሉ በኋላም እንኳ ብዙ ዓሦች ተርፈው ነበር፤ እንዲያውም ከዓሣው ክብደት የተነሳ ጀልባዎቹ መስመጥ ጀመሩ። ጴጥሮስ በሁኔታው በጣም ተገረመ። ጴጥሮስ፣ ክርስቶስ ከዚህ ቀደም ተአምር ሲፈጽም የተመለከተ ቢሆንም ይህ ግን ለእሱ በግል እንደተደረገ ተሰማው! ለካስ ዓሦች ወደ መረብ ሰተት ብለው እንዲገቡ የማድረግ ችሎታ ያለው ሰው አለ! ጴጥሮስ በፍርሃት ተዋጠ። ከዚያም በኢየሱስ ጉልበት ላይ ወድቆ “ጌታ ሆይ፣ እኔ ኃጢአተኛ ሰው ስለሆንኩ ከእኔ ራቅ” አለው። በአምላክ ኃይል እንዲህ ያሉ ተአምራትን መፈጸም የሚችል ሰው ተከታይ ለመሆን የሚያስችል ብቃት መቼም ሊኖረው እንደማይችል ተሰምቶት ነበር!—ሉቃስ 5:6-9

ኢየሱስ ጴጥሮስን በርኅራኄ “አይዞህ አትፍራ፤ ከአሁን ጀምሮ ሰውን በሕይወት እንዳለ የምታጠምድ ትሆናለህ” አለው። (ሉቃስ 5:10, 11) አሁን ጴጥሮስ የሚጠራጠርበትም ሆነ የሚፈራበት ጊዜ አይደለም። ጴጥሮስ ዓሣ ማስገሩን ቢያቆም በምን ሊተዳደር እንደሚችል በማሰብ መጠራጠሩ ተገቢ አልነበርም፤ የሠራቸውን ስህተቶችና ያሉበትን ድክመቶች አስቦ መፍራቱም ምክንያታዊ አልነበረም። ኢየሱስ በዓለም ታሪክ ላይ ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጣ ታላቅ ሥራ አለው። “ይቅርታው ብዙ” የሆነውን አምላክ እያገለገለ ነው። (ኢሳይያስ 55:7) ይሖዋ አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ስለሚያሟላላቸው መፍራትም ሆነ መጠራጠር አያስፈልገውም።—ማቴዎስ 6:33

እንደ ያዕቆብና ዮሐንስ ሁሉ ጴጥሮስም አፋጣኝ እርምጃ ወሰደ። ሦስቱም “ጀልባዎቹን መልሰው ወደ የብስ ካስጠጉ በኋላ ሁሉን ነገር ትተው ተከተሉት።” (ሉቃስ 5:11) ጴጥሮስ እምነቱን በኢየሱስና እሱን በላከው አምላክ ላይ ጣለ። ይህ በሕይወቱ ሊያደርገው ከሚችለው ሁሉ እጅግ የላቀ ውሳኔ ነው። አምላክን ስለማገልገል ሲያስቡ የሚሰማቸውን ፍርሃትና ጥርጣሬ ያሸነፉ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም ተመሳሳይ እምነት እያሳዩ ነው። በይሖዋ ላይ እንዲህ ያለ እምነት በማሳደራቸው አንዳች ነገር አይጎድልባቸውም።—መዝሙር 22:4, 5

“ለምን ተጠራጠርክ?”

ጴጥሮስ ከኢየሱስ ጋር ከተገናኘ ከሁለት ዓመት ገደማ በኋላ በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው ነፋስ በበዛበት በዚያ ሌሊት በገሊላ ባሕር ላይ ጀልባውን እየቀዘፈ ነው። በዚህ ጊዜ እያሰበ የነበረው ስለምን እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር ባንችልም ብዙ አማራጮች አሉን! ኢየሱስ የጴጥሮስን አማት ፈውሶ ነበር። የተራራውን ስብከት ሰጥቶ ነበር። ኢየሱስ ባስተማራቸው ትምህርቶችና ባከናወናቸው ተአምራት አማካኝነት እሱ የይሖዋ ምርጥ ማለትም መሲሑ እንደሆነ በተደጋጋሚ ጊዜ አስመሥክሯል። ወራት እያለፉ ሲሄዱ ጴጥሮስ በፍርሃትና በጥርጣሬ ስሜት ቶሎ እንደመሸነፍ ያሉትን ድክመቶቹን በተወሰነ መጠን አሻሽሎ መሆን አለበት። ኢየሱስም ቢሆን ጴጥሮስን ሐዋርያው እንዲሆን መርጦታል! ይሁን እንጂ ጴጥሮስ ብዙም ሳይቆይ እንደሚገነዘበው ያለበትን ፍርሃትና ጥርጣሬ ገና ሙሉ በሙሉ አላሸነፈም።

በአራተኛው ክፍለ ሌሊት ማለትም ከሌሊቱ 9:00 ሰዓት እስከ ንጋት ባለው ጊዜ ውስጥ ጴጥሮስ ድንገት መቅዘፉን አቁሞ በተቀመጠበት ድርቅ ብሎ ቀረ። ከሞገዱ ባሻገር አንድ የሚንቀሳቀስ ነገር ይታያል! ሞገዱ የሚረጨው ውኃ ከጨረቃዋ ብርሃን ጋር ተዳምሮ የፈጠረው ምስል ይሆን? በፍጹም! ያየው ነገር ታይቶ ጥፍት የሚል ነገር አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሰው ነው! አዎን፣ አንድ ሰው በባሕሩ ላይ እየተራመደ ነው! ሰውየው እየተቃረበ ሲመጣ ወደ እነሱ እየመጣ እንደሆነ ተገነዘቡ። ደቀ መዛሙርቱ በጣም ተደናግጠው ስለነበር ምትሀት የሚያዩ መሰላቸው። በዚህ ጊዜ ሰውየው “አይዟችሁ፤ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ” አላቸው። ለካ ሰውየው ኢየሱስ ነበር!—ማቴዎስ 14:25-28

በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፣ አንተ ከሆንክ በውኃው ላይ እየተራመድኩ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ” አለው። ጴጥሮስ መጀመሪያ ላይ ድፍረት ተሰምቶት ነበር። ጴጥሮስ ባየው ተአምር በጣም ከመደነቁ የተነሳ እምነት እንዳለው ለማሳየት ፈልጎ ነበር። እሱም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ፈልጎ ነበር። ኢየሱስም ወደ እሱ እንዲመጣ ፈቀደለት። ጴጥሮስ በጎን በኩል ከጀልባዋ ላይ ወርዶ በሚናወጠው ባሕር ላይ ቆመ። የቆመበት ባሕር ምንም ሳይከዳው ቀጥ ብሎ መቆም በመቻሉ ምን ያህል ተደንቆ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ወደ ኢየሱስ ሲሄድ በአግራሞት ስሜት ተውጦ መሆን አለበት። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ አንድ ልዩ ስሜት ተሰማው።—ማቴዎስ 14:29

ጴጥሮስ ትኩረቱን ኢየሱስ ላይ ማድረግ ነበረበት። በይሖዋ ኃይል ተጠቅሞ በሞገዱ ላይ ቀጥ ብሎ እንዲራመድ ሊያደርገው የሚችለው ኢየሱስ ነው። ኢየሱስ ደግሞ ይህንን የሚያደርገው የጴጥሮስን እምነት ተመልክቶ ነው። ይሁንና ጴጥሮስ ትኩረቱ ተከፋፈለ። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንደሚናገረው ጴጥሮስ “ማዕበሉን ሲያይ ፈራ።” ጴጥሮስ ሞገዱ ከጀልባዋ ጋር ሲጋጭና ውኃውን ወደ ላይ ሲረጨው በሙሉ ዓይኑ ተመለከተ፤ በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ በፍርሃት ተዋጠ። ምናልባትም ሐይቁ ውስጥ ሰምጦ ሲሞት ታይቶት ሊሆን ይችላል። ፍርሃቱ እየጨመረ ሲሄድ እምነቱም እያሽቆለቆለ ሄደ። ጽኑ አቋም ይኖረዋል በሚል ስሜት “ዐለት” የሚል መጠሪያ ተሰጥቶት የነበረው ይህ ሰው እምነቱ በመዋዠቁ ምክንያት እንደ ድንጋይ መስጠም ጀመረ። የሚገርመው ጴጥሮስ የተዋጣለት ዋናተኛ ነበር፤ ሆኖም ይህ ችሎታው እንኳ ትዝ ሊለው አልቻለም። በጣም ከመጨነቁ የተነሳ “ጌታ ሆይ፣ አድነኝ!” ብሎ ጮኸ። ከዚያም ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ያዘውና ከውኃው አወጣው። እዚያው ውኃው ላይ እያሉም ኢየሱስ “አንተ እምነት የጎደለህ፣ ለምን ተጠራጠርክ?” በማለት ለጴጥሮስ አንድ አስፈላጊ ትምህርት ሰጠው።—ማቴዎስ 14:30, 31

“ለምን ተጠራጠርክ?” የሚለው አነጋገር ምንኛ ተስማሚ ነው! ጥርጣሬ አጥፊ ሊሆን ይችላል። በጥርጣሬ ከተሸነፍን እምነታችንን ሊያዳክመውና በመንፈሳዊ የመስመጥ አደጋ ሊያስከትልብን ይችላል። በመሆኑም ጥርጣሬን አጥብቀን መዋጋት ይኖርብናል! እንዴት? ሁልጊዜም ትኩረታችንን በትክክለኛው ነገር ላይ በማድረግ ነው። በሚያስጨንቁን፣ ተስፋ በሚያስቆርጡን እንዲሁም በይሖዋና በልጁ ላይ እንዳናተኩር በሚያደርጉን ነገሮች ላይ የምናሰላስል ከሆነ የሚሰማን ጥርጣሬ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይመጣል። በይሖዋና በልጁ እንዲሁም እነሱን ለሚወዷቸው ሰዎች ከዚህ ቀደም ባደረጉትና አሁንም ሆነ ወደፊት በሚያደርጉት ነገር ላይ ካተኮርን ግን አጥፊ ከሆነው የጥርጣሬ ስሜት እንጠበቃለን።

ጴጥሮስ ከኢየሱስ ጋር ሆኖ ጀልባው ላይ ከወጣ በኋላ ማዕበሉ ጸጥ አለ። በዚህ ጊዜ በገሊላ ባሕር ላይ ፍጹም ጸጥታ ሰፈነ። ጴጥሮስ ከሌሎቹ ደቀ መዛሙርቱ ጋር ሆኖ ኢየሱስን “አንተ በእርግጥ የአምላክ ልጅ ነህ” አለው። (ማቴዎስ 14:33) ሐይቁ ላይ እያሉ ጎህ ሲቀድ የጴጥሮስ ልብ በአድናቆት ስሜት ተሞልቶ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ከዚያ በኋላ ጥርጣሬና ፍርሃት ሊያሸንፈው እንደማይገባ ጥሩ ትምህርት አግኝቷል። ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረለት እንደ ዐለት ጽኑ የሆነ ክርስቲያን እንዲሆን ብዙ ለውጥ ማድረግ እንደነበረበት ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ መጣጣሩንና እድገት ማድረጉን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር። አንተስ እንዲህ ዓይነት አቋም አለህ? ጴጥሮስ ምሳሌ ሊሆን የሚችል እምነት ትቶልናል ቢባል እንደምትስማማ ምንም ጥርጥር የለውም።

[በገጽ 22, 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ይህ ትሑት ዓሣ አጥማጅ ሊዳብር የሚችል ጥሩ ባሕርይ እንዳለው አስተውሏል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘ጌታ ሆይ፣ እኔ ኃጢአተኛ ሰው ነኝ’

[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ማዕበሉን ሲያይ ፈራ”